“ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ”
ያደግኩት ከሳን ፍራሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ በስተ ሰሜን በምትገኘው ፓታሉማ በምትባል ትንሽ ከተማ ነው። እናቴ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ የነበራት ሲሆን አባቴ ግን ለሃይማኖት ግድ አልነበረውም። ፈጣሪ እንዳለ ባምንም ማንነቱን ግን አላውቅም ነበር።
በልጅነቴ ፍልቅልቅ ነበርኩ። እነዚያ ከጭንቀት ነፃ የሆኑት የልጅነት ጊዜያት ሁልጊዜ ትዝ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ እንደ ልብ መንቀሳቀስ ወደማልችልበት ደረጃ የሚያደርስ በሰውነቴ ውስጥ አንድ ዓይነት ለውጥ እየተካሄደ እንዳለ ፈጽሞ አልጠረጠርኩም ነበር። በ1960 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በማጠናቅቅበት የመጨረሻ ዓመት በጣቶቼ ላይ ይሰማኝ ስለነበረው ሕመም ለቅርብ ጓደኛዬ እነግራት እንደነበር ትዝ ይለኛል።
ብዙም ሳይቆይ እግሬን በጣም ስላመመኝ እናቴ ሳን ፍራንሲስኮ ወደሚገኝ አንድ ሐኪም ቤት ወሰደችኝ። እዚያም ለስድስት ቀናት ያህል ቆየሁ። በዚህ ጊዜ ዕድሜዬ 18 ዓመት ነበር። ሩማቶይድ አርትራይትስ እንደያዘኝ በተደረገልኝ ምርመራ ተረጋገጠ። በመጀመሪያ ጎልድ ሶዲየም ታዮሳልፌት የተባለ መድኃኒት ከዚያም ፕሬድኒሶን ከዚያም ከኮርቲዞን የተቀመመ ሌላ ዓይነት መድኃኒት መወጋት ጀመርኩ። እነዚህን መድኃኒቶች በድምሩ ለ18 ዓመታት በተከታታይ የወሰድኳቸው ሲሆን አንደኛው መድኃኒት የሚሰማኝን ሕመም ለጥቂት ዓመታት ያስታግስልኝና ወዲያው ሰውነቴ ሲለማመደው ደግሞ ሌላኛውን መድኃኒት መወጋት እጀምራለሁ። ሕመሙ ፋታ የማይሰጥና የማይቻል በመሆኑ የተለየ ዓይነት የሕክምና እርዳታ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አደረግኩ። በመጠኑ የረዱኝ አማራጭ ሕክምናዎች አገኘሁ። በአሁኑ ጊዜ፣ በሽታው በጀመረበትና በሰውነቴ ውስጥ ይሰራጭ በነበረበት ጊዜ ይሰማኝ የነበረው አጣዳፊ ሕመም ስለማይሰማኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።
በ1975 አንድ ቀን ወንድ ልጄ፣ እናቴ ልጅ ሳለሁ የጤንነቴን ሁኔታ ትመዘግብበት የነበረውን ማስታወሻ ደብተር አገኘ። የስድስት ወር ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ የታይመስ እጢዬ በማበጡ ምክንያት የጨረር ሕክምና ተሰጥቶኝ እንደነበረ ተረዳሁ። ለዚህ በሽታ የዳረገኝ ገና ጨቅላ ሳለሁ የተሰጠኝ ይህ የጨረር ሕክምና ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ። ከሆነ ትልቅ ስህተት ተፈጽሞብኛል ማለት ነው!
