የሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ የዳኞች ጉባኤ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፍ ውሳኔ አስተላለፈ
የይሖዋ ምሥክሮች እነርሱን በሚመለከት በመገናኛ ብዙሐን የሚቀርቡት ዘገባዎች ኃላፊነት በሚሰማቸው ሰዎች የተዘጋጁ እስከሆኑ ድረስ አይቃወሙም። እንዲያውም ስለ ራሳቸውም ሆነ ስለ ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውና እንቅስቃሴዎቻቸው እውነተኛ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው። ይሁን እንጂ እነርሱን በሚመለከት የተሳሳቱ ወይም ስማቸውን የሚያጠፉ ጽሑፎች ታትመው ሲወጡ ምሥክሮቹ ሃይማኖታዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ሲሉ አንዳንድ ጊዜ ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት አቤት ይላሉ። በቅርቡ የተፈጸመ አንድ ምሳሌ ተመልከት።
በነሐሴ 1, 1997 በሴንት ፒተርስበርግ የሚታተም ኮምሶሞልስካያ ፕራቭዳ የተባለ አንድ ታዋቂ የሩሲያ ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮችን ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ጸሐፊው ኦሌግ ዛሶሪን “የፒተርስበርግ መናፍቃን። ከተማችን ቤተ መቅደሳቸው ትሆናለች” በሚል ርዕስ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያምኑባቸው ነገሮች ጎጂ እንደሆኑና የሚያደርጓቸውም እንቅስቃሴዎች የሩስያን ሕገ መንግሥት እንደሚጻረሩ አትተው ነበር። ጥቃቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱትን የምሥክሮቹን እምነቶች በማጣመም የተሰነዘረ ነበር። ለምሳሌ ያህል ደም መውሰድን በተመለከተ ያላቸው አቋምና የቤተሰብ ሕይወታቸው ተጠቅሷል። ከዚህም በላይ ይኸው ጽሑፍ ምሥክሮቹን “መናፍቃን” ከሚባሉት ተርታ የፈረጃቸው ሲሆን በአንዳንዶች አመለካከት እንዲያውም “እጅግ አደገኛ መናፍቃን” ናቸው ብሏል።
በሩሲያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት አስተዳደር መምሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ሐሰት ነው የሚሉትን የዚህን ጽሑፍ ሐሳብ እንደገና እንዲገመገም በመጠየቅ በመገናኛ ብዙሐን በሚቀርቡ ዘገባዎች ላይ የሚነሱ ክርክሮችን ለሚዳኘው የሩሲያ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንታዊ የዳኞች ጉባኤ አቤት አለ። ጉባኤው የካቲት 12, 1998 ዕለት ባደረገው ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ተወካዮች ተገኝተው የነበረ ሲሆን የጉባኤው አባላት እንዲሁም ጋዜጠኞችና የሕግ ሰዎች ላቀረቧቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ምን እንደሚያምኑና እንደሚያስተምሩ ለማወቅ የጉባኤው አባላት በይሖዋ ምሥክሮች የታተሙ ጽሑፎችን በተለይም ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ መርምረዋል።
የሩሲያ ፌዴሬሽን ዱማ አባል የሆኑት ቪ ቪ ቦርሺኦፍ “መናፍቅ” የሚለው ሐሳብ አሉታዊ አንድምታ እንዳለው ተናግረዋል። ሚስተር ቦርሺኦፍ እንዲህ አሉ:- “[እንዲህ ያለው] መዳፈር እና ያሻውን ስም እያነሱ መለጠፍ እጅግ አደገኛ ነገር ነው። ፕሬዚዳንታዊው የዳኞች ጉባኤ የይሖዋ ምሥክሮች ያቀረቡትን አቤቱታ ለመመርመር ፈቃደኛ መሆኑ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር ነው። ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቶት በተመዘገበ ሃይማኖታዊ ድርጅት ላይ ይህን መሰል ነቀፌታ መዥጎድጎዱ ሊገታ ይገባል።”
