የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 11/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ንባብ እንደ ዋዛ
  • በጫማ ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና እክሎች
  • የዓለማችን ትልቁ ባክቴሪያ?
  • ኤድስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው
  • ሥነ ምግባር እየተሻሻለ ነውን?
  • በቻይና መጽሐፍ ቅዱስ በመታተም ላይ ነው
  • የካናዳ ወጣቶችና ሃይማኖት
  • የጸሎት መመሪያ በዌብ ሳይት
  • ፈጣን በረሮዎች
  • ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አስከሬኖች በጋንጂዝ ወንዝ
  • የአፈና ንግድ
  • አሲድና የጥርስ መበስበስ
  • መፍትሔው የጃፓኖቹ አሻንጉሊት ይሆን?
  • ኃጢአትን በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ጨቅላ ሕፃናት መጠመቅ አለባቸው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—1998
ንቁ!—1999
g99 11/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ንባብ እንደ ዋዛ

መጻሕፍት መደርደሪያውን በመጻሕፍት የሞላ ሁሉ ትጉህ አንባቢ ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል የመጻሕፍት መደብር ባለቤት የሆነው ክሪስ ማቴዎስ “መጽሐፍ መሰብሰብ እወዳለሁ ሆኖም አላነባቸውም” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ማቴዎስ የዚህ ዓይነት ችግር ላለባቸው ቀላል መፍትሔ አግኝቶላቸዋል። ከሥራ ሸሪኩ ጋር ሆኖ በጀርመን የመጀመሪያ የሆነውን የአርቴፊሻል መጻሕፍት መደብር እንደከፈተ ቬዘር ኩሪየር የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል። “ከውጪ ሲታዩ መጽሐፍ የሚመስሉ” ወደ 2,800 የሚጠጉ የኪነ ጥበብ፣ የፍልስፍናና የሳይንስ አርቴፊሻል መጻሕፍት ለገበያ አቅርበዋል። እነዚህ አርቴፊሻል መጻሕፍት የሚዘጋጁት በተለያዩ ንድፎች ነው። አንዳንዶቹ በተራ ካርቶን የሚዘጋጁ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ውድ በሆኑ የመጻሕፍት ሽፋኖች ይዘጋጃሉ። ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡትን የኪነ ጥበብ መጻሕፍት አስመስለው በመሥራት ከ10 እስከ 15 በሚደርስ የአሜሪካ ዶላር ይሸጣሉ። “መጻሕፍቱ ዋጋቸው የሚተመነው በይዘታቸው ሳይሆን በመጠናቸው ነው” በማለት ማቴዎስ ተናግሯል።

በጫማ ሳቢያ የሚከሰቱ የጤና እክሎች

“ከስድስት ሰዎች መካከል አንዱ በአብዛኛው በጫማ ሳቢያ የሚከሰት ከባድ የእግር ችግር እንደሚገጥመው የሕክምና አስተያየቶች ይጠቁማሉ” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። በጉልበት፣ በወገብና በዳሌ ላይ የሕመም ስሜት ከተሰማህ ወይም ራስህን ካመመህ ምናልባት ባደረግከው ጫማ ሳቢያ የተከሰተ ችግር ሊሆን ይችላል። “ጫማው እንደ እግርህ ሁኔታ እየተስተካከለ እንደማይሄድ መዘንጋት የለብህም። ይልቁንም ከጫማው ጋር እየተስተካከለ የሚሄደው እግርህ ነው” በማለት ስታር ይናገራል። “ከጊዜ በኋላ ሰፋ ማለቱ አይቀርም ብለህ በማሰብ ጠባብ ጫማ አትግዛ። እዛው የጫማ መደብር ውስጥ እያለህ ስትለካው እግርህን ከያዘህ ፈጽሞ መግዛት የለብህም።” “ብዙውን ጊዜ እግርህ ከቀኑ የመጀመሪያ ሰዓታት ይልቅ በኋለኞቹ ሰዓታት አበጥ እያለ ስለሚሄድ” ጫማህን ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ብትገዛ ይመረጣል። በተጨማሪም “ጫማው ተረከዝህን ብቻ ሳይሆን ከጎንና ከጎንም ሊይዝህ አይገባም።” አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በእግር ላይ በሚደርስ ችግርና ጉዳት በብዛት የሚጠቁት ሴቶች ሲሆኑ ይህም የሆነበት ምክንያት 90 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች “በጣም ትንሽና እግራቸውን ጥብቅ አድርጎ የሚይዝ ጫማ ስለሚያደርጉ” እንደሆነ ይገመታል። እንዲሁም “ብዙውን ጊዜ ረዥም ተረከዝ ያላቸው ጫማዎች በእግር ላይ አንድ ዓይነት ጉዳት ያደርሳሉ።” “የሕመም ስሜት የሚሰማው ጉዳት ከደረሰ በኋላ እንደሆነ ማስታወሱ በጣም አስፈላጊ ነው” በማለት ጋዜጣው ጨምሮ ገልጿል።