በ1962 አገባሁ። በ1968፣ በሽታው ገና ትኩስ እንደነበረ፣ ባለቤቴ ሊን እና እኔ በዳቦ መጋገሪያ ቤታችን አብረን እንሠራ ነበር። ከሌሊቱ በ10:00 ሰዓት አካባቢ ከመኝታችን ተነስተን ባለቤቴ ሊጡን ያቦካና ፉርኖ ቤት ውስጥ ከከተተ በኋላ በዱቄት ጆንያዎች ላይ ጋደም ይላል። ከዚያም ዳቦዎቹን ቆራርጠን ካሸግን በኋላ ሊን እየዞረ ያድላል። የመድን ድርጅት አሻሻጭ የሆነ አንድ ሰው አልፎ አልፎ ወደ ዳቦ ቤታችን እየመጣ አምላክ ቃል ስለገባው መንግሥት ይነግረናል። የምንሰማው ነገር ቢያስደስተንም በጥሞና ለመከታተል ግን ጊዜ አላገኘንም። ዳቦ የምናድላቸው ደንበኞች ቁጥር እየበዛ በመሄዱ የሥራችን ጫና እየጨመረ መጣ። የሌላ ዳቦ ቤት ባለቤት የእኛን ዳቦ ቤት በመግዛቱ ደስ አለን! ሊን ተቀጥሮ ለእነርሱ መሥራት ሲጀምር እኔ ደግሞ በውበት ሳሎን ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። ይሁን እንጂ በሽታው እየባሰብኝ ስለመጣ በሳምንት ሦስት ቀን ብቻ ለመሥራት ተገደድኩ። በመጨረሻም መሥራት አቆምኩ።
በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ አንዲት የይሖዋ ምሥክር እቤት እየመጣች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ትሰጠኝ ነበር። የአስተዋጽኦ ገንዘብ እየሰጠኋት መጽሔቶቹን ስወስድ ውለታ የዋልኩላት ይመስለኝ ነበር። ከሄደች በኋላ ግን መጽሔቶቹን ሳልገልጣቸው መጻሕፍት መደርደሪያ ላይ አስቀምጣቸዋለሁ። ከጥቂት ቀን በኋላ ከሁለት አንዳችን አውጥተን እንጥላቸዋለን። አሁን እነዚህ መጽሔቶች የያዙትን ከፍተኛ መንፈሳዊ ጥቅም ስለተገነዘብን እንዲህ ማድረጌ ትልቅ ስህተት እንደነበረ ተረድቼአለሁ። በዚያ ወቅት ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ይሄን ያህል ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሆነው አይታዩኝም ነበር።
ስለሚያስፈልጉን መንፈሳዊ ነገሮች ማሰብ
አንድ ቀን ምሽት እኔና ባለቤቴ ሕይወት በመብላት፣ በመተኛትና በሥራ በመድከም ብቻ መወሰን እንደማይኖርበት ተነጋገርን። በሕይወታችን ውስጥ ተጓድሎብን የቆየውን መንፈሳዊነት ለማግኘት ፍለጋ ጀመርን። ከመንገድ በታች ይገኝ ወደነበረው አንድ ትንሽ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርን። ሆኖም የተመኘነውን ያክል መንፈሳዊነታችንን የሚያነቃቃ ነገር አላገኘንም። የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አዘውትረው የሚያወሩት ስለ ግል ችግሮቻቸው ነበር።
መጽሔት ታመጣልን የነበረችው ምሥክር አንድ ዓመት ለሚያክል ጊዜ ተመላለሰች። “ከምታስበው በላይ ጊዜው አልቋልን?” የሚል ርዕስ የያዘውን የጥቅምት 8, 1968 ንቁ! እስካነበብኩበት ቀን ድረስ እንደተለመደው መጽሔቶችን ተቀብዬ መጣሌን አላቆምኩም ነበር። ያነበብኩት ነገር በጣም አስደሰተኝ። ባለቤቴም እንደኔው ደስ አለው። ከዚያም ማጥናት ጀመርንና እውነትን በከፍተኛ ጥማት መከታተል ጀመርን። የተማርናቸውን አስደናቂ ነገሮች በሙሉ ልብ ተቀበልን። በ1969 ሁለታችንም ተጠመቅን።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ መነሳት፣ መቀመጥና ከበድ ያሉ ሥራዎችን መሥራት እያስቸግረኝ መጣ። መኪና ውስጥ ለመግባትና ከመኪና ለመውረድ ጉልበቶቼን ማጠፍ ይከብደኝ ጀመር። እንደልቤ መንቀሳቀስ አለመቻልንና ብዙ ጊዜ እስከማልቀስ የሚያደርሰኝን ከባድ ሕመም ችዬ መኖር ተለማመድኩ። ፊቴን እቀባባና ወደ ስብሰባ ወይም ወደ መስክ አገልግሎት እንሄዳለን። አቅሜ የፈቀደልኝን ያክል ከቤት ወደ ቤት እሄዳለሁ። ሕመሙ ብሶብኝ ጉልበቶቼና እግሮቼ መንቀሳቀስ እስኪከለክሉኝ ድረስ በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ወደ መስክ አገልግሎት እሄድ ነበር። ብወድቅ መነሳት አቅቶኝ እንደ ወደቅኩ እቀር ይሆን ብዬ ብዙ ጊዜ እፈራ ነበር። ከይሖዋ ጋር ስነጋገር ቀለል ይለኛል። እያለቀስኩ የምጸልይበት ጊዜ አለ።
