የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 11/15 ገጽ 31
  • ከውጭ የሚታይ መልክ ሊያታልል ይችላል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከውጭ የሚታይ መልክ ሊያታልል ይችላል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 11/15 ገጽ 31

ከውጭ የሚታይ መልክ ሊያታልል ይችላል

“ከውጭ የሚታይ መልክ አይታመንም” በማለት የአየርላንዱ ቲያትረኛ ሪቻርድ ሸሪዳን ተናግሯል። ይህ አባባል በዛፎችም ሆነ በሰዎች ላይ ይሠራል።

አንድ ቀን በ33 እዘአ ኢየሱስ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ አንዲት የበለስ ዛፍ ተመለከቱ። ዛፏ በጣም ለምልማ ትታይ ነበር፤ ቀርበው ሲያዩአት ግን ምንም ዓይነት ፍሬ የሌለባት ሆና አገኙአት። ስለዚህ ኢየሱስ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት።—ማርቆስ 11:12-14

ማርቆስ እንደገለጸው “የበለስ ወራት አልነበረም”፤ ታዲያ ኢየሱስ ዛፊቱን የረገማት ለምንድን ነው? (ማርቆስ 11:13) የበለስ ዛፍ ቅጠል ካለው ከጊዜው በፊት የሚደርስ ፍሬም እንደሚኖረው የተለመደ ነገር ነው። የበለስ ዛፍ በዚያ የዓመቱ ክፍል ቅጠል ማውጣቱ ያልተለመደ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ ቅጠል ስለነበረው ኢየሱስ ፍሬ ለማግኘት መጠበቁ ተገቢ ነበር። (ከላይ ያለውን ሥዕል ተመልከቱ።) ዛፉ ቅጠል ብቻ ማውጣቱ የማያፈራ መሆኑን ሊያመለክት ይችል ነበር። ከውጭ የሚታይ መልክ አታላይ ነበር። የሚያፈሩ ዛፎች ቀረጥ ይከፈልባቸው ስለነበር ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ኤኮኖሚያዊ ሸክም የሚያስከትል ስለነበር መቆረጥ ያስፈልገው ነበር።

ኢየሱስ ያችን ፍሬ የሌለባት የበለስ ዛፍ እምነትን የሚመለከት በጣም አስፈላጊ ትምህርት ለመስጠት ተጠቅሞባታል። ደቀ መዛሙርቱ በማግስቱ ያች ዛፍ ደርቃ ሲመለከቱ በጣም ተገረሙ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ “በእግዚአብሔር እመኑ። . . . የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፣ ይሆንላችሁማል” ብሏል። (ማርቆስ 11:22-24) የደረቀችው በለስ በእምነት የመጸለይን አስፈላጊነት ለማስረዳት ከማገልገሏም በላይ እምነት የጎደለው ሕዝብ ምን እንደሚደርስበት በጉልህ አመልክታለች።

ኢየሱስ ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ የአይሁድን ሕዝብ ለሦስት ዓመታት ምንም ፍሬ ያላፈራችና የማታፈራ ሆና ከቀረች መቆረጥ ካለባት የበለስ ዛፍ ጋር አመሳስሎአቸዋል። (ሉቃስ 13:6-9) ኢየሱስ ከመሞቱ ከአራት ቀናት አስቀድሞ በለሲቱን በመርገም የአይሁድ ሕዝብ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ እንዳላፈሩና በዚህም ምክንያት ለጥፋት መዘጋጀታቸውን አሳይቷል። እነዚያ ሕዝቦች እንደ በለሲቱ ከውጭ ሲታዩ ጤነኛ ቢመስሉም ቀረብ ተብሎ ሲታዩ ግን መሢሑን አንቀበልም በማለት የተደመደመውን የእምነት ማጣት አሳይተዋል።—ሉቃስ 3:8, 9

ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ስለ “ሐሰተኛ ነቢያት” ካስጠነቀቀ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” (ማቴዎስ 7:15-20) እነዚህ የኢየሱስ ቃላትና የተረገመችው የበለስ ፍሬ ታሪክ ሃይማኖታዊ መልክ አሳሳች ሊሆን ስለሚችል በመንፈሳዊ ረገድ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልገን በግልጽ ያሳያሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