ከዓለም አካባቢ
በመስመጥ ላይ ያለች ከተማ
“ሜክሲኮ ሲቲ በመስመጥ ላይ ነች” ይላል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ። “በከተማዋ የሚኖሩትን 18 ሚልዮን ሰዎች የውኃ ፍላጎት ለማሟላት በከተማዋ ሥር ከሚገኝ ውኃ ያዠንብር ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ በፓምፕ በመመጠጡ መሬቱ በሚያስገርም ፍጥነት ወደ ታች እያዘቀጠ ነው።” ይባስ ብሎ ደግሞ “ሜክሲኮ ሲቲ ውኃ የሚያባክን የውኃ ማሰራጫ መስመር ካላቸው የዓለማችን ከተሞች አንዷ ናት። በፓምፕ እየተሳበ ወደ ውኃ መስመሩ ከሚገባው ጨው አልባ ውኃ መካከል ከእያንዳንዱ ሊትር አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የትም ፈስሶ ይቀራል።” ይህም ብዙ ውኃ ማውጣት የሚጠይቅ በመሆኑ ከተማዋ ይበልጥ እየሰመጠች ትሄዳለች። የጥገና ሠራተኞች በዓመት ውስጥ 40,000 የፈነዱ የቧንቧ መስመሮችን የሚጠግኑ ቢሆንም ሌሎች ብዙ የፈነዱ የቧንቧ መስመሮች ሪፖርት ሳይደረጉ ይቀራሉ። እርግጥ በመስመጥ ላይ የምትገኘው ከተማ ሜክሲኮ ሲቲ ብቻ አይደለችም። ለምሳሌ ያህል የኢጣሊያዋ ቬነስ በ20ኛው መቶ ዘመን 23 ሴንቲ ሜትር ያህል አዝቅጣለች። ሜክሲኮ ሲቲ ግን 9 ሜትር ያህል ሰምጣለች!
ለጎብኚዎች የተዘጋጀ እጀ ጠባብ
በተለይ ሞቃታማ በሆኑ የበጋ ወራት ካናቴራዎችና ቁምጣዎች ለብሰው የካቶሊክ ቅዱስ ቦታዎችን ለመጎብኘት ወደ ኢጣሊያ በሚጎርፉ ቱሪስቶች ላይ እቀባ ተደርጓል። አሁን ግን በአንዳንድ ቦታዎች ዳልቻ ቀለም ያለውንና እስከ ጉልበት የሚደርሰውን “የጎብኚዎች እጀ ጠባብ” የሚለብሱ ጎብኚዎች መግባት እየተፈቀደላቸው ነው። ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች የሚሆን መጠኑ አንድ ዓይነት የሆነ እጀ ጠባብ በቬኒስ እና በሮም ገበያዎች ላይ ውሏል። በሮም የሚሸጠው ልብስ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ አርማና “ኢዮቤልዩ 2000” የሚል ጽሑፍ ተለጥፎበታል። ይሁን እንጂ እነዚህ እጀ ጠባቦች በሁሉም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኖች ዘንድ ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው? ልብሶቹ ቬኒስ በሚገኘው ጉባኤ ተቀባይነት ያገኙ ቢሆንም እነዚህን ልብሶች ገዝተው የለበሱ ወንድ ጎብኚዎች የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካን ቤተ ክርስቲያን እንዳይጎበኙ ተከልክለዋል። “የመንበረ ጵጵስና አባላቱ ልብሱ የሴቶች ብቻ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል” በማለት ኮሪየሬ ዴላ ሴራ የተባለ የኢጣሊያ ጋዜጣ ዘግቧል። “ወንዶቹ ልብሱ ከጉልበታቸው በታች ያለውን የሰውነታቸውን ክፍል የማይሸፍን በመሆኑ እንደ ‘ነውር’ ተቆጥሮ እንዳይጎበኙ ተከልክለዋል።”
ትዳር ደስታ ሊያስገኝ ይችላል
