ኅዳር
ቅዳሜ፣ ኅዳር 1
ከልጆችና ከሕፃናት አፍ ምስጋና አዘጋጀህ።—ማቴ. 21:16
ወላጆች ከሆናችሁ፣ ልጆቻችሁ ዕድሜያቸውን የሚመጥን መልስ እንዲዘጋጁ እርዷቸው። አንዳንድ ጊዜ በስብሰባው ላይ የምናጠናው በትዳር ውስጥ ስለሚያጋጥሙ ችግሮች፣ ስለ ሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ወይም ስለ ሌሎች ከበድ ያሉ ርዕሶች ሊሆን ይችላል። ሆኖም ልጆች ሐሳብ መስጠት የሚችሉበት አንድ ወይም ሁለት አንቀጽ መኖሩ አይቀርም። በተጨማሪም ልጆቻችሁ እጃቸውን ባወጡ ቁጥር የማይጠየቁት ለምን እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። እንዲህ ማድረጋችሁ እነሱ እጃቸውን አውጥተው ሌሎች አጋጣሚ ሲያገኙ ቅር እንዳይሰኙ ይረዳቸዋል። (1 ጢሞ. 6:18) ሁላችንም ይሖዋን የሚያስከብሩና የእምነት ባልንጀሮቻችንን የሚያንጹ መልሶችን መዘጋጀት እንችላለን። (ምሳሌ 25:11) አልፎ አልፎ የግል ተሞክሯችንን በአጭሩ መናገር የምንችል ቢሆንም ስለ ራሳችን ከልክ በላይ ከመናገር መቆጠብ ይኖርብናል። (ምሳሌ 27:2፤ 2 ቆሮ. 10:18) ከዚህ ይልቅ መልሳችን በይሖዋ፣ በቃሉና በሕዝቦቹ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ጥረት እናደርጋለን።—ራእይ 4:11፤ w23.04 24-25 አን. 17-18
እሁድ፣ ኅዳር 2
ነቅተን እንኑር እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን እንጠብቅ እንጂ እንደ ሌሎቹ አናንቀላፋ።—1 ተሰ. 5:6
ንቁ ለመሆንና የማስተዋል ስሜታችንን ለመጠበቅ ፍቅር ያስፈልገናል። (ማቴ. 22:37-39) ለአምላክ ያለን ፍቅር፣ ችግር የሚያስከትልብን ቢሆንም እንኳ በጽናት እንድንሰብክ ይረዳናል። (2 ጢሞ. 1:7, 8) እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎችም ፍቅር ስላለን መስበካችንን እንቀጥላለን፤ በስልክና በደብዳቤ ምሥክርነትም እንካፈላለን። በክልላችን ውስጥ ያሉት ሰዎች ተለውጠው ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንደሚጀምሩ ተስፋ እናደርጋለን። (ሕዝ. 18:27, 28) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንንም እንወዳቸዋለን። ‘እርስ በርስ በመበረታታት እንዲሁም እርስ በርስ በመተናነጽ’ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። (1 ተሰ. 5:11) በአንድ ወገን ተሰልፈው እንደሚዋጉ ወታደሮች እርስ በርስ እንበረታታለን። ሆን ብለን በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ጉዳት እንደማናደርስ ወይም በክፉ ፋንታ ክፉ እንደማንመልስ የታወቀ ነው። (1 ተሰ. 5:13, 15) በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞችን በማክበር ፍቅር እንዳለን እናሳያለን።—1 ተሰ. 5:12፤ w23.06 9 አን. 6፤ 11 አን. 10-11
ሰኞ፣ ኅዳር 3
[ይሖዋ] ያለውን አያደርገውም?—ዘኁ. 23:19
እምነታችንን ማጠናከር የምንችልበት አንዱ መንገድ በቤዛው ላይ ማሰላሰል ነው። ቤዛው አምላክ የገባው ቃል እንደሚፈጸም ዋስትና ይሰጠናል። ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀልን ለምን እንደሆነ እንዲሁም ቤዛውን ለማዘጋጀት ምን ያህል መሥዋዕት እንደከፈለ በጥሞና የምናሰላስል ከሆነ አምላክ በአዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንደምንኖር የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ያለንን እምነት እናጠናክራለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አምላክ ቤዛውን ለማዘጋጀት ምን ያህል መሥዋዕት እንደከፈለ እስቲ አስቡት። ይሖዋ የሚወደውን የበኩር ልጁን፣ የቅርብ ወዳጁን ከሰማይ ወደ ምድር በመላክ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ከዚያም ተሠቃይቶ በአሰቃቂ ሁኔታ ተሰቀለ። በእርግጥም ይሖዋ በጣም ውድ ዋጋ ከፍሎልናል! አፍቃሪው አምላካችን ውድ ልጁ ተሠቃይቶ እንዲሞት የፈቀደው ለአጭር ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንድንኖር ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ጴጥ. 1:18, 19) ይሖዋ የከፈለው ዋጋ በጣም ውድ ከመሆኑ አንጻር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እንደሚያደርገን ምንም ጥርጥር የለውም። w23.04 27 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ኅዳር 4
ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?—ሆሴዕ 13:14
ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ፍላጎቱ አለው? ምንም ጥርጥር የለውም! በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ወደፊት ስለሚከናወነው ትንሣኤ እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል። (ኢሳ. 26:19፤ ራእይ 20:11-13) ይሖዋ ደግሞ የገባውን ቃል ምንጊዜም ይፈጽማል። (ኢያሱ 23:14) እንዲያውም ይሖዋ ሙታንን ለማስነሳት ይጓጓል። እስቲ ኢዮብ የተናገረውን ሐሳብ እንመልከት። ቢሞትም እንኳ ይሖዋ እሱን ለማስነሳት እንደሚጓጓ እርግጠኛ ነበር። (ኢዮብ 14:14, 15 ግርጌ) ይሖዋ የሞቱ አገልጋዮቹን በሙሉ መልሶ ለማየት ይናፍቃል። ከሞት ሊያስነሳቸው እንዲሁም አስደሳችና ጤናማ ሕይወት ሊሰጣቸው ይጓጓል። ስለ ይሖዋ እውነቱን የማወቅ አጋጣሚ ሳያገኙ ስለሞቱት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? አፍቃሪው አምላካችን እነሱንም ከሞት ማስነሳት ይፈልጋል። (ሥራ 24:15) የእሱ ወዳጆች የመሆንና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል።—ዮሐ. 3:16፤ w23.04 9 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ኅዳር 5
