ከዓለም አካባቢ
መጻሕፍትን ማዳን
በሚልዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት በማርጀት፣ በሚደርስባቸው ጉዳት ወይም በመተሻሸት ብዛት እየተበላሹ ነው። በጀርመን ብቻ ወደ 60 ሚልዮን የሚጠጉ ጉዳት የደረሰባቸው ጥራዞች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል በማለት ላይፕሲገር ፎልክስሳይቱንግ የተባለ ጋዜጣ አስታውቋል። በእጅ እደሳ ማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅና ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው። “አንድ መጽሐፍ በእጅ ለማደስ በሚውለው ጊዜ ውስጥ ሌሎች አራት ወይም አምስት መጻሕፍት ይበላሻሉ” በማለት በላይፕሲግ የሚገኘው የመጽሐፍ ጥበቃ ማዕከል ቴክኒካል ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ደብልዩ ቫክተር ይናገራሉ። ማዕከሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን መጻሕፍት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችሉ ማሽኖችን ፈብርኳል። አንደኛው አሲድ የሚጠርግ ማሽን ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 100,000 መጻሕፍትን ሊያጸዳ ይችላል። ሌላው ደግሞ አንዱን ገጽ ለሁለት ሰንጥቆ ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው አንድ ስስ ወረቀት በመካከሉ በመክተት እያንዳንዱን ገጽ የሚያጠንክር ማሽን ነው። በአንድ ቀን ጊዜ ውስጥ በእጅ ከ100 እስከ 200 የሚያክሉ ገጾችን ማጠንከር ሲቻል ማሽኑ ግን 2,000 የሚያክሉ ገጾችን ማጠንከር ይችላል። ይህም በእያንዳንዱ ገጽ 94 በመቶ ወጪ ይቀንሳል። ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ብቻ ሳይሆኑ ግለሰቦችም እደሳ እንዲያደርግላቸው መጻሕፍታቸውን ይዘው ወደ ማዕከሉ በመጉረፍ ላይ ናቸው።
የማጨስን አላዋቂነት የሚያሳይ ተጨማሪ መረጃ
በቅርቡ በኔዘርላንድስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ሲጋራ ማጨስ አንድ ሰው በአእምሮ ሕመምና በአልዛይመርስ በሽታ ሊያዝ የሚችልበትን አጋጣሚ በሁለት እጥፍ እንደሚያሳድገው” ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቡን ዘግቧል። ከ55 ዓመት በላይ በሆኑ 6,870 ሰዎች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው የሚያጨሱ ሰዎች በአልዛይመርስ በሽታ የመያዛቸው አጋጣሚ በሕይወት ዘመናቸው ሲጋራ አጭሰው ከማያውቁ ሰዎች በ2.3 የበለጠ ነው። ማጨስ ያቆሙ ሰዎች በዚህ በሽታ የመያዛቸው አጋጣሚ ፈጽሞ ሲጋራ አጭሰው ከማያውቁት ብዙም የማይበልጥ ነው። የአንጎል ሴሎችን ቀስ በቀስ የሚጨርሰው የአልዛይመርስ በሽታ “በእጅጉ ተስፋፍቶ የሚገኝ የአእምሮ ሕመም ነው።”
ኮምፓስ ያለው ዓሣ