አንዳንዶች ትዳር ሸክም እንደሆነ አድርገው ሲናገሩ በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ኮሜዲዎች ደግሞ ትዳር እጅግ ኋላ ቀር እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። ይሁን እንጂ እውነታዎቹ ምን ያሳያሉ? ያላገቡ ሰዎች ሁሉ ካገቡ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብሎ መናገር ይቻላል? ፊላዴልፊያ ኢንክዋየረር ባወጣው ዘገባ ላይ የጠቀሳቸው አንዲት የማኅበራዊ ጉዳዮች አጥኚ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ ብሎ መናገር አይቻልም። እኚህ ሴት ያገቡ ሰዎች “በጥቅሉ ሲታይ ይበልጥ ደስተኞች፣ ጤናሞችና ባለጸጋዎች” እንደሆኑ ገልጸዋል። በተጨማሪም በቡድን ደረጃ ሲታይ የሚያገቡ ሰዎች የሚደርስባቸው ውጥረት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ወንጀል የመፈጸም ወይም ደግሞ ሕገ ወጥ ዕፆችን የመጠቀም ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ከዚህም ሌላ ከተረጂነት የመላቀቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ያገቡ ሰዎች የበለጠ ዕድሜ ይኖራሉ በማለት ጠበብት መናገራቸው ምንም አያስደንቅም።
ዓይናፋርነትን ማሸነፍ
የካናዳው ቶሮንቶ ስታር እንዳለው ከሆነ “ወደ 13 በመቶ የሚጠጉ ዐዋቂ ሰዎች ከባድ የዓይናፋርነት ችግር አለባቸው።” ይህም “ሕይወታቸውን በተሟላ መንገድ መምራት እንዳይችሉ እንቅፋት” እንደሚሆንባቸው ጋዜጣው ዘግቧል። አንዳንድ ጠበብት ዓይናፋርነትን ለማሸነፍ ይረዳሉ ያሏቸውን የሚከተሉትን ሐሳቦች ሰንዝረዋል:- “ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉህን በዜና እወጃዎች ላይ የሰማሃቸውን፣ በመጽሔቶችና በመጽሐፎች ላይ ያነበብካቸውን፣ በትርፍ ጊዜህ የምትሠራቸውን ወይም በፊልም ላይ ያየሃቸውን ነገሮች ለማሰብ ሞክር።” “የዓይን ግንኙነት ማድረግን [እና] በጥሞና ማዳመጥን ጨምሮ በቃልም ሆነ አለቃል የሐሳብ ግንኙነት ማድረግን ተለማመድ።” “የሚያስፈሩህን ነገሮች ለማድረግ ራስህን አስገድድ።” “ዓይናፋር የሆነ ልጅ ያለህ ወላጅ ከሆንክ ልጅህ ከሌሎች ሰዎች ጋር እየተገናኘ መጫወት የሚችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እንዲያገኝ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው።” የተገኘው ተሞክሮ እንደሚያሳየው አንድ ሰው ዓይናፋርነትን ለማሸነፍ ይበልጥ ጥረት ባደረገ መጠን ትግሉ የዚያኑ ያህል የሚቀልለት በመሆኑ በዚህ ረገድ በምታደርገው ጥረት ተስፋ መቁረጥ የለብህም።
በደም ውስጥ የተገኘ አዲስ ቫይረስ
በአውሮፓ በተለገሱ ደሞች ውስጥ አዲስ የቫይረስ ዓይነት ከተገኘ በኋላ የፈረንሳይ የጤና ባለ ሥልጣናት “ክትትል የሚያደርግ ቋሚ የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን” ለማቋቋም መወሰናቸውን ለ ሞንድ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ዘግቧል። ደም በመውሰድ የሚተላለፈውና (ቲ ቲ ቪ) በመባል የሚታወቀው ይህ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ1997 