አምላክ ኃይል ይሰጠናል።—መዝ. 108:13
ተስፋህን ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ተስፋህ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገነት የሚሰጠውን መግለጫ አንብበህ አሰላስልበት። (ኢሳ. 25:8፤ 32:16-18) በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ምን እንደሚመስል በዓይነ ሕሊናህ ሣል። በዚያ ስትኖር ይታይህ። አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ባለን ተስፋ ላይ ካተኮርን አሁን ያሉብን ችግሮች “ጊዜያዊና ቀላል” ይሆኑልናል። (2 ቆሮ. 4:17) ይሖዋ በተስፋው አማካኝነት ጥንካሬ ይሰጥሃል። ይሖዋ ከእሱ ጥንካሬ ማግኘት የምንችልባቸውን ዝግጅቶች አድርጎልናል። እንግዲያው አንድን ኃላፊነት ለመወጣት፣ አንድን ፈተና በጽናት ለመቋቋም ወይም ደስታህን ለመጠበቅ እርዳታ ሲያስፈልግህ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቅርብ። እንዲሁም በግል ጥናት አማካኝነት የእሱን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርግ። ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ የሚሰጡህን ማበረታቻ ተቀበል። ተስፋህ ምንጊዜም ብሩህ እንዲሆን አድርግ። እንዲህ ካደረግክ ‘በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት እንድትቋቋም የአምላክ ታላቅ ኃይል የሚያስፈልግህን ብርታት ሁሉ ይሰጥሃል።’—ቆላ. 1:11፤ w23.10 17 አን. 19-20
ሐሙስ፣ ኅዳር 6
ለሁሉም ነገር አመስግኑ።—1 ተሰ. 5:18
ይሖዋን በጸሎት የምናመሰግንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን። ስላገኘነው ስለ ማንኛውም መልካም ነገር ልናመሰግነው እንችላለን፤ ደግሞም የመልካም ስጦታ ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። (ያዕ. 1:17) ለምሳሌ ምድራችን ስላላት ውበት እንዲሁም በተፈጥሮ ላይ ስለሚታየው ጥበብ ይሖዋን ልናመሰግነው እንችላለን። በተጨማሪም ስለ ሕይወታችን፣ ስለ ቤተሰቦቻችን፣ ስለ ወዳጆቻችን እና ስለ ተስፋችን ልናመሰግነው እንችላለን። ከዚህም ሌላ፣ ከእሱ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት ውድ መብት ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባል። በግለሰብ ደረጃ ይሖዋን ለማመስገን የሚያነሳሱንን ምክንያቶች ለማሰብ ለየት ያለ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። የምንኖረው ምስጋና ቢስ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። ሰዎች ብዙ ጊዜ የሚያተኩሩት ማግኘት በሚፈልጉት ነገር ላይ እንጂ ላሏቸው ነገሮች አመስጋኝነታቸውን ማሳየት በሚችሉበት መንገድ ላይ አይደለም። እንዲህ ያለው አመለካከት ከተጋባብን ጸሎታችን ልመና ብቻ ያካተተ ይሆንብናል። ይህ እንዲያጋጥመን ካልፈለግን ይሖዋ ላደረገልን ነገር በሙሉ አድናቆት ማዳበራችንን እና ማመስገናችንን መቀጠል አለብን።—ሉቃስ 6:45፤ w23.05 4 አን. 8-9
ዓርብ፣ ኅዳር 7
ምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመኑን ይቀጥል።—ያዕ. 1:6
አፍቃሪ አባታችን ይሖዋ ስንሠቃይ ማየት አይፈልግም። (ኢሳ. 63:9) ያም ቢሆን እንደ ወንዝና ነበልባል ያሉ ፈተናዎች እንዳይደርሱብን አይከላከልልንም። (ኢሳ. 43:2) ነገር ግን በመካከላቸው ‘ለማለፍ’ እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። እንዲሁም የሚደርስብን መከራ ዘላቂ ጉዳት እንዲያስከትልብን አይፈቅድም። ይሖዋ ኃያል ቅዱስ መንፈሱን በመስጠትም እንድንጸና ይረዳናል። (ሉቃስ 11:13፤ ፊልጵ. 4:13) በዚህም የተነሳ፣ ለመጽናትና ለእሱ ምንጊዜም ታማኝ ለመሆን የሚያስፈልገንን ማንኛውንም እርዳታ እንደሚሰጠን መተማመን እንችላለን። ይሖዋ እንድንተማመንበት ይጠብቅብናል። (ዕብ. 11:6) አንዳንድ ጊዜ የሚያጋጥመን መከራ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። እንዲያውም ይሖዋ የሚረዳን መሆኑን መጠራጠር ልንጀምር እንችላለን። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ በአምላክ ኃይል “ቅጥር መውጣት” እንደምንችል ያረጋግጥልናል። (መዝ. 18:29) በመሆኑም በጥርጣሬ ከመዋጥ ይልቅ ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚመልስልን በመተማመን በሙሉ እምነት ልንጸልይ ይገባል።—ያዕ. 1:6, 7፤ w23.11 22 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ኅዳር 8
የፍቅር ወላፈን የእሳት ወላፈን ነው፤ የያህም ነበልባል ነው። ጎርፍ ፍቅርን ሊያጠፋው አይችልም፤ ወንዞችም ጠራርገው ሊወስዱት አይችሉም።—መኃ. 8:6, 7
