መስከረም
ሰኞ፣ መስከረም 1
እንደ ንጋት ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ከላይ ይወጣልናል።—ሉቃስ 1:78
አምላክ ለኢየሱስ የሰው ልጆችን ችግሮች በሙሉ ለመፍታት የሚያስችል ኃይል ሰጥቶታል። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት በራሳችን ፈጽሞ ልናሸንፋቸው የማንችላቸውን ችግሮች የመቅረፍ ኃይል እንዳለው ያሳያሉ። ለምሳሌ የሰው ልጆች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ዋነኛ መንስኤ የሆነውን በዘር የወረስነውን ኃጢአት እንዲሁም የኃጢአት ውጤት የሆኑትን በሽታንና ሞትን ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው። (ማቴ. 9:1-6፤ ሮም 5:12, 18, 19) “ማንኛውንም ዓይነት” በሽታ የመፈወስ፣ አልፎ ተርፎም ሙታንን የማስነሳት ኃይል እንዳለው የፈጸማቸው ተአምራት ያሳያሉ። (ማቴ. 4:23፤ ዮሐ. 11:43, 44) በተጨማሪም ኃይለኛ ማዕበልን ጸጥ የማሰኘት እንዲሁም ክፉ መናፍስትን የማስወጣት ችሎታ አለው። (ማር. 4:37-39፤ ሉቃስ 8:2) ይሖዋ ለልጁ እንዲህ ያለ ኃይል እንደሰጠው ማወቅ በእርግጥም የሚያጽናና ነው። የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች የሚናገሩት ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የፈጸማቸው ተአምራት በሰማይ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በስፋት ስለሚያከናውነው ሥራ ያስተምሩናል። w23.04 3 አን. 5-7
ማክሰኞ፣ መስከረም 2
መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።—1 ቆሮ. 2:10
ጉባኤያችሁ ብዙ አስፋፊዎች ካሉትና ብዙ ጊዜ የመመለስ ዕድል የማታገኙ ከሆነ ተስፋ ልትቆርጡ ትችላላችሁ። ሆኖም መልስ ለመመለስ መሞከራችሁን አታቁሙ። ለእያንዳንዱ ስብሰባ በርከት ያሉ መልሶችን ተዘጋጁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በስብሰባው መጀመሪያ አካባቢ ሐሳብ የመስጠት ዕድል ባታገኙም እንኳ ስብሰባው ሲቀጥል አጋጣሚ ልታገኙ ትችላላችሁ። ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጁ እያንዳንዱ አንቀጽ ከዋናው ጭብጥ ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። እንዲህ ካደረጋችሁ በተለያዩ አንቀጾች ላይ የምትሰጡት ሐሳብ መኖሩ አይቀርም። በተጨማሪም ለማስረዳት የሚከብዱ ጥልቅ እውነቶችን በያዙ አንቀጾች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ልትዘጋጁ ትችላላችሁ። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ባሉ አንቀጾች ላይ እጃቸውን የሚያወጡት ሰዎች ቁጥር ያን ያህል ብዙ ላይሆን ይችላል። ይሁንና ሐሳብ የመስጠት ዕድል ሳታገኙ የተወሰኑ ስብሰባዎች ቢያልፉስ? ከስብሰባው በፊት ወደ መሪው ሄዳችሁ በመረጣችሁት አንቀጽ ላይ ሐሳብ የመስጠት ዕድል እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። w23.04 21-22 አን. 9-10
ረቡዕ፣ መስከረም 3
ዮሴፍ . . . የይሖዋ መልአክ ባዘዘው . . . መሠረት ሚስቱን ወደ ቤቱ ወሰዳት።—ማቴ. 1:24
ዮሴፍ የይሖዋን መመሪያ ለመከተል ፈቃደኛ ነበር፤ ይህም ጥሩ ባል እንዲሆን ረድቶታል። አምላክ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ለዮሴፍ ቤተሰቡን የሚነካ መመሪያ ሰጥቶታል። ትልቅ ለውጥ ማድረግ ቢጠይቅበትም እንኳ በሦስቱም ጊዜያት የይሖዋን መመሪያ ወዲያውኑ ታዟል። (ማቴ. 1:20፤ 2:13-15, 19-21) ዮሴፍ የአምላክን መመሪያ በመከተል ማርያምን ከጉዳት ጠብቋታል፣ ደግፏታል እንዲሁም የሚያስፈልጋትን ነገር አሟልቶላታል። ዮሴፍ ያደረገው ነገር ማርያም ለእሱ ያላትን ፍቅርና አክብሮት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን! ባሎች፣ ቤተሰቦቻችሁን ከምትንከባከቡበት መንገድ ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመፈለግ የዮሴፍን ምሳሌ መከተል ትችላላችሁ። ለውጥ ማድረግ ቢጠይቅባችሁም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር የምትከተሉ ከሆነ ለሚስቶቻችሁ ያላችሁን ፍቅር ታሳያላችሁ፤ ትዳራችሁንም ታጠናክራላችሁ። በትዳር ዓለም ከ20 ዓመት በላይ ያሳለፈች በቫኑዋቱ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግና መመሪያውን በሥራ ላይ ሲያውል ለእሱ ያለኝ አክብሮት ይጨምራል። እተማመንበታለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ ውሳኔ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ።” w23.05 21 አን. 5
ሐሙስ፣ መስከረም 4
በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፤ ደግሞም “የቅድስና ጎዳና” ተብሎ ይጠራል።—ኢሳ. 35:8
ከባቢሎን ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ለአምላካቸው “ቅዱስ ሕዝብ” መሆን ነበረባቸው። (ዘዳ. 7:6) ይህ ሲባል ግን፣ ይሖዋን ለማስደሰት ምንም ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ አይጠበቅባቸውም ማለት አይደለም። በባቢሎን የተወለዱት አብዛኞቹ አይሁዳውያን ከባቢሎናውያን አስተሳሰብና መሥፈርቶች ጋር ተላምደው ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ወደ እስራኤል ከተመለሱ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ገዢው ነህምያ፣ እስራኤል ውስጥ የተወለዱ አንዳንድ ልጆች የአይሁዳውያንን ቋንቋ እንኳ እንደማይችሉ ሲገነዘብ በጣም ደንግጦ ነበር። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ነህ. 13:23, 24) የአምላክ ቃል በዋነኝነት የተጻፈው በዕብራይስጥ ከመሆኑ አንጻር እነዚህ ልጆች ዕብራይስጥ ሳይችሉ ለይሖዋ ፍቅር ማዳበርና እሱን ማምለክ የሚችሉት እንዴት ነው? (ዕዝራ 10:3, 44) ስለዚህ እነዚህ አይሁዳውያን ትልቅ ለውጥ ማድረግ ነበረባቸው። ይሁንና ከባቢሎን ይልቅ ንጹሑ አምልኮ ቀስ በቀስ መልሶ እየተቋቋመ ባለበት በእስራኤል እንዲህ ያለውን ለውጥ ማድረግ ቀላል ነው።—ነህ. 8:8, 9፤ w23.05 15 አን. 6-7