በጃፓን ሲሆን በዚያን ወቅት ከነበሩት ለጋሾች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት በቫይረሱ የተለከፉ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ሐኪሞች ቫይረሱ በሽታ ስለሚያስከትልበት ሁኔታ በትክክል ያወቁት ነገር ባይኖርም መንስኤው ባልታወቀ ከባድ የጉበት በሽታ ከሚሠቃዩ ሕሙማን መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ቲ ቲ ቪ እንደተገኘባቸው በብሪታንያ የተደረጉ ጥናቶች ገልጸዋል። ቫይረሱን ለማግኘት የሚረዳ መደበኛ የሆነ የምርመራ ሂደት እስከ አሁን ድረስ አለመኖሩን ለ ሞንድ ገልጿል።
መቼም ቢሆን ለማቆም ጊዜው አልፎብሃል ሊባል አይችልም
ለ40 ዓመታት የተካሄደ አንድ ጥናት በ60 ዓመታቸው እንኳ ሳይቀር ማጨስ ያቆሙ ሰዎች በካንሰር በሽታ የመያዝ ዕድላቸው በእጅጉ እንደቀነሰ የብሪታንያው ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። በእንግሊዝ ሰተን ውስጥ የሚገኘው የካንሰር ምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጁሊያን ፒቶ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሲጋራ ማጨስ ቀደም ሲል እንደምናስበው አንድ አራተኛዎቹን ብቻ ሳይሆን አንድ ሁለተኛ የሚሆኑትን አጫሾች ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግ የሚያስከትለውን አሰቃቂ እልቂት መገንዘብ የቻልነው ገና ባለፈው ዓመት ነው። ሆኖም በስተርጅና ዕድሜም እንኳ ቢሆን [ሲጋራ ማጨስ] ማቆም ምን ያህል ከፍተኛ ጥቅም እንዳለውም መገንዘብ ችለናል።” ልጆች ሲጋራ ማጨስ ስለሚያስከትላቸው አደጋዎች ዘወትር ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ይሁን እንጂ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ትምባሆን እርግፍ አድርገው መተዋቸው በሳምባ ካንሰር የመለከፍ ዕድላቸውን በእጅጉ ሊቀንሰው እንደሚችል ማወቅ እንዳለባቸው ፒቶ አመልክተዋል።
ዘመናት የፈጀ መዝገበ ቃላት
የደችና የፍሌሚሽ መዝገበ ቃላት አዘጋጆች የዓለማችንን ትልቁን መዝገበ ቃላት በቅርቡ አጠናቅቀዋል። 40 ጥራዞችና 45,000 ገጾች ያሉትን ይህን የደች ቋንቋ መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶ ለመጨረስ 147 ዓመታት እንደወሰደ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል። መዝገበ ቃላቱ የተዘጋጀው “ለዘመናዊ የደች መዝገበ ቃላት ሁሉ ተምሳሌት እንዲሆን ታስቦ” ነው። በመሆኑም ከ1500 አንስቶ ሲሠራባቸው የቆዩትን ቃላት ሁሉ ይዟል። ችግሩ ይላል ዘገባው፣ መዝገበ ቃላቱ የያዘው እስከ 1976 ድረስ ሲሠራባቸው የቆዩ ቃላትን ብቻ በመሆኑ “ገና ከአሁኑ ጊዜ ያለፈበት ሆኗል።” “እንደገና አሻሽሎ የማውጣቱ ሥራ የቀጠለ ቢሆንም ያለፈው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ሁለተኛው እትም በሚወጣበት ጊዜ የዛሬዎቹ አንባቢዎች በሕይወት መኖራቸው ያጠራጥራል።”