ይህ ለእውነተኛ ፍቅር የተሰጠ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! እነዚህ ቃላት ለባለትዳሮች የሚያበረታታ ሐሳብ ይዘዋል፦ በመካከላችሁ የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል። ባለትዳሮች ዕድሜያቸውን በሙሉ የማይከስም ፍቅር ሊኖራቸው የሚችለው የበኩላቸውን ጥረት ካደረጉ ብቻ ነው። ለምሳሌ እሳት ያለማቋረጥ እንዲነድ ከተፈለገ ማገዶ ሊጨመርበት ይገባል። ማገዶ ካልተጨመረበት እሳቱ ቀስ በቀስ መጥፋቱ አይቀርም። በተመሳሳይም አንድ ባልና ሚስት ዕድሜያቸውን በሙሉ በመካከላቸው ጠንካራ ፍቅር ሊኖር ይችላል። ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ጥምረታቸውን ለማጠናከር ጥረት ካደረጉ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ባለትዳሮች በመካከላቸው ያለው ፍቅር እየቀዘቀዘ እንዳለ ሊሰማቸው ይችላል፤ በተለይም በኢኮኖሚ ችግር፣ በጤና እክል ወይም ልጆችን ማሳደግ በሚፈጥረው ውጥረት የተነሳ ጫና ሲበዛባቸው እንዲህ ሊሰማቸው ይችላል። ስለዚህ ‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም ከተፈለገ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። w23.05 20-21 አን. 1-3
እሁድ፣ ኅዳር 9
አትፍራ።—ዳን. 10:19
ድፍረት ለማዳበር ምን ማድረግ ያስፈልገናል? ወላጆቻችን ደፋር እንድንሆን ሊያበረታቱን ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ይህን ባሕርይ እንደ ንብረት ሊያወርሱን አይችሉም። ድፍረት ማዳበር አዲስ ክህሎት ከመማር ጋር ይመሳሰላል። አዲስ ክህሎት ማዳበር የሚቻልበት አንዱ መንገድ አስተማሪው የሚያደርገውን ነገር በጥንቃቄ ማየትና ምሳሌውን መኮረጅ ነው። በተመሳሳይም ሌሎች ድፍረት የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ በጥንቃቄ በማየትና የእነሱን ምሳሌ በመኮረጅ ይህን ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። እንደ ዳንኤል የአምላክን ቃል በደንብ ማወቅ ይኖርብናል። ስሜታችንን አውጥተን ከይሖዋ ጋር አዘውትረን በመነጋገር ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት ያስፈልገናል። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚደግፈን እርግጠኛ በመሆን ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት ይገባል። እንዲህ ካደረግን እምነታችን በሚፈተንበት ወቅት ድፍረት ማሳየት እንችላለን። ደፋር የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሌሎችን አክብሮት ያተርፋሉ። በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ሊረዱ ይችላሉ። በእርግጥም ድፍረት ለማዳበር የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለን። w23.08 2 አን. 2፤ 4 አን. 8-9
ሰኞ፣ ኅዳር 10
ሁሉንም ነገር መርምሩ።—1 ተሰ. 5:21
“መርምሩ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ውድ ማዕድናትን ከመፈተን ጋር በተያያዘ ይሠራበት ነበር። በመሆኑም የምንሰማው ወይም የምናነበው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ መፈተን ይኖርብናል። በተለይ ታላቁ መከራ እየተቃረበ ሲመጣ እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ሌሎች የሚናገሩትን ነገር ሁሉ በሞኝነት ከመቀበል ይልቅ የማመዛዘን ችሎታችንን በመጠቀም፣ የምናነበውን ወይም የምንሰማውን ነገር መጽሐፍ ቅዱስና የይሖዋ ድርጅት ከሚናገሩት ነገር ጋር ማወዳደር ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን በአጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳ አንታለልም። (ምሳሌ 14:15፤ 1 ጢሞ. 4:1) የአምላክ አገልጋዮች በቡድን ደረጃ ከታላቁ መከራ ይተርፋሉ። በግለሰብ ደረጃ ግን ነገ ምን እንደሚደርስብን አናውቅም። (ያዕ. 4:14) ያም ቢሆን ታላቁን መከራ በሕይወት ብናልፍም ሆነ ከዚያ በፊት ብንሞት ታማኝነታችንን እስከጠበቅን ድረስ የዘላለም ሕይወት ሽልማት እናገኛለን። እንግዲያው ሁላችንም አስደናቂ በሆነው ተስፋችን ላይ ትኩረት በማድረግ የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን እንጠብቅ! w23.06 13 አን. 15-16
ማክሰኞ፣ ኅዳር 11
ይሖዋ ለአገልጋዮቹ . . . ሚስጥሩን [ገልጧል]።—አሞጽ 3:7
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ አናውቅም። (ዳን. 12:8, 9) ያም ቢሆን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ አልተረዳንም ማለት ትንቢቱ አይፈጸምም ማለት አይደለም። ይሖዋ ቀደም ሲል እንዳደረገው ማወቅ ያለብንን ነገር በትክክለኛው ጊዜ ላይ እንደሚገልጥልን ልንተማመን እንችላለን። “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚል አዋጅ ይታወጃል። (1 ተሰ. 5:3) ከዚያም የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ይነሱና ሙሉ በሙሉ ያጠፏቸዋል። (ራእይ 17:16, 17) ቀጥሎም በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። (ሕዝ. 38:18, 19) ከዚያም የአርማጌዶን ጦርነት ይነሳል። (ራእይ 16:14, 16) እነዚህ ክንውኖች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እስከዚያው ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረት በመስጠትና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ በመርዳት በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ያለንን አድናቆት ማሳየታችንን እንቀጥል። w23.08 13 አን. 19-20
ረቡዕ፣ ኅዳር 12
እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው።—1 ዮሐ. 4:7
