ይሖዋ ላደረገልኝ ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስጋኝ ነኝ
ሻሮን ጋስኪንስ እንደተናገረችው
ምድር ገነት ሆና በመስክ ላይ ስቦርቅ፣ ቢራቢሮዎችን ለመያዝ ስሮጥና ከአንበሳ ግልገሎች ጋር ስጫወት ታየኝ። ምንኛ ደስ የሚል ነገር ነው! ሆኖም በጣም የምጠራጠራቸው ነገሮች ነበሩ። ብዙ ጊዜም ተስፋ እቆርጥ ነበር።
እስከማስታውሰው ድረስ ተሽከርካሪ ወንበር ያልተለየኝ ጓደኛዬ ሆኖ ቆይቷል። ስወለድ ጀምሮ ያጋጠመኝ ሴሬብራል ፓልሲ የተባለ የአእምሮ በሽታ የልጅነት ደስታዬን ገፎብኛል። ሌሎች ልጆች በበረዶ እየተንሸራተቱ ሲጫወቱና ብስክሌት ሲነዱ እኔ ግን መራመድ ስለማልችል ብቻዬን እቀመጥ ነበር። ተዓምራታዊ ፈውስ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ እናቴ ከአንዱ የእምነት ፈዋሽ ወደ ሌላው ትወስደኝ ነበር። ይሁን እንጂ ያለ ምንም ውጤት ትመልሰኛለች። ሁኔታው እኔን የሚያበሳጨኝ ቢሆንም እናቴን ግን በጣም ተስፋ ያስቆርጣት ነበር።
እውነተኛ ተስፋ ለማግኘት በመጓጓት እናቴ በ1964 መጀመሪያ ላይ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ ስድስት ዓመት ተኩል ያህል ነበር።
በዚህች ምድር ላይ በአንድ ወቅት ውብ የሆነች ገነት እንደነበረች ማወቃችን በጣም አስደንቆን ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ግን የመጀመሪያው ሰው አዳም ያችን ገነት ማጣቱ ነው። ይሁን እንጂ አዳም በመጀመሪያ ላይ ከአምላክ ጋር እንደነበረው ዓይነት ቅርርብ እንዲኖረኝ ፈለግሁ። ከአምላክ ጋር ተቀራርቦ መኖር ምን ይመስል ነበር? ወይም ደግሞ የገዛ ልጁ ምድር ላይ በኖረበት ዘመን መኖር ምን ይመስል ነበር? ወደፊት ምድር እንደገና ገነት ወደምትሆንበት ጊዜ በምኞት ሃሳብ ተጓዝኩ። በዕድሜ ትንሽ በሆንኩበት በዚያ ጊዜም እንኳ እውነትን እንዳገኘን ግልጽ ሆኖልኝ ነበር።
እናቴ ቤተሰቡን ወደ ይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሽ ይዛ መሄድ ጀመረች። ስብሰባዎቻቸው በብዙ ቤተ ክርስቲያኖች ካየነው በጣም የተለዩ ነበሩ። በሰዎቹና በአካባቢው ልቤ በጣም ተነካ።
እኛን ወደ መንግሥት አዳራሽ ይዞ መሄድ ለእናቴ በጣም ከብዷት ነበር። እናቴ ከእኔ ሌላ የእኔ ታናናሾች የሆኑ ሦስት ልጆች ነበሯት፤ መኪናም አልነበረንም። ገንዘብ ሲኖራት በታክሲ ይዛን ትሄድ ነበር። አንድ እሁድ ቀን ላይ እናቴ ምን ያህል እንደተቸገረች እስካሁን ድረስ ይታወሰኛል። ታክሲ የሚባል ነገር ፈጽሞ በመንገዱ ላይ አልነበረም። ከየት መጣ ሳንል አንድ ሰው ከባድ መኪናውን አቁሞ አሳፈረን። ቢረፍድብንም እንኳ በስብሰባው ላይ ተገኘን። ይሖዋን በጣም አመሰገንነው!