ሬይንቦ ትሮት የሚባለው የዓሣ ዝርያ የባሕር ላይ ጉዞውን የሚያከናውነው እንዴት ነው? “በአፍንጫው ላይ ባለው መግነጢሳዊ ኮምፓስ” መሆኑን በኒውዚላንድ የሚገኙ የስነ ሕይወት ተመራማሪዎች እንደ ደረሱበት ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። በርካታ አእዋፍና ገበሎ አስተኔዎች (reptiles) እንዲሁም አንዳንድ አጥቢ እንስሳት የምድርን መግነጢሳዊ መስክ ተከትለው አቅጣጫቸውን ማስተካከል ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች የሰሜንን አቅጣጫ የሚጠቁም ማግኔቲት የሚባል መግነጢሳዊ ማእድን የያዙ ሕዋሳት መኖራቸውን አያውቁም ነበር። በኦክላንድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ትሮት በተባለው የዓሣ ዝርያ ላይ ባካሄዱት ምርምር ዓሣው ወደ መግነጢሳዊ መስክ በሚቀርብበት ጊዜ መልእክት የሚያስተላልፍ የነርቭ ቃጫ (nerve fiber) በፊቱ ላይ አግኝተዋል። የነርቭ ቃጫው ከየት እንደሚነሳ ለማወቅ ሲጥሩ በዓሣው አፍንጫ ውስጥ ማግኔቲት የሚባለውን ማእድን የያዙ የነርቭ ሕዋሳት ሊያገኙ ችለዋል።
በአሳዳጊዎችና በማደጎ ልጆች መካከል ያለ ዝምድና
አንዳንድ ጊዜ የማደጎ ልጅ የማሳደግ ዕቅድ ያላቸው ወላጆች ልጁ ሁልጊዜ ጥሩ እንደሚሆንና የሚከሰቱት ችግሮች በቀላሉ እንደሚፈቱና የመግባባት መንፈስ እንደሚሰፍን በማሰብ በመካከላቸው የሚኖረው ዝምድና ምንም እንከን የማይወጣለት እንደሚሆን አድርገው በምናባቸው ለመሳል ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ሁኔታው ከዚህ የተለየ እንደሚሆን ኦ ኤስታዶ ደ ኤስ ፓውሎ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ ዘግቧል። የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ኤሎኢዘ ማርቶን “በአጠቃላይ ሲታይ ወላጆች ለሚፈጠሩት አለመግባባቶች ዝግጁ አይደሉም” ሲሉ ገልጸዋል። “ልጁ ለዘለቄታው አመስጋኝ ይሆናል ብለው የሚጠብቁ ባልና ሚስት” ያልጠበቁት ዱብ ዕዳ እንደሚገጥማቸው ጥርጥር የለውም ሲሉ በሳኦ ፓውሎ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ሚርያም ዴብዮ ሮዛ ተናግረዋል። ሁልጊዜ ደስተኛ የሆነ ሰው እንደሌለ ከገለጹ በኋላ “ብዙውን ጊዜ ወላጆች ለሚፈጠሩት ችግሮች እንደ ምክንያት አድርገው የሚጠቅሱት የሥጋ ዝምድና አለመኖሩን ነው። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። ወላጆች ለማደጎ ልጁ ማሳየት ያለባቸውን ፍቅር በተመለከተም ሲናገሩ “ቁሳዊ ድጋፍ ማድረጉ ብቻ አይበቃም” ብለዋል። ከልጁ ጋር ስሜታዊ ዝምድና መፍጠሩም በጣም አስፈላጊ ነው።
ቴሌቪዥንና አደጋዎቹ
ቴሌቪዥን በመመልከት ረዥም ጊዜ የሚያጠፉ ልጆች የሚያዩትን አደገኛ ትርኢት ለመኮረጅ ይሞክራሉ። ዶክተር ሆሴ ኡምቤሮስ ፈርናንዴዝ የተባሉ ስፔናዊ ተመራማሪ ባካሄዱት ጥናት እንደተረጋገጠው ከሆነ አንድ ልጅ ለአደጋ ሊጋለጥ የሚችልበት አጋጣሚ ቴሌቪዥን በመመልከት በሚያጠፋው በእያንዳንዱ ሰዓት እየጨመረ ይሄዳል። ይህ የሆነበት ምክንያት ቴሌቪዥን እውነታውን አዛብቶ ስለሚያቀርብ እንደሆነ ፈርናንዴዝ ሐሳብ ሰጥተዋል። ወላጆች ይህን ተጽዕኖ ለመቀልበስ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በግሪክ የሚታተመው ቶ ቪማ የተባለው ጋዜጣ እንደሚለው ወላጆች ልጆቹ የሚመለከቱትን ፕሮግራም መምረጥና የሚያዩት ነገር ሁሉ በእውነታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አድርገው ከመቀበል ይልቅ “ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ” እንዲኖራቸው መርዳት ይኖርባቸዋል።