የዓለማችን ትልቁ ባክቴሪያ?

ሃይዲ ሹልትስ የተባሉ በማክስ ፕላንክ የባሕር ውስጥ ማይክሮባዮሎጂ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ አንዲት ሳይንቲስት አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በናሚቢያ የባሕር ዳርቻ በውቅያኖስ ወለል ውስጥ ባለ ደለል ላይ አንድ ግዙፍ ባክቴሪያ አገኙ። ይህ ዘአካል ዲያሜትሩ 0.75 ሚሊ ሜትር ሲሆን እስካሁን ድረስ ከሚታወቁት ከየትኞቹም ባክቴሪያዎች 100 ጊዜ እጥፍ ይተልቃል። “እንበልና አማካይ የሆነ መጠን ያለው አንድ ባክቴሪያ የአይጥ ግልገልን ያህል የሚሆን መጠን ቢኖረው ይህ በቅርቡ የተገኘው ባክቴሪያ አንድ ግዙፍ ዓሣ ነባሪ ያክላል ማለት ነው” ሲል የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል። እነዚህ ዘአካላት ታዮማርጋሪታ ናሚቢየንሲስ በመባል የሚታወቁ ሲሆን ልክ በክር እንደተያያዙ ሉሎች እርስ በርሳቸው በስሱ የተያያዙ ናቸው። ዘ ታይምስ እንዳለው ከሆነ ባክቴሪያዎቹ “ምግባቸውን የሚያገኙት በባሕር ውኃ ውስጥ በሚገኘው ናይትሬት አማካኝነት ኬሚካላዊ ለውጥ ከሚያካሂዱበት ሰልፋይድ ከተባለ ውሁድ ነው።”

ኤድስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው

ባለፉት አሥር ዓመታት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የሰዎች አማካይ የዕድሜ ጣሪያ ስድስት ዓመት ገደማ የቀነሰ ሲሆን ወደፊትም ገና ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በእዚህ አካባቢ ባሉ አገሮች “የኤድስ ወረርሽኝ በአስደንጋጭ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ ስለሆነ ነው” በማለት ዘ ዩኔስኮ ኩርዬር ዘግቧል። በአሁኑ ወቅት ከ10 በመቶ የሚልቀው የዚህ አካባቢ ነዋሪ ኤድስ አማጭ በሆነው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ተለክፏል። ክፉኛ የተጠቁት አገሮች ቦትስዋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚብያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ “በአፍሪካ በየቀኑ 5,500 የሚሆኑ ከኤድስ ጋር ግንኙነት ያላቸው የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ይፈጸማሉ” በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰጠውን መግለጫ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጠቅሶ ዘግቧል።

ሥነ ምግባር እየተሻሻለ ነውን?

በቻይና በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው “ከትዳር ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም በቻይናውያን አዋቂዎች ዘንድ የተለመደ ነገር ቢሆንም በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙት አብዛኞቹ ወጣቶች ግን አሁንም ቢሆን እንዲህ ያለውን ድርጊት ይቃወማሉ” በማለት ቻይና ቱዴይ መጽሔት ዘግቧል። ይህ 8,000 የሚያክሉ ሰዎች ተጠይቀው ከሰጡት አስተያየት የተገኘ መረጃ ነው። “ከእነዚህ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ሦስት አምስተኛ የሚሆኑት አጉል ቅርርብ በመፍጠር የሌላን ሰው ትዳር የሚያፈርሱ ሁሉ በገንዘብ ወይም በሌላ መንገድ መቀጣት እንዳለባቸው ሲናገሩ፣ ከ37 እስከ 45 በሚደርስ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ግን እንዲህ የሚያደርጉትን መቅጣት አስፈላጊ ሆኖ እንደማይታያቸው” ጥናቱ አመልክቷል።

