ጣዕም የመለየት ችሎታ አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ
ጣዕም የመለየት ችሎታን በሚመለከት ምርምር በማካሄድ የሚታወቁት ሊንዳ ባርቶሽክ “ጣዕም የመለየት ችሎታ [የአምስቱ] የስሜት ሕዋሳት ንጉሥ ነው” ብለዋል። ጣዕም የመለየት ችሎታ ጠቃሚውን ከጎጂው እንድንለይ በማድረግ ከችግር የሚጠብቀን አስደሳች የስሜት ሕዋስ ነው።
የበሰለውን ብርቱካን፣ የሜንታ ጣዕም ያለውን የሚያረካ ቅዝቃዜ ያለው ጀላቲ፣ በጠዋት ነቃ የሚያደርግ አንድ ስኒ ወፍራም ቡና እንዲሁም አንድ የወጥ ቤት ባለሙያ የሚጠቀምበትን ማጣፈጫ እንድናጣጥም የሚያስችለን ድንቅ የሆነው ጣዕም የመለየት ችሎታችን ነው። ጣዕም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር ከመሆኑ የተነሣ በአንዳንድ ቋንቋዎች የሰዎች ባሕርይ መግለጫ ሆኖ ያገለግላል።
ምናልባትም ቃላቸው የሚጣፍጥ ደስ የሚሉ ሰዎች ታውቅ ይሆናል። በአንጻሩ ደግሞ ምን ነው ይህ ሰው ፊቱ ኮሶ መሰለ ብለህ ታውቅ ይሆናል። በሌሎች ላይ ቂም የሚይዝ ሰው መራራ እንደሆነ ተደርጎ ይገለጻል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ “በነፍሳቸው መራራ” ስለሆኑ ሰዎችና ስለ “መራራ ቃል” ይናገራል።—መሳፍንት 18:25 NW፤ መዝሙር 64:3 NW፤ 2 ሳሙኤል 17:8
ጣዕም የመለየት ችሎታና የዓለም ታሪክ
በ15ኛውና በ16ኛው መቶ ዘመን ለተደረጉት የአሰሳ ጉዞዎች ዋነኛው ምክንያት የጣዕም ጉዳይ ነበር። ከዛሬ 500 ዓመታት በፊት ቫስኮ ዳ ጋማ በአፍሪካ ጫፍ ዞሮ ሕንድ ከደረሰ በኋላ ብዙ ቅመማ ቅመሞችን ጭኖ ወደ ፖርቹጋል ተመልሷል። ከዚያ በኋላ ባሉት ሦስት መቶ ዘመናት እንደ ፈረንሳይ፣ ታላቋ ብሪታንያ፣ ሆላንድ፣ ፖርቹጋልና ስፔይን ያሉት የአውሮፓ አገሮች ቅመም የሚገኝባቸውን ምንጮች ለመቆጣጠር ሲሉ ተሻኩተዋል።
‘መንግሥታት ለቅመማ ቅመሞች ይህን ያህል የሚጋደሉት ለምንድን ነው’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የጣዕም ፍላጎትን ለማርካት ነው! አዎን፣ አውሮፓውያን ለቅመማ ቅመሞች ጣዕም የነበራቸው ፍላጎት ያን ያህል ጠንካራ ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ ዘመናዊው ኢንዱስትሪ፣ ንግድና፣ ሳይንስ የጣዕምን ፍላጎት ለማርካት ተሰልፈዋል።
ይሁንና ጣዕም የመለየት ችሎታ ምንድን ነው? ከሌሎች የስሜት ሕዋሶቻችን ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራውስ እንዴት ነው?