ብዙም ሳይቆይ መኪና ያላቸው ውድ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተራ ገብተው ያመላልሱን ጀመር። በጣም ካልታመምን በስተቀር በፍጹም ከስብሰባዎች እንዳንቀር እናታችን የምትሰጠን ማበረታቻ ‘የመሰብሰባችንን’ አስፈላጊነት በጨቅላ አእምሮዬ ውስጥ እንዲቀረጽብኝ አድርጓል። (ዕብራውያን 10:24, 25) እናቴ በተማረችው ነገር በጣም በመነካቷ ራሷን ለይሖዋ ወሰነችና በ1965 ተጠመቀች።
በዚያን ጊዜ የስብሰባዎችን አስፈላጊነት ለመገንዘብ በምችልበት ዕድሜ ላይ ነበርኩ። በኒው ዮርክ ብሩክሊን በሳይፕረስ ሂልስ ጉባኤ አውሮፓውያን፣ ጥቁሮች፣ ስፓኞች፣ ፖርቱጋሎችና ሌሎች በሕብረት አምልኮታቸውን ያከናውኑ ነበር። አምላክን የሚፈሩ ሰዎች በዚህ ዓይነት እውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ መኖራቸው ትክክለኛ ይመስላል። — መዝሙር 133:1
እናቴ ለስብሰባዎች እንዴት መዘጋጀት እንደምችል አሳየችኝ። ይህ በአእምሮዬ በኩል ምንም ችግር አልፈጠረብኝም። ችግሩ አካላዊ ሁኔታዬ ነበረ። ሴሬብራል ፓልሲ የተባለው የአእምሮ በሽታዬ ቀላል ሥራዎችን ከባድ ያደርግብኝ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ላይ መልሱን ቀጥ አድርጌ ለማስመር አልችልም ነበር። እስካሁን ድረስ ይህ ችግር አለብኝ። ሆኖም ቀጥ አድርጌ የማስመር ችሎታዬ ተሻሽሎልኛል።
በአእምሮዬ ውስጥ ብዙ መናገር የምፈልጋቸው ነገሮች ነበሩ። ሆኖም ስናገር እዘባርቅ ነበር። በምናገርበት ጊዜ ጡንቻዎቼ እንዳይወጣጠሩ ራሴን ዘና ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነበር። በተጨማሪም አጥርቼ እንድናገር በምናገራቸው ቃላት ላይ የተቻለኝን ያህል ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብኝ። የምሰጠው ሃሳብ እንደፈለግኩት ሳይሆን ሲቀር ወይም ሰዎች እንዳልተረዱልኝ ሲሰማኝ በውስጤ እበሳጭ ነበር። በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች እያወቁኝ ሲሄዱ ንግግሬ ይገባቸው ጀመር። ሆኖም ይህ ችግር ቀለል የሚልበትና የሚብስበትም ጊዜ ዛሬም ያጋጥመኛል።
የተበሳጨሁባቸው ስድስት ወሮች
ስምንት ዓመት ሲሞላኝ እስከ ዛሬ ድረስ ሕይወቴን የለወጠ የስድስት ወር ስልጠና አጋጠመኝ። ቀደም ብሎ ከሕመሜ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ከወሰድኩት አካላዊ እና የሥራ አሠራር ስልጠና እንዲሁም የንግግር ሕክምና በተጨማሪ ዶክተሮቹ በኒው ዮርክ ከተማ በምዕራብ ሃቫስትሮው ውስጥ ወደሚገኝ የማገገሚያ ሆስፒታል ላኩኝ። እናቴም ሆነች እኔ ተስፋ ቆረጥን። ከጥቂት ዓመታት በፊት ዶክተሮች በስህተት የአስተሳሰቤ ችሎታ ከአእምሮዬ ጋር አይመጣጠንም ባሉኝ ጊዜ የአእምሮ ሕክምና ወደሚደረግበት ሆስፒታል እንደማታስገባኝ ነግራቸዋለች። ስለዚህ ለትንሽ ጊዜም እንኳን ቢሆን ከእኔ መለየት በጣም ይከብዳት ነበር። ይሁን እንጂ ከእሷም ሆነ ከአባቴ እርዳታ ነጻ ሆኜ በተቻለኝ መጠን ራሴን ችዬ ጥሩ ሕይወት እንድመራ በአካል ራሴን መቻል እንደሚኖርብኝ ተሰማት።