ይሁን እንጂ እንባ ማፍሰስም ቢሆን ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት አሉ። ሩማቶይድ አርትራይትስ ያለበት ሰው የእንባ መድረቅ ችግር ሊገጥመው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ዓይኔ በጣም ከመድረቁ የተነሳ ማንበብ እንኳ የማልችልባቸው ጊዜያት ነበሩ። ዓይኔ ሲደርቅ በቴፕ ክር የተቀዱ ንግግሮችን አዳምጣለሁ። የዓይኔ ሽፋን ሲንቀሳቀስ ዓይኔን ስለሚቧጥጠው ብዙውን ጊዜ የምንቀሳቀሰው ዓይኖቼን ጨፍኜ ነው። ከዓይነ ስውር የማልሻልባቸው ጊዜያት አሉ። አንዳንድ ጊዜ በየአምስት ደቂቃው ሰው ሠራሽ እንባ በዓይኔ ውስጥ ለመጨመር እገደዳለሁ። ሲብስብኝ ደግሞ ዓይኔ ውስጥ ቅባት ጨምሬ እስኪሻለኝ ድረስ ለአምስት ወይም ለስድስት ቀናት ዓይኖቼን በጨርቅ እሸፍናለሁ። በዚህ ሥርዓት ይድናል ተብሎ ከማይታሰብ በሽታ ጋር እየታገሉ አመስጋኝ እንደሆኑ መቀጠል በጣም ያስቸግራል።
በ1978 ተሽከርካሪ ጋሪ ላይ ተቀምጬ ካልሆነ በስተቀር መንቀሳቀስ ወደማልችልበት ደረጃ ደረስኩ። ይህንን መቀበል በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። በተሽከርካሪ ጋሪ ላለመጠቀም የቻልኩትን ያክል ስከላከል ብቆይም አሁን ግን ምንም አማራጭ አላገኘሁም። አንድ ቀን በተሽከርካሪ ጋሪ ለመጠቀም የምገደድበት ጊዜ እንደሚመጣ ባውቅም የአምላክ አዲስ ዓለም ቀድሞ ይመጣል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ሊን አምስት ሰፋፊ ጎማ ያለው አንድ ትልቅ ተሽከርካሪ ጋሪ ገዛ። እዚህ ጋሪ ላይ ተቀምጬ ራሴን እየገፋሁ ቤት ውስጥ እዘዋወራለሁ።
እጆቼን ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ስለሚያቅተኝና በተቆለመሙትና በተቆላለፉት ጣቶቼ ዕቃ ማንሳት ስለማልችል እጆቼን ዘርግቼ አንድ ነገር ለማንሳት ሞክሬ ሲያቅተኝ በጣም እበሳጫለሁ። በዚህም የተነሳ እንደ “መያዣ” በሚያገለግል በትር መጠቀም ጀመርኩ። በዚህ በትር በመጠቀም መሬት ላይ የወደቀ ዕቃ ማንሳት፣ ቁም ሣጥን መክፈትና ሳህን ማውጣት እንዲሁም ከማቀዝቀዣ ውስጥ አንድ ነገር ማውጣት እችላለሁ። በዚህ “መያዣ” በትር የመጠቀም ችሎታዬን እያዳበርኩ ስሄድ አንዳንድ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን ቻልኩ። ማብሰል፣ የተበላባቸውን ዕቃዎች ማጠብና ማድረቅ፣ ልብሶችን መተኮስና ማጠፍ እንዲሁም ወለል ማጽዳት ለመድኩ። ችሎታዬ እየተሻሻለ ሲመጣ የኩራት ስሜት ተሰማኝ። አሁንም ቢሆን ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ በመቻሌ ደስ ይለኛል። ይሁን እንጂ በፊት በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ማከናወን እችል የነበረው ሥራ አሁን ግን ረዥም ሰዓት ይወስድብኛል።
በስልክ መመሥከር
ጊዜ ቢወስድብኝም በስልክ ለመመሥከር የሚያስችል ችሎታና ድፍረት አገኘሁ። በስልክ መመሥከር እችላለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር። አሁን ግን በጣም የምደሰትበት ሥራ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ፍሬ አግኝቼበታለሁ። እንዲያውም ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች ከመናገር የተለየ ሆኖ አይታየኝም።
