ይሖዋን ለመፈለግ ጊዜው አሁን ነው
“የሚያስተውል፣ [ይሖዋንም (አዓት)] የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ [ይሖዋ (አዓት)] ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።”—መዝሙር 14:2
1, 2. (ሀ) ብዙ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን የሚመለከቱት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የሰውን ልጅ ቸልተኛነት እንደተገነዘበ እንዴት እናውቃለን?
ዛሬ አምላክ የለም ባዮች፣ ስለ አምላክ ምንም ማወቅ አይቻልም የሚሉ አግኖስቲኮች፣ የሐሰት አማልክት አምላኪዎችና በአምላክ እናምናለን ቢሉም በሥራቸው የሚክዱት በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን አንፈልግህም ብለውታል። (ቲቶ 1:16) ብዙዎቹ በ19ኛው መቶ ዘመን ይኖር እንደነበረውና “አምላክ ሞቷል” ብሎ እንደተናገረው የጀርመን ፈላስፋ እንደ ናይትሺ ያለ እምነት አላቸው። ይሖዋ ይህን የግድ የለሽነት ሁኔታ ሳይገነዘበው ቀርቷልን? አልቀረም፤ ምክንያቱም ዳዊት እንደሚከተለው በማለት እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል፦ “ሰነፍ በልቡ፦ [ይሖዋ (አዓት)] የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፣ ጎሰቆሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም።”—መዝሙር 14:1
2 ዳዊት ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “የሚያስተውል፤ [ይሖዋንም (አዓት)] የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ [ይሖዋ (አዓት)] ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።” አዎን፣ የሁሉም የበላይ ጌታ እርሱን ለማወቅና ለማገልገል የሚፈልጉትን ያውቃል። ስለዚህ እርሱን አሁንኑ ተግተን መፈለጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህም በዘላለም ሕይወትና በዘላለም ጥፋት መካከል ያለ ልዩነት ማለት ነው።—መዝሙር 14:2፤ ማቴዎስ 25:41, 46፤ ዕብራውያን 11:6
3. ወደፊት ምን ጭማሪ መገኘት ይችላል?
3 ስለዚህ አሁንኑ ይሖዋን እንዲፈልጉ ሌሎችን መርዳታችን ለምን አስፈላጊ እንደሆነ መመልከት እንችላለን። ከይሖዋ ምስክሮች ጋር ፈጽሞ ያልተገናኙ ወይም “የመንግሥቱን ምሥራች” ሰምተው የማያውቁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም አሉ። በተጨማሪም “ታላቁ መከራ” ከመምጣቱ በፊት “እጅግ ብዙ ሰዎች” የተባሉት ቁጥራቸው ምን ላይ እንደሚደርስ ገና አናውቅም። ሆኖም ጊዜው ከማለቁ በፊት ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ይሖዋ አምላክን ለመፈለግና ለማግኘት የሚችሉ ብዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ነው። አሁን ያለው ጥያቄ እጅግ ብዙ ተጨማሪ ሰዎች አምላክን እንዲያገኙ ለመርዳት ምን ልናደርግ እንችላለን? የሚል ነው።—ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 7:9, 14
4, 5. ብዙ ሰዎች አምላክን ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ ምን ቢሆን ይመርጣሉ?
