ከሐሰት ሃይማኖት መላቀቅ
“‘ከመካከላቸው ውጡ። . . .’ርኩስንም አትንኩ ይላል ይሖዋ . . . ‘እኔም እቀበላችኋለሁ።’”—2 ቆሮንቶስ 6:17
1. ሰይጣን ከኢየሱስ ጋር ምን ውል ለማድረግ ሞክሮ ነበር? ይህንን ስጦታ ማቅረቡስ ምን ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል?
“ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ።” ይህ ስጦታ የቀረበው የሐሰት ሃይማኖት ከጀመረ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ካለፉ በኋላ ቢሆንም ከሐሰት አምልኮ በስተጀርባ ያለው ማን እንደሆነና ዓላማውም ምን እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችል ፍንጭ ይሰጠናል። በ29 እዘአ ማብቂያ ላይ ሰይጣን ለኢየሱስ አንድ ጊዜ ቢሰግድለት የዓለምን ሁሉ መንግሥታት እንደሚሰጠው ሐሳብ አቅርቦለት ነበር። ይህ ታሪክ ሁለት ነገሮችን ይነግረናል፦ ሰይጣን ለስጦታ ያቀረባቸው የዚህ ዓለም መንግሥታት የሰይጣን መሆናቸውንና የሐሰት ሃይማኖት የመጨረሻው ዓላማ የዲያብሎስ አምልኮ መሆኑን ነው።—ማቴዎስ 4:8, 9
2.በማቴዎስ 4:10 ላይ ካሉት የኢየሱስ ቃላት ምን እንማራለን?
2 ኢየሱስ በሰጠው መልስ የሐሰት ሃይማኖትን ከመቃወሙም በላይ እውነተኛ ሃይማኖት ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል አመልክቷል። እንዲህ አለ፦ “ሄድ አንተ ሰይጣን ለይሖዋ ስገድ እሱንም ብቻ አምልክ ቅዱስ አገልግሎትህን ለእሱ ብቻ አቅርብ ተብሎ ተጽፏልና።” (ማቴዎስ 4:10) እንግዲያው የእውነተኛ ሃይማኖት ዓላማ የአንዱ እውነተኛ አምላክ የይሖዋ አምልኮ ነው። እሱም እምነትን፣ ታዛዥነትንና የይሖዋን ፈቃድ ማድረግን ይጠይቃል።
የሐሰት ሃይማኖት ምንጭ
3. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖት በምድር ላይ የጀመረው መቼና እንዴት ነው?(ለ) በታሪክ መዝገብ የመጀመሪያው የሆነው ሃይማኖታዊ ተቃውሞ የትኛው ነው? ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ስደት የቀጠለው እንዴት ነው?
3 የሐሰት ሃይማኖት በምድር ላይ የጀመረው የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የአምላክን ትዕዛዝ ጥሰው “መልካሙንና ክፉውን” ለራሳቸው እንዲወስኑ እባቡ ያቀረበላቸውን ሐሳብ በተቀበሉት ጊዜ ነው። (ዘፍጥረት 3:5) እንዲህ በማድረጋቸውም የይሖዋን ጻድቅ የበላይ ገዥነት ተቃውመዋል፣ እውነተኛ ሃይማኖት የሆነውን ትክክለኛ አምልኮም ትተዋል። “የአምላክን እውነት በውሸት ለመለወጥና በፈጣሪም ፋንታ የተፈጠረውን ለማምለክና ለማገልገል” የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ሆኑ። (ሮሜ 1:25) ሳያስቡት ለማምለክ የመረጡት ፍጡር “የቀድሞው እባብ” ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ሌላ ማንም አልነበረም። (ራእይ 12:9) የበኩር ልጃቸው ቃየንም የይሖዋን የደግነት ምክር ለመከተል እምቢ በማለት በበላይ ገዥነቱ ላይ አምጿል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ “የክፉው የሰይጣን ልጅ” በመሆን የዲያብሎስ አምላኪ ሆኗል። እውነተኛውን ሃይማኖት፣ እውነተኛውን አምልኮ ይከተል የነበረውን ታናሽ ወንድሙን አቤልን ገደለ። (1 ዮሐንስ 3:12፤ ዘፍጥረት 4:3-8፤ ዕብራውያን 11:4) የአቤል ደም በሃይማኖታዊ ተቃውሞ ምክንያት የፈሰሰ የመጀመሪያው ደም ሆኗል። የሐሰት ሃይማኖት እስከ ዘመናችን ድረስ ንጹሕ ደም ማፍሰሱን አለማቆሙ ያሳዝናል።— ማቴዎስ 23:29-35፤ 24:3, 9ን ተመልከት
4. በኖህ ረገድ የእውነተኛ ሃይማኖትን ባሕርይ የሚገልጹት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
4 ከጥፋት ውኃ በፊት ሰይጣን አብዛኛውን የሰው ዘር ከእውነተኛ ሃይማኖት ዘወር ለማድረግ ተሳክቶለታል። ይሁን እንጂ ኖህ “በይሖዋ ፊት ሞገስን አገኘ።” ለምን? ‘አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር ስላደረገ’ ነበር። በሌላ አባባል በእውነተኛው አምልኮ ተመላልሷል ማለት ነው። እውነተኛ ሃይማኖት የአምልኮ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የሕይወት መንገድ ነው። በይሖዋ ማመንንና እሱን በታዛዥነት ማገልገልን፣ “አካሄዱን ከእርሱ ጋር ማድረግን” ይጨምራል። ኖህ ያደረገው ይህንን ነበር። —ዘፍጥረት 6:8, 9, 22፤ 7:1፤ ዕብራውያን 11:6, 7
5. (ሀ) ዲያብሎስ ከጥፋት ውኃ በኋላ ለማቋቋም የሞከረው ምንን ነው? እንዴትስ? (ለ) ይሖዋ የዲያብሎስን ዕቅድ ያከሸፈው እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
5 ከጥፋቱ ውኃ በኋል ብዙም ሳይቆይ ዲያብሎስ ይሖዋን በሚቃወም የአምልኮ ዓይነት የሰው ዘሮችን ሁሉ እንደገና ለማስተባበር ባደረገው ጥረት “ይሖዋን በመቃወም” የታወቀ ሰው የነበረውን ናምሩድን እንደተጠቀመ በግልጽ ሊታይ ይችላል። (ዘፍጥረት 10:8, 9፤ 11:2-4) ይህም አምልኮ በከተማዋና አምላኪዎች በገነቡት ግንብ ላይ ያተኮረ አንድ የተባበረ የሐሰት ሃይማኖት፣ አንድነት ያለው የዲያብሎስ አምልኮ ሊሆን ነበር። ይሖዋ በሰው ይነገር የነበረውን “አንድ ቋንቋ” በመዘበራረቅ ይህን ዕቅድ አከሸፈው። (ዘፍጥረት 11:5-9) ስለዚህ በከተማዋ ባቤል በኋላም ባቢሎን የተባለች ሲሆን ሁለቱም ስሞች ትርጉማቸው መዘበራረቅ ማለት ነው። ይህም የቋንቋ መዘበራረቅ የሰው ዘሮች በምድር ሁሉ ላይ እንዲበታተኑ አድርጓል።
6. (ሀ) በባቢሎን የሰይጣን አምላኪዎች ከመበታተናቸው በፊት በውስጣቸው ምን ዓይነት ሃይማኖታዊ ሐሳቦች ሠርፀው ነበር? (ለ) በዓለም ዙሪያ ያሉ ሃይማኖቶች ተመሳሳይ እምነቶች ያሏቸው ለምንድን ነው?(ሐ) ባቢሎን ያገለገለችው ለምን ዓይነት ሰይጣናዊ ዓላማ ነው? ያቺ ጥንታዊት ከተማ የምን ምሳሌ ሆነች?
