አዝጋሚ ለውጥ ተጨባጭ ሐቅ አይደለም
ብዙ አሜሪካውያን የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በቀጥታ በአምላክ መፈጠራቸውን እንጂ ከዝቅተኛ ሕያዋን ነገሮች በአዝጋሚ ለውጥ ሂደት መፈጠራቸውን እንደማያምኑ የሕዝብ አስተያየቶች ጠቁመዋል። ታዲያ አሜሪካ ውስጥ ያሉ በርካታ የሳይንስ መምህራን የማንም ወገን የማሰብ ችሎታ ያልታከለበትና በአጋጣሚ የተገኘ ነው የሚባለውን አዝጋሚ ለውጥ እንደ ተጨባጭ ሐቅ አድርገው የሚያስተምሩት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት “ፅንፈኛ ዳርዊናውያን . . . በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙትን የሳይንስ ክፍሎች ስለሚቆጣጠሩ ነው” ሲሉ በርክሌይ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ፊሊፕ ኢ ጆንሰን ተናግረዋል።
ጆንሰን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “በአንዳንድ አጋጣሚዎች የስነ ሕይወት መምህራን የማንም ወገን የማሰብ ችሎታ ሳይታከልበት የቁስ አካል ሂደቶች አስደናቂ የሆነውን ስነ ሕይወት ሊያስገኙ እንደሚችሉና እንዳስገኙም የሚሰጠውን መግለጫ አጠራጣሪ የሚያደርጉ ምንም ዓይነት ምክንያቶች መኖራቸውን ለተማሪዎቻቸው እንዳይነግሩ ተከልክለዋል።”
የሳይንስ ሊቅና መሐንዲስ የሆኑት መርፊ ኦዴን እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “‘የአዝጋሚ ለውጥ ሳይንስ’ ትክክል ያልሆነን ንድፈ ሐሳብ ከመሻር ይልቅ ‘አዝጋሚ ለውጥ ትክክል መሆን አለበት’ የሚል የእምነት ጎዳና ለመከተል መርጧል” ብለዋል። ይህን የሚቃረኑ ማስረጃዎች ብቅ ሲሉ ወይም ማስረጃዎች ሲጠፉ አንድም ጉዳዩ ቸል ተብሎ ይታለፋል አሊያም እንደምንም ተምታትቶና ተድበስብሶ ይቀራል።
ለምን? የሞለኪላዊ ስነ ሕይወት ሊቅ የሆኑት ማይክል ቤ ዳርዊንስ ብላክ ቦክስ በተባለው መጽሐፍ ላይ “እውቅ የሆኑና ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ብዙ የሳይንስ ሊቃውንትን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ተጨባጭ ከሆኑት ነገሮች ውጭ ሌላ ነገር አለ ብለው ማመን አይፈልጉም። ከሰው በላይ ኃይል ያለው አካል በተፈጥሮ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ አይፈልጉም” ብለዋል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ሳይንስ ይሻላሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ለማራመድ ሲል ተቃራኒ የሆኑ ማስረጃዎችን ገሸሽ አያደርግም። ደግሞም በአዝጋሚ ለውጥ የሚያምኑት ሁሉም የሳይንስ ሊቃውንት አይደሉም።
በብራዚል የሚታተመው ቬዛ መጽሔት በፊዚክስ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ለሆኑት ለካርሎ ሩቢያ “በአምላክ ያምናሉ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ምንም እንኳ የራሱ ባሕርያት ያሉት አምላክ ስለመኖሩ ባይገልጹም እንዲህ ሲሉ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል:- “ስለ ተፈጥሮ ይበልጥ ባወቃችሁ መጠን በሁሉም ነገሮች ረገድ አስገራሚ ቅንብር መኖሩን ትገነዘባላችሁ። ታላቅ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ከመሆናቸው የተነሣ የተፈጥሮ ክስተቶችን በመመልከት ብቻ ፈጣሪ አለ የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ።”
እርሳቸው የተናገሩት ነገር ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አምላክ የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሰናል:- “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።”—ሮሜ 1:20