ስትሮክና የማስጠንቀቂያ ምልክቶቹ
“ብዙ ሰዎች አንድም የስትሮክ በሽታ ምልክት አያውቁም” ይላል ኤፍ ዲ ኤ ከንስዩመር። መጽሔቱ እንዲህ ሲል አክሎ ይገልጻል:- “ጥናቱ ከተካሄደባቸው ሰዎች መካከል ቢያንስ ቢያንስ አንድ የስቶሮክ በሽታ ምልክት መጥቀስ የቻሉት ከግማሽ ብዙም የማይበልጡ ሰዎች ናቸው። በተጨማሪም ለስቶሮክ በሽታ ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከል አንዱን እንኳ መጥቀስ የቻሉት 68 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።” ይህ የሆነው ስትሮክ ብዙዎችን ለሕልፈተ ሕይወት በመዳረግና የአካል ጉዳተኛ በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ በያዘባቸው የበለጸጉ ምዕራባውያን አገሮች ውስጥ ነው። በስትሮክ ምክንያት የሚደርስብህን ጉዳት መቀነስ እንድትችል የበሽታውን የመጀመሪያ የማስጠንቀቂያ ምልክት እንዳየህ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት መጣርህ በጣም አስፈላጊ ነው። በጣም የተለመዱት የስትሮክ ምልክቶች ድንገተኛ የሆነ ድካም፣ የመደንዘዝ ስሜት፣ ወይም የፊት፣ የእጅ ወይም ደግሞ የእግር ሽባነት፣ በድንገት የሚከሰት አጥርቶ የማየት ችግር ወይም በተለይ በአንድ ዓይን ላይ የሚፈጠር ዓይነ ሥውርነት፣ የመናገር ወይም ሌላው የሚናገረውን የመረዳት ችግር፣ እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ማስጠንቀቂያ ምልክቶች ጋር ተጣምሮ የሚከሰት ሊገለጽ የማይችል ዓይነት አጥርቶ ያለማሰብ ወይም ሚዛንን ያለመጠበቅ ችግር ናቸው።
የዝሆን መብቶች
በብዙዎቹ የሕንድ ክፍለ ሀገሮች ዝሆኖች የሠራተኛውን ኃይል በማጠናከር ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ። በሰሜናዊዋ የሕንድ ግዛት በኡታር ፕራዴሽ ዝሆኖች ሙሉ ዕውቅና አግኝተው በመንግሥት የሠራተኞች ቅጥር መዝገብ ላይ መስፈራቸውን ዘ ዊክ የተባለው መጽሔት ሪፖርት አድርጓል። አንድ ዝሆን ከ10 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ እስከ 50 ዓመቱ ድረስ ለአሠሪዎቹ ግልጋሎት ሊሰጥ ይችላል። ልክ እንደ ሌሎቹ የመንግሥት ሠራተኞች ሁሉ አንድ ዝሆንም ጡረታ በሚወጣበት ጊዜ የጡረታ አበል የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ ዝሆኑ በሚገባ እየተመገበና ጥሩ እንክብካቤ እየተደረገለት መሆኑን የሚከታተል አንድ የዝሆን አሠልጣኝና ጠባቂ ይመደብለታል። እንስት ዝሆኖች በሥራ ዘመናቸው የሚያገኙት ጥቅም በወሊድ ወቅት ለአንድ ዓመት ያህል በአራዊት መጠበቂያ ውስጥ ጥሩ ዕረፍት የሚያገኙበትን የወሊድ ፈቃድ ይጨምራል። እንጨት ማጓጓዝን፣ የዱር ዝሆኖችን ወደ አራዊት መጠበቂያ ቤት ማስገባትና ማሠልጠንን፣ እንዲሁም ብሔራዊ ፓርኮችንና ጥብቅ ደኖችን እየተዘዋወሩ መጠበቅን ወደመሳሰሉት ጠቃሚ ሥራዎች የሚመለሱት ይህን ዕረፍት ከወሰዱ በኋላ ነው።
ወደ አንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ እያመራን ነው?