6 ይሁን እንጂ ከአፈታሪኮችና ከሃይማኖቶች ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው የሰው ዘሮች ከመበታተናቸው በፊት ሰይጣን በአምላኪዎቹ አእምሮ ውስጥ አንዳንድ የሐሰት ሃይማኖት መሠረታዊ ሐሳቦችን የተከለ ይመስላል። እነዚህ መሠረታዊ ሐሳቦችም ከሞት በኋላ የምትኖር ነፍስ አለች የሚለውን እምነት፣ ሙታንን መፍራትን፣ በምድር ከርስ ውስጥ የመቃጠያ ቦታ አለ ብሎ ማመንን፣ አንዳንዶቹ በሦስት በሦስት ቡድን የሚመለኩ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ብዙ አማልክትንና እንስት አማልክትን ማምለክን ይጨምራሉ። የተለያየ ቋንቋ መናገር የጀመሩት የሰው ልጆች በየቋንቋ ቡድናቸው እነዚህን እምነቶች ይዘው እስከ ምድር ዳርቻ ተሠራጩ። በጊዜ ብዛት እነዚህ መሠረታዊ ሐሳቦች እየተለያዩ መጡ። በጠቅላላው ሲታይ ግን በምድር ክፍሎች በሙሉ ያሉት ሃይማኖቶች የተገነቡት ከእነዚህ መሠረታዊ ሐሳቦች ነው። ሰይጣን ዋና ከተማው ባቢሎን የሆነ አንድ የተባበረ የሐሰት አምልኮ ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ ቢከሽፍበትም ባቢሎናዊ አነሳስ ያላቸውና አምልኮትን ከይሖዋ መልሶ ወደራሱ ለመውሰድ የታለሙ የተለያዩ የሐሰት አምልኮቶችን አደራጅቷል። ባቢሎን በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት የሐሰት አምልኮ ዋነኛ ክፍሎች የሆኑት የጣዖት አምልኮ፣ የአስማት፣ የጥንቆላና የከዋክብት ቆጠራ ማዕከል በመሆን ተደማጭነት ያላት ከተማ ሆና ኖራለች። የራእይ መጽሐፍ የዓለምን የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ታላቂቱ ባቢሎን በተባለች እርኩስ አመንዝራ መመሰሉ አያስደንቅም።—ራእይ 17:1-5
እውነተኛ ሃይማኖት
7. (ሀ) እውነተኛው ሃይማኖት በቋንቋ መዘበራረቅ ያልተነካው ለምን ነበር? (ለ) “ለሚያምኑት አባት” በመሆን የታወቀው ማነው?
7 በግልጽ እንደሚታየው ይሖዋ በባቢሎን የሰዎችን የመግባቢያ ቋንቋ ባዘበራረቀ ጊዜ እውነተኛው ሃይማኖት በዚህ መዘበራረቅ አልተነካም ነበር። ከጥፋት ውኃ በፊት እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ የኖኅ ሚስት፣ የኖኅ ልጆችና ምራቶችን የመሳሰሉት ወንዶችና ሴቶች እውነተኛውን አምልኮ ተከትለዋል። ከጥፋት ውኃ በኋላም እውነተኛው አምልኮ በኖኅ ልጅ በሴም የዘር ሐረግ ተጠብቆ ቀጥሏል። የሴም ዘር የሆነው አብርሃም እውነተኛውን አምልኮ ተከትሏል። ይህን በማድረጉም “ለሚያምኑት ሁሉ አባት” በመሆን የታወቀ ሰው ሆኗል። (ሮሜ 4:11) እምነቱ በሥራ የተደገፈ ነበር። (ያዕቆብ 2:21-23) ሃይማኖቱ የሕይወት ወይም የአኗኗር መንገድ ሆኖለት ነበር።
8. (ሀ) በ16 መቶ ዘመን ከዘአበ እውነተኛ ሃይማኖት ከሐሰተኛ ሃይማኖት ጋር የተጋጨው እንዴት ነበር? ምንስ ውጤት አስከተለ? (ለ) ይሖዋ ንጹሕ አምልኮውን በሚመለከት ምን አዲስ ዝግጅት ነበር?