በሆስፒታሉ ውስጥ ሁሉ ነገር የተሟላ ቢሆንም የተጣልኩ መስሎ ተሰማኝ። አሁንም አሁንም ደጋግሜ ማልቀሴና ተለዋዋጭ ጠባይ ማሳየቴ ለቦታው የነበረኝን ስሜት የሚገልጽ ነበር። ወላጆቼ በተለይም እናቴ አምስተኛውን ልጅዋን እርጉዝ ሆና ለሦስት ሰዓት በአውቶቡስ እየተጓዙ አልፎ አልፎ ይጠይቁኝ ነበር። ለመሄድ ሲዘጋጁ በጣም እበሳጭ ስለነበር ዶክተሩ ጉብኝቱ አልፎ አልፎ መሆን አለበት ሲል ተናገረ። ወደ ቤት እንድሄድ የተፈቀደልኝ ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር።
ሐኪሞቹ በመደገፊያና በብረት ምርኩዝ እየተረዳሁ እንዴት እንደምራመድ አስተማሩኝ። በመጀመሪያ ምርኩዙ ከመጠን በላይ የሚከብድ መስሎኝ ነበር። ይሁን እንጂ መክበዱ ሚዛኔን እንድጠብቅና እንዳልወድቅ ረድቶኛል። ይህም ያለ መደገፊያ ለመሄድ የሚያስችል የመጀመሪያው ደረጃ ነበር።
ምግብ ቆርሶ መብላት፣ የልብሴን ቁልፍ መቆለፍና ጣቶችን መጠቀም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ብችልም ይህንን ለማድረግ እቸገር ነበር። ሆኖም በትንሹም ቢሆን ራሴን መመገብና ማልበስ ተማርኩ። ይህም በመጠኑም ቢሆን ራሴን እንድችልና በኋላም ለአምላክ ለማቀርበው አገልግሎት ረድቶኛል።
የተሰጠኝ ስልጠና ስላበቃ እንደገና ወደ ቤቴ ተመለስኩ። እናቴ በተማርኩት አዲስ ትምህርት እንድሠራበት አደረገችኝ። ነገሮችን ራሴ ማድረግ ብፈልግም ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ጊዜ የሚያባክኑና አሰልቺ በመሆናቸው ከስሜቴ ጋር መዋጋት ነበረብኝ። ወደ ስብሰባ ለመሄድ ልብሴን መልበሱ እንኳ ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ትልቅ ሥራ ይሆንብኝ ነበር።
ወደ መንግሥት አዳራሹ ወደሚወስደው መንገድ ስንደርስ ለብቻዬ እየተራመድኩ እሄድ ነበር። ይህ ታላቅ ድል ነበር!
በሕይወቴ በጣም የተደሰትኩበት ቀን
እናቴ ቤተሰቡ የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘቱን ትከታተል ነበር። እኔን ታስጠናኝ እንዲሁም የሚወጡትን እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶቻችንን እትም እንዳነብ ትጠብቅብኝ ነበር። በጉባኤ ስብሰባዎች መሳተፍ እንድችል አብረን እንዘጋጅ ነበር። አእምሮዬም ሆነ ልቤ በዚህ እውቀት የተሞላ ቢሆንም እንኳ ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ለመጠመቅ የነበረኝ ስሜት በጣም ዝቅተኛ ነበር። አካለ ስንኩል ብሆንም እንኳን አምላክ በመንፈሳዊ ነገሮች ረገድ ያለብኝን ኃላፊነት ራሴው እንድሸከመው የሚጠብቅብኝ መሆኑን እናቴ እንድገነዘብ ረዳችኝ። በእናቴ ትከሻ ላይ ተንጠልጥዬ ወደ አዲሱ ሥርዓት እገባለሁ ብዬ ማሰብ እንደማልችል ተገነዝብኩ።
አምላክን እወደዋለሁ። ይሁን እንጂ ያለሁበት ሁኔታ ከሌሎች የተለየሁ እንድሆን አደረገኝ። ይህ ደግሞ ለአንድ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ለሚገኝ ሰው በጣም አሳዛኝ ነው። አቅሜን አውቄ መቀበል በጣም ይከብደኝ ነበር። ቁጣ ይቀናኝ ስለነበር ከመጠመቄ በፊት ይህን ማሻሻል ነበረብኝ። (ገላትያ 5:19, 20) ራሴን ለይሖዋ ከወሰንኩበት ውሳኔ ጋር ተስማምቼ ባልኖር ምን ይደርስብኛል?