ቤተሰብ አንድ ላይ ሲመገብ
በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 527 ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ቢያንስ በሳምንት አምስት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ እራት የሚመገቡ ወጣቶች “አደገኛ ዕፅ የመውሰዳቸው፣ ወይም በጭንቀት ስሜት የመያዛቸው አጋጣሚ ዝቅተኛ እንደሆነና በትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎቻቸው የበለጠ ትጋት እንደሚያሳዩ፣ ከእኩዮቻቸውም ጋር ያላቸው ግንኙነት የተሻለ እንደሆነ አመልክቷል” ሲል የካናዳው ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። “‘ጥሩ ምግባር የላቸውም’ የሚባሉ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚመገቡት በሳምንት ውስጥ ለሦስት ወይም ከዚያ ላነሱ ቀናት ብቻ ነው።” ብሩስ ብራይን የተባሉት የስነ ልቦና ተመራማሪ የቤተሰብ መመገቢያ ሰዓት መኖር “የአንድ ጤናማ ቤተሰብ ባሕርይ” መሆኑን አረጋግጠዋል። አብሮ መመገብ የቤተሰቡን ትስስር እንደሚያጠናክር፣ ሐሳብ የመግለጽ ችሎታ እንደሚያዳብር እንዲሁም አንድ የመሆን መንፈስ እንደሚያሳድር ሪፖርቱ ይገልጻል። በተጨማሪም ጥሩ የገበታ ሥርዓት ለማስተማር፣ ለመጨዋወት፣ ለመቀላለድና ለመጸለይ ጥሩ አጋጣሚ ያስገኛል። ዘወትር አብሮ በሚመገብ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ልጅ ሁልጊዜ አብረን የማንመገብ ቢሆን ኖሮ “ከቤተሰቦቼ ጋር ይህን ያህል ቅርበት የሚኖረኝ አይመስለኝም” ብላለች።
ማግባት ጤናማ ነው
አንድ ተመራማሪ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ እንዳሉት ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ባለትዳር መሆን “ዕድሜ ያስረዝማል፣ አካላዊና ስሜታዊ ጤንነት ያሻሽላል፣ የገቢ መጠን ከፍ እንዲል ያደርጋል።” የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሊንዳ ጄ ዌይት ያደረጉት ጥናት በ1972 ወጥቶ የነበረውን ባለ ትዳር ሴቶች የበለጠ ሥነ ልቦናዊ ጫና ይደርስባቸዋል የሚለውን ሪፖርት ያስተባብላል። ዶክተር ዌይት “ትዳር በሰዎች ባሕርይ ላይ” ብዙ አልኮል ከመጠጣት መቆጠብን የመሰለ “በጎ ለውጥ እንደሚያስከትል” ደርሰውበታል። በተጨማሪም ትዳር ጭንቀት የሚቀንስ ይመስላል። እንዲያውም “ወንደ ላጤዎች በአብዛኛው የመንፈስ ጭንቀት እንዳለባቸው በጥናቱ መጀመሪያ ላይ የታየ ሲሆን በላጤነታቸው በቆዩ መጠን ጭንቀታቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ተረጋግጧል።” ይሁን እንጂ የሚነሶታ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዊልያም ጀ ዶርቲ ይህ አኃዝ የሚያመለክተው አማካይ ሁኔታዎችን ብቻ እንደሆነና ያገባ ሁሉ የተሻለ ሕይወት ይመራል ወይም ጥሩ የትዳር ጓደኛ ምርጫ ያላደረገም ቢሆን ይበልጥ ደስተኛና ጤነኛ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።
ልጅ መውለድ የሚያስገኘው ደስታና የሚያስከትለው ሥራ!