ምላስ የሚጫወተው ሚና
ጣዕም በመለየት ረገድ ትልቁን ሚና የሚጫወተው ምላሳችን ነው። አብዛኞቹ የማጣጣሚያ ቀንበጦች (taste buds) የሚገኙት በምላስ ላይ ነው። በአፍ ውስጥ ባሉ ሌሎች ክፍሎችና በጉሮሮም ላይ ይገኛሉ። እስቲ ወደ መስተዋት ጠጋ በልና ምላስህን በደንብ ተመልከተው። ምላስህን ለስላሳ ምንጣፍ ያስመሰሉትን ትናንሽ ጉጥ ነገሮችን ልብ ብለህ ተመልከት። እነዚህ ፓፒሌ ይባላሉ። በምላሳችን ላይ በብዛት ከሚገኙት እነዚህ ትናንሽ ጉጥ መሰል ነገሮች መካከል ጥቃቅን ቀንበጦች ጥቅጥቅ ብለው ይገኛሉ። ሳይንስ መጽሔት እንዳለው ከሆነ “እያንዳንዱ ቀንበጥ እስከ 100 የሚደርሱ የጣዕም መለያ ሕዋሳት ሲኖሩት ለሥራ የሚቀሰቅሳቸው ነገር ካገኙ መልእክቱን ለነርቭ ሕዋሳት በማስተላለፍ ለአንጎል እንዲደርስ ያደርጋሉ።”
የማጣጣሚያ ቀንበጦቹ ቁጥር ከሰው ወደ ሰው በእጅጉ ሊለያይ የሚችል ሲሆን ይህም ጣዕም በመለየት ችሎታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል። የሰው ልጅ ምላስ ቢበዛ እስከ 10,000 ወይም ቢያንስ 500 የሚሆኑ የማጣጣሚያ ቀንበጦች ይኖሩታል። የማጣጣሚያ ቀንበጦችን አናቶሚ ያጠኑት ኢሊስ ሚለር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ብዙ የማጣጣሚያ ቀንበጥ ያላቸው ሰዎች ይበልጥ ጣዕሞችን መለየት የሚችሉ ሲሆን ቁጥሩ ሲቀንስ የማጣጣም ችሎታቸውም ይቀንሳል።”
ጣዕም የመለየት ችሎታ የሚሠራው እንዴት ነው?
ጣዕም የመለየት ችሎታ እጅግ ውስብስብ የሆነ የስሜት ሕዋስ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የኬሚስትሪ ጉዳይ ነው። በአፋችን ውስጥ ከገባው ምግብ የተፈጠሩት ኬሚካላዊ ምንዝሮች (chemical components) በምላሳችን ላይ በሚገኙት ቀዳዳዎች ላይ ብቅ ብቅ ያሉትን ጣዕም ተቀባይ ሕዋሳት ያነሳሳሉ። እነዚህ ሕዋሳት በተራቸው ሕዋሰ ነርቮችን በማነቃቃት ከማጣጣሚያ ቀንበጦች ወደ አንጎል መልእክት እንዲተላለፍ ያደርጋሉ።
የሚያስገርመው አንዷ ማጣጣሚያ ቀንበጥ የተለያዩ ሕዋሰ ነርቮችን ልታነቃቃ የምትችል ሲሆን አንድ ሕዋሰ ነርቭ ደግሞ ከተለያዩ ማጣጣሚያ ቀንበጦች መልእክት ሊቀበል ይችላል። ጣዕም ተቀባዮቹ ሕዋሳትና ውስብስብ የሆነው አሠራራቸው አንዱን ጣዕም ከሌላው እንዴት እንደሚለዩት የሚያውቅ የለም። ዚ ኢንሳይክለፒዲያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው በአንጎል ውስጥ አንድ ዓይነት ስሜት የሚፈጠረው ተቀባይ ሕዋሳቱ በሚያስተላልፏቸው የኤሌክትሪካዊ ግፊት ውስብስብ ኮዶች አማካኝነት ነው።”
አንድን ነገር አጣጥመን በመለየት ረገድ ሌሎች ሕዋሳትም የሚጫወቱት ሚና አለ። ዘ ኒው ቡክ ኦቭ ፖፒውለር ሳይንስ የተባለው መጽሐፍ “አንዳንድ ጊዜ አንድን ነገር እያሸተትነው ይሁን ወይም አፋችን ውስጥ እያጣጣምነው መለየት አስቸጋሪ ይሆናል” ብሏል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ዳቦ መጋገሪያ በኩል ስናልፍ የትኩስ ዳቦ ሽታ ያውደን ይሆናል። አፋችን ምራቅ ይሞላል። ከዚያም ወደ ዳቦ ቤቱ ገብተን ዳቦውን እናየዋለን ምናልባትም በእጃችን ነካ ነካ እናደርገው ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ስሜታችን ይበልጥ ይነሳሳና ዳቦውን ግመጠው ግመጠው ያሰኘናል!
