ትምባሆ ሕንድ እና ቻይናን ስጋት ላይ ጥሏቸዋል
ሕንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በምዕራቡ ዓለም በትምባሆ ማስታወቂያ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እየጨመረና ሲጋራ ማጨስ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ የሚሰጠው ትምህርት እየተስፋፋ በሄደ መጠን ግዙፎቹ የትንባሆ ኩባንያዎች ሸቀጣቸውን ለማራገፍ ወደ ምሥራቁ ዓለም ዞር ብለዋል። በዓለም ባንክ የተደገፉ ጥናቶች እንደተነበዩት በ2010 ቻይና ውስጥ በየዓመቱ በትምባሆ ሳቢያ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር አንድ ሚልዮን ሊደርስ ይችላል። ከ29 ዓመት በታች የሆኑ 100 ሚልዮን ቻይናውያን ሲጋራ አጫሽ በመሆናቸው ምክንያት ሞት እንደሚጠብቃቸው የብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ዘግቧል።
ወደ አንድ ቢልዮን የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት ያላት ሕንድም እንደ ቻይና ሁሉ “ከትንባሆ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር የሚሠቃዩ ሕዝቦቿ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረና እያሻቀበ” እንዳለ የዓለም ጤና ድርጅት አስልቷል። በዚህች አገር በየዓመቱ ወደ 20 ሚልዮን የሚጠጉ ልጆች ማጨስ እንደሚጀምሩ ዘገባዎች ያሳያሉ። በደቡብ ሕንድ የሚኖር አንድ ሰው ለበርካታ ዓመታት ከባድ አጫሽ ነበር። ሲጋራን እርግፍ አድርጎ ለመተው እንዲችል ለረዳው አንድ የንቁ! መጽሔት ጽሑፍ የተሰማውን አድናቆት ለመግለጽ ለአዘጋጆቹ ደብዳቤ ጻፈ። ጽሑፉ “እኛ አቁመናል—አንተም ማቆም ትችላለህ!” በሚል ርዕስ በየካቲት 1999 እትም ላይ የወጣ ነበር።
ማጨስ ለማቆም ምን ምክንያቶች ማቅረብ ይችላሉ? አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? በተባለው ባለ 32 ገጽ ብሮሹር ገጽ 25 ላይ አንዳንድ ትኩረት የሚስቡ ምክንያቶች ቀርበዋል። ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ አለዚያም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው በመላክ አንድ ቅጂ እንዲላክልዎት መጠየቅ ይችላሉ።
□ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር ላኩልኝ።
□ መጽሐፍ ቅዱስ መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።