በቻይና መጽሐፍ ቅዱስ በመታተም ላይ ነው

“ቻይና ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ያሳተመች ሲሆን ከ1990ዎቹ ዓመታት መግቢያ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ በአገሪቷ ከፍተኛ እውቅና ካተረፉ መጻሕፍት መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል” በማለት ሺንሁዋ የተባለ የዜና ወኪል ተናግሯል። በቻይና የማኅበራዊ ሳይንስ አካዳሚ የዓለም ሃይማኖቶች ተቋም ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ፈንግ ጂንዩአን እንዳሉት በቻይና የሚገኙ ክርስቲያኖች ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች የመግዛት መብት አላቸው። እስከ አሁን “የቻይንኛ ትርጉም የያዙ የእንግሊዝኛ እትሞችን፣ በነባሩና ቀለል ብሎ በቀረበው ፊደል የተዘጋጀ የቻይንኛ እትምን፣ በአናሳ ጎሳዎች ቋንቋ የተዘጋጁ እትሞችን እንዲሁም በቀላሉ በእጅ ሊያዙ የሚችሉና በአትራኖስ ላይ የሚቀመጡትን ጨምሮ” ከ20 የሚበልጡ የተለያዩ እትሞች ተዘጋጅተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዙ በርካታ መጻሕፍት የታተሙ ሲሆን በሽያጭ መጽሐፍ ቅዱስን ልቀው እንደሚሄዱ ይገመታል። “ከ1990ዎቹ ዓመታት መግቢያ ጀምሮ በአገሪቷ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩት መጻሕፍት መካከል መጽሐፍ ቅዱስ 32ኛውን ደረጃ የያዘ ቢሆንም በጥቅሉ ሲታይ ግን ሃይማኖት በቻይና ሕዝብ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ በምዕራቡ ዓለም ሕዝብ ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ ያነሰ እንደሆነ” ጽሑፉ ጨምሮ ተናግሯል።

የካናዳ ወጣቶችና ሃይማኖት

“በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኙት የካናዳ ወጣቶች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በአምላክ የሚያምኑ” ሲሆን “ወደ ሃይማኖታዊ ተቋሞች አዘውትረው የሚሄዱት ግን 15 በመቶዎቹ ብቻ” እንደሆኑ ቫንኩቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ይህን ያህል የጎላ ልዩነት ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? አንዳንዶቹ ሃይማኖታቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ያደረጋቸው “ብዙዎቹ ሥርዓተ ቅዳሴዎች አሰልቺ” መሆናቸው ሲሆን “የማያፈናፍኑት መሠረተ ትምህርቶች የወጣቶቹን ስሜት ያኮላሹታል።” ጋዜጣው እንዲህ ሲል አክሎ ገልጿል:- “የሃይማኖት ድርጅቶች ስም በጋዜጦች የመጀመሪያ ገጾች ላይ በሚወጡ ወሲባዊ በደል ስለፈጸሙ የክርስትና ቀሳውስት፣ ስለ ሲኪዎች ዓመፅ፣ ስለ ጽንፈኛ አይሁዶችና ስለ ሂንዱ ነውጠኞች በሚያወሱ ዘገባዎች በእጅጉ እንደጎደፈ ምንም ጥርጥር የለውም። በ1984 በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ የካናዳ ወጣቶች መካከል 62 በመቶዎቹ በሃይማኖት መሪዎች ላይ እምነት የነበራቸው ሲሆን ዛሬ ግን ቁጥራቸው አሽቆልቁሎ ወደ 39 በመቶ እንደወረደ የተካሄዱት ጥናቶች አመልክተዋል።” ዘገባው እንዲህ ሲል ደምድሟል:- “ወይ ወጣቶቹ የሃይማኖት ቀሳውስቱ ልባዊ አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ሆኖ አይሰማቸውም፣ ወይም በብዙሃኑ ዘንድ የተለመደው ነገር በሃይማኖት ተቋማቱ ዘንድ በጥሩ ዓይን አይታይም፣ አለዚያም ደግሞ የሚተላለፈው መንፈሳዊ መልእክት የአብዛኞቹን ወጣቶች ስሜት አይማርክም። ወይም ሁሉም ምክንያቶች ተጠቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ።”

