የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 10/8 ገጽ 26-28
  • ሐሳቤን ማሰባሰብ የማልችለው ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐሳቤን ማሰባሰብ የማልችለው ለምንድን ነው?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በለውጥ ሂደት ላይ ያለው አስተሳሰብህ
  • ስሜቶችና ሆርሞኖች
  • የእንቅልፍ ልማድህ
  • ምግብና ሐሳብን ማሰባሰብ
  • የቴሌቪዥንና የኮምፒዩተር ትውልድ
  • አእምሮዬ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—1998
  • የጉርምስና ዕድሜ​—ሙሉ ሰው ለመሆን ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት
    ንቁ!—2011
  • በሰውነቴ ላይ የማየው ለውጥ ምንድን ነው?
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2
  • ተጨማሪ ክፍል—ወላጆች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች
    ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 1
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 10/8 ገጽ 26-28

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

ሐሳቤን ማሰባሰብ የማልችለው ለምንድን ነው?

“አንዳንድ ጊዜ ድንገተኛ ነው። በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ እያዳመጥኩ ሳለሁ ከመቅጽበት አእምሮዬ ሽርሽር ይጀምራል። ከአሥር ደቂቃ በኋላ እባንናለሁ።”—ጄሲ

“አዳምጥ!” አስተማሪዎችህ ወይም ወላጆችህ ብዙ ጊዜ እንደዚያ ይሉሃልን? ከሆነ ምናልባት አእምሮህን በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር የማድረግ ችግር ይኖርብህ ይሆናል። ከዚህ የተነሣ የትምህርት ውጤትህ ዝቅተኛ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ለአንተ አሉታዊ አመለካከት እንዳላቸውና የአጉል ልማድ ሱሰኛ ወይም ሥርዓት አልባ እንደሆንክ አድርገው እንደሚመለከቱህ ተገንዝበህ ይሆናል።

ከሁሉ በላይ ደግሞ በትኩረት መከታተል አለመቻል በመንፈሳዊነትህ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ” በማለት ያዛል። (ሉቃስ 8:18) እንዲያውም ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ነገሮች ‘አብልጠው እንዲጠነቀቁ’ ታዝዘዋል። (ዕብራውያን 2:1) ሐሳብህን ማሰባሰብ የሚቸግርህ ከሆነ ይህንንም ምክር መከተል ይከብድህ ይሆናል።

ችግሩ ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንድ ጊዜ ሐሳባችንን ሰብሰብ አድርገን በአንድ ነገር ላይ ማተኮር የሚያቅተን በአካላዊ እክል ምክንያት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ተመራማሪዎች ሐሳብን የማሰባሰብ ችግር [አቴንሽን ዲፊሲት ዲስኦርደር] ከአእምሮ የነርቭ መልእክት ዝውውር መዛባት ጋር የተያያዘ ነው ብለው ያምናሉ።a አንዳንድ ልጆች ሳይታወቅ የመስማት ወይም የማየት ችግር ይኖርባቸዋል። እነዚህም ቢሆኑ ሐሳብን ሰብሰብ አድርጎ በትኩረት መከታተልን አስቸጋሪ ሊያደርጉት ይችላሉ። ተመራማሪዎች እንደደረሱበት ከሆነ በአጠቃላይ ሲታይ ከአዋቂዎች ይልቅ ሐሳብን የማሰባሰብ ችግር ያለባቸው ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም በሐሳብ መባዘን በወጣቶች ዘንድ በሰፊው የሚታይ ነገር ነው። ይሁንና ሁልጊዜ ከጤና እክል ጋር የተያያዘ ነው ማለት አይደለም።

