የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 12/07 ገጽ 26-27
  • ታላላቅ ስኬቶችን ያገኙ ንጉሥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታላላቅ ስኬቶችን ያገኙ ንጉሥ
  • ንቁ!—2007
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ታሪክ በጽሑፍ እንዲሰፍር አስችለዋል
  • የአምላክን ስም በስዋሂሊ ማሳወቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ‘ንጹሑን ቋንቋ’ አጥርተህ ትናገራለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ቋንቋዎች ለሐሳብ ልውውጥ እንደ ድልድይ ወይም እንደ አጥር ሊሆኑ ይችላሉ
    ንቁ!—2000
  • በሕይወት በሚገኙ ቋንቋዎች “የሚናገር” መጽሐፍ
    ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2007
g 12/07 ገጽ 26-27

ታላላቅ ስኬቶችን ያገኙ ንጉሥ

ካሜሩን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ኢብራሂም ጆያ አሁንም ድረስ በምዕራብ ካሜሩን የሣር ምድር ላይ የሚኖረው ባሙም በመባል የሚታወቀው ትልቅ ጎሳ 17ኛው ንጉሥ ነበሩ። ከ12ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የገዙ ነገሥታትን ስም የያዘው በቀጣዩ ገጽ ላይ የሚገኘው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው እኚህ ንጉሥ ከ1889 አንስቶ እስከ ሞቱበት እስከ 1933 ድረስ ገዝተዋል። በጆያ የግዛት ዘመን ፈረንሳዮችና ጀርመኖች አካባቢውን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ሞክረው ነበር።

ጆያ ከወጣትነታቸው ጊዜ አንስቶ ብልህና በተፈጥሮ አስተዋይ የነበሩ ከመሆኑም ሌላ አስተሳሰባቸውን ከሚጋሩ ጥሩ እውቀትና የፈጠራ ችሎታ ካላቸው ሰዎች ጋር ይቀራረቡ ነበር። ከዚህ በታች ባለው ፎቶ ግራፍ ላይ የሚታየው ጆያ የገነቡት አስደናቂ ንድፍ ያለው ቤተ መንግሥት እኚህ ንጉሥ የተዋጣላቸው መሃንዲስ እንደነበሩ ይጠቁማል። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ገጽ ላይ የሚታየውን በቆሎ ለመፍጨት የሚያገለግል ወፍጮ ፈልስፈዋል። ይበልጥ ትኩረት የሚስበው ግን የባሙምን ቋንቋ በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችል ዘዴ መፈልሰፋቸው ነው።

ታሪክ በጽሑፍ እንዲሰፍር አስችለዋል

እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ድረስ የባሙም ሕዝብ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው በቃል ነበር። ጆያ ታሪክን በዚህ መንገድ ማስተላለፉ አንዳንድ ዝርዝር ሐሳቦች እንዲዘነጉ ወይም የሌለ ነገር እንዲጨማመርባቸው ሊያደርግ እንደሚችል ተገነዘቡ። ግዛቱን አቋርጠው ከሚያልፉት ነጋዴዎች በአረብኛ የተጻፉ መጻሕፍት አግኝተው ስለነበር ይህን ቋንቋ ያውቁ ነበር። እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካ ላይቤሪያ ውስጥ ጥቅም ላይ ይውሉ ስለነበሩት ጥንታዊ የቫይ ፊደላት ሳያውቁ አይቀሩም። ከዚህ በመነሳት የራሳቸውን ቋንቋ በጽሑፍ ለማስፈር የሚያስችል አዲስ ዘዴ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመሩ።

ጆያ በመቶ የሚቆጠሩ ምልክቶችን በመቅረጽ ሥራቸውን ጀመሩ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በሥዕል መልክ የተቀመጡ ናቸው። ይህ ዘዴ እያንዳንዱ ምልክት ምን ነገር እንደሚወክል ማስታወስ ይጠይቃል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ጆያ በባለሟሎቻቸው እየታገዙ ይህንን የአጻጻፍ ዘዴ ይበልጥ ቀላል እያደረጉት መጡ። በፊደላቱ ላይ ቀለማትን ወይም ክፍለ ቃላትን በመጨመር (syllables) የምልክቶቹን ቁጥር ለመቀነስ ጥረት አደረጉ። አንዳንዶቹን ምልክቶች ወይም ፊደላት አንድ ላይ በማጣመር ቃላትን መመሥረት ተቻለ። አንባቢው ማስታወስ የሚያስፈልገው በጣም ጥቂት ፊደላትንና አነባበባቸውን ብቻ ነው። ጆያ ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሰባ ፊደላት ያሉትን ይህን አዲስ የአጻጻፍ ስልት አካኡኩ ብለው ሰየሙት።