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ከተናገረ በኋላ “ከእነዚህ [ባሕርያት] መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 13:13) ጳውሎስ ይህን ያለው ለምንድን ነው? ወደፊት፣ አምላክ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ላይ እምነት ማሳደር ወይም ቃሉ እንደሚፈጸም ተስፋ ማድረግ አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም ያኔ ተስፋው ተፈጽሟል። ሆኖም ለይሖዋና ለሕዝቡ ምንጊዜም ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል። እንዲያውም ለእነሱ ያለን ፍቅር ለዘላለም እየጨመረ ይሄዳል። በተጨማሪም ፍቅር እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን የሚያሳይ መለያ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:35) ከዚህም ሌላ፣ እርስ በርስ መዋደዳችን አንድነት እንዲኖረን ያደርጋል። ጳውሎስ “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው” ብሏል። (ቆላ. 3:14) ሐዋርያው ዮሐንስ ለእምነት አጋሮቹ “አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ዮሐ. 4:21) እርስ በርስ ስንዋደድ አምላክን እንደምንወደው እናሳያለን። w23.11 8 አን. 1, 3
ሐሙስ፣ ኅዳር 13
ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን አንስተን እንጣል።—ዕብ. 12:1
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያኖችን ሕይወት ከሩጫ ውድድር ጋር ያመሳስለዋል። ሩጫውን የሚያጠናቅቁ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያገኛሉ። (2 ጢሞ. 4:7, 8) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ መጨረሻው መስመር እየተጠጋን ስለሆነ በሩጫው ለመቀጠል የቻልነውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ውድድሩን ለማሸነፍ ምን ማድረግ እንዳለብን ነግሮናል። “ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ” የሚል መመሪያ ሰጥቶናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል አንድ ክርስቲያን መሸከም ያለበት ምንም ዓይነት ሸክም እንደሌለ መግለጹ ነበር? በፍጹም፣ እንደዚያ ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ማስወገድ እንዳለብን መግለጹ ነበር። እንዲህ ያለው ሸክም ፍጥነታችንን ሊቀንሰውና ሊያደክመን ይችላል። በሩጫው መጽናት ከፈለግን ፍጥነታችንን ሊቀንስ የሚችልን ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ለይተን ማወቅና ማስወገድ ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ መሸከም ያለብንን ሸክም ችላ ልንል አይገባም። አለዚያ ከውድድሩ ልንባረር እንችላለን።—2 ጢሞ. 2:5፤ w23.08 26 አን. 1-2
ዓርብ፣ ኅዳር 14
ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ . . . አይሁን።—1 ጴጥ. 3:3
ምክንያታዊነት የሌሎችን አመለካከት እንድናከብርም ይረዳናል። ለምሳሌ አንዳንድ እህቶች መኳኳያ መጠቀም ይወዳሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይወዱም። አንዳንድ ክርስቲያኖች በልክ መጠጣት ያስደስታቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ጨርሶ ላለመጠጣት ወስነዋል። ሁሉም ክርስቲያኖች ጤናማ መሆን ይፈልጋሉ፤ ጤንነታቸውን የሚንከባከቡበት ዘዴ ግን እንደ ምርጫቸው ይለያያል። የእኛ ምርጫ ብቻ ትክክል እንደሆነ በማሰብ ሌሎችን የምንጫን ከሆነ በጉባኤ ውስጥ ማሰናከያ ልንሆንና ክፍፍል ልንፈጥር እንችላለን። (1 ቆሮ. 8:9፤ 10:23, 24) ለምሳሌ ይሖዋ ከአለባበስ ጋር በተያያዘ ዝርዝር ደንቦች ከማውጣት ይልቅ ልንከተላቸው የሚገቡ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። አለባበሳችን ለአምላክ አገልጋዮች የሚመጥን እንዲሁም ምክንያታዊነት፣ ልከኝነትና “ማስተዋል” የተንጸባረቀበት ሊሆን ይገባል። (1 ጢሞ. 2:9, 10) ስለዚህ አለባበሳችን ወደ ራሳችን አላስፈላጊ ትኩረት የሚስብ ሊሆን አይገባም። ሽማግሌዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተላቸው ከአለባበስና ከፀጉር ስታይል ጋር በተያያዘ የራሳቸውን ደንብ እንዳያወጡ ይረዳቸዋል። w23.07 23 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ኅዳር 15
እኔን በጥሞና አዳምጡ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤ ምርጥ ምግብ በመብላትም ሐሴት ታደርጋላችሁ።—ኢሳ. 55:2
ይሖዋ አስደሳች የወደፊት ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን መንገድ አሳይቶናል። “ማስተዋል የጎደላት” ጯኺ ሴት የምታቀርበውን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች በድብቅ ብልግና በመፈጸም ደስታ ለማግኘት ይፈልጋሉ። መጨረሻቸው ወደ “መቃብር ጥልቅ” መውረድ ነው። (ምሳሌ 9:13, 17, 18) “እውነተኛ ጥበብ” የምታቀርበውን ግብዣ የሚቀበሉ ሰዎች ግን የሚያገኙት ውጤት ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው! (ምሳሌ 9:1) ይሖዋ የሚወደውን ነገር እንድንወድና እሱ የሚጠላውን ነገር እንድንጠላ እንማራለን። (መዝ. 97:10) እንዲሁም ሌሎች ‘ከእውነተኛ ጥበብ’ ጥቅም እንዲያገኙ ግብዣ በማቅረብ እርካታ እናገኛለን። “ከከተማዋ በላይ ባሉ ከፍታ ቦታዎች ላይ [ሆነን] ‘ተሞክሮ የሌለው ሁሉ ወደዚህ ይምጣ’” ብለን የምንጣራ ያህል ነው። ግብዣችንን የሚቀበሉ ሰዎችም ሆኑ እኛ የምናገኘው ጥቅም በአሁኑ ጊዜ ብቻ የሚወሰን አይደለም። የምናገኘው በረከት ዘላቂ ነው፤ ‘በማስተዋል መንገድ ወደ ፊት እየሄድን’ ለዘላለም እንድንኖር ያስችለናል።—ምሳሌ 9:3, 4, 6፤ w23.06 24 አን. 17-18