8 የአብርሃም ዝርያዎች የሆኑት ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ (ወይም እሥራኤል) እና የአሥራ ሁለቱ የእሥራኤል ነገድ አባቶች የሆኑት አሥራ ሁለቱ የእሥራኤል (የያዕቆብ) ልጆች እውነተኛውን አምልኮ ተከትለዋል። በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የይስሐቅና የአብርሃም ዝርያዎች ጠላትና አረማዊ በሆነ አካባቢ በባርነት ይኖሩ በነበረበት በግብጽ ምድር እውነተኛ አምልኮትን ጠብቀው ለማቆየት መታገል ግዴታ ሆኖባቸው ነበር። ይሖዋ ከሌዊ ነገድ በሆነው በታማኝ ባሪያው በሙሴ ተጠቅሞ አምላኪዎቹን በሐሰት ሃይማኖት ከተዘፈቀችው ከግብጽ ቀንበር ነፃ አውጥቷል። ይሖዋ እሥራኤልን የራሱ ምርጥ ሕዝቦች በማድረግ በሙሴ በኩል ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ በዚያን ጊዜ በመጀመሪያ በተጓጓዥ ድንኳን ከቆየ በኋላ በኢየሩሳሌም በተሠራ ቤተመቅደስ ውስጥ በክህነት ሥርዓት አማካኝነት በሚፈጸም የመሥዋዕቶች ክልል ውስጥ አምልኮቱን በማቋቋም በጽሑፍ የተደነገገ አምልኮ እንዲኖረው አደረገ።
9. (ሀ) እውነተኛ አምልኮ ከሕጉ ቃል ኪዳን በፊት ይፈጸም የነበረው እንዴት ነው? (ለ) የሕጉ አካላዊ ገጽታዎች ዘላቂ እንዳልነበሩ ኢየሱስ ያሳየው እንዴት ነበር?
9 ይሁን እንጂ እነዚህን ግዑዛን የሆኑ የአምልኮ ገጽታዎች የእውነተኛ ሃይማኖት ክፍል ሆነው ለሁልጊዜ እንዲቀጥሉ የታሰቡ አልነበሩም። ሕጉ “ሊመጡ ያሉ ነገሮች ጥላ” ነበር። (ቆላስይስ 2:17፤ ዕብራውያን 9:8-10፤ 10:1) ከሙሴ ሕግ አስቀድሞ በአበው ዘመን የቤተሰብ ራሶች በሠሩአቸው መሠዊያዎች ላይ መሥዋዕቶች ያቀርቡ የነበረው ቤተሰቦቻቸውንም ወክለው እንደነበር ግልጽ ነው። (ዘፍጥረት 12:8፤ 26:25፤ 35:2, 3፤ ኢዮብ 1:5) ነገር ግን የተወሰኑ ሥነ ሥርዓቶች ወይም ቅዳሴዎች ያሉት የተደራጀ የክህነት ወይም የመሥዋዕት ሥርዓት አልነበረም። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ራሱ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት “በዚህ ተራራ (ቀድሞ የሳምራውያን ቤተ መቅደስ የነበረበት ቦታ በነበረው የጌሪዚም ተራራ) ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። . . . ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፣ አሁንም ሆኗል።” ብሎ በነገራት ጊዜ ማዕከሉ በኢየሩሳሌም የነበረውን በጽሑፍ የተደነገገ አምልኮት ጊዜያዊ ባሕርይ ገልጾአል። (ዮሐንስ 4:21-23) ኢየሱስ የእውነተኛ ሃይማኖት አምልኮ መፈጸም ያለበት በሚታዩ ነገሮች ሳይሆን በመንፈስና በእውነት መሆኑን ገልጿል።
ባቢሎናዊ ምርኮ
10. (ሀ) ይሖዋ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን ምርኮ እንዲወስዱ የፈቀደው ለምን ነበር? (ለ) ይሖዋ ታማኝ ቀሪዎቹን በ537 ከዘአበ ነፃ ያወጣቸው በምን ሁለት መንገዶች ነበር? ወደ ይሁዳ የተመለሱበት ዋን ዓላማስ ምን ነበር?