ጆያ ይህ አዲስ የአጻጻፍ ስልት በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ እንዲሁም በመላው ግዛቱ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ እንዲጠቀሙበት አዘዙ። በእሳቸው ሥርወ መንግሥትም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ የተከናወኑ አስደናቂ ታሪኮች በዚህ አዲስ የአጻጻፍ ስልት አማካኝነት እንዲጻፍ ትእዛዝ አስተላለፉ። በዚህም ምክንያት የባሙም ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚመራበት ሕግና ስለ ባሕሉ በራሱ ቋንቋ ማንበብ ቻለ። ከዚህም በተጨማሪ ጆያ መድኃኒት ለመቀመም የሚያስችሉ መመሪያዎች በዚህ አዲስ ዘዴ አማካኝነት በጽሑፍ እንዲሰፍሩ አድርገው ነበር። በዚያ ጊዜ ከተጻፉት ጽሑፎች መካከል ከ8,000 የሚበልጡት አሁን ድረስ በቤተ መዛግብት ውስጥ ይገኛሉ።

ጀርመናውያን ቅኝ ገዢዎች በ1902 አካባቢውን ከተቆጣጠሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዚህ አጻጻፍ ዘዴ ጠቀሜታ ይበልጥ ግልጽ ሆነ። ጆያ በወቅቱ ከተገኘው የኢኮኖሚ እድገት የተጠቀሙ ቢሆንም የጀርመን ባለ ሥልጣናት በሚሉት ሐሳብ ያልተስማሙባቸው ጊዜያት ነበሩ። የማይስማሙባቸው ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ለጀርመኖች እንግዳ የሆነውን ይህን አዲስ የአጻጻፍ ስልት በመጠቀም መመሪያ ያስተላልፉ ነበር። ይሁንና ይህ የባሙም የአጻጻፍ ዘዴ የቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነበር?

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት (1914-1918) ጀርመን በጆያ ግዛት ላይ የነበራትን የበላይነት አጣች። ከጊዜ በኋላ አዲስ የተቋቋመው የመንግሥታቱ ቃል ኪዳን ማኅበር ፈንሳይ አካባቢውን በሞግዚትነት እንድታስተዳድር ፈቀደ። ጆያ አዳዲስ ሐሳቦችን ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆኑም በአገራቸው ባሕል የሚኮሩ ከመሆኑም በላይ የሕዝቡን ባሕል ጠብቆ ለማቆየትና ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው። ግዛቱን በቅኝ ከያዙት ከፈረንሳዮች ጋር ያጋጫቸው ይህ አመለካከታቸው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ቅኝ ገዥዎች ታማኝ ያልሆኑ የአካባቢው መሪዎችን እንደሚያደርጓቸው ሁሉ ፈረንሳይም ጆያን በ1931 ከሥልጣን አስወገደቻቸው። ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ በስደት ላይ እያሉ ሕይወታቸው አለፈ።

ፈረንሳይ አዲሱ ፊደል በትምህርት ቤቶች ጥቅም ላይ እንዳይውል ስላገደችና ጆያ ከሞቱ በኋላ ማሻሻያዎችን የሚያደርግ ሰው ባለመኖሩ ምክንያት ይህ የአጻጻፍ ስልት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ቀስ በቀስ እየተረሳ መጣ። የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን ወደ አካባቢው ከመጡ በኋላ የባሙም ሕዝብ ለመግባቢያነት የሚጠቀምበትን ቋንቋ በማጥናት የሰዋሰው ሕግ አውጥተውለት በትምህርት ቤቶቻቸው ውስጥ እንዲሰጥ አደረጉ። እነዚህ ሚስዮናውያን ከጆያ በተለየ መልኩ የተጠቀሙት የላቲን ፊደላትንና አነባበባቸውን ነበር።

በቅርቡ የባሙምን ፊደላት እንደገና በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው። የአሁኑ ሱልጣን ኢብራሂም ምቦምቦ ጆያ አያታቸው በገነቡት ቤተ መንግሥት ውስጥ ትምህርት ቤት ከፍተዋል። ይህ የአጻጻፍ ስልት ሙሉ በሙሉ እንዳይረሳ በአካባቢው የሚገኙ ልጆች እንዲማሩት እየተደረገ ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በባሙም ሥርወ መንግሥት ሥር ከ14ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የነገሡትን ነገሥታት ስም ዝርዝር የያዘ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ። በስተግራ የተጻፈው በላቲን ፊደል ሲሆን በስተቀኝ ያለው የተጻፈው ደግሞ በባሙም ፊደል ነው

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሁሉም ፎቶዎች:- Courtesy and permission of Sultan Ibrahim Mbombo Njoya, Foumban, Cameroon

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