እሁድ፣ ኅዳር 16
ቶሎ የማይቆጣ ሰው ከኃያል ሰው፣ ስሜቱን የሚቆጣጠርም ከተማን ድል ከሚያደርግ ሰው ይሻላል።—ምሳሌ 16:32
የሥራ ባልደረባህ ወይም አብሮህ የሚማር ልጅ ስለ እምነትህ ሲጠይቅህ ምን ይሰማሃል? ፍርሃት ፍርሃት ይልሃል? ብዙዎቻችን እንደዚያ ይሰማናል። ይሁንና እንዲህ ያለው ጥያቄ ስለ ግለሰቡ አስተሳሰብ ወይም እምነት እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ምሥራቹን ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትልናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጥያቄ የሚያነሱት የማወቅ ፍላጎት ኖሯቸው ሳይሆን እኛን ለማፋጠጥ ብለው ነው። ይህ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም። ምክንያቱም አንዳንዶች ስለ እምነታችን የተሳሳተ መረጃ ሰምተዋል። (ሥራ 28:22) በተጨማሪም የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ ነው፤ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ብዙዎቹ ሰዎች ደግሞ “ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ” አልፎ ተርፎም “ጨካኞች” ናቸው። (2 ጢሞ. 3:1, 3) ‘አንድ ሰው የማምንባቸውን ነገሮች በተመለከተ በጥያቄ ቢያፋጥጠኝ በደግነትና በዘዴ ምላሽ መስጠት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በዚህ ረገድ ገርነት ይረዳሃል። ገር የሆነ ሰው የሚያስቆጣ ሁኔታ ሲያጋጥመው ወይም ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ግራ ሲገባው በቀላሉ አይበሳጭም፤ ከዚህ ይልቅ ራሱን መቆጣጠር ይችላል። w23.09 14 አን. 1-2
ሰኞ፣ ኅዳር 17
በምድር ሁሉ ላይ መኳንንት አድርገህ ትሾማቸዋለህ።—መዝ. 45:16
ከድርጅቱ የምናገኘው ምክር ጥበቃም ያስገኝልናል። ለምሳሌ ከፍቅረ ነዋይ እንዲሁም የይሖዋን ሕጎች እንድንጥስ ሊያደርጉን ከሚችሉ አንዳንድ ድርጊቶች እንድንርቅ ምክር ይሰጠናል። በእነዚህ ጉዳዮች ረገድም የይሖዋን መመሪያ መከተላችን ይጠቅመናል። (ኢሳ. 48:17, 18፤ 1 ጢሞ. 6:9, 10) ይሖዋ በታላቁ መከራም ሆነ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት እኛን ለመምራት ሰብዓዊ ወኪሎቹን መጠቀሙን እንደሚቀጥል ምንም ጥያቄ የለውም። ይህን መመሪያ መከተላችንን እንቀጥላለን? ይህ በዋነኝነት የተመካው በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ አመራር በምንሰጠው ምላሽ ላይ ነው። እንግዲያው ተግተው እንዲጠብቁን በተሾሙ ወንድሞች አማካኝነት የምናገኘውን መመሪያ ጨምሮ የይሖዋን አመራር ምንጊዜም እንከተል። (ኢሳ. 32:1, 2፤ ዕብ. 13:17) እንዲህ ካደረግን፣ መሪያችን ይሖዋ ከመንፈሳዊ አደጋዎች ጠብቆ ወደ መዳረሻችን ማለትም የዘላለም ሕይወት ወደምናገኝበት አዲስ ዓለም እንደሚመራን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w24.02 25 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ኅዳር 18
የዳናችሁት በጸጋ ነው።—ኤፌ. 2:5
ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት አስደሳች ሕይወት አሳልፏል፤ ሆኖም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለታል ማለት አይደለም። ጳውሎስ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ብዙ ጊዜ ተጉዟል፤ በዚያ ዘመን ደግሞ ጉዞ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ጳውሎስ በጉዞው ላይ “በወንዝ ሙላት ለሚመጣ አደጋ” እንዲሁም “ዘራፊዎች ለሚያደርሱት አደጋ” የተጋለጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። በተቃዋሚዎች እጅ ተደብድቧል እንዲሁም እንግልት ደርሶበታል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ክርስቲያን ወንድሞቹም ቢሆኑ ለእነሱ ሲል ብዙ መድከሙን ያላደነቁበት ጊዜ አለ። (2 ቆሮ. 10:10፤ ፊልጵ. 4:15) ታዲያ ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? ከቅዱሳን መጻሕፍትና ከራሱ ተሞክሮ ስለ ይሖዋ ባሕርያት ብዙ ተምሯል። ጳውሎስ ይሖዋ አምላክ እንደሚወደው እርግጠኛ ነበር። (ሮም 8:38, 39፤ ኤፌ. 2:4, 5) እሱም ይሖዋን በጣም ይወደው ነበር። ይህ ፍቅር ‘ቅዱሳንን እንዲያገለግልና ወደፊትም ማገልገሉን እንዲቀጥል’ አነሳስቶታል።—ዕብ. 6:10፤ w23.07 9 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ኅዳር 19
ለበላይ ባለሥልጣናት [ተገዙ]።—ሮም 13:1