4 በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ፍለጋ ይዘዋል፤ ግን ምን ለማግኘት ነው የሚፈልጉት? ብቸኛ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚፈልጉት በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው። ብዛት ያላቸው ሰዎች ግን የሚፈልጉት ከግል ምኞታቸውና ጥላቻቸው ጋር የሚስማማላቸውን አምላክ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ አስተያየት የሚሰጥበትን ስብሰባ የሚመሩት ጆርጅ ጋለፕ እንዲህ ሲሉ እንደገለጹት ነው፦ “ማጭበርበርን፣ የቀረጥ መክፈል ግዴታን መሸሽን፣ ስርቆትን በተመለከተ ቤተክርስቲያን በሚያዘወትሩትና በማይሄዱት ሰዎች መካከል ልዩነት አይታይም። ይህም የሆነበት ምክንያት ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለማራመድ የቆሙ ብዙ ሃይማኖቶች በመኖራቸው ነው።” በተጨማሪም እንዲህ አሉ፦ “ብዙዎች አንድን ሃይማኖት የሚከተሉት የሚስማማቸውና የሚያስደስታቸው ሲሆን ነው። . . . አንድ ሰው ይህንን ሁኔታ “ሆቴል ውስጥ በመግባት የምግብ ዓይነቶችን ዝርዝር አይቶ የወደዱትን እንደ መምረጥ ያህል ነው” ብለዋል።
5 ሌሎቹም “ሃይማኖቴ ለእኔ ተስማሚ ነው” ይላሉ። ሆኖም እዚህ ላይ መጠየቅ ያለበት “ሃይማኖቴ ለአምላክ ተስማሚ ነውን?” የሚለው ጥያቄ መሆን ነበረበት። በሕዝበ ክርስትና ውስጥና በሂንዱ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ምስሎቻቸውንና ጣዖቶቻቸውን ማምለኩ ብቻ ያረካቸዋል። ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ አብዛኞቹ ሰዎች ስም የለሹን የስላሴ አምላክ ለእነርሱ በቂ ሆኖ አግኝተውታል። ከ900 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ እስላሞችም በአላህ ያምናሉ። በሌላም በኩል ኤቲስት የሚባሉ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክ የለም ይላሉ።
እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች
6. ብዙ የመጠበቂያ ግንብ አንባቢዎች ምንን አውቀዋል?
6 ይሁን እንጂ ዘወትር ይህንን መጽሔት የምናነበው እኛስ እንዴት ነን? እውነተኛውን አምላክ ፈልገን አግኝተነዋል። “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚሉት የያዕቆብ 4:8 ቃላት እውነት መሆናቸውን አረጋግጠናል። ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር የቅርብ ግንኙነት በመመሥረት ወደ አምላክ ቀርበናል፣ ይሖዋም እንዴት ወደ እኛ እንደሚቀርብ ለማየት ችለናል።—ዮሐንስ 6:44, 65
7. በእውነት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ እንዴት እናውቃለን?
7 ይሁን እንጂ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አልፎ አልፎ በደስታ የሚሰበሰቡ ነገር ግን ራሳቸውን ወስነውና ተጠምቀው ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ገና በግልጽ የሚታይ እርምጃ ያልወሰዱ ብዙ ሰዎች አሉ። ይህንን ለማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በ1990 በተከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ወደ አሥር ሚልዮን የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ይህንን የመንግሥት ምሥራች በትጋት የሚያውጁት ስንት ናቸው? ቁጥራቸው ከአራት ሚልዮን በትንሹ ብቻ ከፍ የሚሉ ናቸው። ይህ የሚያሳየው እውነትን የሚወዱና አንዳንድ ጊዜ ከእኛ ጋር በመሰብሰባቸው የሚደሰቱ ነገር ግን የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ የእውነትን ንፁህ ልሳን ለሌሎች ማስተዋወቅ ያልጀመሩ ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች መኖራቸውን ነው። ብዙዎቹ አጋጣሚ ሲያገኙ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ መንግሥታዊ አገዛዙ እንደሚናገሩ ምንም አያጠራጥርም። ሆኖም ራሳቸውን የይሖዋ ምስክሮች እንደሆኑ ገና በግልጽ አላሳወቁም። እነዚህንም ጭምር መርዳት እንፈልጋለን።—ሶፎንያስ 3:9፤ ማርቆስ 13:10
8, 9. (ሀ) ይሖዋ ምን እንድናደርግ ያበረታታናል? (ለ) የይሖዋን ምክር ቸል ማለቱ አዋቂነት ያልሆነው ለምንድን ነው?