የጸሎት መመሪያ በዌብ ሳይት

የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ የራሷ የሆነ የኢንተርኔት ዌብ ሳይት ከፍታለች። በዚህ ዌብ ሳይት ውስጥ የጸሎት መመሪያ ይገኛል። ቤተ ክርስቲያኗ አምላክ ማንኛውንም ጸሎት እንደሚሰማ በመግለጽ ሰዎች የራሳቸው የሆነ ጸሎት በማዳበር እንዲጸልዩ አጥብቃ በመገፋፋት ላይ ትገኛለች። “ሐሳባችሁን ማሰባሰብ እንድትችሉ ይረዳችሁ ዘንድ ሙዚቃ፣ ድንጋይ፣ ላባ፣ አበባ ወይም ሻማ ተጠቀሙ፤” እንዲሁም “እጃችሁን ተጠቀሙ። ጣቶቻችሁ ልትጸልዩባቸው የሚገቡ የተለያዩ ነገሮችን [ወደ] አእምሯችሁ ለማምጣት ሊረዷችሁ ይችላሉ።” ለምሳሌ ያህል አውራ ጣታችሁ ከጣቶቻችሁ ሁሉ ይበልጥ ጠንካራ እንደመሆኑ መጠን በሕይወታችሁ ውስጥ ከፍ ያለ ግምት ለምትሰጧቸው እንደ ቤትና ቤተሰብ ላሉ ነገሮች እንድትጸልዩ ሊያስታውሳችሁ ይችላል ሲል መመሪያው ይገልጻል። መካከል ላይ ያለው ረጅሙ ጣት “በዓለም ላይ በሥልጣን ቦታ ላይ ላሉ ሰዎች” እንድትጸልዩ ሊያስታውሳችሁ ይችላል። ትንሿ ጣት ደግሞ “ስለ ራሳችሁ እንድትጸልዩ” ልታስታውሳችሁ ትችላለች። ዘ ታይምስ በዚህ አዲስ አሠራር ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “የዌብሳይቱ ይዘት ቤተ ክርስቲያኗ ሕዝቡ ምን ያህል ዓለማዊ ሆኖ እንደሚታያት የሚያመለክት ነው። ዌብሳይቱ የጸሎትን ሥርዓት የተመጠነ ምግብን ከመመገብ ወይም የአትክልት ሥፍራን ከማረም ጋር አመሳስሎታል:- ‘ጸሎቱ አጭር ሆኖ የሚዘወተር ቢሆን ይመረጣል፤ መቋረጥ ግን የለበትም።’”

ፈጣን በረሮዎች

በረሮዎችን ለመያዝ የሞከረ ማንኛውም ሰው በረሮን መያዝ ቀላል እንዳልሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። ምስጢሩ ምንድን ነው? አንደኛ ነገር፣ በሆዳቸው ግራና ቀኝ ጠላት በሚወስደው እርምጃ ሳቢያ የሚከሰተውን እያንዳንዱን የአየር እንቅስቃሴ የሚጠቁሙና አቅጣጫውን የሚያመለክቱ ጥቃቅን ጸጉሮች አሏቸው። በተጨማሪም ነርቫዊ ቅንባሯቸው ከፍተኛ ቅልጥፍና ያለው በመሆኑ በረሮዎቹ በአንድ ሴኮንድ አንድ መቶኛ ጊዜ ውስጥ እርምጃ መውሰድና ማምለጥ ይችላሉ። ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ጄፍሪ ካምሂ እና ባልደረቦቻቸው ከፍተኛ ፍጥነት ያላቸውን ነገሮች የሚያነሳ ካሜራ በመጠቀም ሌላም ነገር ማስተዋል እንደቻሉ በርሊነር ሞርገንፖስት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በረሮዎች በአንድ ሴኮንድ ውስጥ 1 ሜትር መሮጥ የሚችሉ ሲሆን በዚሁ ፍጥነት በአንድ ሴኮንድ ውስጥ 25 ጊዜ አቅጣጫቸውን መቀያየር ይችላሉ። ካምሂ “በእንዲህ ያለ ከፍተኛ ፍጥነት አቅጣጫውን መለዋወጥ የሚችል ሌላ እንስሳ እስካሁን አልገጠመንም” ሲሉ መናገራቸውን ኒው ሳይንቲስት ጠቅሶ ዘግቧል። “በረሮ ጠንቀኛ ባትሆን ኖሮ የሚገባትን አድናቆት ባገኘች ነበር።”

ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አስከሬኖች በጋንጂዝ ወንዝ

“ሂንዱዎች ሞክሻን ያስገኛል ወይም ነፍስ ከሥጋዊ ሕልውና ዑደት እንድትላቀቅ ያደርጋል በሚል እምነት ለበርካታ መቶ ዘመናት የሞቱ ዘመዶቻቸውን ጋንጂዝ ወንዝ ውስጥ ሲጨምሩ ኖረዋል” ሲል ኤሌክትሮኒክ ቴሌግራፍ ገልጿል። “ከፍተኛ ጥልቀት ያለው የጋንጂዝ ወንዝ 2,500 ኪሎ ሜትሮችን በሚያቋርጥበት ጊዜ ፈረሰኛው ውኃ በመቶዎች የሚቆጠሩ አስከሬኖችን እያግበሰበሰ ይሄዳል። ሆኖም ባለፉት ዓመታት ወደ ወንዙ በሚገቡት የኢንዱስትሪ ዝቃጮችና ቆሻሻዎች ሳቢያ የወንዙ ፍጥነትና ጥልቀት እየቀነሰ መጥቷል።” በዚህም የተነሳ አስከሬኖቹ “ወንዙ ውስጥ ባሉት አረሞችና ቆሻሻዎች ተይዘው ለሳምንታት ይቆያሉ።” በ1980ዎቹ ዓመታት መገባደጃ ላይ መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ ስጋ በል ኤሊዎችን ጋንጂዝ ወንዝ ውስጥ በመጨመር ችግሩን ለመቅረፍ ሞክሮ ነበር። ሆኖም ኤሊዎቹ ሊመገቡት ከሚችሉት በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አስከሬን በመኖሩና ኤሊዎቹ ራሳቸው በአዳኞች ስለሚወሰዱ ፕሮጄክቱ በ1994 ሊቋረጥ ችሏል። ሰዎች የዘመዶቻቸውን አስከሬኖች አንድም እንዲያቃጥሉ አለዚያም በወንዙ ዳርቻ ባለው አሸዋ ውስጥ እንዲቀብሩ ለማግባባት አዲስ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።

የአፈና ንግድ

“አፈና ... እንደ ሜክሲኮ፣ ኮሎምቢያ፣ ሆንግ ኮንግና ሩስያ ባሉ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ የሚዛቅበት ንግድ ሆኗል” ይላል ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት። “በዓለም ዙሪያ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል የሚታገቱት ሰዎች ቁጥር ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ከምንጊዜውም በበለጠ እየጨመረ መጥቷል።” ከፍተኛውን ቁጥር ያስመዘገበችው ላቲን አሜሪካ ስትሆን በዚህች አህጉር ከ1995 እስከ 1998 ባሉት ዓመታት ውስጥ 6,755 የአፈና ድርጊቶች ተፈጽመዋል። ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ደረጃዎች የያዙት እስያና የሩቅ ምሥራቅ አገሮች (617)፣ አውሮፓ (271)፣ አፍሪካ (211)፣ መካከለኛው ምሥራቅ (118) እና ሰሜን አሜሪካ (80) ናቸው። ከሚታገቱት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ነጋዴዎችና ባለርስቶች ቢሆኑም እንኳ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞችን፣ ለንግድ ሥራ ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችንና ጎብኚዎችን ጨምሮ ማንኛውም ሰው ለዚህ አደጋ ሊጋለጥ ይችላል። ኢንተርናሽናል የሆኑ ኩባንያዎች የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ እንዲሁም ፕሮፌሽናል የሆኑ አደራዳሪዎችና የሥነ ልቦና አማካሪዎች የሚጠይቁትን ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ኢንሹራንስ በመግባት ላይ ናቸው። አጋቾቹ ሊያግቷቸው ያሰቧቸውን ሰዎች በተመለከተ የተሟላ መረጃ የሚያሰባስቡና ሊከተል የሚችለውን አደጋ በሚገባ የሚያጠኑ የተደራጁ ሰዎች ናቸው። ያገቷቸው ሰዎች ለማምለጥ የሚያደርጉትን ሙከራ በእጅጉ ለመቀነስና ገንዘቡን ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ ለማስፋት ሲሉ ብዙውን ጊዜ ያገቷቸውን ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ይይዟቸዋል። “በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ ከ10 የአፈና ድርጊቶች መካከል ለሞት የሚዳረገው አንድ ታጋች ብቻ ነው” ይላል መጽሔቱ፤ ሆኖም የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አላለፈም:- “የአካባቢውንም ፖሊሶች በጥርጣሬ ዓይን ልታዩአቸው ይገባል። ብዙውን ጊዜ ከአጋቾቹ ጋር ይሻረካሉ።”