ብዙ ሰዎች፣ መንግሥታት መኖራቸው ጠቃሚ እንደሆነና ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ ከሚያወጧቸው ሕጎች መካከል ቢያንስ የተወሰኑትን መታዘዝ እንዳለብን ያምናሉ። ሆኖም እነዚያው ሰዎች፣ አንድ ሕግ ፍትሐዊ እንዳልሆነ ወይም ብዙ መሥዋዕት እንደሚያስከፍላቸው ከተሰማቸው ያንን ሕግ ለመታዘዝ ፈቃደኞች ላይሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰብዓዊ መንግሥታት መከራ እንደሚያመጡ፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንደሆኑና በቅርቡ እንደሚጠፉ ይናገራል። (መዝ. 110:5, 6፤ መክ. 8:9፤ ሉቃስ 4:5, 6) በሌላ በኩል ደግሞ “ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል” ይላል። ይሖዋ ሥርዓት እንዲሰፍን ሲል የበላይ ባለሥልጣናት ለተወሰነ ጊዜ እንዲገዙ ፈቅዶላቸዋል፤ ስለዚህ እንድንታዘዛቸው ይጠብቅብናል። በመሆኑም ግብርን፣ አክብሮትንና ታዛዥነትን ጨምሮ ‘ለሁሉም የሚገባውን ማስረከብ’ ይጠበቅብናል። (ሮም 13:1-7) አንድ ሕግ የማይመች፣ ፍትሐዊ ያልሆነ ወይም ብዙ ወጪ የሚያስወጣን እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ይሖዋን መታዘዝ እንፈልጋለን፤ እሱ ደግሞ ያወጣውን ሕግ እንድንጥስ እስካልጠየቁን ድረስ ለበላይ ባለሥልጣናት እንድንታዘዝ ነግሮናል።—ሥራ 5:29፤ w23.10 8 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ኅዳር 20
የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው።—መሳ. 15:14
ሳምሶን በተወለደ ጊዜ እስራኤላውያን በፍልስጤማውያን ግዛት ሥር ነበሩ፤ እነሱም ይጨቁኗቸው ነበር። (መሳ. 13:1) ጭካኔ በተሞላበት አገዛዛቸው የተነሳ እስራኤላውያን ለከፍተኛ ሥቃይ ተዳርገዋል። ይሖዋ “እስራኤልን ከፍልስጤማውያን እጅ በማዳን ረገድ ግንባር ቀደም” እንዲሆን ሳምሶንን መረጠው። (መሳ. 13:5) ሳምሶን ይህን ተፈታታኝ ኃላፊነት ለመወጣት በይሖዋ መታመን ነበረበት። በአንድ ወቅት የፍልስጤም ሠራዊት ሳምሶንን ለመያዝ ወደ ሊሃይ መጥቶ ነበር፤ ሊሃይ የምትገኘው ይሁዳ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። የይሁዳ ሰዎች ስለፈሩ ሳምሶንን ለጠላት አሳልፈው ለመስጠት ወሰኑ። የገዛ ወገኖቹ ሳምሶንን በሁለት አዳዲስ ገመዶች ጥፍር አድርገው አስረው ወደ ፍልስጤማውያን አመጡት። (መሳ. 15:9-13) ነገር ግን “የይሖዋ መንፈስ ኃይል ሰጠው”፤ ሳምሶንም ገመዶቹን በጣጠሳቸው። ከዚያም “በቅርቡ የሞተ የአንድ አህያ መንጋጋ አገኘ”፤ መንጋጋውንም አንስቶ በእሱ 1,000 ፍልስጤማውያንን ገደለ።—መሳ. 15:14-16፤ w23.09 2-3 አን. 3-4
ዓርብ፣ ኅዳር 21
ይህም አምላክ ከጌታችን ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ ባዘጋጀው ዘላለማዊ ዓላማ መሠረት ነው።—ኤፌ. 3:11
የይሖዋ ዓላማ በማንኛውም መንገድ መፈጸሙ አይቀርም፤ ምክንያቱም “ማንኛውንም ነገር ያዘጋጀው ለራሱ ዓላማ ነው።” (ምሳሌ 16:4) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ዓላማ “ዘላለማዊ” እንደሆነም ይናገራል። “ዘላለማዊ” የተባለው ይሖዋ ዓላማው ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ ረጅም ጊዜ እንዲያልፍ ስለፈቀደ ነው። በተጨማሪም የይሖዋ ዓላማ የሚያስገኘው ውጤት ዘላለማዊ ነው። ለመሆኑ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው? ዓላማውን ለመፈጸምስ የትኞቹን ማስተካከያዎች አድርጓል? አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለእነሱ ያለውን ዓላማ ነግሯቸዋል። “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም። እንዲሁም . . . በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው” ብሏቸዋል። (ዘፍ. 1:28) አዳምና ሔዋን በማመፃቸው የተነሳ የሰው ልጆች ኃጢአተኛ ቢሆኑም የአምላክ ዓላማ አልከሸፈም። ከዚህ ይልቅ ዓላማውን በሚፈጽምበት መንገድ ላይ ማስተካከያ አደረገ። ለሰው ልጆችና ለምድር ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ ለመፈጸም በሰማይ መንግሥት እንደሚያቋቁም ወዲያውኑ ወሰነ።—ማቴ. 25:34፤ w23.10 20 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ ኅዳር 22
ይሖዋ ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በጠፋሁ ነበር።—መዝ. 94:17
ይሖዋ እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። በተለይ ከአንድ ድክመት ጋር ለረጅም ጊዜ ስንታገል ከቆየን መጽናት ከባድ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የእኛ ድክመት ከሐዋርያው ጴጥሮስ ድክመት አንጻር ከባድ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ተስፋ እንዳንቆርጥ ብርታት ሊሰጠን ይችላል። (መዝ. 94:18, 19) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም እውነትን ከመስማቱ በፊት ለበርካታ ዓመታት ግብረ ሰዶማዊ ነበር። በኋላ ግን ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗሩን ሙሉ በሙሉ ተወ። ይሁንና ከመጥፎ ምኞቶች ጋር አልፎ አልፎ ይታገል ነበር። ታዲያ እንዲጸና የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ያጠናክረናል። የይሖዋ መንፈስ እስከረዳኝ ድረስ . . . በእውነት መንገድ ላይ መጓዜን [መቀጠል] እንደምችል ተምሬያለሁ። . . . ይሖዋ አሁንም እየተጠቀመብኝ ነው። ድክመት ቢኖርብኝም እንኳ ምንጊዜም ያጠናክረኛል።” w23.09 23 አን. 12
እሁድ፣ ኅዳር 23
ትሕትናና ይሖዋን መፍራት ሀብት፣ ክብርና ሕይወት ያስገኛል።—ምሳሌ 22:4