10 በኤደን ከተነሣው አመጽ በኋላ በእውነተኛና በሐሰተኛ ሃይማኖቶች መሃል የማያቋርጥ ጠላትነት ተፈጠረ። አንዳንድ ጊዜ እውነተኛ አምላኪዎች ከናምሩድ ዘመን ጀምሮ በምሳሌያዊ ሁኔታ የባቢሎን አምሳያ የሆነችው የሐሰት ሃይማኖት ምርኮኞቹ የሆኑበት ጊዜ ነበር። ይሖዋ ሕዝቡ በ617 ከዘአበ እና በ607 ከዘአበ ወደ ባቢሎን እንዲማረኩ ከመፍቀዱ በፊት እንኳ በባቢሎናዊ ሐሰት ሃይማኖቶች ተሸንፈው ነበር። (ኤርምያስ 2:13-23፤ 15:2፤ 20:6፤ ሕዝቅኤል 12:10, 11) ታማኝ ቀሪዎች በ537 ከዘአበ ወደ ይሁዳ ተመለሱ። (ኢሳይያስ 10:21) “ከባቢሎን ውጡ!” የሚለውን ትንቢታዊ ጥሪ ተቀብለው ነበር። (ኢሳይያስ 48:20) በዚያ ጊዜ ያገኙት ነፃነት ሥጋዊ ብቻ አልነበረም። እርኩስ ከሆነና ጣዖት አምልኮ ከተስፋፋበት የሐሰት ሃይማኖት አካባቢ መውጣታቸው መንፈሳዊ ነፃነት ነበር። እነዚህ ታማኝ ቀሪዎች “እናንተ የይሖዋን ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ እልፍ በሉ፤ እልፍ በሉ ከዚያ ውጡ ርኩስንም አትንኩ። ከመካከሏ ውጡ። ንጹሐን ሁኑ” የሚለውን ትዕዛዝ ፈጽመዋል። (ኢሳይያስ 52:11) ወደ ይሁዳ የተመለሱበት ዋና ዓላማ ንጹሕ አምልኮ የሆነውን እውነተኛ ሃይማኖት እንደገና ማቋቋም ነበር።
11. በይሁዳ ምድር ንጹሕ አምልኮ ከመመለሱ በተጨማሪ በ6ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ምን አዳዲስ ሃይማኖታዊ ዕድገቶች ተፈጸሙ?
11 በዚያው በ6ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የሐሰት ሃይማኖት በታላቂቱ ባቢሎን ውስጥ አዳዲስ ዘርፎች ማውጣቱን ልናስተውለው ይገባናል። ቡዲሂዝም፣ ኮንፊሺያኒዝም፣ ዞራስትሪያንዝምና ጃይኒዝም የተባሉት ሃይማኖቶች ተወለዱ። ከእነዚህም በተጨማሪ የኋላ ኋላ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተደማጭነት ያገኘው የግሪክ የምርምር ፍልስፍና ያን ጊዜ መስፋፋት ጀምሯል። ስለዚህ ንጹሕ አምልኮ በይሁዳ ተመልሶ ሲቋቋም የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ሠፊ የሆነ የሐሰት ሃይማኖት አማራጮችን ማቅረብ ጀምሮ ነበር።
12. በአንደኛው መቶ ዘመን እዘአ ከባቢሎናዊ ምርኮኛነት ምን ዓይነት ነፃነት ተገኘ? ጳውሎስስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?