ዓርብ፣ መስከረም 5
ይሖዋ ሊወድቁ የተቃረቡትን ሁሉ ይደግፋል፤ ያጎነበሱትንም ሁሉ ቀና ያደርጋል።—መዝ. 145:14
የሚያሳዝነው፣ ምንም ያህል ተነሳሽነትም ሆነ ራስን የመግዛት ችሎታ ቢኖረን እንቅፋት ሊያጋጥመን ይችላል። ለምሳሌ “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ግባችን ላይ ለመሥራት የመደብነውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። (መክ. 9:11) ተስፋ የሚያስቆርጥና ጉልበታችንን የሚያዳክም ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ከግባችን ጋር የሚቃረን ድርጊት እንድንፈጽም ሊያደርገን ይችላል። (ሮም 7:23) ወይም ደግሞ ሊደክመን ይችላል። (ማቴ. 26:43) ታዲያ የሚያጋጥመንን እንቅፋት ወይም ያልተጠበቀ ሁኔታ ለመወጣት ምን ይረዳናል? እንቅፋት አጋጥሞሃል ማለት ግብህ ላይ መድረስ አትችልም ማለት እንዳልሆነ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ይናገራል። ያም ቢሆን መልሰን መነሳት እንደምንችል በግልጽ ይናገራል። በእርግጥም፣ እንቅፋት ቢያጋጥምህም እንኳ ግብህ ላይ መሥራትህን መቀጠልህ ይሖዋን ማስደሰት እንደምትፈልግ ያሳያል። ይሖዋ ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግህን እንደቀጠልክ ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን! w23.05 30 አን. 14-15
ቅዳሜ፣ መስከረም 6
ለመንጋው ምሳሌ [ሁኑ]።—1 ጴጥ. 5:3
ወጣት ወንድሞች በአቅኚነት ማገልገላቸው ከተለያዩ ዓይነት ሰዎች ጋር ተባብሮ መሥራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ምክንያታዊ የሆነ በጀት ማውጣትና በበጀታቸው መመራት የሚችሉበትን መንገድ ያስተምራቸዋል። (ፊልጵ. 4:11-13) በረዳት አቅኚነት ማገልገላችሁ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ይረዳችኋል። ረዳት አቅኚ መሆናችሁ የዘወትር አቅኚነት ለመጀመር ዝግጁ እንድትሆኑ ይረዳችኋል። አቅኚነት ወደ ሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ለመግባት መንገድ ሊከፍትላችሁ ይችላል፤ ይህም የግንባታ አገልጋይ ወይም ቤቴላዊ መሆንን ይጨምራል። ክርስቲያን ወንዶች የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነው ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የማገልገል ግብ ሊኖራቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚጣጣሩ ወንድሞች ‘መልካም ሥራን እንደሚመኙ’ ይናገራል። (1 ጢሞ. 3:1) በመጀመሪያ አንድ ወንድም ብቃቱን አሟልቶ የጉባኤ አገልጋይ መሆን አለበት። የጉባኤ አገልጋዮች በተለያዩ መንገዶች የጉባኤ ሽማግሌዎችን ይረዳሉ። ሽማግሌዎችም ሆኑ የጉባኤ አገልጋዮች ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በትሕትና ያገለግላሉ፤ እንዲሁም በአገልግሎት በቅንዓት ይካፈላሉ። w23.12 28 አን. 14-16
እሁድ፣ መስከረም 7
ገና ልጅ ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ።—2 ዜና 34:3
ንጉሥ ኢዮስያስ ይሖዋን መፈለግ የጀመረው ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለ ነው። ስለ ይሖዋ መማርና የእሱን ፈቃድ ማድረግ ይፈልግ ነበር። ያም ቢሆን፣ ለዚህ ወጣት ንጉሥ ሕይወት ቀላል አልነበረም። የሐሰት አምልኮ በተስፋፋበት ዘመን ከንጹሑ አምልኮ ጎን መቆም ነበረበት። ያደረገውም ይህንኑ ነው! ኢዮስያስ ገና 20 ዓመት ሳይሞላው በፊት የሐሰት አምልኮን ከይሁዳ ማስወገድ ጀመረ። (2 ዜና 34:1, 2) ገና ልጅ ብትሆንም እንኳ ይሖዋን በመፈለግና ስለ ባሕርያቱ በመማር የኢዮስያስን ምሳሌ መከተል ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ራስህን ለእሱ ለመወሰን ያነሳሳሃል። ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? በ14 ዓመቱ የተጠመቀው ሉክ እንዲህ ብሏል፦ “ከአሁን ጀምሮ በሕይወቴ ውስጥ የይሖዋን አገልግሎት አስቀድማለሁ፤ እሱን ለማስደሰትም ጥረት አደርጋለሁ።” (ማር. 12:30) አንተም እንዲህ ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ ትልቅ በረከት ታገኛለህ! w23.09 11 አን. 12-13
ሰኞ፣ መስከረም 8
በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩና በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን [አክብሯቸው]።—1 ተሰ. 5:12