አሲድና የጥርስ መበስበስ

ኦራል ሄልዝ:- ዳይት ኤንድ አዘር ፋክተርስ የተባለውን ጽሑፍ ካዘጋጁት ሰዎች አንዱ የሆኑት ማይክ ኤድጋር “ሰዎች ለጥርስ መቦርቦር ምክንያቱ ስኳር ብቻ እንደሆነ አድርገው ከማሰብ ይልቅ አፋቸው ውስጥ አሲድ በሚተዉ ምግቦች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል። በቁርስ ሰዓት የብርቱካን ጭማቂ የሚጠጡ ወይም ደግሞ አሲድ ያላቸውን ምግቦች የሚበሉ ሰዎች እነዚህን ምግቦች ከተመገቡ በኋላ ጥርሳቸውን ከመቦረሻቸው በፊት ቢያንስ ቢያንስ ግማሽ ሰዓት ያህል እንዲቆዩ ሪፖርቱ ምክሩን ይለግሳል። ለምን? በአፍ ውስጥ ያለው አሲድ ከአንድ የተወሰነ መጠን በሚያልፍበት ጊዜ ከላይ የሚገኘው ነጩ የጥርስ ክፍል ስለሚሳሳ በሚቦረሽበት ጊዜ መፈግፈግ ይጀምራል። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው እንደ ፎርማጆ ወይም ኦቾሎኒ ያሉ ፕሮቲን በብዛት ያላቸውን ምግቦች በመመገብ የአሲድ መጠኑን መቀነስ እንደሚችል ተገልጿል። ሆኖም አንድ ሰው ይህን ማድረግ ያለበት አሲድ ያላቸውን ምግቦች በተመገበ በ20 ደቂቃ ጊዜ ውስጥ መሆን እንዳለበት የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል።

መፍትሔው የጃፓኖቹ አሻንጉሊት ይሆን?

ከልጅ ልጆቻቸው ርቀው ለሚኖሩና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር እምብዛም የመገናኘት አጋጣሚ ለሌላቸው አያቶች አንድ የቶኪዮ የንግድ ድርጅት አንድ መፍትሔ አቅርቧል:- የሕፃኑን ልጅ ፎቶ ለድርጅቱ መላክ ብቻ ነው፤ በስድስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሕፃኑን ልጅ የሚመስል አሻንጉሊት ታገኛላችሁ። “በዚህ ብቻ አያበቃም” ይላል የኒው ሳይንቲስት ዘገባ። “አሻንጉሊቱ ውስጥ ያለው አሃዛዊ ማይክሮቺፕ መቅጃ ልጃችሁ በደስታ ስሜት የሚያሰማውን ድምፅ ስለሚቀዳ ልክ የልጃችሁ ዓይነት ድምፅ ማውጣት ይችላል። የአሻንጉሊቱን እጅ ያዝ ስታደርጉት የሕፃኑን ድምፅም ሆነ የቀዳችሁትን ማንኛውንም ዓይነት ድምፅ ያሰማችኋል። ዘ ኒኬይ ዊክሊ የተባለው ጋዜጣ እንዳለው ከሆነ 400 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣውን ይህን አሻንጉሊት በአብዛኛው የሚያዙት የልጅ ልጆቻቸውን እምብዛም የማየት አጋጣሚ የሌላቸው አያቶች ናቸው።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