ከዓለም አካባቢ
ተስፋ የቆረጠ ትውልድ
ዛሬ ከ15 እስከ 24 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ዝንባሌ ከሁለት ትውልድ በፊት ይኖሩ ከነበሩ በተመሳሳይ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ዝንባሌ ጋር በማወዳደር የተደረጉ ጥናቶች እንዳመለከቱት ዕፅ መውሰድ፣ ወንጀልና ራስን መግደል በጣም እንደጨመረ ዚ አውስትራሊያን ዘግቧል። የስትራቴጅያዊ ጥናቶች ተንታኝና የሳይንሳዊ ጽሑፎች አዘጋጅ የሆኑት ሪቻርድ ኤከርዝሊ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩትን የበርካታ ወጣቶች ስሜት አጠቃለው ሲገልጹ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ወጣቶች ሕይወት በብዙ እንቅስቃሴዎችና በሚያስደስቱ ነገሮች የተሞላ መሆን እንዳለበት፣ በማንም ላይ መመርኮዝ ሳያስፈልጋቸው የራሳቸውን ኑሮ ተጣጥረው ማሸነፍ እንደሚኖርባቸው፣ ማንኛውም ዓይነት የአኗኗር አማራጭ ለሁሉም ክፍት መሆን እንደሚገባው፣ መንግሥታት የኅብረተሰባችንን ችግሮች የመፍታት ችሎታ እንደሌላቸው፣ እነርሱ ራሳቸውም ቢሆኑ ማህበራዊ ሁኔታዎችን የመለወጥ አቅም እንደሌላቸው ያምናሉ።” ሻኑ የተባለች አንዲት የ15 ዓመት ወጣት “የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ መጠን በመጨመር ላይ ነው፣ ዘወትር እየቀነሱ የመጡትን ሥራዎች፣ ቤቶች፣ ሁሉንም ነገሮች ለማግኘት መሻማት ግዴታችን ነው” ብላለች።
ተዛማች በሽታዎች እየተበራከቱ ነው
ናሱሼ ኑዌ ፕሬሴ ሪፖርት እንዳደረገው “ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ጨርሶ እንግዳ የሆኑና ከፍተኛ የተዛማችነት ባሕርይ ያላቸው 30 ዓይነት በሽታዎች ብቅ ብለዋል።” እንደ ኢቦላ፣ ኤድስና ሄፓታይተስ ሲ ላሉት አብዛኞቹ መሰል በሽታዎች መድኃኒት አልተገኘላቸውም። ከዚህም በተጨማሪ እንደ ወባ፣ ኮሌራና ሳንባ ነቀርሳ ያሉት ተዛማች በሽታዎችም እየተስፋፉ መጥተዋል። ለምን? የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደዘገበው “ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ቫይረሶች እስካሁን በሰፊው የሚሠራባቸውን አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች የመቋቋም ኃይል እያዳበሩ በመምጣታቸው ብዙ በሽታዎች ዳግም እያገረሹ ነው። አዳዲስ የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን ማዘጋጀት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ የሚሠሩት አዳዲስ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች እጅግ ጥቂት ናቸው።” የዓለም የጤና ድርጅት ሁኔታውን ለመለወጥ በማሰብ መንግሥታትና መድኃኒት አምራች ተቋማት “አዳዲስ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን በማዘጋጀቱና ተላላፊ በሽታዎችን በምርመራ ለይቶ የማወቁን ዘዴ በማጠናከሩ መስክ ይበልጥ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ” ተማጽኗል። በ1996 ወደ 55 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች በተዛማች በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ጦረኛ ዝንጀሮዎች
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተሽከርካሪ ከሚበዛባቸው የደቡብ አፍሪካ አውራ ጎዳናዎች በአንዱ ላይ ይጓዙ የነበሩ አሽከርካሪዎች እንግዳ የሆነ አደጋ አጋጥሟቸዋል። የዝንጀሮዎች ጭፍራ የድንጋይ ውርጅብኝ አወረደባቸው። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪብዩን እንዳለው ዝንጀሮዎቹ ከኬፕ ታውን ወደ ጆሃንስበርግ በሚወስደው መንገድ በአንድ ተራራማ መተላለፊያ ላይ ደፈጣ አድርገው በአሽከርካሪዎች ላይ አደጋ ጥለዋል። በዚህ ምክንያት ከባድ አደጋ የደረሰበት ወይም የተጋጨ አሽከርካሪ ባይኖርም የትራፊክ ፖሊሶች አራዊቱን ከጎዳናው ለማራቅ የቻሉት ብዙ ድንጋይ ከተወራወሩ በኋላ ነበር። በዚህ በፖሊሶችና በዝንጀሮዎች መካከል በተደረገው የድንጋይ ውርወራ ጦርነት አሸናፊው በውል ሊታወቅ አልቻለም።