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት የተሰሎንቄ ጉባኤ ከተቋቋመ አንድ ዓመትም አልሞላውም ነበር። በመሆኑም በዚያ ጉባኤ የነበሩት የተሾሙ ወንዶች ተሞክሮ ስለሚጎድላቸው አንዳንድ ስህተቶችን ሠርተው ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። ታላቁ መከራ እየተቃረበ ሲመጣ ከዋናው መሥሪያ ቤትም ሆነ ከቅርንጫፍ ቢሮው መመሪያ ማግኘት አንችል ይሆናል፤ ስለዚህ በዚያ ወቅት ከአሁኑ ይበልጥ መመሪያ የምናገኝበት ዋነኛ መስመር ሽማግሌዎቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ከአሁኑ ለሽማግሌዎቻችን ፍቅርና አክብሮት ማዳበራችን አስፈላጊ ነው። ምንም ነገር ቢመጣ የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ፤ በእነዚህ ታማኝ ወንድሞች አለፍጽምና ላይ ሳይሆን ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት እየመራቸው በመሆኑ ላይ ትኩረት እናድርግ። የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት እንደሚጠብቅለት ሁሉ የመዳን ተስፋችንም አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል። ይህ ዓለም የሚያቀርብልን ማንኛውም ነገር ከንቱ እንደሆነ እንገነዘባለን። (ፊልጵ. 3:8) ተስፋችን እንድንረጋጋና ሚዛናችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። w23.06 11-12 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ መስከረም 9
ማስተዋል የጎደላት ሴት ጯኺ ናት። እሷ ጨርሶ ማመዛዘን አትችልም።—ምሳሌ 9:13
“ማስተዋል የጎደላት ሴት” የምታቀርበውን ግብዣ የሚሰሙ ሰዎች ግብዣዋን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰን ይኖርባቸዋል። ከፆታ ብልግና ለመራቅ የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። የምሳሌ መጽሐፍ፣ “ማስተዋል የጎደላት ሴት” “የተሰረቀ ውኃ ይጣፍጣል” እንደምትል ይናገራል። (ምሳሌ 9:17) “የተሰረቀ ውኃ” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል? መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር አጋሮች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት አርኪ ከሆነ ውኃ ጋር ያመሳስለዋል። (ምሳሌ 5:15-18) ሕጋዊ ጋብቻ የፈጸሙ ባለትዳሮች በፆታ ግንኙነት መደሰት ይችላሉ። ‘ከተሰረቀ ውኃ’ ጋር በተያያዘ ግን ሁኔታው በእጅጉ የተለየ ነው። ይህ አገላለጽ ያልተፈቀደ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነትን ሊያመለክት ይችላል። ሌቦች ብዙውን ጊዜ የሚሰርቁት ተደብቀው እንደሆነ ሁሉ ብዙዎች እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን የሚፈጽሙት በድብቅ ነው። በተለይ ኃጢአት የሚፈጽሙት ሰዎች ድርጊታቸው ካልታወቀባቸው ደግሞ ‘የተሰረቀው ውኃ’ ይበልጥ ጣፋጭ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። በዚህ መልኩ መታለላቸው እንዴት ያሳዝናል! ይሖዋ ሁሉንም ነገር ይመለከታል። የእሱን ሞገስ ማጣት ከምንም በላይ መራራ ነው፤ ስለዚህ የእሱን ሞገስ የሚያሳጣ ነገር ፈጽሞ ‘ጣፋጭ’ ሊሆን አይችልም።—1 ቆሮ. 6:9, 10፤ w23.06 22 አን. 7-9
ረቡዕ፣ መስከረም 10
ሳልወድ ባደርገውም እንኳ የመጋቢነት አደራ ተጥሎብኛል።—1 ቆሮ. 9:17
ጸሎትህ ተደጋጋሚ፣ አገልግሎትህ ደግሞ አሰልቺ እየሆነ እንደመጣ ቢሰማህስ? ‘የይሖዋን መንፈስ አጥቻለሁ’ የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አትቸኩል። ፍጹም ስላልሆንክ ስሜትህ ሊለዋወጥ ይችላል። ቅንዓትህ መቀዝቀዝ ከጀመረ በሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ላይ አሰላስል። ጳውሎስ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ቢያደርግም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ተነሳሽነቱ ሊቀንስ እንደሚችል ተገንዝቧል። ጳውሎስ ስሜቱ ቢለዋወጥም እንኳ አገልግሎቱን ለማከናወን ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። አንተም ፍጹም ባልሆነው ስሜትህ ላይ ተመሥርተህ ውሳኔ ከማድረግ ተቆጠብ። ተነሳሽነት ባይኖርህም እንኳ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ትክክለኛውን ነገር ማድረግህን ከቀጠልክ ውሎ አድሮ ተነሳሽነትህ ሊጨምር ይችላል።—1 ቆሮ. 9:16፤ w24.03 11-12 አን. 12-13
ሐሙስ፣ መስከረም 11
ለእነሱ ያላችሁን ፍቅር እውነተኝነት በተጨባጭ አስመሥክሩ።—2 ቆሮ. 8:24
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጓደኞቻችን እንዲሆኑ በመፍቀድ ፍቅር ማሳየት እንችላለን። (2 ቆሮ. 6:11-13) በብዙዎቹ ጉባኤዎች ውስጥ የተለያየ አስተዳደግና ባሕርይ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች ይገኛሉ። ባሏቸው መልካም ባሕርያት ላይ በማተኮር ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። ሌሎችን በይሖዋ ዓይን በማየት እንደምንወዳቸው እናስመሠክራለን። በታላቁ መከራ ወቅት ፍቅር በጣም አስፈላጊ ነገር ይሆናል። መከራው ሲጀምር ጥበቃ ማግኘት የምንችለው የት ነው? ይሖዋ በጥንቷ ባቢሎን ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ለሕዝቡ ምን መመሪያ እንደሰጠ እንመልከት፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ ሂድ ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” (ኢሳ. 26:20) እነዚህ ቃላት ታላቁን መከራ ለምንጋፈጥ ክርስቲያኖችም የሚሠሩ ይመስላል። w23.07 6-7 አን. 14-16
ዓርብ፣ መስከረም 12
የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው።—1 ቆሮ. 7:31