8 እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ባለው የመጨረሻ ዙር ታላቅ ሥራ የሚሳተፉ ደስተኛና ንቁ የይሖዋ ምስክሮች እንዲሆኑ ልናበረታታቸው እንፈልጋለን። በምሳሌ 1:23 ላይ ይሖዋ ያቀረበውን ፍቅራዊ ግብዣ እባካችሁ ልብ በሉት፦ “ወደ ዘለፋዬ ተመለሱ፤ እነሆ፣ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ፤ ቃሌን አስተምራችኋለሁ።” (ከዮሐንስ 4:14 ጋር አወዳድር) ይሖዋ ከስሙና ከአምልኮቱ ጋር የተዛመድን እንደሆንን ራሳችንን ለማስተዋወቅ አዎንታዊ እርምጃዎችን ስንወስድ እርሱም በበኩሉ አስፈላጊውን ነገር እንደሚያደርግ ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! በእውነቱ በምሳሌ 1:24, 25 ላይ፦ “በጠራሁ ጊዜ እምቢ ስላላችሁ፣ እጄን በዘረጋሁ ጊዜ ማንም ስላላስተዋለ፣ ምክሬን ሁሉ ግን ቸል ስላላችሁ፣ ዘለፋዬንም ስላልፈቀዳችሁ” ከተባሉት ጋር ለመደመር አንፈልግም።
9 ይሖዋ ሊገኝ በሚችልበት ጊዜ እንዲፈልጉት የቀረበላቸውን ምክር ቸል የሚሉትና ታላቁ መከራ መጀመሩን እስኪያዩ ድረስ ራሳቸውን ሳይወስኑ የሚቆዩት ሁሉ ጊዜው እንዳለፈባቸው የሚገነዘቡበት ሰዓት ይመጣል። እንደዚህ ያለው አካሄድ የእምነትና የጥበብ መጉደል እንዳለ ያሳያል፤ የይሖዋን የማይገባ ደግነትም መናቅ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:1, 2
10. ፍላጎት አለመኖርና ግድየለሽነት አደገኛ የሆኑት ለምንድን ነው?
10 ፈጣን እርምጃ የመውሰድን አስፈላጊነት በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ሐኪሞች ለሳምባ ምች የሚሰጡትን ጥሩ ምክር የምትከተለው በሽታው በጣም ከባሰበት በኋላ ነውን? ወይስ የበሽታውን የመጀመሪያ ምልክት ስትመለከት ነው? እንግዲያው ራስህን ከበሽተኛው የሰይጣን ዓለም ለማላቀቅና ከይሖዋና ከምስክሮቹ ጎን ለመሰለፍ ለምን ትቆያለህ? ፍላጎት ማጣት፣ ግድየለሽነትና ቸልተኝነት የሚያስከትሏቸው ውጤቶች በምሳሌ 1:26-29 ላይ በግልጽ ቀርበዋል፦ “እኔም ስለዚህ በጥፋታችሁ እስቃለሁ፤ ጥፋታችሁም በመጣ ጊዜ አላግጥባችኋለሁ . . . የዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፣ እኔ ግን አልመልስም፤ ተግተው ይሹኛል፣ ነገር ግን አያገኙኝም። እውቀትን ጠልተዋልና፣ [ይሖዋንም (አዓት)] መፍራት አልመረጡምና።” ጊዜው ካለፈባቸው በኋላ ‘ይሖዋ ለመፈለግ ከሚነሱት’ መካከል አንሁን!
11. አምላክን ለማገልገል የሚፈልጉት ምን እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ?
11 ይህን መጽሔት ከሚያነቡት መካከል አንዳንዶቹ እውነተኛውን አምላክ በመፈለግ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ። ፍለጋችሁን ስለቀጠላችሁበት ደስ ይለናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኛችሁት እውቀት ለእውነት ጠንክራችሁ ለመቆም የሚያስችል ተጨማሪ አዎንታዊ እርምጃ እንድትወስዱ እንዲቀሰቅሳችሁ እንጸልያለን። እያንዳንዱ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ በምታደርጉት ምርምር እናንተን ለመርዳት ዝግጁ ሆኖ እንደሚጠብቅ እርግጠኞች ሁኑ።—ፊልጵስዩስ 2:1-4
ቅንዓት ማሳየትና እርምጃ መውሰድ የሚቻልበት ጊዜ
12, 13. እውነተኛውን አምልኮ በተመለከተ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
12 ከይሖዋና ከእውነተኛው አምልኮቱ ጎን መቆማችንን ለማሳየት ሁላችንም እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ምክንያቱም የዓለም ሁኔታዎች ወደ መጨረሻቸው በማምራት ላይ በመሆናቸው ነው። የታሪክ ገጾች ሰው አንብቦ ሳይጨርሳቸው በፍጥነት እየተገለበጡ ናቸው። አሁን ዳር የምንቆምበት ወይም ለብ ያልን የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። ኢየሱስ፦ “ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፣ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል” በማለት በግልጽ ተናግሯል። በተጨማሪም እንዲህ አለ፦ “በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል።”—ማቴዎስ 12:30፤ ሉቃስ 9:26