እንግዲያው ይህ የማጣጣም ስሜት ምንድን ነው? ኦምኒ የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ያስረዳል:- “ሌላው ሰው ጣዕም የሚለው ነገር የተለያዩ የስሜት ሕዋሳት ማለትም መዓዛን፣ ቅምሻን፣ መዳሰስን፣ መሻከርና መለስለስን፣ ማየትን፣ ኬሚካላዊ ነገሮችን (የበርበሬ ማቃጠልን፣ የጀላቲ ቅዝቃዜን) እና የሙቀት ሁኔታን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።”
በሌላ በኩል ግን ጽሑፉ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “ጣዕም . . . በጣም ቀላል ነገር ነው። ጣዕም በአራት ዓይነት (በአራት ብቻ) ይከፈላል። እነዚህም ጣፋጭ፣ ጨዋማ፣ ጎምዛዛና መራራ ናቸው።” ምንም እንኳን የተለያዩት የምላስ ክፍሎች የተለያዩ ጣዕሞችን እንደሚለዩ አድርጎ መከፋፈል የተለመደ ነገር ቢሆንም በየትኛውም የምላስ ክፍል ላይ የሚገኘው እያንዳንዱ የማጣጣሚያ ቀንበጥ ከእነዚህ መካከል ከሁለት በላይ የሚሆኑትን ወይም ሁሉንም ለማጣጣም እንደሚችል በአሁኑ ጊዜ ይታመናል።
ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ጣዕም የመለየት ችሎታን ኬሚስትሪ በተመለከተ ገና ግልጽ ያልሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል ጎምዛዛ ከሆነ የሎሚ ጭማቂ ጥቂት ጠብ ስናደርግ የምግቡን ጨዋማነት የሚጨምረው ለምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። እንዲሁም እንደ ጣፋጭ፣ ጎምዛዛና ጨዋማ ጣዕም ያላቸው ነገሮች በጣዕም መለያ ሕዋሳት ውስጥ ኤሌክትሪካዊ መልእክት እንዲተላለፍ የሚያደርጉ ሲሆን መራራ ጣዕም ያላቸው ነገሮች ደግሞ በእነዚሁ ሕዋሳት ውስጥ እንዲተላለፍ የሚያደርጉት መልእክት ኬሚካላዊ መሆኑ ሌላው ትኩረት የሚስብ ነገር ነው።
አንድን ጣዕም መልመድ
ለመጀመሪያ ጊዜ ስትቀምሳቸው ያልወደድካቸውን ጣዕሞች ከጊዜ በኋላ እንደለመድካቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ከነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የወይራ ፍሬ፣ ብሉ ቺዝ፣ የሚያቃጥሉ ቅመሞችና ሌሎች መራራ ምግቦች ሊሆኑ ይችላሉ። ከጥንት ጀምሮ እንደ ኤንዳይቭ እንዲሁም ቺኮሪ ያሉት ‘መራራ ቅጠሎች’ ለምግቦችና ለሰላጣዎች ልዩ ጣዕም ለመጨመር ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ መራራ ነገር እንድትለምድ ጣዕም የመለየት ችሎታህ ሊሰለጥን ይገባል።—ዘጸአት 12:8
የአንድን ምግብ ጣዕም መልመድ ያንን ምግብ ከምትመገብበት ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለምሳሌ ያህል አንዲት ሴት ቦሎኛ የተባለውን ምግብ ጨርሶ ቀምሳ አታውቅም። እናቷ ለዚህ ምግብ ከፍተኛ ጥላቻ ስለነበራት ልጅቷ ገና ስታየውም ሆነ ሲሸታት ያንገፈግፋት ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለች በጣም ይርባትና ከቦሎኛ በቀር የሚበላ ነገር ታጣለች። ከዚያም ትንሽ ስትቀምሰው ጣዕሙን በመውደዷ በጣም ተገረመች!