“በርካታ ወጣት ባልና ሚስቶች ልጅ መውለድ የሚያስከትለውን ተጨማሪ የሥራ ጫና አቅልለው ይመለከቱታል። ይህም ብዙውን ጊዜ ልጅ ከተወለደ በኋላ በባልና በሚስት መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር መንገድ ይከፍታል” በማለት የጀርመኑ ናሱሼ ኖዬ ፕሬሴ ዘግቧል። በኔዘርላንድስ፣ በግሮኒንገን ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው ወጣት እናቶች ልጅ በመውለዳቸው ምክንያት በሚፈጠረው ከፍተኛ ለውጥ ብዙውን ጊዜ ቅር ይሰኛሉ። አንዲት እናት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለልጅዋ በአማካይ 40 ሰዓት ማዋል ይኖርባታል። ከዚህ ውስጥ 6 ሰዓቱ ለጽዳት፣ ልብስ ለማጠብና ምግብ ለማብሰል የሚውል ሲሆን 34ቱ ሰዓት ግን በቀጥታ ልጅዋን በመንከባከብ የምታሳልፈው ጊዜ ነው። አባቶች ደግሞ በቀጥታ ለልጁ የሚያውሉት ጊዜ 17 ሰዓት ብቻ ነው። በዘገባው መሠረት በቤተሰብ ውስጥ ውጥረት የሚፈጠረው “በአብዛኛው የልጁን የሽንት ጨርቅ ማን ይቀይር ወይም ሌሊት ተነስቶ ልጁን ማን ጡጦ ያጥባ በሚለው ጉዳይ ሳይሆን የቤቱን ሥራ ተከፋፍሎ በመሥራት ላይ ነው።”
በሕሙማን ላይ የሚፈጸም ዝርፊያ
የጀርመን ሆስፒታሎች በሌቦች እየተወረሩ ነው። ኤምስደትነር ታግብላት እንደዘገበው ከሆነ “ኮሎኝ በሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች በየዓመቱ እስከ ሦስት መቶ የሚደርሱ የስርቆት ወንጀሎች ሪፖርት ይደረጋሉ። በእጁ እቅፍ አበባ ይዞና ፊቱ ላይ ፈገግታ እየተነበበበት የሚመጣው ሌባ ጠቀም ያለ ነገር ይዞ መውጣቱ አይቀርም።” ሕሙማን ጠያቂ መስለው የሚመጡት እነዚሁ ሌቦች አልጋ አጠገብ ካሉት ጠረጴዛዎች አንስቶ እስከ ኮት መስቀያ ድረስ ሁሉንም ያስሳሉ። በተለይ አረጋውያን ሕሙማን ለሌቦቹ የተጋለጡ ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንድ አረጋዊ ሰው በሺህ የሚቆጠር ደች ማርክ በሆስፒታል አልጋቸው ትራስ ሥር ሸጉጠው ተገኝተዋል። የመጠየቂያ ሰዓቱ ገደብ የሌለው መሆኑ ለሌቦቹ ትልቅ ነፃነት የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ማንኛውም ሰው ለማለት ይቻላል ያለ ማንም ጠያቂ ወደ ሆስፒታሉ ሊገባ ይችላል። በመሆኑም ሕሙማኑ ገንዘባቸውን ወይም ውድ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶቻቸውን በሆስፒታሉ ካዝና ውስጥ ወይም ሌላ ቦታ ቆልፈው እንዲያስቀምጡ አለዚያም አስተማማኝ ቦታ ሊያስቀምጥላቸው ለሚችል ሰው እንዲሰጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
የጆሮ አሻራ
በቅርቡ በለንደን የተከሰሰ አንድ ቤት ሰርሳሪ ሌባ በጆሮዎቹ እንደተጋለጠ ታውቋል። እንዴት? ወንጀሉን በፈጸመበት ጊዜ የእጅ አሻራ ላለመተው ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደረገ ቢሆንም ሰብሮ ገብቶ ዝርፊያ ከመፈጸሙ በፊት ቤት ውስጥ ሰው መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጆሮውን መስኮት ላይ ወይም ቁልፍ ማስገቢያ ቀዳዳ ላይ ለጥፎ የመስማት ልማድ ስለነበረው የጆሮው አሻራ ተገኝቷል። በስኮትላንድ ግላስኮ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት የአሻራ ምርመራ ስፔሺያሊስት ፒተር ቫኔስ “የጆሮ አሻራዎች እንደ እጅ አሻራዎች ሁሉ ከሰው ወደ ሰው ይለያያሉ” ብለዋል። ይሁን እንጂ ከእጅ አሻራዎች በተለየ መልኩ ጆሮዎች በአዋቂነት ዕድሜ ክልል ሳይቀር እንደ ፀጉርና ጥፍር ማደጋቸውን ይቀጥላሉ ሲል የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ይሁን እንጂ ፖሊሶች የጆሮዎቻችን መጠን ምንም ያክል ቢሆን በዚህ ዘራፊ ሁኔታ እንደታየው የአንዳችን ከሌላው የተለየ መሆኑን ያውቃሉ። በብሪታንያ በጆሮ አሻራ ተይዞ ለክስ ሲቀርብ የመጀመሪያው ይህ ሰው ሲሆን ካሁን ቀደም አምስት ጊዜ በቤት ዝርፊያ ወንጀል ተከስሶ እንደነበር አምኗል።