በለውጥ ሂደት ላይ ያለው አስተሳሰብህ

ሐሳብህን የማሰባሰብ ችግር ካለብህ የምታደርገው የእድገት ለውጥ ያስከተለው ውጤት እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፣ እንደ ልጅም አስብ ነበር፣ እንደ ልጅም እቈጥር [“እመራመር፣” የ1980 ትርጉም] ነበር፤ ጒልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:11) አዎን፣ ሙሉ ሰው ወደ መሆን እያደግህ ስትሄድ የምታስብበት መንገድ ይለወጣል። አዶለሰንት ዴቨሎፕመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ከሆነ “በመጀመሪያዎቹ የጉርምስና ዓመታት . . . ከሐሳብ ጋር የተያያዙ አዳዲስ ችሎታዎች ብቅ ማለት ይጀምራሉ።” ስውር የሆኑ ሐሳቦችንና ጽንሰ ሐሳቦችን የመረዳትና የማገናዘብ ችሎታ ታዳብራለህ። ስለ ሥነ ምግባር፣ ግብረገብነት እንዲሁም ስለ ሌሎች ሰፋ ያሉ ጉዳዮች ጥልቀት ያለው ግንዛቤ ማግኘት ትጀምራለህ። ወደ ፊት ትልቅ ሰው ስትሆን ስለሚኖርህ ሁኔታ ታስባለህ።

ታዲያ ችግሩ ምን ላይ ነው? እነዚህን ሁሉ አዳዲስ ሐሳቦችና ጽንሰ ሐሳቦች በአእምሮ ዙሪያ ማስተናገድ ሐሳብህ በቀላሉ እንዲሠረቅ ሊያደርግ ይችላል። ከእንግዲህ እንደ ልጅ ቀላልና መሠረታዊ ስለሆኑ ነገሮች ብቻ ማሰብህን ታቆማለህ። ከዚህ በኋላ አእምሮህ የምታየውንና የምትሰማውን ነገር ሁሉ እንድትገመግምና ስለዚያ እንድትጠይቅ ያስገድድሃል። አንድ አስተማሪ ወይም ተናጋሪ የሚሰነዝረው አስተያየት የአእምሮ ሽርሽር እንድትጀምር ሊያደርግህ ይችላል። ሐሳብህ እንዳይባዝን መቆጣጠር ካልቻልክ ግን በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦች ሊያመልጡህ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ጻድቅ ሰው የነበረው ይስሐቅ በፀጥታ ለማሰላሰል ጊዜ ይመድብ እንደነበር የሚናገረው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው። (ዘፍጥረት 24:63) ምናልባትም በየዕለቱ ዘና ብለህ ማሰላሰልህና ነገሮችን በአእምሮህ ውስጥ መልክ መልክ እንዲይዙ ማድረግህ በሌላ ጊዜ ትኩረትህ እንዳይሰረቅ ሊረዳህ ይችላል።

ስሜቶችና ሆርሞኖች

ስሜቶችህም ሐሳብህ እንዲሰረቅ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በምታነብበው ወይም በምትሰማው ነገር ላይ ለማተኮር ስትጥር ሐሳብህ ድንገት በሌሎች ነገሮች ይሰረቃል። አንዳንድ ጊዜ ሁሉ ነገር ያስጠላህ ወይም ጭንቅ ይልህ ይሆናል፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ደስ ደስ ይልህ ወይም ፍንድቅድቅ ትል ይሆናል። አትረበሽ! ልታብድ ነው ማለት አይደለም። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ሆርሞኖችህ ናቸው። ለአካለ መጠን እንደደረስክ የሚያመላክቱትን ለውጦች እያስተናገድህ ነው ማለት ነው።

