የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 10/1 ገጽ 5-9
  • ብርቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ውርስ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ብርቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ውርስ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አባቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማረ
  • በልጅነቴ አገልግሎት ጀመርኩ
  • ከወላጆቼ ጋር አምላክን ማገልገል
  • ከአያቶቼ ያገኘሁት ስልጠና
  • የስደት ዓመታት
  • ላገኘሁት የወላጅ መመሪያ አመስጋኝ ነኝ
  • ጋብቻና የተጓዥነት ሥራ
  • ወላጆችን መጦር
  • ወላጆቻችን አምላክን መውደድ አስተምረውናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ከአምላክና ከእናቴ ጋር ሰላም መፍጠር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • አባቴ ወይም እናቴ ታማሚ ቢሆኑስ?
    የወጣቶች ጥያቄ
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 10/1 ገጽ 5-9

ብርቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ውርስ

ብሎሰም ብራንት እንደተናገረችው

በጥር 17, 1923 እኔ በተወለድኩበት ቀን በሳን አንቶኒዮ ቴክሳስ በረዶ ይጥል ነበር። ውጪው በጣም ይቀዘቅዝ ነበር፤ ነገር ግን ጀጅ እና ሄለን ኖሪስ የተባሉ አፍቃሪ ክርስቲያን ወላጆቼ የሞቀ እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉኝ። ከልጅነቴ ጀምሬ እንደማስታውሰው ወላጆቼ ያደርጉት የነበረው ማንኛውም ነገር ለይሖዋ አምላክ ባላቸው አምልኮ ላይ ያተኮረ ነበር።

በ1910 እናቴ የስምንት ዓመት ልጅ ሳለች ወላጆቿ በፔንሲልቫኒያ ፒትስበርግ አቅራቢ ከአልቪን ቴክሳስ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ አንድ የእርሻ ቦታ ተዛወሩ። እዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከአንድ ጎረቤታቸው በመማራቸው በጣም ተደሰቱ። እማማ ቀሪውን ሕይወቷን ያሳለፈችው ለመንግሥቱ ተስፋ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች በመፈለግ ነበር። እማማ የተጠመቀችው ቤተሰቡ ወደ ሂውስተን ቴክሳስ ከተዛወረ በኋላ በ1912 ነበር።

የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል በሂውስተን የሚገኘውን ጉባኤያቸውን ሲጎበኝ እናቴና ወላጆቿ ለመጀመሪያ ጊዜ ራስልን አገኙት። ቤተሰቡ በዚያን ጊዜ ፒልግሪምስ እየተባሉ የሚጠሩትን የማኅበሩን ተጓዥ ተወካዮች ብዙ ጊዜ ቤታቸው ያስተናግዱ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እማማ ከወላጆቿ ጋር በመሆን ወደ ኢሊኖይስ ቺካጎ ተዛወረች። ወንድም ራስል ደግሞ እዚያ ያለውን ጉባኤ ይጎበኝ ነበር።

በ1918 ሴት አያቴ የኅዳር በሽታ ያዛት። በሽታው እያዳከማት ስለሄደ ዶክተሮች ሞቃት አካባቢ እንድትኖር አዘዙ። ወንድ አያቴ ለፑልማን የባቡር ኩባንያ ይሠራ ስለነበረ በ1919 ወደ ቴክሳስ ለመመለስ ዝውውር አገኘ። በዚያ በሳን አንቶኒዮ እማማ ጀጅ ኖሪስ የሚባል አንድ ወጣት ቀናተኛ የጉባኤ አባል አገኘች። ወዲያው ሁለቱም ተዋደዱና ከጊዜ በኋላ ተጋቡ። ጀጅም የእኔ አባት ሆነ።

አባቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማረ

ጀጅ ልዩ የሆነውን ስሙን ያገኘው ልክ እንደተወለደ ነው። አባቱ ገና ሲያየው “ይህ ልጅ ልክ እንደ ዳኛ ኮስታራ ነው” ሲል ተናገረ። ስሙም ይህ ሆነ። በ1917 አባባ የ16 ዓመት ልጅ ሳለ በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙትን ሙታን የት ናቸው? እና ነፍስ ምንድን ነች? የተባሉ ትራክቶች ተሰጡት። የአባባ አባት ከሁለት ዓመት በፊት ሞተው ነበር። አባባ ስለ ሙታን ሁኔታ ለማወቅ ይፈልግ ስለነበረ መልሱን ከትራክቶቹ አገኘ። ብዙም ሳይቆይ በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩትን የይሖዋ ምስክሮችን ስብሰባ መከታተል ጀመረ።

አባባ ወዲያው በጉባኤ ሥራዎች ለመካፈል ፈለገ። የሚሰብክበት የአገልግሎት ክልል ተቀበለ። ከትምህርት ቤት በኋላ ትራክት ለማሰራጨት በብስክሌቱ ወደዚያ ይሄዳል። የመንግሥቱን ተስፋ በማካፈሉ ሥራ ሙሉ በሙሉ ተካፋይ ሆነ። በመጋቢት 24, 1918 ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን በውኃ ጥምቀት አሳየ።

በሚቀጥለው ዓመት እማማ ወደ ሳን አንቶኒዮ በተዛወረችበት ጊዜ አባባ አያትና በጣም ወደዳት። እሱም እንደሚለው እስከ ዛሬ ካየው ሁሉ የሚበልጥ “በጣም ደስ የሚል ፈገግታና ሰማያዊ ዓይኖች” ተመለከተ። ወዲያው ለመጋባት እንደሚፈልጉ አስታወቁ። ይሁን እንጂ የእናቴን ወላጆች ማሳመን በጣም አስቸግሯቸው ነበር። ሆኖም ሚያዝያ 15, 1921 የሠርጋቸው ሥነ ሥርዓት ተካሄደ። ሁለቱም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን እንደ ግባቸው አድርገው ይዘው ነበር።