ውይይት ለመክፈት የምጠቀምበት አንደኛው መንገድ ይህን ይመስላል:- “ሃሎ፣ አቶ— ነዎት? ወይዘሮ ማስ እባላለሁ። ለጥቂት ደቂቃዎች ሰዎችን እያነጋገርኩኝ ነው። ጥቂት ደቂቃ ካሎት እርሶንም ላነጋግሮዎት እችላለሁ? (ብዙውን ጊዜ የሚሰጡት መልስ “ስለ ምን ጉዳይ?” የሚል ነው) በዓለም ውስጥ የሚፈጸሙትን ሁኔታዎች ማየት በጣም ያስፈራል። አይመስልዎትም? (መልስ እንዲሰጡ እጠብቃለሁ።) ስለወደፊቱ ጊዜ እውነተኛ ተስፋ ሊሰጠን የሚችለውን ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ባካፍልዎት ደስ ይለኛል።” ከዚያም የጌታን ጸሎትና ምናልባትም 2 ጴጥሮስ 3:13ን አክዬ አነብባለሁ። ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ተከታትለው እንዲረዱልኝ የአንዳንዶቹን ሰዎች ስም ለክርስቲያን እህቶች ወይም ለሊን እሰጣለሁ።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ውይይቶችን በማድረግ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ብሮሹሮችን፣ መጽሔቶችንና መጻሕፍትን ለመላክ ችዬአለሁ። አንዳንዶች በስልክ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል። ያነጋገርኳት አንዲት ሴት ለብቻዋ ብታጠና በቂ እንደሚሆን ነገረችኝ። ይሁን እንጂ ተደጋጋሚ ውይይት ካደረግን በኋላ ሁኔታዬን ነግሬያት ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እቤታችን ለመምጣት ተስማማች።
በአንድ ወቅት ስልክ ስደውል የስልክ መልእክት የሚቀበል ማሽን ሌላ ቁጥር ሰጠኝ። ሁልጊዜ የምደውለው አካባቢዬ ለሚኖሩ ሰዎች ቢሆንም ከከተማ ውጭ የሆነውን ይህን ቁጥር ከመደወል ወደኋላ አላልኩም። ስልኩን ያነሳችው ሴት ጥቂት ካነጋገረችኝ በኋላ እርሷና ባለቤቷ እውነተኛ ክርስቲያን ከሆኑ ሰዎች ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉ ገለጸችልኝ። ስለዚህ እኔ እና ሊን ከእነርሱ ጋር ለማጥናት ስንል አንድ ሰዓት ያክል ርቆ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄድን።
ስለ ይሖዋና ቃል ስለገባልን ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ለሌሎች ሰዎች በመናገር አሁንም ቢሆን ደስታና እርካታ እያገኘሁ ነው። በቅርቡ ለበርካታ ወራት ያነጋገርኳት አንዲት ሴት “ምንጊዜም ሳነጋግርሽ ተጨማሪ እውቀት እያገኘሁ እንዳለ አውቃለሁ” ብላኛለች። ለሰዎች የማካፍላቸው እውቀት ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚመራና ያካል ጉዳተኛ ብሆንም እንኳ ደስታ ሊሰጥ የሚችል መልእክት እያደረስኩ እንዳለሁ አውቃለሁ። አገልግሎቴን ከፍ ላደርግ የቻልኩባቸው ጊዜያት አሉ። ቢሆንም ከዚህ ይበልጥ ብዙ መሥራት ብችል ደስ ይለኝ ነበር። ይሖዋ እያንዳንዱ ሰው ያለበትን ሁኔታ እንደሚያውቅና አነሰም በዛ መሥራት የቻልነውን በአድናቆት እንደሚቀበል አውቃለሁ። ምሳሌ 27:11 ላይ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚለውን ቃል ዘወትር ስለማስታውስ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ከሚያረጋግጡ ሰዎች መካከል መሆን እፈልጋለሁ።