12 ኢየሱስ በእሥራኤል በተገለጠበት ወቅት አብዛኞቹ አይሁዳውያን ብዙ ባቢሎናዊ የሃይማኖት ጽንሰ ሐሳቦችን የወረሰ ልዩ ልዩ ዓይነት አይሁዳዊነትን ይከተሉ ነበር። አይሁዳዊነት የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ሆኖ ነበር። ክርስቶስም ይህን በማውገዝ ደቀመዛሙርቱን ከባቢሎናዊ ባርነት ነፃ አወጣቸው። (ማቴዎስ ምዕራፍ 23፤ ሉቃስ 4:18) ሐዋርያው ጳውሎስ በሰበከባቸው ቦታዎች ሁሉ የሐሰት ሃይማኖትን የግሪክ ፍልስፍና ተንሰራፍቶ ስለነበር የኢሳይያስን ትንቢት ጠቅሶ ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን ርኩስ ተጽእኖ መጠበቅ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስቧል፣ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቀደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል፦ በእነርሱ አኖራለሁ። በመካከላቸውም እመላለሳለሁ። አምላካቸውም እሆናለሁ። እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። ስለዚህም ጌታ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ። ርኩስንም አትንኩ ይላል ሁሉንም የሚገዛ ጌታ።”—2 ቆሮንቶስ 6:16, 17
በፍጻሜው ዘመን ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ መውጣት
13. ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሹ እስያ ወደሚገኙ ሰባት ጉባኤዎች የላከው መልእክት ምን ያመለክታል? በዚህስ ምክንያት ምን ነገር ብቅ ማለት ጀምሯል?
13 ክርስቶስ ለሐዋርያው ዮሐንስ በሰጠው ራእይ አማካኝነት በትንሹ እስያ ለሚገኙ ለሰባቱ ጉባኤዎች የላከው መልእክት በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ባቢሎናዊ የሃይማኖት ልማዶችና ዝንባሌዎች ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልከው በመግባት ላይ እንደነበሩ በግልጽ ያመለክታል። (ራእይ ምዕራፍ 2 እና 3) ንጹሑን የክርስትና ሃይማኖት የሚመስል ብልሹ አስመሳይ ሃይማኖትን ያስከተለው ክህደት በተለይ ከሁለተኛው መቶ ዘመን እስከ 5ኛው መቶ ዘመን ድረስ አበበ። የነፍስ አለመሞት፣ የመቃጠያ ሲኦል፣ ሥላሴና የመሳሰሉትን ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶች ወደ ክህደቱ ክርስትና ሰርገው ገቡ። የካቶሊክ፣ የኦርቶዶክስና በኋላም የፕሮቴስታን አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ትምህርቶች ወረሱና የዲያብሎስ ዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው የታላቂቱ ባቢሎን ክፍል ሆኑ።
14, 15. (ሀ) የኢየሱስ የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ ምን አሳይቷል? (ለ) በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ምን ተፈጸመ? በ1914 እውነተኛ ክርስቲያኖች በመሠረተ ትምህርት ረገድ ምን መሻሻል አደረጉ?
14 እውነተኛ ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ የጠፋበት ጊዜ አልነበረም። ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ለይሖዋና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ላላቸው ታማኝነት ሲሉ ሕይወታቸውን የከፈሉ የእውነት አፍቃሪዎች ነበሩ። ነገር ግን የኢየሱስ የስንዴና የእንክርዳድ ምሳሌ እንደሚያሳየው ምሳሌያዊው ስንዴ ወይም የመንግሥቲቱ ቅቡዓን ልጆች “በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ላይ ከእንክርዳዱ ወይም ከክፉው ልጆች መለየት ነበረባቸው። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) የፍጻሜው ዘመን ማለትም ይህ የመለየት ሥራ መፈጸም የሚኖርበት ጊዜ ሲቀርብ ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ19ኛው መቶ ዘመን የመጨረሻ ላይ ከሐሰት ሃይማኖት ባርነት ነፃ መውጣት ጀመሩ።
15 በ1914 ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት እነዚህ ክርስቲያኖች በቤዛው ላይ ጠንካራ እምነት አሳድረው ነበር። የክርስቶስ መገኘት የማይታይ መሆን እንዳለበት አውቀው ነበር። “የአሕዛብ ዘመን” በ1914 እንደሚፈጸም ተረድተው ነበር። (ሉቃስ 21:24) የነፍስንና የትንሳኤን ትርጉም በግልጽ ተረድተዋል። አብያተ ክርስቲያናት ስለ ሲኦል እሳትና ስለ ሥላሴ የሚያስተምሩት ሁሉ ስሕተት መሆኑን ተገንዝበዋል። መለኮታዊውን ስም አውቀው በስሙም መጠቀም ጀምረዋል። እንዲሁም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብና የመናፍስትነት ሥራ ስሕተት መሆኑን ተገንዝበዋል።
16. በ1919 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለምን ጥሪ ምላሽ ሰጡ?