“የምዕራባውያን ቋንቋዎች እምብዛም በማይነገሩበት በአንድ የማዕከላዊ እስያ አገር” የሚኖር አንድ የስምንት ዓመት ልጅ እንግሊዝኛ መማር እንዳለበት ለአባቱ ይነግረዋል። አባትየውም ለምን ሲል ይጠይቀዋል። “ምክንያቱም አባዬ፣ ኮምፒዩተሩ የሚናገረው በእንግሊዝኛ ነው” ሲል መለሰለት። ይህ ታሪክ ይላል ኤሽያዊክ፣ “ብዙዎች የኢንተርኔት ስውር ወጥመድ አድርገው የሚቆጥሩትን ነገር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። . . . ኢንተርኔት እየገነነ የመጣው የእንግሊዝኛ ቋንቋ በበለጠ ፍጥነት እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል።” መጽሔቱ እንዲህ ሲል አክሎ ይገልጻል:- “ይህ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ለማስፈን ተብሎ የተደረገ አይደለም። አመቺ ሆኖ ስለተገኘ ብቻ ነው። በኢንተርኔት ውይይት ወይም የንግድ ልውውጥ የምናደርግ ከሆነ በቀላሉ ሐሳብ ለመለዋወጥ አንድ የጋራ መግባቢያ ያስፈልጋል።” ታዲያ ይህ የጋራ መግባቢያ እንግሊዝኛ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም “እንደ ኢንተርኔት ሁሉ የኮምፒዩተሮችም [PC] ንግድ የተጀመረው በዩናይትድ ስቴትስ ነው። በአሁኑ ጊዜ ከኮምፒዩተሮች መረጃ መካከል 80% የሚሆነው የሚገኘው በእንግሊዝኛ ነው።” እንግሊዝኛን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁትን ቁልፍ ሰሌዳዎች ተጠቅሞ በሌሎች ቋንቋዎች መሥራቱ ቀላል ስላይደለ በአንዳንድ ሁኔታዎች በሌሎች ቋንቋዎች የመጠቀሙ ሂደት ተጓትቷል። “ይህ ሁኔታ የሚያስከትለው ኪሳራ ይኖራል” ሲል ኤሽያዊክ ዘግቧል። “የቋንቋ ምሁራን በአሁኑ ጊዜ ከሚነገሩት 6,000 ገደማ የሚሆኑ ቋንቋዎች መካከል ግማሽ ያህሉ በሚቀጥለው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ፣ ምናልባትም በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ሊከስሙ ይችላሉ በማለት ይተነብያሉ።”
የእግር ኳስ ግጥሚያና ዓመፅ
በተለያዩ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ያለፈው ዓመት የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ያስከተላቸው ፈንጠዝያዎች በዓመፅ ተደምድመዋል። በሜክሲኮ የሜክሲኮን ቡድን ደጋፊዎች ለመጠበቅ ከ1,500 የሚበልጡ ፖሊሶች ተሰማርተው ነበር። ፖሊስ ከ200 የሚበልጡ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ ኤል ዩኒቨርሳል የተባለው የሜክሲኮ ጋዜጣ ዘግቧል። ዓመፅ በተቀሰቀሰ ጊዜ የተወረወረ አንድ ርችት በአንድ ወጣት ደጋፊ ፊት ፈንድቶ በከፊል የራስ ቅሉ ላይ ጉዳት አድርሶበታል። በአርጀንቲና፣ በቤልጅየምና በብራዚል በተካሄዱት ፈንጠዝያዎች ላይ የተቀሰቀሰው ሁከት ለብዙዎች መጎዳትና መታሰር ምክንያት ሆኗል። በፈረንሳይ ከዓለም ዋንጫ ውድድሮች ጋር በተያያዘ 1,000 የሚሆኑ ሰዎች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን 1,586 ሰዎች ደግሞ ዳግመኛ ወደዚያች አገር እንዳይገቡ እገዳ እንደተጣለባቸው ኤክሴልስዮር የተባለ የሜክሲኮ ሲቲ ጋዜጣ ዘግቧል።