ጉባኤው ማስረጃዎቹን ሁሉ ካዳመጠ በኋላ ኮምሶሞለስካያ ፕራቭዳ ላይ የወጣው ጽሑፍ ሕገ ወጥና ግብረገብነት የጎደለው ነው ሲል ደምድሟል፤ ከዚህም ሌላ ጽሑፉ ሐሰት የሞላበትና መሠረተ ቢስ መሆኑን አረጋግጧል። ፕሬዚዳንታዊው የዳኞች ጉባኤ እንዳለው “ጸሐፊው ምንም ተጨባጭ ማስረጃ አላቀረበም . . . የጽሑፉ አዘጋጅ የጋዜጠኝነት መብቱን አላግባብ በመጠቀም ተራ ወሬን ተዓማኒነት እንዳለው ሪፖርት አድርጎ አቅርቧል።” የጋዜጣው ጽሑፍ ካወጣው ሐሳብ በተቃራኒ ጉባኤው የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ አክባሪ መሆናቸውንና አባሎቻቸውም የእነርሱን ሃይማኖታዊ እምነቶች ከማይጋሩ የቤተሰብ አባሎችና ወዳጆቻቸው ጋር በሰላም እንዲኖሩ የሚያስተምሩ መሆናቸውን ተገንዝቧል።
የመጨረሻው ምሥክርነት ከተሰማ ከአንድ ሰዓት በኋላ ፕሬዚዳንታዊው የዳኞች ጉባኤ የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል:-
“1. ‘የፒተርስበርግ መናፍቃን። ከተማችን ቤተ መቅደሳቸው ትሆናለች’ የሚለው ጽሑፍ የሩሲያ ፌደሬሽን ሕግ ‘ስለ መገናኛ ብዙሐን’ የሚደነግገውን አንቀጽ 4, 49 እና 51 የሚጥስ ሆኖ ተገኝቷል።
“2. ታትመው የሚወጡ ጽሑፎችን በበላይነት የሚቆጣጠረው የሩሲያ ፌደሬሽን ኮሚቴ ለኮምሶሞልስካያ ፕራቭዳ ጋዜጣ አዘጋጆች ቦርድ ማስጠንቀቂያ እንዲያስተላልፍ።
“3. ጋዜጠኛው ኦ ዛሶሪን ጠንካራ ወቀሳ እንዲሰጣቸው።
“4. የኮምሶሞለስካያ ፕራቭዳ ዝግጅት ክፍል ያለምንም መሠረት የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ ድርጅት ስም በማጥፋት ስላቀረበው ያልተረጋገጠ መረጃ ይቅርታ እንዲጠይቅ።”
ፕሬዚዳንታዊው የዳኞች ጉባኤ የደረሰበት ይህ ውሳኔ ፍልስፍና የሚያጠኑትና የሃይማኖት ምሁር የሆኑት ሰርጊዬ ኢቫኔንኮ ከደረሱበት መደምደሚያ ጋር ይስማማል። ሚስተር ኢቫኔንኮ የይሖዋ ምሥክር ባይሆኑም የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት በጥንቃቄ ከመረመሩና ከእነርሱ ጋር ከተሰበሰቡ በኋላ በሞስኮ ኒውስ የየካቲት 20–26, 1997 እትም ላይ ሐሳባቸውን አስፍረዋል።a ሚስተር ኢቫኔንኮ እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት መመላለስን በተመለከተ ባላቸው ጽኑ እምነት የሚታወቁ ሰዎች ናቸው። ... ለይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ሕገ መንግሥት፣ ፍትሐ ብሔርና ከሁሉ የላቀ የእውነት ምንጭ ነው። ... የይሖዋ ምሥክሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያደሩ በመሆንና ራሳቸውን ክደው ለእምነታቸው ለመቆም ፈቃደኛ በመሆን ረገድ ለአገራቸው ዜጎች ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው።”
የጉባኤው ውሳኔም ሆነ የሚስተር ኢቫኔንኮ አስተያየት የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ እምነት ለኅብረተሰቡ ስጋት የማይፈጥር እንዲያውም ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ሁሉ የሚጠቅም መሆኑን አረጋግጧል። የይሖዋ ምሥክሮች ‘በእነርሱ ዘንድ ስላለው ተስፋ ለማወቅ ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጁ ናቸው።’ ሆኖም ይህን የሚያደርጉት ‘በየዋሕነትና በጥልቅ አክብሮት’ ነው።—1 ጴጥሮስ 3:15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የይሖዋ ምሥክሮችን ልንፈራቸው ይገባልን?” ከሚለው የሚስተር ኢቫኔንኮ ጽሑፍ መካከል አብዛኛው ክፍል በእርሳቸው ፈቃድ በነሐሴ 22, 1997 ንቁ! መጽሔት (የእንግሊዝኛ) ገጽ 22–7 ላይ ታትሞ ወጥቷል።