ስብሰባ መሄድ አስቸጋሪ ቢሆንብኝም በስብሰባዎች መገኘት በጣም ያበረታታኛል። ይሖዋ በመንፈሳዊ እንድናድግ የሚረዱ አስደናቂ ዝግጅቶች አዘጋጅቶልናል። እኔም ከእነዚህ ዝግጅቶች የተሟላ ጥቅም ለማግኘት እፈልጋለሁ። ሁለቱ ልጆቻችን በእውነት ውስጥ የሚመላለሱ በመሆናቸው ደስታችን የላቀ ነው! ቴሪ የተባለችው ሴት ልጃችን ጥሩ ወንድም አግብታ በጣም የምወዳቸው አራት ልጆች ወልዳለች። የልጅ ልጆቻችንም ይሖዋን የሚወዱ በመሆናቸው ልባችን በደስታ ተሞልቷል። ጀምስ የተባለው ወንዱ ልጃችን እና ሚስቱ ቱስዴይ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና ጽሕፈት ቤት በብሩክሊን ቤቴል ይሖዋን ለማገልገል መርጠዋል።
በይሖዋ ኃይል የሚመጣ ምድራዊ ገነት
ይሖዋ እንደሚያመጣ ቃል ስለገባው አስደናቂ ምድራዊ ገነት ሁልጊዜ አስባለሁ። አሁንም እንኳ ቢሆን ሊያስደስቱን የሚችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የፍጥረት ሥራዎች አሉ። ፀሐይ ስትጠልቅ መመልከት ያስደስተኛል። የተለያዩ አበቦችን መመልከትና መዓዛቸውን ማሽተት በጣም ያስደስተኛል። የጽጌረዳ አበባ እወዳለሁ! ሁልጊዜ ከቤት መውጣት ባልችልም አንዳንዴ ወጣ ስል ግን የፀሐይ ብርሃን በሚሰጠው ሙቀት እደሰታለሁ። ዓይኔን እጨፍንና በዓይነ ሕሊናዬ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ተራሮችንና በተራሮቹ ግርጌ ባለው አበቦች በተላበሰው ለጥ ባለው ሜዳ ላይ ቤተሰቦቼ በደስታ ሲጫወቱ እመለከታለሁ። እየተንዶለዶለ የሚወርድ ጅረትና ሁሉም ሰው ጣፋጭ የከርቡሽ ጭማቂ ሲጠጡ በዓይነ ሕሊናዬ እመለከታለሁ! አንዳንዴ ሻል ሲለኝ ወደፊት የሚመጣውን ምድራዊ ገነት እንዳስብ የሚረዱኝን የተለያዩ ሥዕሎች እስላለሁ። በምስልበት ጊዜ እዚያ ውስጥ እንዳለሁ አድርጌ አስባለሁ። አሁን በዓይነ ሕሊናዬ የማያቸውን ነገሮች ይሖዋ እውን ሊያደርጋቸው እንደሚችል አውቃለሁ።
ያዕቆብ 1:12 ላይ ያለውን ጥቅስ ሁልጊዜ አስባለሁ። እንዲህ ይላል:- “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።” ጳውሎስ የነበረበትን ሕመም ‘በሚጎስመው የሰይጣን መልእክተኛ’ መስሎታል። ያለበትን ድካም እንዲያስወግድለት ይሖዋን ጠይቆት ነበር። ሆኖም በእርሱ ድካም የአምላክ ኃይል ፍጹም እንደሚሆን ነገረው። ስለዚህ ጳውሎስ ድካም እያለበት የተሳካ አገልግሎት ለማከናወን መቻሉ የአምላክ ኃይል በእርሱ ላይ ይሠራ እንደነበረ አረጋግጧል። ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 12:7-10) ባለኝ የአቅም ውስንነት ይህችኑ አነስተኛ አገልግሎት ማከናወን የቻልኩት በአምላክ ኃይል እንደሆነ ይሰማኛል።
ዮሐንስ የመዘገበው መግለጫ በእርግጥም ያበረታታኛል። ከልጅነቱ ጀምሮ ለ38 ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ስለሆነ አንድ ሰው ይናገራል። እርሱና ሌሎች በሽተኞች በጉድጓድ ውኃው ለመነከር በጣም ይመኙ ነበር። ይፈውሰኛል ብሎ በሚያስበው ውኃ ውስጥ ለመግባት ግን አልቻለም። አንድ ቀን ኢየሱስ አየውና “ልትድን ትወዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ይህ ጥያቄ ለእኔም ቀርቦ ቢሆን ኖሮ እንባ በተቀላቀለበት ደስታ እመልስ ነበር! “ኢየሱስ:- ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው።” (ዮሐንስ 5:2-9) እንዲህ ያለውን ጥሪ ለመስማት በናፍቆት የምንጠባበቅ በርካታ ሰዎች አለን!—ሉሬታ ማስ እንደተናገረችው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የደስታ ስሜት ተሰምቶኝ በነበረበት ጊዜ ውሻው ከበታቹ ሆኖ ምርኩዝ ላይ ቆሞ እየተራመደ ስለሚሄድ ጀብደኛ ልጅ በዓይነ ሕሊናዬ ሳልኩ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመስክ አገልግሎት የሚሆነኝን የስልክ ቁጥር ስፈልግ
ስልክ ስደውል