እናቴ ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አነጋገረኝ። ነቢዩ ኤልያስ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ?” በማለት እስራኤላውያንን የጠየቃቸውን ጥያቄ ጠቀሰልኝ። (1 ነገሥት 18:21) በእኔ መወላወል ይሖዋ እንዳልተደሰተ ግልጽ ነው።
በመንፈሳዊ በመነቃቃት ራሴን ለእሱ ለመወሰን እንድችልና በውሳኔዬ ቆራጥ እንድሆን እንዲረዳኝ በትህትና ይሖዋን በጸሎት ለመንኩት። በጉባኤያችን ውስጥ የምትገኝ አንዲት እህት እኔን ማስጠናት ጀመረች። ከእኔ በዕድሜ የምታንስ ስትሆን እናቷ የሞቱባት ገና በሕጻንነቷ ነው። ይሁን እንጂ ራሷን የወሰነችው ገና በልጅነት ዕድሜዋ ነበር።
17 ዓመት ሲሆነኝ ዝግጁ ሆንኩ። ምንም እንኳን አካላዊ አቅሜ ውስን ቢሆንም ይሖዋን እስከምችለው ድረስ ለማገልገል ቆርጬ ተነሳሁ። የተጠመቅሁበት የነሐሴ 9, 1974 ዕለት በሕይወቴ ውስጥ በጣም ደስ የተሰኘሁበት ቀን ነበር።
በአገልግሎት መደሰት
በአገልግሎት መሳተፍ ስጀምር ተራራ የሚያካክሉ ችግሮች ይገጥሙኝ ጀመር። ትልቁ ችግሬ የምናገረውን ሰዎች እንዲረዱት ማድረግ ነበር። የምችለውን ያህል አጣርቼ ለመናገር እሞክራለሁ። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ በአገልግሎት ላይ አብራኝ የምትመደበው እህት የሰጠሁትን ሃሳብ ለቤቱ ባለቤት ደግማ ትናገራለች። አንዳንዶች ሰዎች ምስክሮቹ ለመበዝበዣ መሣሪያነት እየተጠቀሙብኝ እንዳለ ይሰማቸውና መጥፎ አመለካከት ያሳያሉ። ይሁን እንጂ መስበክ መብቴና ልባዊ ፍላጎቴ ነው።
ጥቂት ቤቶችን እንኳን ከበር ወደ በር ሄጄ ማንኳኳት በጣም ያደክመኛል። በምንመሰክርበት ክልል ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ቤቶች ለእኔ የማይመቹ ደረጃዎች አሏቸው። በክረምቱ ወራት በበረዶ የሚሸፈኑት መንገዶች ከቤት ወደ ቤት የማደርገውን ሥራ ፈጽሞ አዳጋች ያደርጉብኛል። (ሥራ 20:20) ሆኖም የመንፈሳዊ ወንድሞቼ እርዳታ አይቋረጥብኝም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ አገልግሎቴን በጣም ቀላል እንዲሆን ያደረገልኝን ባለ ሞተር ተሽከርካሪ ወንበር በመስጠት ባርኮኛል።
ቀጥሎም በመጻጻፍ መመስከር ጀመርኩ። ብዙ ሰዎች የእጅ ጽሕፈቴን ማንበብ ስለሚቸገሩ በእጅ መጻፌ ዋጋ ቢስ ነበር። በዚህ ምክንያት በኤሌክትሪክ የሚሠራ የጽሕፈት መኪና መጠቀም ጀመርኩ። እጆቼ በአንድ ላይ ተቀናጅተው መሥራት ስለሚያዳግታቸው ፍጥነቴ በጣም ዝቅተኛ ነበር። አንድ ፊደል ለመምታት ጣቶቼን አስተካከልና ለመምታት ስሞክር የምመታው ሌላ ፊደል ይሆናል። አንዲት ገጽ ለመጻፍ አንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ይወስድብኛል።