ወጣት ወንድሞች፣ ያለምንም ጥረት የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች መሆን አትችሉም። ጥሩ ምሳሌ የሚሆኗችሁን ሰዎች መምረጥ፣ የማመዛዘን ችሎታን ማዳበር፣ እምነት የሚጣልባችሁ መሆን፣ ጠቃሚ ክህሎቶችን ማዳበር እንዲሁም ወደፊት ለምትቀበሏቸው ኃላፊነቶች መዘጋጀት ያስፈልጋችኋል። ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ መድረስ የሚጠይቀውን ጥረት ስታስቡ ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ሆኖም ሊሳካላችሁ ይችላል። ይሖዋ ሊረዳችሁ እንደሚፈልግ አስታውሱ። (ኢሳ. 41:10, 13) በጉባኤያችሁ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም ይረዷችኋል። እድገት አድርጋችሁ የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች ስትሆኑ ሕይወታችሁ አስደሳችና እርካታ ያለው ይሆንላችኋል። ወጣት ወንድሞች፣ እንወዳችኋለን! የጎለመሳችሁ ክርስቲያኖች ለመሆን ከአሁኑ ጥረት ስታደርጉ ይሖዋ አትረፍርፎ እንዲባርካችሁ እንመኛለን። w23.12 29 አን. 19-20
ሰኞ፣ ኅዳር 24
በደልን . . . ተዉ።—ምሳሌ 19:11
ከተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተሰብስባችሁ እየተጫወታችሁ ነው እንበል። በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፋችሁ አንድ ላይ ፎቶ ትነሳላችሁ። ፎቶውን ስታነሱ ለማንኛውም ብላችሁ ሁለት ተጨማሪ ፎቶዎችን አነሳችሁ። በድምሩ ሦስት ፎቶዎች አንስታችኋል ማለት ነው። አንደኛው ፎቶ ላይ አንድ ወንድም እንደተኮሳተረ አስተዋላችሁ። ስለዚህ ፎቶውን ታጠፉታላችሁ፤ ምክንያቱም በሌሎቹ ሁለት ፎቶዎች ላይ ይህን ወንድም ጨምሮ ሁሉም ሰው ፈገግ ብሏል። ብዙውን ጊዜ፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጊዜ ስናሳልፍ ጥሩ ትዝታ ይኖረናል። ሆኖም በአንድ ወቅት አንድ ወንድማችን ወይም እህታችን ደግነት የጎደለው ነገር ቢያደርጉ ወይም ቢናገሩስ? ይህን ትዝታ ምን ልናደርገው ይገባል? አንደኛውን ፎቶ እንደሰረዝነው ሁሉ ይህን ትዝታ ከአእምሯችን ብናጠፋው የተሻለ አይሆንም? (ኤፌ. 4:32) ከዚያ ግለሰብ ጋር ብዙ አስደሳች ትዝታዎች ስላሉን እንዲህ ማድረግ እንችላለን። አእምሯችን ውስጥ መያዝ የምንፈልገው እንዲህ ያሉትን ትዝታዎች ነው። w23.11 12-13 አን. 16-17
ማክሰኞ፣ ኅዳር 25
ሴቶች . . . ተገቢ በሆነ ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ፤ ለአምላክ ያደርን ነን የሚሉ ሴቶች ሊያደርጉት እንደሚገባ . . . ይዋቡ።—1 ጢሞ. 2:9, 10
እዚህ ላይ የተሠራባቸው የግሪክኛ ቃላት አንዲት ክርስቲያን የሚያስከብር እንዲሁም ለሌሎች ስሜት እንደምትጠነቀቅ የሚያሳይ አለባበስ ሊኖራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ። የጎለመሱ እህቶቻችን ልከኛ የሆነ ልብስ ስለሚለብሱ በጣም እናደንቃቸዋለን! ሁሉም የጎለመሱ እህቶች ሊያዳብሩት የሚገባው ሌላው ባሕርይ ማስተዋል ነው። ማስተዋል ምንድን ነው? የማመዛዘን ችሎታ ማለትም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ከዚያም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ነው። የአቢጋኤልን ምሳሌ እንመልከት። ባለቤቷ በመላው ቤተሰቡ ላይ አስከፊ መዘዝ የሚያስከትል መጥፎ ውሳኔ አድርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ አቢጋኤል አፋጣኝ እርምጃ ወሰደች። የወሰደችው ማስተዋል የሚንጸባረቅበት እርምጃ የብዙ ሰዎችን ሕይወት አድኗል። (1 ሳሙ. 25:14-23, 32-35) ከዚህም ሌላ ማስተዋል መቼ መናገር፣ መቼ ደግሞ ዝም ማለት እንዳለብን ለማወቅ ይረዳናል። በተጨማሪም ለሌሎች አሳቢነት በምናሳይበት ወቅት በግል ሕይወታቸው ውስጥ ጣልቃ እንዳንገባ ይረዳናል።—1 ተሰ. 4:11፤ w23.12 20 አን. 8-9
ረቡዕ፣ ኅዳር 26
[የአምላክን] ክብር እንደምናገኝ ተስፋ በማድረግ እጅግ እንደሰት።—ሮም 5:2
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው በሮም ለነበረው ጉባኤ ነው። በዚያ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ተምረዋል፤ እምነት አዳብረዋል፤ እንዲሁም ክርስቲያኖች ሆነዋል። በመሆኑም አምላክ ‘በእምነት አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ብሏቸዋል’፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ቀብቷቸዋል። (ሮም 5:1) አዎ፣ አስተማማኝና አስደናቂ ተስፋ አግኝተዋል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ፣ በኤፌሶን ለነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለተጠሩበት ተስፋ ጽፎላቸዋል። ይህ ተስፋ ‘ለቅዱሳን የተዘጋጀውን ውርሻ’ መቀበልን ያካትታል። (ኤፌ. 1:18) በተጨማሪም ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ተስፋቸው የሚፈጸመው የት እንደሆነ ነግሯቸዋል። ‘በሰማይ የሚጠብቃችሁ ተስፋ’ በማለት ጠርቶታል። (ቆላ. 1:4, 5) በመሆኑም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ተስፋ ከሞት ተነስተው በሰማይ የዘላለም ሕይወት ማግኘትና ከክርስቶስ ጋር መግዛት ነው።—1 ተሰ. 4:13-17፤ ራእይ 20:6፤ w23.12 9 አን. 4-5
ሐሙስ፣ ኅዳር 27
ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም . . . ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።—ፊልጵ. 4:7