የባሕር ላይ ውንብድና ተስፋፍቷል
ዓለም አቀፍ ማሪታይም ቢሮ በመርከቦች ላይ የሚደርስ የወንበዴዎች ጥቃት እየጨመረ መሄዱን ገልጿል። በ1994 የደረሱት ጥቃቶች 90 ሲሆኑ ይህ ቁጥር ከሁለት ዓመት በኋላ 226 ደርሷል። የዚህ ወንጀል እድገት የንግድ መርከብ መኮንኖችንም ሆነ ቱሪስቶችን የሚያሳስብ ሆኗል። የለንደኑ ዘ ሳንደይ ቴሌግራፍ “ብዙ የመርከብ ባለንብረቶች ሊያስከትልባቸው የሚችለውን አክሳሪ መጓተት በመፍራት ሪፖርት ስለማያደርጉ ነው እንጂ” ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ከሁለት እጥፍ በላይ ሊሆን ይችላል ብሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይበልጥ አደገኛ የሆኑት አካባቢዎች በአልባኒያና በሊቢያ ጠረፎች አካባቢ የሚገኘው የሜድትራንያን ባሕርና የደቡብ ቻይና ባሕር ናቸው። አንድ የብሪታንያ ንግድ መርከብ ተወካይ የባሕር ላይ ውንብድናን ለመከላከል በተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ግብረ ኃይል ውስጥ ብሪታንያ በግንባር ቀደምትነት እንድትሰለፍ ተማጽነዋል። ይሁን እንጂ አንድ የመርከብ ባለንብረቶች ቃል አቀባይ “ብዙዎቹ ውንብድናዎች የሚፈጸሙት በአገሮች የባሕር ክልል ውስጥ ስለሆነ የተባበሩት መንግሥታት ግብረ ኃይል ችግሩን ያስወግዳል ብለው እንደማያምኑ” መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
አስከፊ አደጋ ያስከተሉ አለመግባባቶች
ዘ ዩሮፒያን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በ1977 በአንዲት ቃል ትርጉም ላይ የተፈጠረው አለመግባባት በዓለም ላይ ከደረሱት የአውሮፕላን አደጋዎቸ ሁሉ የከፋ አደጋ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። የዳች ተወላጅ የሆነው የ747 አውሮፕላን አብራሪ ከካናሪ ደሴቶች አንዷ በሆነችው በቴነሪፌ ለሚገኘው የበራራ ተቆጣጣሪ “ልነሳ ነው” የሚል የራዲዮ መልእክት ያስተላልፋል። የበረራ ተቆጣጣሪው የተረዳው ገና አውሮፕላኑ መንቀሳቀስ እንዳልጀመረ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ አብራሪው ጭጋግ በሸፈነው ማኮብኮቢያ ላይ ለመነሳት እያኮበኮብኩ ነው ማለቱ ነበር። ከዚህ የተነሣ አውሮፕላኑ ከሌላ 747 አውሮፕላን ጋር ተጋጭቶ 583 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በተመሳሳይም ለ349 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ለሆነው በ1996 በሕንድ ዴልሂ አቅራቢያ ለደረሰው የአየር ላይ ግጭት አስተዋጽኦ ያደረገው የቋንቋ ችሎታ ማነስ ነበር። በዚህ ምክንያት የሚከሰቱት ከባድ አደጋዎች ከስንት አንድ ናቸው፤ እንዲሁም የበረራ ሠራተኞች ደረጃውን የጠበቀ የበረራ መግባቢያ እንግሊዝኛ ይማራሉ። ቢሆንም አንዳንድ የበራራ ሠራተኞች የሚያውቁት ሙያው የሚጠይቅባቸውን ውስን ቃላት ብቻ ነው። አንድ ድንገተኛ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ የቋንቋ ችሎታቸው ይከዳቸዋል። ኤክስፐርቶች ሐሳብን በትክክል ለማስተላለፍ የሚረዳ በበረራ ክፍል ውስጥ የሚገጠም ኮምፒዩተር እንዲሠራ ሐሳብ አቅርበዋል።
የሳይንስ ሊቃውንት በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት
በ1916 ጀምስ ለበ የተባሉት አሜሪካዊ የሥነ ልቦና ምሁር 1,000 የሚያክሉ በነሲብ የተመረጡ ሳይንቲስቶችን በአምላክ ያምኑ እንደሆነ ጠይቀው ነበር። መልሳቸው ምን ነበር? መልስ ከሰጡት ሳይንቲስቶች መካከል 42 በመቶ የሚሆኑት በአምላክ እንደሚያምኑ መናገራቸውን ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ለበ ትምህርት እየተስፋፋ በሄደ መጠን በአምላክ ማመን ይቀንሳል ብለው ተንብየው ነበር። አሁን 80 ዓመት ያህል ቆይቶ የጆርጅያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ኤድዋርድ ላርሰን የለበን ጥናት ደግመዋል። ላርሰን የለበን ጥያቄዎችና ዘዴዎች በመጠቀም የባዮሎጂ፣ የፊዚክስና የሂሣብ ሊቃውንትን ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት ያለው አምላክ በመኖሩ ያምኑ እንደሆነ ጠይቀዋል። የጥናቱ ውጤት እንደሚያመለክተው አሁንም ከቀድሞው ጋር የሚመጣጠኑ ሳይንቲስቶች ማለትም 40 በመቶ የሚሆኑ በአምላክ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ዶክተር ላርሰን እንዳሉት “ለበ የሰውን አእምሮ ወይም ሳይንስ የሰውን ፍላጎቶች በሙሉ የማርካት ችሎታ የሌለው መሆኑን በትክክል አልተረዱም።”
ሕንድ በሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ ተመታች
የሳንባ ነቀርሳን ባክቴሪያ በቁጥጥር ሥር ለማዋል መጠነ ሰፊ ጥረት ቢደረግም የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በሕንድ ውስጥ ከሚገኙት ሁለት ጎልማሶች መካከል አንዱ በበሽታው እንደሚለከፍ ተናግሯል። ከ900 ሚልዮን በላይ ከሚሆኑት የሕንድ ነዋሪዎች መካከል በየዓመቱ 2 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ ሲለከፉ 500,000 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ሕመም ምክንያት ይሞታሉ ሲል ዚ ኤዢያን ኤጅ የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። የዓለም ጤና ድርጅት በገለጸው መሠረት በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥርና ከዚሁ ጋር አብሮ የሚመጣው በበሽታው የመያዙ አጋጣሚ በእጅጉ አድጓል። በሳንባ ነቀርሳ የሚለከፉት ሰዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ችግር በሽታው የሚያስከትለውን ሕመም መቋቋም ብቻ አይደለም። በአብዛኛው ከበሽታው ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ሌሎች ነገሮችም መቀበል ይኖርባቸዋል። ይህም በጎረቤቶቻቸው፣ በአሠሪዎቻቸው እና አብረዋቸው በሚሠሩት ሰዎች ዘንድ መገለልን ሊጨምር ይችላል። ወጣት ሙሽሮች ሳንባ ነቀርሳ እንዳለባቸው ከታወቀ ልጆች ለመውለድ ብቁ አይደሉም በሚል ብዙውን ጊዜ ወደ ወላጆቻቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።
ደምና የኤች አይ ቪ ልክፍት
በዓለም ዙሪያ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ከተለከፉት 22 ሚልዮን ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ፓኖስ የተባለው የመረጃ ድርጅት ሪፖርት እንዳደረገው ከሆነ “በታዳጊ አገሮች ውስጥ በዚህ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚለከፉት አዲስ ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚያክሉት የተያዙት ደምን ለሕክምና ሲሉ በመውሰዳቸው ምክንያት ነው።” በብዙ አገሮች የኤች አይ ቪን ቫይረስ ለመለየት የሚደረገው የላቦራቶሪ ምርመራ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ባለመሆኑ የደም አቅርቦት ከችግር ነጻ መሆኑ እርግጠኛ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ፓኪስታን ውስጥ ከሚገኙት የደም ባንኮች ውስጥ የኤች አይ ቪን ቫይረስ ለመለየት የሚያስችል መሣሪያ ያላቸው ከግማሽ በታች የሚሆኑት ናቸው። በዚህ ምክንያት በዚህች አገር ለመጀመሪያ ጊዜ በቫይረሱ ከሚለከፉት ሰዎች መካከል 12 በመቶ የሚሆኑት የሚለከፉት ደምን ለሕክምና ሲሉ በመውሰዳቸው ነው። ኤድስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት ከተደረገበት ከ15 ዓመታት ወዲህ በዓለም ዙሪያ 30 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች የበሽታው ተሸካሚ በሆነው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ተለክፈዋል።
