ይህ የማይቻል ነው!
“ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል።” (ማቴዎስ 19:24) ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የተናገረው ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርት ለመስጠት ብሎ ነበር። አንድ ሀብታም የሆነ ወጣት የሕዝብ መሪ የኢየሱስ ተከታይ እንዲሆንና በኋላም አስደናቂ መንፈሳዊ አጋጣሚዎች ተካፋይ እንዲሆን የቀረበለትን ግብዣ አልቀበልም ብሎ እንደተመለሰ የተናገረው ቃል ነው። ሰውየው መሢሑን ከመከተል ይልቅ ከብዙ ንብረቶቹ ጋር መጣበቅን መረጠ።
አንዳንድ ሀብታም ግለሰቦች የኢየሱስ ተከታዮች ሊሆኑ ስለቻሉ ኢየሱስ አንድ ሀብታም ሰው በመንግሥቱ ዝግጅት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ፈጽሞ ሊያገኝ አይችልም ማለቱ አልነበረም። (ማቴዎስ 27:57፤ ሉቃስ 19:2, 9) ይሁን እንጂ ከመንፈሳዊ ነገሮች ይልቅ ለንብረቱ የበለጠ ፍቅር ላለው ለማንኛውም ሀብታም ሰው የአምላክን መንግሥት መውረስ የማይቻል ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከአምላክ የሚያገኘውን መዳን ሊቀበል የሚችለው በመንፈሳዊ በኩል የሚያስፈልጉት ነገሮች ንቁ በመሆንና መለኮታዊ ድጋፍ ለማግኘት በመጣር ብቻ ነው።—ማቴዎስ 5:3፤ 19:16-26
የግመሊቱና የመርፌው ቀዳዳ ምሳሌ ቃል በቃል የሚወሰድ አይደለም። ኢየሱስ የሀብትና የፍቅረ ንዋይ አኗኗር እየተከተሉ አምላክንም ለማስደሰት የሚሞክሩ ሀብታም ሰዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር አጉልቶ ለመግለጽ የቃለ አጋኖ አገላለጽ መጠቀሙ ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 6:17-19
አንዳንድ ሰዎች የመርፌው ቀዳዳ አንድ ግመል ጭነቱ ከተራገፈለት በችግር ሊያልፍ የሚችልበት ትንሽ የከተማ በር ነው ብለው ይናገራሉ። በማቴዎስ 19:24 እና በማርቆስ 10:25 ላይ “መርፌ” ተብሎ የተተረጎመው ርሃፊስ የተሰኘው የግሪክኛ ቃል “መስፋት” የሚል ትርጉም ካለው ግሥ የመጣ ነው። በሉቃስ 18:25 ላይ የመስፊያ መርፌን የሚያመለክተው ቤሎኔ የተሰኘ አነጋገር ሲሆን እዚህ ላይ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም “እንዲያውም አንድ ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመስፊያ መርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል” በማለት ይነበባል። የተለያዩ ምንጮች ይህን አተረጓጉም ይደግፋሉ። ደብልዩ ኢ ቫይን “‘የመርፌ ቀዳዳን’ ለትናንሽ በሮች ማዋሉ ዘመናዊ ሐሳብ ይመስላል፤ ጥንታዊ ማስረጃ የለውም” በማለት ተናግረዋል።—የአዲስ ኪዳን ቃላት ገላጭ መዝገበ ቃላት
አንድ የቃላትን ፍቺ የሚመለከት ጽሑፍ አንድን ግመል በመርፌ ቀዳዳ ለማስገባት የመሞከር ምሳሌ “የምሥራቃዊ የማጋነን አገላለጽ ቃና ያለው ነው” ይላል። የማይቻለውን ነገር ማድረግ የሚችሉ የሚመስሉ አንዳንድ በጣም ብልጣብልጦችን በሚመለከት ዘ ባቢሎኒያን ታልሙድ “ዝሆንን በመርፌ ዓይን ያስገባሉ” ይላል። ከዚህ አንፃር ኢየሱስ አንድን የማይቻል ነገር ለመግለጽ የተለመደ ማጋነንና ሕያው በሆነ ማነጻጸሪያ ተጠቅሟል። አንድ ዝሆን ወይም ግመል በስፌት መርፌ ዓይን ማለፍ የማይቻል ነገር ነው። ይሁን እንጂ በአምላክ እርዳታ አንድ ሀብታም ሰው የፍቅረ ንዋይ አመለካከቱን ሊተውና የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ሊጥር ይችላል። የልዑሉን አምላክ የይሖዋን ፈቃድ ለመማርና ለማድረግ ከልብ የመነጨ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ እንዲሁ ሊያደርጉ ይችላሉ።