13 ቅንዓት ለማሳየትና እርምጃ ለመውሰድ ጊዜው አሁን ነው። የዓለም ሁኔታዎች ወዴት አቅጣጫ እያመሩ እንዳሉ እናውቃለን፤ አርማጌዶንም ዳር ዳር እያለ ነው። ስለዚህም አሁን የቀረበው ጥሪ ‘ከቁጣው ቀን’ በፊት ይሖዋ ሊገኝ በሚችልበት ጊዜ አሁንኑ ፈልጉት የሚል ነው። ታላቁ መከራ ከጀመረ ግን ዕድሉ ያልፍብናል።—ሶፎንያስ 2:2, 3፤ ሮሜ 13:11, 12፤ ራእይ 16:14, 16
14. አምላክን የምንፈልግባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
14 በእርግጥም የሰው ዘር የአምላክን ሞገስ አሁን መፈለግ ይኖርበታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን በሥራ 17:26-28 ላይ በትክክል ገልጾታል፦ “ምናልባት እየመረመሩ ያገኙት እንደሆነ፣ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ፣ የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ሥፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። . . . በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።” ይህ በመጨረሻ ላይ የተገለጸው “በእርሱ ሕያዋን ነንና እንኖርማለን” የሚለው አባባል አምላክን ለመፈለግ በቂ ምክንያት ይሆነናል። ይሖዋ ላሳየን የማይገባ ደግነት ምስጋና ይድረሰውና በዚህች ምድር ላይ በሚገኘው ጠባብ፣ ነገር ግን አስፈላጊ በሆነ አካባቢ ውስጥ እንኖራለን። ታዲያ የጽንፈ ዓለሙን የበላይ ገዥ ልናመሰግን አይገባንምን? ምስጋናችንንስ ተግባራዊ በሆኑ መንገዶች መግለጽ አይገባንምን?—ሥራ 4:24
15. (ሀ) የታሪክ ምሁር የሆኑት አርኖልድ ቶይንቢ የአንድ ትልቅ ሃይማኖት ዓላማ ምን መሆን እንዳለበት ተናገሩ? (ለ) አምላክን ለማክበር እንድንችል ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 የታሪክ ምሁር የሆኑት አርኖልድ ቶይንቢ አንድ ጊዜ እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር፦ “ከፍተኛ የአቋም ደረጃ ያለው ሃይማኖት እውነተኛ ዓላማው የቆመላቸውን መንፈሳዊ ምክሮችና እውነቶች በተቻለ መጠን በብዙ ነፍሳት ውስጥ መርጨት ነው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት እነዚህን ነፍሳት የሰውን እውነተኛ የመጨረሻ ዓላማ ለመፈጸም እንዲያስችላቸው ነው። የሰው እውነተኛ የመጨረሻ ዓላማ አምላክን ማክበሩና በእርሱ ለዘላለም እየተደሰቱ መኖር ነው።” (አንድ ታሪክ ጸሐፊ ለሃይማኖት ያለው አመለካከት ገጽ 268-9) አምላክን ለማክበር በመጀመሪያ እርሱን መፈለግና ስለ እርሱና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይኖርብናል። ስለዚህ ኢሳይያስ ያቀረበው ቀጥሎ ያለው ጥሪ ተገቢ ነው፦ “[ይሖዋ (አዓት)] በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ስለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ [ይሖዋም (አዓት)] ይመለስ እርሱም ይምረዋል፣ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።”—ኢሳይያስ 55:6, 7
ተግባራዊ የሆነ ምን እርዳታ መስጠት እንችላለን?
16. (ሀ) የክርስቲያን ጉባኤ ሊወጣው የሚገባው ምን ታላቅ ሥራ ከፊቱ ተደቅኖበታል? (ለ) ሌሎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ በምን ተግባራዊ መንገዶች ልንረዳቸው እንችላለን?