16 ከሐሰት ሃይማኖት እግር ብረት ለመውጣት የሚያስችል ጥሩ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በ1919 ታላቂቱ ባቢሎን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የነበራትን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ አጣች። የአይሁድ ቀሪዎች በ537 ከዘአበ ከባቢሎን ነፃ እንደወጡ ሁሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም “ከባቢሎን እንዲወጡ” የተሰጣቸውን ጥሪ ተቀበሉ።—ኢሳይያስ 52:11
17. (ሀ) ከ1922 ወዲህ የተስፋፋው ምንድነው? በአምላክ ሕዝቦች ዘንድ ምን እንደሚያስፈልግ ታወቀ? (ለ) ምን የከረረ አቋም ነበር የተወሰደው? ይህስ በቂ ምክንያት የነበረው ለምንድን ነው?
17 ከ1922 ወዲህ ባቢሎናዊውን የሐሰት ሃይማኖት፣ በተለይም የሕዝበ ክርስትናን አብያት ክርስቲያናት የሚያጋልጡ ኃይለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መታተምና በይፋ መሠራጨት ጀመሩ። የአምላክ ሕዝቦች ከማንኛውም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ የመለየት አስፈላጊነት ተሰማቸው። ስለዚህ ለበርካታ ዓመታት ስለንጹሕ አምልኮ በሚናገሩበት ጊዜ “ሃይማኖት” የሚለው ቃል እንኳን መጠቀም ትተው ነበር። በታላላቅ ከተሞች መሃል “ሃይማኖት ወጥመድ ነው” የሚሉ መፈክሮች ይዘው በሠልፍ ተዘዋውረዋል። መንግሥት (1928) እና “እውነት ነፃ ያወጣችኋል” (1943) የተሰኙ መጻሕፍት “በክርስትናና” በሃይማኖት መሃል ያለውን ልዩነት በግልጽ አስረድተው ነበር። በጣም ተስፋፍተው ከሚገኙት የታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ መውጣት ያስፈልግ ስለነበረ ይህን የመሰለ የከረረ አቋም መያዛቸው በቂ ምክንያት ነበረው።
እውነተኛና ሐሰተኛ ሃይማኖት
18.በ1951 ምን አዲስ የ “ሃይማኖት” ዕውቀት ነበር የተሰጠው? ይህስ በ1975 የዓመት መጽሐፍ ላይ የተገለጸው እንዴት ነው?