ኬቲ ማኮይ እና ቻርልስ ዊብልስመን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጉርምስና ወቅት የተለያዩ ስሜቶች ይፈራረቃሉ። . . . ይህ የባሕርይ መለዋወጥ በተወሰነ መጠን ወደ ጉርምስና የመግባታችሁ ምልክት ነው። ለዚህ በከፊል አስተዋጽኦ የሚያደርገው በአሁኑ ጊዜ የገጠሟችሁ ለውጦች የሚፈጥሩት ውጥረት ነው።” ከዚህም በተጨማሪ የፆታ ፍላጎት ወደሚያይልባቸው ‘አፍላ የጉርምስና’ ዓመታት እየተቃረባችሁ ነው ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) ሩዝ ቤል ደግሞ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ለአካለ መጠን በሚደርሱበት የዕድሜ ክልል ውስጥ በሰውነት ላይ የሚታዩት ለውጦች ብዙውን ጊዜ ጠንካራ የፆታ ፍላጎት እንዲፈጠር ያደርጋሉ። አንዳንድ ጊዜ ስለ ፆታ ብዙ እንደምታስብ፣ የፆታ ስሜትህ በቀላሉ እንደሚቀሰቀስ አልፎ ተርፎም ስለ ፆታ በማሰብ ብቻ እንደምትጠመድ ታስተውል ይሆናል።”b

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ጄሲ በአሥራዎቹ ዕድሜ ባሉ ወጣቶች ዘንድ የተለመደው የአእምሮ ሽርሽር ያጋጥመዋል። “አንዳንድ ጊዜ ስለ ሴቶች አስባለሁ ወይም ደግሞ ስላስጨነቀኝ ወይም በኋላ ልሠራው ስለምፈልገው ነገር አስባለሁ።” የኋላ ኋላ ይህ የስሜት ማዕበል ይሰክናል። እስከዚያው ድረስ ግን ራስህን መገሰጽን ተማር። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) ስሜትህን ይበልጥ መቆጣጠር በተማርክ መጠን ሐሳብህን ሰብሰብ የማድረግ ችሎታህም ይጨምራል።

የእንቅልፍ ልማድህ

በአካል እየጎለመስህ እንድትሄድ ለመርዳት እንዲሁም አእምሮህ በየዕለቱ የሚመጡለትን አዳዲስ ሐሳቦችና ስሜቶች ለማስተናገድ እንዲችል ለማድረግ እያደገ ያለው አካልህ በቂ እንቅልፍ ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉት ብዙ ወጣቶች ለእንቅልፍ የሚመድቡት ጊዜ በጣም ትንሽ ነው። አንድ ኒውሮሎጂስት እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ሰውነታችን ያለብንን የእንቅልፍ ዕዳ አይረሳም። ይልቁንም በየጊዜው ሲያጠራቅም የቆየውን ዕዳ የመርሳት ችግር በማስከተል፣ ሐሳብ የማሰባሰብ ችግር በመፍጠር እንዲሁም የማሰብ ችሎታን ፍጥነት በመቀነስ በድንገት ይጠይቀናል።”

አንዳንድ ተመራማሪዎች በእያንዳንዱ ምሽት አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ተጨማሪ እንቅልፍ ማግኘት ሐሳብን የማሰባሰብ ችሎታችንን እንደሚያሻሽለው ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስንፍናንም ሆነ እንቅልፍ ወዳድ መሆንን እንደማያበረታታ ግልጽ ነው። (ምሳሌ 20:13) ይሁን እንጂ የተቀላጠፈ ሥራ ለመሥራት ጥሩ እረፍት ማግኘት ያስፈልጋል የሚለው ሐሳብ ምክንያታዊ ነው።—መክብብ 4:6

ምግብና ሐሳብን ማሰባሰብ

ሌላው ችግር ደግሞ ምግብ ሊሆን ይችላል። ስብነትና ስኳርነት ያላቸው ምግቦች በአሥራዎቹ ዓመት ዕድሜ ውስጥ ባሉ ልጆች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው። ከፍተኛ የካሎሪ መጠን ኖሯቸው የገንቢነት ይዘታቸው አነስተኛ የሆኑ ምግቦች የሚጣፍጡ ቢሆኑም የአእምሮን ንቃት ይቀንሳሉ። በተመሳሳይም እንደ ዳቦ፣ ጥራጥሬ፣ ሩዝ ወይም ፓስታ የመሳሰሉትን ካርቦሃይድሬት ያላቸው ምግቦች ከተመገቡ በኋላ የአእምሮአችን የመሥራት አቅም እንደሚዳከም ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይህ የሚሆነው ካርቦሃይድሬት በአእምሮአችን ውስጥ ያለውን ሴሮቶኒን የሚባለውን ኬሚካል መጠን በመጨመር ሰውየው እንቅልፍ እንቅልፍ እንዲለው ስለሚያደርግ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም አንዳንድ የስነ ምግብ ተመራማሪዎች የአእምሮ ንቃት የሚጠይቅ ማንኛውንም ሥራ ከመሥራታችን በፊት ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያላቸውን ምግቦች መመገቡ ጥሩ እንደሚሆን ሐሳብ ይሰጣሉ።