“ይጠብቃል” ተብሎ የተተረጎመው የበኩረ ጽሑፉ ቃል አንዲትን ከተማ ከጥቃት የሚጠብቁ ወታደሮችን ለማመልከት ይሠራበት ነበር። በወታደር በምትጠበቅ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጠባቂዎች እንዳሉ ስለሚያውቁ በሰላም ተኝተው ያድራሉ። በተመሳሳይም የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን ሲጠብቅልን ምንም ጉዳት እንደማይደርስብን ስለምናውቅ የመረጋጋት ስሜት ይሰማናል። (መዝ. 4:8) ያለንበት ሁኔታ ወዲያውኑ ባይቀየርም እንኳ እንደ ሐና በተወሰነ መጠን ሰላም ማግኘት እንችላለን። (1 ሳሙ. 1:16-18) ውስጣችን ሲረጋጋ ደግሞ አጥርተን ማሰብና ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን ማድረግ ቀላል ይሆንልናል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ጠባቂውን ጥራ። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክን ሰላም እስክታገኝ ድረስ ጸልይ። (ሉቃስ 11:9፤ 1 ተሰ. 5:17) ከባድ መከራ ካጋጠመህ ሳትታክት ጸልይ። እንዲህ ካደረግክ፣ የይሖዋ ሰላም ልብህንና አእምሮህን ይጠብቅልሃል።—ሮም 12:12፤ w24.01 21 አን. 5-6
ዓርብ፣ ኅዳር 28
በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።—ማቴ. 6:9
ኢየሱስ የአባቱን ስም ለማስቀደስ ሲል የደረሰበትን ስድብ፣ ሥቃይና የሐሰት ክስ በጽናት ተቋቁሟል። አባቱን ሙሉ በሙሉ እንደታዘዘ ስለሚያውቅ የሚያፍርበት ነገር አልነበረውም። (ዕብ. 12:2) በእነዚያ አስጨናቂ ሰዓታት በቀጥታ ጥቃት እየሰነዘረበት ያለው ሰይጣን እንደሆነም ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 22:2-4፤ 23:33, 34) ሰይጣን፣ ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን ያላላል ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም የሰይጣን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል! ኢየሱስ፣ ሰይጣን የለየለት ውሸታም እንደሆነና ይሖዋ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ታማኝ አገልጋዮች እንዳሉት በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል። አንተስ ንጉሣችንን ማስደሰት ትፈልጋለህ? ከሆነ የይሖዋን ስም ማወደስህን ቀጥል። ሰዎች የአምላካችንን አስደናቂ ማንነት እንዲያውቁ እርዳቸው። እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ፈለግ ትከተላለህ። (1 ጴጥ. 2:21) እንደ ኢየሱስ ይሖዋን ታስደስተዋለህ፤ እንዲሁም ጠላቱ ሰይጣን ውሸታም እንደሆነ ታጋልጣለህ። w24.02 11-12 አን. 11-13
ቅዳሜ፣ ኅዳር 29
ላደረገልኝ መልካም ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምን እመልስለታለሁ?—መዝ. 116:12
ባለፉት አምስት ዓመታት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ራስህን ለይሖዋ ስትወስን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆንና በሕይወትህ ውስጥ ምንጊዜም የአምላክን ፈቃድ ለማስቀደም ትመርጣለህ። ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ምን ማድረግ ይጠበቅብሃል? ኢየሱስ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ” ብሏል። (ማቴ. 16:24) “ራሱን ይካድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ሐረግ “ራሱን እንቢ ይበል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ራስህን የወሰንክ የይሖዋ አገልጋይ ስትሆን ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚጋጭን ማንኛውንም ነገር እንቢ ማለት ይኖርብሃል። (2 ቆሮ. 5:14, 15) ይህም እንደ ፆታ ብልግና ካሉት “የሥጋ ሥራዎች” ጋር በተያያዘ እንቢ ማለትን ይጨምራል። (ገላ. 5:19-21፤ 1 ቆሮ. 6:18) እንዲህ ያሉት ገደቦች ሕይወትህን ያከብዱብሃል? ይሖዋን የምትወድና የእሱን ሕጎች መከተል እንደሚጠቅምህ የምታምን ከሆነ እነዚህን ሕጎች መከተል ከባድ አይሆንብህም።—መዝ. 119:97፤ ኢሳ. 48:17, 18፤ w24.03 2 አን. 1፤ 3 አን. 4
እሁድ፣ ኅዳር 30
በአንተ ደስ ይለኛል።—ሉቃስ 3:22
ይሖዋ ለሚደሰትባቸው ሰዎች ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣል። (ማቴ. 12:18) እስቲ የሚከተለውን ጥያቄ አስብበት፦ ‘የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆኑ ባሕርያትን በሕይወቴ ውስጥ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማፍራት ችያለሁ?’ ለምሳሌ እውነትን ከማወቅህ በፊት ከነበርከው ይበልጥ ታጋሽ እንደሆንክ ታስተውል ይሆናል። አዎ፣ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆኑ ባሕርያትን ይበልጥ ባዳበርክ መጠን ይሖዋ እንደሚደሰትብህ ያለህ እርግጠኝነትም እየጨመረ ይሄዳል። ይሖዋ፣ የሚደሰትባቸው ሰዎች ከቤዛው ጥቅም እንዲያገኙ ያደርጋል። (1 ጢሞ. 2:5, 6) አንዳንድ ጊዜ ግን በቤዛው አምነን ተጠምቀንም እንኳ ልባችን፣ ይሖዋ እንደሚደሰትብን መቀበል ሊከብደው ይችላል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ይህን አስታውስ፦ የእኛ ስሜት አይታመንም፤ ይሖዋን ግን ሁሌም ልንተማመንበት እንችላለን። በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች በእሱ ዓይን ጻድቅ ተደርገው ይቆጠራሉ፤ እንደሚባርካቸውም ቃል ገብቷል።—መዝ. 5:12፤ ሮም 3:26፤ w24.03 30 አን. 15፤ 31 አን. 17