18 ከዚያም በ1951 ይሖዋ ለሕዝቡ በእውነተኛ ሃይማኖትና በሐሰተኛ ሃይማኖት መሃል ያለው የጠራ ልዩነት ግልጽ እንዲሆን የሚያደርግበት ጊዜ ደረሰ። የ1975 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ እንዲህ በማለት ዘግቧል፦ “በ1951 የእውነተኛ አምልኮ ጠበቆች ‘ሃይማኖት’ ስለሚለው ቃል አንድ ቁም ነገር አወቁ። አንዳንዶቻቸው በ1938 “ሃይማኖት ወጥመድ ነው” የሚለውን ትኩረት የሚስብ ጽሑፍ ይዘው ይዞሩ እንደነበረ በደንብ ያስታውሱ ነበር። በዚያ ጊዜ በነበረው አስተሳሰብ መሠረት ሁሉም “ሃይማኖት” ክርስቲያናዊ ያልሆነ የዲያብሎስ መሣሪያ ነበር። የመጋቢት 1951 መጠበቂያ ግንብ ግን ሃይማኖትን በሚመለከት “እውነተኛ” እና “ሐሰተኛ” የሚሉትን ቅጽሎች ጨምሮ መጠቀም እንደሚቻል ገለጸ። ከዚህም በላይ በ1951 የታተመውን በእንግሊዝ አገር ሎንዶን በዌምብሌይ እስታዲየም በተደረገው የ“ንጹህ አምልኮ” ስብሰባ ላይ የወጣው ሃይማኖት ለሰው ልጅ ምን አድርጎለታል? የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይል ነበር፦ “ሃይማኖት” የሚለው ቃል በቃሉ አጠቃቀም መሠረት ሲታይ ተራ ፍቺው እውነተኛም ይሁን ሐሰተኛ አምልኮን የማይለይ የአምልኮ ሥርዓት ወይም የአምልኮ መልክ ማለት ነው። ይህም ‘አቦህዳህ’ ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ትርጉም ጋር ይስማማል። የዚህ ቃል ትርጉም “አገልግሎት” ማለት ሲሆን አገልግሎቱ የሚቀርብለትን ክፍል አይለይም። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ‘የሐሰት ሃይማኖት’ የሚሉት ቃላት በይሖዋ ምሥክሮች መሃል የተለመዱ ሆኑ።”—ገጽ 225
19, 20. (ሀ) እውነተኛ አምላኪዎች ለንጹሕ አምልኮታችን “ሃይማኖት” የሚለውን ቃል በመጠቀማችን መበሳጨት የሌለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ይህ አዲስ እውቀት የይሖዋን ሕዝቦች ምን እንዲያደርጉ አስችሏል?
19 የነሐሴ 15, 1951 መጠበቂያ ግንብ ዕትም ለአንባቢዎች ጥያቄ መልስ ሲሰጥ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “‘ሃይማኖት’ የሚለውን አጠራር በመጠቀማችን ማንም ሰው መናደድ አይገባውም። ምክንያቱም ራሳችንን ክርስቲያን ብለን መጥራታችን ከሕዝበ ክርስትና የሐሰት ክርስቲያኖች ጋር እንደማያስመድበን ሁሉ ሃይማኖት በሚለው ቃል መጠቀማችንም በወግ ከተተበተቡት የሐሰት ሃይማኖቶች ጋር አያስመድበንም።”
20 “ሃይማኖት” የሚለውን ቃል በዚህ መንገድ መረዳት የአቋም ለውጥ ማድረግ ሳይሆን ቀጥሎ የምንመለከተው ርዕሰ ትምህርት እንደሚያሳየው በእውነተኛና በሐሰተኛ አምልኮት መሃል ያለውን ትልቅ ገደል የይሖዋ ሕዝቦች እንዲያስተውሉ አስችሏቸዋል።
መረዳታችንን ለመፈተን
◻ የሐሰት ሃይማኖት በምድር ላይ የጀመረው መቼና እንዴት ነው?
◻ ሰይጣን ከጥፋት ውኃ በኋላ ለማቋቋም የሞከረው ምንድን ነው? ዕቅዱስ የከሸፈው እንዴት ነው?
◻ ባቢሎን የምን ምሳሌ ሆነች?
◻ በ537 ከዘአበ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ እና በ1919 ምን ዓይነት ነፃነት ተገኘ?
◻ 1951 “ሃይማኖት” የሚለውን ቃል በምን መንገድ መረዳት ተቻለ? በዚያ ጊዜ የሆነውስ ለምንድን ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በዓለም ዙሪያ የሚታመኑ የሐሰት መሠረተ ትምህርቶች ሁሉ የመነጩት ከባቢሎን ነው። እነርሱም
◻ ሥላሴዎች ወይም ሦስት አካላት ያሉበት የአማልክት ቡድኖች
◻ የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት
◻መናፍስትነት፣—“ከሙታን” ጋር መነጋገር
◻ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም፣ አስማቶች ወይም መተቶች
◻ አጋንንትን ለመለማመን የሚደረጉ ሥርዓቶች
◻ በቀሳውስት ሥልጣን መገዛት