ለኑሮ የሚበጅ ትምህርት የያዘ መጽሐፍ
በአፍሪካ ውስጥ በዚምቧቤ የሚኖር አንድ አስተማሪ በሚያስተምርበት በናይትሲም ኮሌጅ “ለኑሮ የሚበጅ ትምህርት” በሚል ርዕስ ንግግር በተሰጠበት ወቅት ይህን መጽሐፍ ጠቁሟል። በቤተሰቡ ውስጥ ያጋጠሙትን ችግሮች ከገለጸ በኋላ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል እርዳታ ያስፈልገው እንደነበር አምኗል።
በትዳሩ ውስጥ ያጋጠመውን ሲገልጽ “ችግሮች ብቅ ማለት የጀመሩት ወዲያው ነበር ለማለት ይቻላል፤ በመሆኑም በኅዳር 1989 ለመለያየት ወሰንን” ብሏል። ሌሎች ችግሮችም ነበሩት። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለአባቴ የመጀመሪያ ሚስት የበኩር ልጅ ነበርኩ። በአስተማሪዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ አባቴ 16 ታናናሽ ወንድሞቼንና እህቶቼን ጥሎብኝ ሞተ።”
ይህ አስተማሪ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ የቤተሰቡን ችግሮች ለመፍታት አስችሎታል። እሱና ባለቤቱ እንደገና አብረው በደስታ መኖራቸውን ቀጥለዋል። “እኔና ባለቤቴ ሰው ያለ አምላክ እርዳታ የራሱን ችግሮች ለመፍታት የሚያደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ ከንቱ ልፋት መሆናቸውን ከራሳችን መከራ የተሞላበት ተሞክሮ ተምረናል” ሲል ጽፏል። ታዲያ ተማሪዎቹ ችግሮቻቸውን እንዲቋቋሙ ለመርዳት ምን አድርጓል?
“ርዕሰ መምህራንና ሌሎች አስተማሪዎች ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ እንደማስተማሪያ መጽሐፍ አድርገው እንዲጠቀሙበት አበረታታኋቸው” ሲል ጽፏል። “ሁሉም ተስማሙ፤ ትምህርት ቤቱ 56 መጻሕፍት አዘዘና እነዚህን መጻሕፍት አመጣሁላቸው።”
ይህ በማራኪ ሥዕሎች የተደገፈ ባለ 320 ገጽ ትምህርት ሰጭ መጽሐፍ ለአንተም በጣም እንደሚጠቅምህ እናምናለን። የዚህን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ማግኘት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ማጥናት የምትፈልግ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖ. ሣ. ቁ. 5522፣ አዲስ አበባ ብለህ ወይም በገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደ ሆነው ጻፍ።