በመሆኑም አንድን አዲስ ጣዕም ለመልመድ የምትፈልግ ከሆነ እርቦህ እያለ ቅመሰው። ወላጅ ከሆናችሁ ደግሞ ለአንዳንድ ምግቦች እናንተ የምታሳዩት ስሜት እነዚህን ምግቦች ለልጆቻችሁ የምታስተዋውቁበት ሁኔታ በልጆቻችሁ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አትዘንጉ። አዳዲስ ምግቦችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታስተዋውቋቸው ደስ የሚል ሁኔታ ለማስፈን ጣሩ። ልጆቻችሁ እንዲሳተፉ አድርጉ። አንድ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:-
“ምግብ በምታዘጋጁበት ጊዜ ሕፃን ልጃችሁን ማዕድ ቤት ውስጥ በጋሪው አድርጋችሁ አስቀምጡት። ደስ በሚልና በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ የቤተሰቡን ምግብ የሚያይበትና የሚያሸትበት አጋጣሚ ይሆንለታል። ሌላው ቀርቶ እነዚህን ምግቦች መብላት በማይችልበት ዕድሜ ላይ እንኳን ሳለ ስለ ምግቦቹ ሊማር ይችላል። ከጥቂት ወራት በኋላ ከምታበስሉት ምግብ ላይ ጥሬውን ወይም በከፊል የበሰለውን ትንሽ ቁራሽ ልትሰጡት ትችላላችሁ።”
በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል:- “አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣትና ትርፍ ጊዜ ማግኘት ይጠይቅባችሁ ይሆናል። ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚቀርቡ ምግቦችን ስታዘጋጁ ልጃችሁ አዲስ የሆነውን ወይም ደግሞ የማይወደደውን ምግብ በመሥራት ሊረዳችሁ የሚችልበትን ቀለል ያለ መንገድ ፈልጉ። ምግቡን እያዘጋጃችሁ ሳለ እንዲቀምስ አበረታቱት። ረዳታችሁ ሲቀምሰው ደስ ይለዋል ለመብላትም ያጓጓዋል። ይህ ምግብን በተሳካ መንገድ ለማስለመድ የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታ ነው።”
ጣዕም የመለየት ችሎታ ሲቀንስ
የሚያሳዝነው በዕድሜ የገፋው የዳዊት ወዳጅ ቤርዜሊ እንደተናገረው ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ጣዕም የመለየት ችሎታ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። ቤርዜሊ እንዲህ ብሏል:- “ዛሬ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ . . . እኔ ባርያህ የምበላውንና የምጠጣውን ጣዕሙን መለየት እችላለሁን?” (2 ሳሙኤል 19:35) ጣዕም የመለየት ችሎታችን እንዲቀንስ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ እንዲጠፋ የሚያደርጉ ሌሎች ነገሮችም ይኖራሉ።
ችግሩ ምናልባት በጭንቅላት ላይ የደረሰ ጉዳት፣ አለርጂ፣ ኢንፌክሽን፣ የሕክምና መድኃኒቶች፣ መርዘኛ ለሆኑ ኬሚካሎች መጋለጥ ወይም በቀላል ጉንፋንም ሊመጣ ይችላል። የማሽተትና ጣዕም የመለየት ችሎታቸውን ያጡ ሰዎች ምን ያህል ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደሚያድርባቸው ተመሳሳይ ችግር የገጠማት ሴት ከሰጠችው የሚያሳዝን አስተያየት መረዳት እንችላለን። እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “የሚያውደውን የቡና ሽታ እንዲሁም ጣፋጭ የሆነውን የብርቱካን ጣዕም ከቁም ነገር አንቆጥራቸው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እነዚህን ስሜቶች ስናጣ እንዴት መተንፈስ እንዳለብን የረሳን ያህል ነው።”
ውልታ የሚባለው ነገር ሰውዬው በአካባቢው የሌለ ነገር እያጣጣመ ስሜቱ እንዲረበሽ የሚያደርግ ችግር ነው። የኬሞቴራፒ ሕክምና የሚከታተሉ የካንሰር በሽተኞች አንዳንድ ጊዜ ጣዕምና ሽታ የመለየት ችሎታቸው ይዛባል።
ከአምላክ የተገኘ በረከት
በትክክል የሚሠራ ጣዕም የመለየት ችሎታ እንዴት የሚያስደስት ነው! በዕድሜ የገፉ በርካታ ሰዎች ወጣት በነበሩበት ጊዜ ከዛፍ ላይ እያወረዱ ስለበሏቸው ፍሬዎች ወይም በልዩ ሁኔታ ስለተዘጋጁ ምግቦች በአድናቆት ሲናገሩ እንሰማለን። ፈጣሪያችን ሥቃይ፣ እርጅና እንዲሁም ሞት በማይኖርበት ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ “ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች” እንዲኖሩ ተስፋ መስጠቱ ጣዕም በመለየት ችሎታችን እንድንደሰት እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው።—ኢሳይያስ 25:6–9፤ ኢዮብ 33:25፤ ራእይ 21:3, 4
ጣዕም የመለየት ችሎታ በእርግጥም ለሕይወታችን ቅመም ነው። ይህ ችሎታ ባይኖረን ኖሮ ምግብ መብላት መኪናዎችን ነዳጅ ከመሙላት ያልተለየ ይሆን ነበር። በእርግጥም የላቀ ጥበብ ካለውና አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያችን የተገኘ በረከት ነው!
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆቻችሁ ለገንቢ ምግቦች ፍቅር እንዲኖራቸው አስተምሯቸው