አቅም ባይኖረኝም እንኳ ከጊዜ ወደ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆኜ በማገልገል 60 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ በወር ውስጥ እመልሳለሁ። ይህም ጥሩ ፕሮግራም ማውጣት፣ ተጨማሪ ጥረት ማድረግንና በየቀኑ የእምነት ጓደኞቼን ድጋፍ ማግኘትን ይጠይቅ ነበር። ያላቸው የአቅኚነት መንፈስ ያበረታታኛል። በተጨማሪም እናቴ ችግሮች፣ የጤና እክል፣ በእምነት በተከፋፈለ ቤት ውስጥ ሰባት ልጆችን የማሳደግ ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማትም ዘውትር አቅኚ ወይም ረዳት አቅኚ ሆና ስለምታገለግል ጥሩ ምሳሌ ሆናልኛለች።
ራሴን መቻል
24 ዓመት ሲሞላኝ ራሴን ችዬ ለመውጣት ወሰንኩ። ብሩክሊን ውስጥ ወደሚገኘው ቤንሰንሃረስት መዛወሬ በረከት ሆነልኝ። በማርልቦሮ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ የሚተያዩ ነበሩ። ከእነርሱ ጋር መሆን ምንኛ እምነት የሚያጠነክር ነበር! በጉባኤው ውስጥ ያሉት ሁለት ወይም ሦስት መኪኖች ብቻ ቢሆኑም መንፈሳዊ ወንድሞቼ ወደ ሁሉም ስብሰባዎች ይወስዱኝ ነበር። ግን እዚያ ለረዥም ጊዜ አልኖርኩም።
ልክ ጨለማ ውስጥ እንዳለሁ ያህል ተሰማኝና ወደ ቤተሰቦቼ ተመለስኩ። ከዚያም ለሦስት ዓመት ያህል ከባድ የመንፈስ ጭንቀት በሽታ ያዘኝ። የድሮው ንዴቴ እንደገና ተቀሰቀሰብኝ። ከዚያም ራሴን የማጥፋት ሃሳብ መጣብኝና ራሴን ለመግደል ተደጋጋሚ ሙከራ አደረግኩኝ። ሞት ልክ እንደ ጥቁር ደመና አጠላብኝ። ሆኖም በአምላክ ላይ በመመካት ለሰጠኝ ሕይወት አድናቆት ለማሳየት ቃል ገባሁ። ፍቅራዊ መጽናናትና ምክር ከሽማግሌዎች አገኘሁ። ከሽማግሌዎች ያገኘሁት መጽናናት፣ ጸሎት፣ የግል ጥናት፣ የቤተሰቦቼ ታጋሽነትና ከበሽታው ባለሙያዎች ያገኘሁት እርዳታ አስተሳሰቤን አስተካከለልኝ።
በከባድ ጭንቀት በተጠቃሁበት ወቅት ይሖዋ በመጠበቂያ ግንብ ላይ በወጡት ትምህርቶች አማካኝነት አብዝቶ ማስተዋልን ሰጥቶኛል። አዎ፣ እሱ ሕዝቡን ይጠብቃል። ስሜቶቻችንንም ይገነዘብልናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ከጊዜ በኋላ ከባዱ የመንፈስ ጭንቀቴ ቀለል ማለት ጀመረ። አሥር ዓመት ቢያልፍም ብስጭትና የመንፈስ ጭንቀት ሲገጥመኝ ይሖዋ አሁንም ይረዳኛል። አንዳንድ ጊዜ የማልረባ ነኝ በሚል ስሜት እዋጣለሁ። ይሁን እንጂ ጸሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና መንፈሳዊ ቤተሰቤ ችግሮቼን እንድወጣ ያገዙኝ የቅርብ ረዳቶቼ ናቸው።
ሌላ መኖሪያ ቤት ለማግኝት ብዙ ከደከምኩ በኋላ የቀረውን ሕይወቴን ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ ለማሳለፍ ተገደድኩ። ከዚያም ይሖዋ ጸሎቴን መለሰልኝ። በብሩክሊን ቤድ ፎርድ ስቴዩቬሳንት ውስጥ አንድ ቤት አገኘሁ። የ1984 የበጋው ወር ሲገባደድ ወደዚያው ተዛወርኩና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እዚያው መኖር ጀመረኩ።