ምክንያታዊ ነው የሚል ስም አትርፉ። ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦ ‘ሰዎች ምክንያታዊ፣ እሺ ባይና ሰው የሚለኝን የምሰማ እንደሆንኩ ይሰማቸዋል? ወይስ ድርቅ ያልኩ፣ ግትርና አልሰማም ባይ አድርገው ይመለከቱኛል? ሌሎችን ለማዳመጥ፣ የሚቻል ከሆነም ሐሳባቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ?’ ይበልጥ ምክንያታዊ በሆንን መጠን ይሖዋንና ኢየሱስን ይበልጥ እንመስላለን። ምክንያታዊ መሆን፣ ለውጦች ሲያጋጥሙን ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው ለማስተናገድ ያስችለናል። አንዳንድ ጊዜ ለውጦች ባልጠበቅነው አቅጣጫ ሕይወታችንን ሊያከብዱብን ይችላሉ። በድንገት ከባድ የጤና ችግር ሊያጋጥመን ይችላል፤ ወይም በምንኖርበት አካባቢ በኢኮኖሚው አሊያም በፖለቲካው ሥርዓት ላይ ድንገተኛ ለውጥ ተከስቶ ኑሯችን ሊመሰቃቀልብን ይችላል። (መክ. 9:11) የአገልግሎት ምድብ ለውጥ እንኳ ፈተና የሚሆንበት ጊዜ አለ። የሚከተሉትን አራት እርምጃዎች ከወሰድን አዲሱን ሁኔታ መልመድ ቀላል ይሆንልናል፦ (1) እውነታውን መቀበል፣ (2) ነገን አሻግሮ ማየት፣ (3) በጎ በጎውን ማሰብ እንዲሁም (4) ሌሎችን መርዳት። w23.07 21-22 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ መስከረም 13
አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ።—ዳን. 9:23
ነቢዩ ዳንኤል በባቢሎናውያን ተማርኮ ወደ ሩቅ አገር በተወሰደበት ወቅት ገና ወጣት ነበር። ዳንኤል ልጅ ቢሆንም የባቢሎን ባለሥልጣናት በጣም ተደመሙበት። እነሱ ያዩት ‘ውጫዊ ገጽታውን’ ማለትም ‘እንከን የሌለበት፣ መልከ መልካም’ እና ከታዋቂ ቤተሰብ የመጣ መሆኑን ነው። (1 ሳሙ. 16:7) በመሆኑም ባቢሎናውያን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲያገለግል አሠለጠኑት። (ዳን. 1:3, 4, 6) ይሖዋ ዳንኤልን የወደደው ምን ዓይነት ሰው ለመሆን እንደመረጠ ስላየ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ዳንኤልን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እሱን በታማኝነት ካገለገሉት ከኖኅና ከኢዮብ ጋር አብሮ የጠቀሰው ዳንኤል ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በሃያዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ሳለ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 5:32፤ 6:9, 10፤ ኢዮብ 42:16, 17፤ ሕዝ. 14:14) ደግሞም ዳንኤል ባሳለፈው ረጅምና አስደናቂ ሕይወት በሙሉ ይሖዋ ይወደው ነበር።—ዳን. 10:11, 19፤ w23.08 2 አን. 1-2
እሁድ፣ መስከረም 14
ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ [በሚገባ ተረዱ]።—ኤፌ. 3:18
አንድን ቤት ለመግዛት ስታስብ የምትገዛውን ቤት ከሁሉም አቅጣጫ በአካል በደንብ ማየት እንደምትፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብና ስናጠናም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። በጥድፊያ ካነበብከው፣ የምትማረው “የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች” ብቻ ነው። (ዕብ. 5:12) ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ ቤቱ ሁሉ ወደ ውስጥ ገብተህ ዝርዝር መረጃዎችን ለመመርመር ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የምትችልበት አንዱ ግሩም መንገድ በውስጡ ያሉት መልእክቶች እንዴት እንደሚያያዙ ማስተዋል ነው። የምታምንባቸውን እውነቶች ምንነት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ እውነቶች የምታምነው ለምን እንደሆነም ለመመርመር ጥረት አድርግ። የአምላክን ቃል በሚገባ ለመረዳት ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መማር ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ የእውነት ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ መረዳት እንዲችሉ’ የአምላክን ቃል በትጋት እንዲያጠኑ አበረታቷቸዋል። እንዲህ ካደረጉ በእምነታቸው ይበልጥ ‘ሥር መስደድና መታነጽ’ ይችላሉ። (ኤፌ. 3:14-19) እኛም ይህንኑ ልናደርግ ይገባል። w23.10 18 አን. 1-3
ሰኞ፣ መስከረም 15
ወንድሞች፣ በይሖዋ ስም የተናገሩትን ነቢያት መከራ በመቀበልና ትዕግሥት በማሳየት ረገድ አርዓያ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው።—ያዕ. 5:10
መጽሐፍ ቅዱስ ትዕግሥት ያሳዩ በርካታ ሰዎችን ምሳሌ ይዟል። በግል ጥናትህ ላይ የእነዚህን ሰዎች ምሳሌ ለመመርመር ለምን አትሞክርም? ለአብነት ያህል፣ ዳዊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ገና በልጅነቱ ቢሆንም ንግሥናውን እስኪቀበል ድረስ ለበርካታ ዓመታት መጠበቅ አስፈልጎታል። ስምዖን እና ሐና፣ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ እስኪመጣ በሚጠባበቁበት ወቅት ይሖዋን በታማኝነት ያገለግሉ ነበር። (ሉቃስ 2:25, 36-38) እንዲህ ያሉትን ዘገባዎች በምታጠናበት ወቅት የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለመፈለግ ጥረት አድርግ፦ ይህ ሰው ትዕግሥት እንዲያሳይ የረዳው ምን ሊሆን ይችላል? ትዕግሥተኛ መሆኑ የጠቀመው እንዴት ነው? የእሱን ምሳሌ መከተል የምችለው እንዴት ነው? ትዕግሥት ስላላሳዩ ሰዎች ማጥናትህም ሊጠቅምህ ይችላል። (1 ሳሙ. 13:8-14) የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልታነሳ ትችላለህ፦ ‘ትዕግሥት እንዳያሳይ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል? ትዕግሥት አለማሳየቱ ምን መዘዝ አስከትሎበታል?’ w23.08 25 አን. 15