የቴሌቪዥንና የኮምፒዩተር ትውልድ

ምሁራን ለበርካታ ዓመታት ቴሌቪዥንና በፍጥነት የሚንቀሳቀሱት ምስሎቹ የወጣቶችን በአንድ ነገር ላይ የማተኮር ችሎታ ያዳክማል በማለት መናገር ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ዛሬ ደግሞ በኮምፒዩተርም ላይ ተመሳሳይ ወቀሳ እየሰነዘሩ ነው። እነዚህ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በወጣቶች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ነው የሚለው ጉዳይ ገና ምሁራን ራሳቸው ስምምነት ላይ ያልደረሱበት ነገር ቢሆንም ቴሌቪዥን በመመልከት ወይም የኮምፒዩተር ጨዋታዎችን በመጫወት ከልክ ያለፈ ጊዜ ማጥፋት ለጤና ይበጃል ማለት ግን ዘበት ነው። አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “እንደ ቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ኮምፒዩተርና ኢንተርኔት ያሉት ነገሮች የምንፈልገውን ነገር ቶሎ የማግኘት ፍላጎት ቀርጸውብናል።”

ችግሩ በሕይወት ውስጥ ብዙ ነገሮችን ማግኘት የሚቻለው በጥረት፣ በጽናትና ዘመን እንዳለፈበት ተደርጎ በሚታየው ትዕግሥት በማሳየት ብቻ ነው። (ከዕብራውያን 6:12፤ ያዕቆብ 5:7 ጋር አወዳድር።) እንግዲያውስ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር በፍጥነት የሚንቀሳቀስና የሚያዝናና ነገር ብቻ ነው ብለህ ፈጽሞ አታስብ። ቴሌቪዠን መመልከትም ሆነ የኮምፒዩተር ጨዋታዎችን መጫወት የሚያዝናና ነገር ቢሆንም ለምን ስዕል መሳልን ወይም የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጫወትን አትማርም? እንደነዚህ ያሉት ችሎታዎች ሐሳብን የማሰባሰብ ኃይልህን ሊያዳብሩልህ ይችላሉ።

ሐሳብን የማሰባሰብ ኃይል የምታዳብርባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖራሉን? አዎን አሉ። ወደፊት የሚወጣው ርዕስ እነዚህን ዘዴዎች የሚጠቁም ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የሚከተሉትን ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትሞች ተመልከት:- ኅዳር 22, 1994 ገጽ 3–12፤ ሰኔ 22, 1996 ገጽ 11–13፤ እንዲሁም የካቲት 22, 1997 ገጽ 5–10

b በነሐሴ 8, 1994 (የእንግሊዝኛ) ንቁ! ላይ የወጣውን “ሁልጊዜ ስለ ተቃራኒ ፆታ ከማሰብ መቆጠብ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ተመልከት።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ በክፍል ውስጥ ሐሳብህን ማሰባሰብ ያስቸግርሃል?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከፍተኛ የካሎሪ መጠን ኖሯቸው የገንቢነት ይዘታቸው አነስተኛ የሆኑ ምግቦች የአእምሮን ንቃት እንደሚቀንሱ ተመራማሪዎች ይናገራሉ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አንዳንድ ጊዜ ስለ ሴቶች ወይም ስላስጨነቀኝ . . . ነገር አስባለሁ”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