የአፍቃሪው የላፌይት ጉባኤ አባሎች በደግነት ወደ ስብሰባዎች ይወስዱኛል። ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈልኩበት የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እስካሁን ድረስ ይታወሰኛል። ስብሰባው የተደረገው በአራተኛ ፎቅ ላይ ሲሆን ፎቁም አሳንሰር አልበረውም። እነዚያን ደረጃዎች ወጥቼ የወረድኩት በይሖዋ እርዳታ ነበር። በኋላም ለእኔ አመቺ የሆነ የጉባኤ ሥፍራ ተመረጠልኝ። አሁን የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት በቤቴ ውስጥ እንዲጀመር በማድረግ ይሖዋ ባርኮኛል።
በላፌይት ጉባኤ ውስጥ አስደናቂ የሆነ የአቅኚነት መንፈስ አለ። ወደዚህ ጉባኤ ስመጣ ጥሩ ምሳሌ ሆነው የሚያገለግሉ 30 ያህል አቅኚዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ ጥሩ እንክብካቤ አድርገውልኛል። በጉባኤው ውስጥ የሚታየው የአገልግሎት ቅናት መንፈስ እኔም አዘውትሬ ረዳት አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል አነሳስቶኛል።
በ1990 ሚያዝያ ወር ላይ የላፌይት እና የፕራት ጉባኤ እኔ በምኖርበት ቤት አጠገብ በሚገኘው መንገድ ዳርቻ አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ሠሩ። ጤንነቴም እንደገና እየተባባሰብኝ በመሄዱ ምክንያት ለመራመድ ስለተቸገርኩ የመንግሥት አዳራሹ መሠራት ለእኔ ወቅታዊ ነበር። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ከጎኔ በመሆን በሚሰጡኝ ድጋፍና በሞተር ብስክሌት እየተረዳሁ ወደ ስብሰባዎች ስንሄድና ስንመጣ የምናደርገው ጉዞ አስደሳች ነበር። ይህን ለመሰለው ፍቅራዊ እርዳታ ምንኛ አመስጋኝ ነኝ!
አምላክ ላደረገልኝ ድጋፍ አመስጋኝ ነኝ
ምንም እንኳን እግሮቼ መቆም ባይችሉም ልቤ ግን ጽኑ ነው። ጥሩ ትምህርት ማግኘት ኑሮን ትንሽ ቀለል ቢያደርግም ነገር ግን ሕይወቴን የጠበቀልኝ አምላክ ነው። አንዳንድ ጊዜ ምግቤን ከየት እንደማገኝ አላውቅም። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ ለጋሽ በመሆን ይደግፈኝ ነበር። “ጎለመስሁ አረጀሁም፤ ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” የሚሉትን የዳዊት ቃላት በጣም እወዳቸዋለሁ። — መዝሙር 37:23–25
በተደጋጋሚ ጊዜያት የቀዶ ሕክምና በሚደረግልኝ ወቅት ደም እንዳልወስድና ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋሜን እንድጠብቅ ይሖዋ ረድቶኛል። (ሥራ 15:28, 29) በቅርቡ አባቴ ሞተ። በጣም የሚቀርቡትን ሰው በሞት ማጣት በእርግጥ አስደንጋጭ ነው። ይህንንና ሌሎች መከራዎችን ይሖዋ በሚሰጠኝ ኃይል ተወጥቻቸዋለሁ።
ምናልባት ጤንነቴ እየተቃወሰ መሄዱን ሊቀጥል ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በይሖዋ ላይ ያለኝ ትምክህትና ቅርርብ የሕይወቴ አለኝታ ነው። ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል አንዷ በመሆኔና የእርሱን ያልተቋረጠ ድጋፍ በማግኘቴ ምን ያህል ደስተኛ ነኝ!