ማክሰኞ፣ መስከረም 16
አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ እንደሆንክ አምነናል፤ ደግሞም አውቀናል።—ዮሐ. 6:69
ሐዋርያው ጴጥሮስ ታማኝ ነበር፤ ምንም ነገር ኢየሱስን መከተሉን እንዲያስቆመው አልፈቀደም። በአንድ ወቅት ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ደቀ መዛሙርቱ መረዳት ባቃታቸው ጊዜ ጴጥሮስ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐ. 6:68) ብዙዎች፣ ኢየሱስ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ሳይጠብቁ እሱን መከተላቸውን አቆሙ። ጴጥሮስ ግን እንደዚያ አላደረገም። “የዘላለም ሕይወት ቃል” ያለው ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ጴጥሮስና ሌሎቹ ሐዋርያት ትተውት እንደሚሄዱ አውቆ ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚመለስና ታማኝ ሆኖ እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነበር። (ሉቃስ 22:31, 32) ኢየሱስ “መንፈስ ዝግጁ . . . ሥጋ ግን ደካማ” እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ማር. 14:38) በመሆኑም ጴጥሮስ ከካደው በኋላም እንኳ ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠበትም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገለጠለት፤ በዚህ ወቅት ጴጥሮስ ብቻውን ሳይሆን አይቀርም። (ማር. 16:7፤ ሉቃስ 24:34፤ 1 ቆሮ. 15:5) ቅስሙ የተሰበረው ይህ ሐዋርያ በዚህ ምንኛ ተጽናንቶ ይሆን! w23.09 22 አን. 9-10
ረቡዕ፣ መስከረም 17
የዓመፅ ሥራቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸውም የተሸፈነላቸው ደስተኞች ናቸው።—ሮም 4:7
አምላክ በእሱ የሚያምኑ ሰዎችን ኃጢአታቸውን ይሰርዝላቸዋል ወይም ይሸፍንላቸዋል። ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላቸዋል፤ እንዲሁም ኃጢአታቸውን አይቆጥርባቸውም። (መዝ. 32:1, 2) እንዲህ ያሉትን ሰዎች፣ እምነታቸውን መሠረት በማድረግ ነቀፋ የሌለባቸው ወይም ጻድቃን አድርጎ ይቆጥራቸዋል። አብርሃም፣ ዳዊትና ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጻድቃን ተደርገው ቢቆጠሩም ፍጽምና የጎደላቸው ኃጢአተኞች ነበሩ። ሆኖም በእምነታቸው ምክንያት አምላክ ነቀፋ የሌለባቸው አድርጎ ቆጥሯቸዋል። በተለይ በእሱ ላይ እምነት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደሩ ጻድቃን ተደርገው መቆጠራቸው ተገቢ ነው። (ኤፌ. 2:12) ሐዋርያው ጳውሎስ በደብዳቤው ላይ በግልጽ እንደተናገረው ከአምላክ ጋር የቅርብ ወዳጅነት ለመመሥረት እምነት የግድ አስፈላጊ ነው። አብርሃምና ዳዊት የአምላክ ወዳጅ መሆን የቻሉት እምነት ስለነበራቸው ነው። እኛም ብንሆን የአምላክ ወዳጅ ለመሆን እምነት ያስፈልገናል። w23.12 3 አን. 6-7
ሐሙስ፣ መስከረም 18
የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ፤ ይህም ስሙን በይፋ የምናውጅበት የከንፈራችን ፍሬ ነው።—ዕብ. 13:15
በዛሬው ጊዜ ሁሉም ክርስቲያኖች ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ተጠቅመው ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማራመድ ለይሖዋ መሥዋዕት የማቅረብ መብት አላቸው። ካሉን ነገሮች መካከል ምርጡን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገን በማቅረብ እሱን የማምለክ መብታችንን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳያለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ፈጽሞ ችላ ልንላቸው የማይገቡ የተለያዩ የአምልኳችንን ገጽታዎች ጠቅሷል። (ዕብ. 10:22-25) ከእነዚህ መካከል ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ፣ ተስፋችንን በይፋ ማወጅ፣ በጉባኤ ደረጃ አንድ ላይ መሰብሰብ እንዲሁም “[የይሖዋ ቀን] እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ” እርስ በርስ መበረታታት ይገኙበታል። በራእይ መጽሐፍ መደምደሚያ አካባቢ የይሖዋ መልአክ ሁለት ጊዜ “ለአምላክ ስገድ!” ብሏል፤ ይህም ይሖዋን የማምለክን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ራእይ 19:10፤ 22:9) ታላቁን የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አስመልክቶ ያገኘነውን ጥልቅ መንፈሳዊ እውነት እንዲሁም ያለንን ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን የማምለክ ውድ መብት ፈጽሞ ልንረሳው አይገባም! w23.10 29 አን. 17-18
ዓርብ፣ መስከረም 19
እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል።—1 ዮሐ. 4:7