16 በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ለእውነት ፍላጎት ያሳዩ ነገር ግን ገና ንቁ አስፋፊዎች ያልሆኑ ሰዎች ለሁላችንም አንድ ልንወጣው የሚገባ ትልቅ ሥራ ከፊታችን ደቅነውብናል። ሽማግሌ፣ ዲያቆን፣ አቅኚ ወይም አስፋፊ በመሆናችን ባለን ኃላፊነት እነዚህ እውነትን የሚወዱ ሰዎች በእውነተኛው አምልኮ ከእኛ ጋር ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ለመርዳት ምን ተግባራዊ ነገር ልናደርግ እንችላለን? አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተግባራዊ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችለን አንዱ መንገድ ወደ ቤታቸው በመሄድ በመንግሥት አዳራሹ ወደሚደረጉት ስብሰባዎች እነርሱን መውሰድ ነው። ይህም እነርሱም ጭምር ዘወትር የይሖዋ መንፈስ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ጳውሎስ ለዕብራውያን በምዕራፍ 10 ቁጥር 24 እና 25 ላይ የሰጠው ምክር የዚያን ጊዜ ያህል ዛሬም አጣዳፊ እርምጃ መውሰድን የሚጠይቅ ነው፦ “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህንን አድርጉ።” የይሖዋን በጎ ፈቃድ ለመቅመስ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ በአካባቢያቸው በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር አዘውትረው እንዲሰበሰቡ እናበረታታቸዋለን።
17. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋን እንዲያገኙ እንድንረዳቸው ከተፈለገ የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?
17 አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ የሚገኝን አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው ከሆነ ይህ ሰው የምሥራቹ አስፋፊ እንዲሆን ልንረዳው እንችላለንን? (አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት፣ ገጽ 51-52 ተመልከት) እርሱ ወይም እርስዋ አንድ ጊዜ ያልተጠመቁ አስፋፊ ከሆኑ በኋላ ለሕዝብ ወደሚደረገው የስብከት ሥራ አብረውን እንዲሄዱና በአንዳንድ ጥናቶቻችንና ተመላልሶ መጠይቃችን ላይ እንዲገኙ ግብዣ እናቀርብላቸዋለንን? (23-110 መጠበቂያ ግንብ ዕትም ገጽ 31 ተመልከት) በሌላ አባባል እነዚህ ሰዎች ብቃቱን ሲያሟሉ በመጀመሪያ ከስብከት ሥራችን የምናገኛቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ውጤቶች እንዲያዩ በማድረግ እናበረታታቸዋለንን?—ማቴዎስ 28:19, 20
ይሖዋ ሊፈለግ የሚገባው ነው
18. ይሖዋ ለሰው ዘር ምሕረቱን ያሳየው እንዴት ነው?
18 የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት ስላለ ንስሐ ከገባንና ካመንን ይሖዋ ያለፈ ኃጢአታችንን በመቁጠር ችላ ብሎ አይተወንም። ዳዊት የተናገረውን ቃል ልብ በሉ፦ “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ [ይሖዋን (አዓት)] ለሚፈሩት ይራራል፤ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ።”—መዝሙር 103:10-14፤ ዕብራውያን 10:10, 12-14
19. ከእውነት ተንሸራተው ላሉት ምን ማበረታቻ አለላቸው?
19 ይሖዋ በእርግጥም መልካም የሚያደርግ መሐሪ አምላክ ነው። በትሕትናና ንስሐ በመግባት ወደ እርሱ ከቀረብን ይቅር ይለናል፣ በደላችንንም ይረሳዋል። የማያቋርጥ የሲኦል ስቃይ የሚያስከትል ዘላለማዊ ቂም አይዝብንም። ነገሩ በፍጹም እንደዚያ አይደለም ምክንያቱም “መተላለፍህን፦ ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም” ብሎ የተናገረው ይሖዋ ነው። ይህ ሁኔታ ከእውነት ለተንሸራተቱትና ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ችላ ላሉት እንዴት ያለ ማበረታቻ ነው! እነርሱም ጭምር አሁንኑ ይሖዋን እንዲፈልጉና በስሙ ከሚጠሩት ሕዝቦቹ ጋር ተመልሰው በትጋት እንዲተባበሩ እናበረታታቸዋለን።—ኢሳይያስ 43:25
20, 21. (ሀ) በጥንትዋ ይሁዳ ውስጥ ምን የሚያበረታታ ምሳሌ እናገኛለን? (ለ) የይሁዳ ነዋሪዎች የይሖዋን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ ነበረባቸው?