የልጃገረዶች ግርዘትና በልጅነት መውለድ
ስለ ጤና፣ የተመጣጠነ ምግብና የልጆች ትምህርት የሚያወሳው ዘ ፕሮግሬስ ኦቭ ኔሽንስ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ጽሑፍ በ1996 እትሙ ላይ “በየዓመቱ በግምት ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ ልጃገረዶች ይገረዛሉ” ሲል አትቷል። “እንዲህ ያለውን ድርጊት 75 በመቶ የሚያስተናግዱት አገሮች ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄርያ፣ ሶማሊያና ሱዳን ናቸው። በጅቡቲና በሱማሊያ ከሚገኙት ልጃገረዶች መካከል 98 በመቶ የሚሆኑት ይገረዛሉ።” ግርዛቱ ከሚያስከትለው ሕመም ሌላ ለጀርም ወለድ በሽታ፣ ለብዙ ደም መፍሰስ፣ ለመካንነትና ለሞት ሊዳርጋቸው ይችላል። ሪፖርቱ እንደገለጸው “የትኛውም ሃይማኖት የሴቶች ግርዘት እንዲከናወን አይጠይቅም። ይህ ድንግልናን ለማቆየት፣ ለጋብቻ ብቁ እንድትሆንና የፆታ ፍላጎትን ለመግታት ሲባል የሚደረግ ልማዳዊ ድርጊት ነው።” ለሴቶች መብትና ለሕፃናት ደህንነት የሚቆረቆሩ ቡድኖችና ድርጅቶች መንግሥታት ይህን ድርጊት በሕግ እንዲያግዱ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው።
ሌላ ሪፖርት እንደጠቆመው ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች መውለድ በብዙ አገሮች ቋሚ ችግር ሆኗል። ለምሳሌ ያህል ዩናይትድ ስቴትስ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትገኝ ሲሆን በየዓመቱ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ከሚሆነው 1,000 ልጃገረዶች መካከል 64ቱ ይወልዳሉ። ትንሹን ቁጥር ያስመዘገበችው ጃፓን ስትሆን በዚህ የዕድሜ ክልል ከሚገኙት ሴቶች መካከል በዓመት ውስጥ የሚወልዱት 4 ብቻ ናቸው። በልጅነት መውለድ የወጣት ሴቶችን እድገት፣ ትምህርት እና ሌሎች አጋጣሚዎች ከማጨናገፉም ሌላ በሕፃኑ ላይ ችግር ያስከትላል። ይህም በቂ እንክብካቤ አለማግኘትን፣ ድህነትንና ባልሰከነ የቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ማደግን ይጨምራል።
‘የቅድስቲቷ ከተማ’ ነዋሪዎች የአምልኮ ፍቅር እያሽቆለቆለ ነው
ሮም ቅድስት ከተማ እየተባለች የምትጠራና ሊቀ ጳጳሷም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ ቢሆኑም አንዳንዶች የሚያስቡትን ያህል ሃይማኖታዊ ከተማ መሆኗ ቀርቷል። በሮም ሰርድ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ አንድ አገር አቀፍ ጥናት እንዳረጋገጠው 10 በመቶ የሚያክሉት ጣልያናውያን የክርስትናን እምነት “ጨርሶ” እንደማይፈልጉ ሲገልጹ ሮም ውስጥ ይህ ቁጥር ወደ 19 በመቶ ይደርሳል። ሌሎች 21 በመቶ የሚያክሉ ሮማውያን ደግሞ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “እምብዛም” ጉጉት እንደሌላቸው ላ ሪፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ ስለ ሃይማኖታቸው ከልብ የሚጨነቁት 10 በመቶ የሚያክሉት ብቻ ናቸው። ሶሺዎሎጂስቱ ሮቤርቶ ቺፕሪያኒ እንዳሉት ከሆነ ቤተ ክርስቲያን ስለ አስተሳሰብና ስለ ግል ባሕርይ የምታስተምረውን ነገር በጥብቅ የሚከታተለው ከ4 ሮማውያን አንዱ ብቻ ነው።