ሁላችንም ‘እርስ በርስ መዋደዳችንን መቀጠል’ እንፈልጋለን። ሆኖም ኢየሱስ “የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴ. 24:12) ኢየሱስ ይህን ሲል የአብዛኞቹ ደቀ መዛሙርቱ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ መናገሩ አልነበረም። ያም ቢሆን፣ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ፍቅር መጥፋቱ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ልንጠነቀቅ ይገባል። ይህን ሐሳብ በአእምሯችን በመያዝ የሚከተለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር፦ ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ጠንካራ መሆኑን መፈተን የምንችልበት መንገድ አለ? ፍቅራችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ መፈተን የምንችልበት አንዱ መንገድ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን አንዳንድ ሁኔታዎች እንዴት እንደምንይዝ መገምገም ነው። (2 ቆሮ. 8:8) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከእነዚህ ሁኔታዎች መካከል አንዱን ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦ “ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥ. 4:8) በመሆኑም የሌሎች ድክመትና አለፍጽምና ፍቅራችንን ሊፈትነው ይችላል። w23.11 10-11 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ መስከረም 20
እርስ በርሳችሁ [ተዋደዱ]።—ዮሐ. 13:34
በጉባኤው ውስጥ ላሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ፍቅር እያሳየን ለሌሎቹ ግን የማናሳይ ከሆነ ኢየሱስ ስለ ፍቅር የሰጠውን ትእዛዝ ተከትለናል ሊባል አይችልም። እርግጥ ነው፣ እኛም እንደ ኢየሱስ ከአንዳንዶቹ ወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንቀራረብ ይሆናል። (ዮሐ. 13:23፤ 20:2) ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን “የወንድማማች መዋደድ” ማለትም በቤተሰብ ውስጥ ያለው ዓይነት ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ አሳስቦናል። (1 ጴጥ. 2:17) ጴጥሮስ “እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቶናል። (1 ጴጥ. 1:22) ‘አጥብቆ መዋደድ’ የሚለው አገላለጽ ፍቅር ማሳየት በሚከብደን ጊዜም ጭምር መዋደድን ያካትታል። ለምሳሌ አንድ ወንድም ቅር ቢያሰኘን ወይም በሆነ መንገድ ቢጎዳንስ? የሚቀናን ፍቅር ማሳየት ሳይሆን አጸፋውን መመለስ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጴጥሮስ አጸፋ መመለስ አምላክን እንደማያስደስተው ከኢየሱስ ተምሯል። (ዮሐ. 18:10, 11) ጴጥሮስ “ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ አትመልሱ። ከዚህ ይልቅ ባርኩ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 3:9) ሌሎችን አጥብቀን የምንወድ ከሆነ ደግነትና አሳቢነት ለማሳየት እንነሳሳለን። w23.09 28-29 አን. 9-11
እሁድ፣ መስከረም 21
ሴቶችም እንደዚሁ . . . በልማዶቻቸው ልከኞችና በሁሉም ነገር ታማኞች ሊሆኑ ይገባል።—1 ጢሞ. 3:11
አንድ ልጅ አድጎ ትልቅ ሰው የሚሆንበት ፍጥነት በጣም ያስገርመናል። ይህ እድገት በራሱ የሚከናወን ይመስል ይሆናል። ይሁንና እድገት አድርጎ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ መድረስ በራሱ የሚመጣ ነገር አይደለም። (1 ቆሮ. 13:11፤ ዕብ. 6:1) እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሊኖረን ይገባል። በተጨማሪም አምላካዊ ባሕርያትን ለማዳበር፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን ለመማር እንዲሁም ወደፊት ለምንቀበላቸው ኃላፊነቶች ለመዘጋጀት የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 1:5) ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው ወንድ እና ሴት አድርጎ ነው። (ዘፍ. 1:27) ወንዶችና ሴቶች አካላዊ ልዩነት እንዳላቸው ግልጽ ነው፤ ይሁንና በሌሎች መንገዶችም ይለያያሉ። ለምሳሌ ይሖዋ ወንዶችንና ሴቶችን የፈጠራቸው የየራሳቸው ሚና ሰጥቶ ነው። በመሆኑም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችሉ ባሕርያትና ክህሎቶች ያስፈልጓቸዋል።—ዘፍ. 2:18፤ w23.12 18 አን. 1-2
ሰኞ፣ መስከረም 22
ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20
ኢየሱስ ሌሎች ሰዎች የአባቱን የግል ስም እንዲጠቀሙ ይፈልግ ነበር? ምንም ጥያቄ የለውም። በዘመኑ የነበሩ አንዳንድ አክራሪ የሃይማኖት መሪዎች ‘የአምላክ ስም በጣም ቅዱስ ከመሆኑ የተነሳ ሊጠራ አይገባም’ የሚል አመለካከት ሳይኖራቸው አይቀርም። ኢየሱስ ግን እንዲህ ያሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች የአባቱን ስም ከማክበር እንዲያግዱት አልፈቀደም። ለምሳሌ ኢየሱስ በጌርጌሴኖን ክልል አጋንንት የያዘውን ሰው በፈወሰ ጊዜ የሆነውን ነገር እንመልከት። ሰዎቹ በጣም ስለፈሩ ኢየሱስ አካባቢያቸውን ለቆ እንዲሄድ ተማጸኑት፤ በመሆኑም ኢየሱስ እዚያ አልቆየም። (ማር. 5:16, 17) ያም ቢሆን ኢየሱስ በዚያ አካባቢ የይሖዋ ስም እንዲታወቅ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም የፈወሰውን ሰው፣ እሱ ያደረገለትን ሳይሆን ይሖዋ ያደረገለትን ነገር ለሌሎች እንዲናገር አዘዘው። (ማር. 5:19) በዛሬው ጊዜም ይህንኑ እንድናደርግ ማለትም የአባቱን ስም ለመላው ዓለም እንድናሳውቅ ይፈልጋል። (ማቴ. 24:14፤ 28:20) ይህን ስናደርግ ንጉሣችንን ኢየሱስን እናስደስተዋለን። w24.02 10 አን. 10
ማክሰኞ፣ መስከረም 23
ስለ [ስሜ] ስትል ብዙ ችግሮችን ተቋቁመሃል።—ራእይ 2:3
በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ድርጅት ክፍል መሆናችን በእርግጥም ትልቅ በረከት ነው። በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ቢሄድም እንኳ ይሖዋ ግሩም ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ አንድነት ያለው መንፈሳዊ ቤተሰብ ሰጥቶናል። (መዝ. 133:1) አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖረን ይረዳናል። (ኤፌ. 5:33–6:1) በተጨማሪም ውስጣዊ ሰላም ለማጣጣም የሚያስችል ጥበብና ማስተዋል ይሰጠናል። ይሁንና ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን ለመቀጠል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በሌሎች አለፍጽምና ምክንያት ቅር ልንሰኝ እንችላለን። ከዚህም ሌላ፣ ያለብን ድክመት ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል፤ በተለይም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ስህተት የምንሠራ ከሆነ መጽናት ሊከብደን ይችላል። (1) የእምነት አጋራችን ስሜታችንን ሲጎዳን፣ (2) የትዳር ጓደኛችን ቅር ሲያሰኘን እንዲሁም (3) በሠራነው ስህተት የተነሳ ቅስማችን ሲሰበር በይሖዋ አገልግሎት መጽናት ይኖርብናል። w24.03 14 አን. 1-2
ረቡዕ፣ መስከረም 24
ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።—ፊልጵ. 3:16
አልፎ አልፎ፣ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን ቅዱስ አገልግሎት ለማስፋት ጥረት ስላደረጉ ወንድሞችና እህቶች የሚገልጽ ተሞክሮ ትሰማ ይሆናል። ምናልባት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተካፍለው ወይም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ሊሆን ይችላል። እንዲህ ያለ ግብ ማውጣት የምትችል ከሆነ እባክህ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ሕዝቦች አገልግሎታቸውን ለማስፋት ይጓጓሉ። (ሥራ 16:9) ይሁንና በአሁኑ ወቅት እንዲህ ለማድረግ ሁኔታህ የማይፈቅድልህ ቢሆንስ? እንዲህ ማድረግ ከቻሉ ክርስቲያኖች እንደምታንስ ሊሰማህ አይገባም። የክርስቲያኖች ሩጫ ጽናት ይጠይቃል። (ማቴ. 10:22) ዋናው ነገር አቅምህና ሁኔታህ በሚፈቅድልህ መጠን ይሖዋን ማገልገልህ እንደሆነ አትርሳ። ከተጠመቅክ በኋላ ኢየሱስን ያለማቋረጥ መከተል የምትችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ይህ ነው።—መዝ. 26:1፤ w24.03 10 አን. 11
ሐሙስ፣ መስከረም 25
በደላችንን ሁሉ በደግነት ይቅር ብሎናል።—ቆላ. 2:13
ሰማያዊው አባታችን ንስሐ ከገባን ይቅር እንደሚለን ቃል ገብቶልናል። (መዝ. 86:5) ስለዚህ ከልባችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ይቅር እንዳለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ከእኛ በሚጠብቀው ነገር ድርቅ ያለ እንዳልሆነ አስታውስ። ማድረግ ከምንችለው በላይ አይጠብቅብንም። ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በምናደርገው ነገር ይደሰታል። ይሖዋን በሙሉ ነፍሳቸው ባገለገሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንም ጠቃሚ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ለዓመታት በትጋት ሠርቷል፤ በርካታ ጉባኤዎችንም አቋቁሟል። በኋላ ላይ ግን በስብከቱ ሥራ የሚያደርገውን ተሳትፎ የሚገድብ ነገር አጋጠመው። ታዲያ በዚህ ጊዜ የአምላክን ሞገስ አጣ? በፍጹም። አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረጉን ቀጥሏል፤ ይሖዋም ባርኮታል። (ሥራ 28:30, 31) እኛም ለይሖዋ መስጠት የምንችለው ነገር እንደ ሁኔታው ሊለያይ ይችላል። እሱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግን ለመስጠት የተነሳሳንበትን ምክንያት ነው። w24.03 27 አን. 7, 9
ዓርብ፣ መስከረም 26
ኢየሱስ በማለዳ ገና ጎህ ሳይቀድ ተነስቶ ከቤት ወጣና ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ፤ እዚያም መጸለይ ጀመረ።—ማር. 1:35
ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ባቀረባቸው ጸሎቶች አማካኝነት ለደቀ መዛሙርቱ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ብዙ ጊዜ ጸልዮአል። ሥራ ስለሚበዛበት እንዲሁም ብዙዎች ወደ እሱ ይመጡ ስለነበር ለጸሎት የሚሆን ጊዜ መመደብ ነበረበት። (ማር. 6:31, 45, 46) ብቻውን የሚጸልይበት ጊዜ ለማግኘት ሲል በማለዳ ይነሳ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ ከባድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል። (ሉቃስ 6:12, 13) በተጨማሪም ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት በምድራዊ አገልግሎቱ ከተሰጡት ኃላፊነቶች በጣም ከባዱን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ጸልዮአል። (ማቴ. 26:39, 42, 44) ምንም ያህል ሥራ ቢበዛብን ለጸሎት ጊዜ መመደብ እንዳለብን የኢየሱስ ታሪክ ያስተምረናል። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ለጸሎት የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ስንል በማለዳ መነሳት ወይም ትንሽ ማምሸት ሊኖርብን ይችላል። እንዲህ ስናደርግ፣ ይሖዋ ለሰጠን ውድ ስጦታ አመስጋኝ መሆናችንን እናሳያለን። w23.05 3 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ መስከረም 27