20 ይህን በተመለከተ በጥንት ይሁዳ የነበረው ንጉሥ አሳ የሚያበረታታ ምሳሌ ይሆነናል። እርሱ ከመንግሥቱ የሐሰት አምልኮትን አጥፍቶ ነበር፤ ሆኖም የአረመኔዎች አምልኮት ርዝራዥ ቀርቶ ነበር። በ2 ዜና መዋዕል 15 ቁጥር ከ2 እስከ 4 ላይ የሚገኘው ታሪክ ነቢዩ ዓዛሪያስ አሳን ለማሳሰብ የተናገረውን ይገልጽልናል፦ “እናንተ [ከይሖዋ (አዓት)] ጋር ስትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ነው፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፣ . . . ይኖሩ ነበር። በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት።”
21 ይሖዋ ፈልገህ አግኘኝ በማለት ከንጉሥ አልተደበቀም። ‘ተገኝቶለታል።’ ንጉሡ ይህን መልዕክት ሲሰማ ምን እርምጃ ወሰደ? በዚሁ ምዕራፍ ከቁጥር 8 እስከ 12 ላይ መልሱን እናገኛለን፦ “አሳም ይህን ቃል . . . በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፣ (ከአገሩ) ሁሉ . . . ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ [በይሖዋም (አዓት)] ቤት ፊት የነበረውን [የይሖዋን (አዓት)] መሠዊያ አደሰ። በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ [ይሖዋን (አዓት)] ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ።” አዎን “በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው” ይሖዋን ተግተው ፈለጉት። ይህስ ለሕዝቡ ምን ነገር አመጣላቸው? ቁጥር 15 መልሱን ይሰጠናል፦ “በፍጹም ልባቸው ምለዋልና፣ በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፣ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ [ይሖዋም (አዓት)] በዙሪያቸው ዕረፍት ሰጣቸው።”
22. በይሖዋ አገልግሎት ንቁ ተሳታፊዎች እንድንሆን የሚያበረታታን ምንድን ነው?
22 ይህ ታሪክ አሁን ሁላችንም የይሖዋን ንጹህ አምልኮ በተመለከተ ግልጽ የሆነ እርምጃ እንድንወስድ ማበረታቻ የሚሆነን አይደለምን? ይሖዋን የሚያወድሱ ብዙ ሰዎች ገና ሊመጡ እንደሚችሉ እናውቃለን። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ለይሖዋ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ለማሟላት በአኗኗራቸው ለውጦችን እያደረጉ እንደሆኑ አያጠራጥርም። ሌሎቹም በማስተዋልና በእምነት እያደጉ ናቸው፤ በቅርቡም ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን ጥልቅ የእውነት እውቀት ለሌሎች በማስተላለፍ ንጹሑን ልሳን ለሌሎች ለማስታወቅ በቅርቡ መነሳሳታቸው አይቀርም። ሁላችንም ይሖዋ ሊገኝ በሚችልበት ጊዜ ልንፈልገው የሚገባን ለምንድን ነው? ምክንያቱም አመጣላችኋለሁ በማለት ቃል የገባልን የእርሱ አዲስ ዓለም መምጫው ደርሷል።—ኢሳይያስ 65:17-25፤ ሉቃስ 21:29-33፤ ሮሜ 10:13-15
ታስታውሳለህን?
◻ ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ የግድየለሽነት መንፈስ የሚያሳዩት እነማን ናቸው?
◻ ብዙውን ጊዜ ሃይማኖት የአንድን ሰው አኗኗር እስከ ምን ድረስ ይነካዋል?
◻ የንቁ ምስክሮች ቁጥር ለመጨመር የመቻሉ ሁኔታ እንዴት ነው?
◻ ያሁኑ ጊዜ ቅንዓት ለማሳየትና እርምጃ ለመውሰድ ተገቢ ጊዜ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ይሖዋ ሊፈለግ የሚገባው ለምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ ያለው ሥዕል]
በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚወዱ ብዙ ሰዎች የአምላክ አገልጋዮች ለመሆን የሚችሉ ናቸው
የ1990 የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች፦ 9,950,058
የ1990 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር፦ 4,017,213
[በገጽ 12 ላይ ያለው ሥዕል]
በንጉሥ አሣ ዘመን ሕዝቡ ወደ ይሖዋ ተመለሰ