የአምላክ ፍቅር፣ በተሰጠን መንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልባችን ውስጥ ፈሷል።—ሮም 5:5
ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ላይ “ፈሷል” የሚለውን ቃል ልብ በል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ፣ ቃሉ “እንደ ጅረት ወርዶብናል” ሊባል እንደሚችል ገልጿል። ይሖዋ ለቅቡዓኑ ያለው ፍቅር ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! ቅቡዓኑ ‘በአምላክ የተወደዱ’ እንደሆኑ ያውቃሉ። (ይሁዳ 1) ሐዋርያው ዮሐንስ “የአምላክ ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ ምን ያህል ታላቅ ፍቅር እንዳሳየን ተመልከቱ!” በማለት ስሜታቸውን ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። (1 ዮሐ. 3:1) ይሁንና ይሖዋ ፍቅር የሚያሳየው ለቅቡዓኑ ብቻ ነው? በፍጹም! ይሖዋ ሁላችንንም እንደሚወደን አሳይቷል። የይሖዋ ፍቅር የታየበት ከሁሉ የላቀው መንገድ የትኛው ነው? ቤዛው ነው። በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ እንዲህ ያለ ፍቅር ታይቶ አያውቅም!—ዮሐ. 3:16፤ ሮም 5:8፤ w24.01 28 አን. 9-10
እሁድ፣ መስከረም 28
እርዳታ ለማግኘት በምጣራበት ቀን ጠላቶቼ ያፈገፍጋሉ። አምላክ ከጎኔ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።—መዝ. 56:9
ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ፣ ዳዊት ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ የረዳውን ነገር ይገልጻል፤ ሕይወቱ አደጋ ውስጥ ቢሆንም ይሖዋ ወደፊት በሚያደርግለት ነገር ላይ አሰላስሏል። ዳዊት፣ ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እንደሚታደገው እርግጠኛ ነበር። ደግሞም ይሖዋ፣ ዳዊት ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (1 ሳሙ. 16:1, 13) ዳዊት፣ ይሖዋ የተናገረው ነገር ሁሉ እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነበር። ይሖዋ ለአንተስ ምን እንደሚያደርግልህ ቃል ገብቷል? እርግጥ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይደርስብን ይከላከልልናል ብለን አንጠብቅም። ያም ቢሆን በዚህ ሥርዓት ውስጥ የሚያጋጥምህ ፈተና ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ያስወግደዋል። (ኢሳ. 25:7-9) ፈጣሪያችን የሞቱትን ለማስነሳት፣ እኛን ለመፈወስ እንዲሁም ተቃዋሚዎቻችንን በሙሉ ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል አለው።—1 ዮሐ. 4:4፤ w24.01 6 አን. 12-13
ሰኞ፣ መስከረም 29
በደሉ ይቅር የተባለለት፣ ኃጢአቱ የተሸፈነለት ሰው ደስተኛ ነው።—መዝ. 32:1
ራስህን ለመወሰንና ለመጠመቅ ያደረግኸውን ውሳኔ መለስ ብለህ አስብ። እነዚህን እርምጃዎች የወሰድከው ከይሖዋ ጎን መቆም ስለፈለግህ ነው። እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ እንድትሆን ያስቻሉህን ነገሮች መለስ ብለህ አስብ። በቅድሚያ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት ቀሰምክ። ይህ ደግሞ ለሰማዩ አባትህ ያለህ ፍቅርና አክብሮት እያደገ እንዲሄድ አደረገ። እምነትህ እየጨመረ ሄደ፤ በመሆኑም ንስሐ ለመግባት ተነሳሳህ። ከመጥፎ ድርጊቶች ለመራቅና በአምላክ ፈቃድ መሠረት ለመኖር ቆረጥክ። (መዝ. 32:2) የአምላክን ይቅርታ ስታገኝ ትልቅ እፎይታ ተሰማህ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም የተማርካቸውን አስደሳች ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ጀመርክ። አሁን ደግሞ ራስህን ወስነህ የተጠመቅህ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን በሕይወት ጎዳና ላይ እየተጓዝክ ነው፤ ከዚህ መንገድ ፈጽሞ ላለመውጣት ቆርጠሃል። (ማቴ. 7:13, 14) ጸንተህ ቁም፤ ለይሖዋ በምታቀርበው አምልኮ ጽኑ፣ ሕግጋቱን በመታዘዝ ረገድ ደግሞ የማትነቃነቅ ሁን። w23.07 17 አን. 14፤ 19 አን. 19
ማክሰኞ፣ መስከረም 30
አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ፈተና ሲደርስባችሁ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።—1 ቆሮ. 10:13
ለይሖዋ ራስህን ስትወስን ባቀረብከው ጸሎት ላይ ማሰላሰልህ ማንኛውንም ፈተና ለማሸነፍ ብርታት ይሰጥሃል። ለምሳሌ ባለትዳር የሆነች ሴት ታሽኮረምማለህ? በፍጹም! እንዲህ ያለውን ነገር እንደማታደርግ ቀድሞውንም ወስነሃል። መጀመሪያውኑም ተገቢ ያልሆነ ስሜት በልብህ ውስጥ እንዲያቆጠቁጥ ስለማትፈቅድ እንዲህ ያለው ስሜት ሥር ከሰደደ በኋላ ለማስወገድ መታገል አያስፈልግህም። ‘ከክፉዎች መንገድ ፈቀቅ ትላለህ።’ (ምሳሌ 4:14, 15) ኢየሱስ አባቱን ለማስደሰት ቁርጠኛ እንደነበረ ሁሉ አንተም ራስህን የወሰንክለትን አምላክ የሚያሳዝንን ማንኛውንም ነገር ወዲያውኑ አጥብቀህ ትቃወማለህ። (ማቴ. 4:10፤ ዮሐ. 8:29) እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የሚያጋጥምህ መከራና ፈተና ኢየሱስን ‘ያለማቋረጥ ለመከተል’ ያለህን ቁርጠኝነት ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጥሃል። እንዲህ ስታደርግ ይሖዋ እንደሚረዳህ መተማመን ትችላለህ። w24.03 9-10 አን. 8-10