በልጅነቴ አገልግሎት ጀመርኩ

እማማና አባባ በ1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ለመገኘት ዝግጅት በማድረግ እየተጣደፉ ሳሉ እማማ እኔን እርጉዝ እንደሆነች ታወቀ። ወዲያው እኔ እንደተወለድሁ አባባ ገና በ22 ዓመቱ የጉባኤ የአገልግሎት ዲሬክተር ሆኖ ተሾመ። ይህም ማለት ሁሉንም የመስክ አገልግሎት ዝግጅቶች ያደርጋል ማለት ነው። ከተወለድኩ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እማማ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ይዛኝ መሄድ ጀመረች። እርግጥ አያቶቼም ወደ አገልግሎት ይዘውኝ መሄድ ይወዱ ነበር።

እኔ የሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ ወደ ዳላስ ቴክሳስ ተዛወሩ። ከሦስት ዓመት በኋላ አቅኚ በመሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጀመሩ። ሌሊት መንገድ ዳር በሸራ አልጋ ላይ ይተኛሉ፤ እኔን ደግሞ መኪናው ውስጥ የኋለኛው ወንበር ላይ ያስተኙኛል። ይህ ለእኔ እንደ ጨዋታ ይመስለኝ ነበር። ሆኖም ገና ለአቅኚነት ሕይወት ዝግጁ እንዳልሆኑ ወዲያው ግልጽ ሆነ። ስለዚህ አባባ አንድ ንግድ ጀመረ። ከዚያም አቅኚነትን እንደገና ለመጀመር አንድ ተጎታች ቤት ሠራ።

ትምህርት ቤት ከመጀመሬ በፊት እናቴ ማንበብና መጻፍ አስተማረችኝ። እንዲሁም እስከ አራት ቤት ድረስ ጊዜ ቤት አወቅሁ። ሁልጊዜ የእናቴ ዋና ትኩረት እንድማር እኔን መርዳት ነበር። እሷ ያጠበቻቸውን ሳህኖች እንዳደርቅ በወንበር ላይ አጠገቧ ታቆመኝ ነበር። እንዲሁም ጥቅሶችን ማስታወስና የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ታስተምረኝ ነበር።

ከወላጆቼ ጋር አምላክን ማገልገል

በ1931 የይሖዋ ምስክሮች የሚለውን ስማችንን የተቀበልንበትን በኦሃዮ ኮለምበስ የተካሄደውን አስደሳች ስብሰባ ተካፈልን። ምንም እንኳን ዕድሜዬ ገና ስምንት ዓመት ቢሆንም እስከ ዛሬ ከሰማኋቸው ስሞች ሁሉ እጅግ በጣም ጥሩ ስም ነው ብዬ አሰብኩ። ወዲያው ወደ ቤት እንደተመለስን አባባ የነበረው ንግድ ተቃጥሎ ወደመ። እማማና አባባ አቅኚነትን እንዲጀምሩ ሲል ይህ “የጌታ ፈቃድ ነው” ሲሉ አሰቡ። ስለሆነም ከ1932 በጋ ጀምረን ለብዙ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፈልን።

ወላጆቼ እዚያው ሳን አንቶንዮ ይኖሩ ከነበሩት የእማማ ወላጆች ላለመራቅ ሲሉ በመካከለኛው ቴክሳስ አቅኚ ሆነው ያገለግሉ ነበር። ከአንድ ምድብ ወደ ሌላ ምድብ ስለሚዘዋወሩ በየጊዜው ትምህርት ቤት እቀይር ነበር። አንዳንድ በግዴለሽነት የሚናገሩ ወንድሞችና እኅቶች “ለምን አንድ ቦታ አርፋችሁ ተቀምጣችሁ ይህቺ ልጅ ቤት እንዲኖራት አታደርጉም” በማለት እኔ በሚገባ እንዳልተያዝኩ አድርገው ይናገሩ ነበር። እኔ ግን አኗኗራችን በጣም የሚያስደስትና አባባንና እማማን በአገልግሎት እየረዳኋቸው እንዳለሁ አድርጌ አስብ ነበር። በእርግጥ በኋላ የራሴ የሕይወት መንገድ ለሆነው ሥራ እየሰለጠንኩ ነበር።

አባባንና እማማ ካልተጠመቅሁ እያልኩ ለብዙ ወራት እጨቀጭቃቸው ነበር። እነሱም ብዙ ጊዜ ስለ ጥምቀት ይነግሩኝ ነበር። ውሳኔዬ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዳውቅ ፈልገው ነበር። ታኅሣሥ 31, 1934 በሕይወቴ ውስጥ ይህን ልዩ እርምጃ የምወስድበት ቀን ደረሰ። ሆኖም ከምጠመቅበት ቀን በፊት በነበረው ምሽት አባባ በጸሎት ወደ ይሖዋ ቀርቤ እንደሆነ ጠየቀኝ። ከዚያም አንድ ጥሩ ነገር አደረገ። ሁላችንም እንድንበረከክ ካደረገ በኋላ ጸሎት አቀረበ። ትንሿ ልጁ ሕይወቷን ለይሖዋ በመወሰኗ በጣም የተደሰተ መሆኑን ለይሖዋ ነገረው። መቼም ቢሆን ያን ምሽት በፍጹም አልረሳውም!

ከአያቶቼ ያገኘሁት ስልጠና

በ1928 እና በ1938 መካከል ባሉት ዓመታት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜዬን የማጠፋው በሳን አንቶንዮ ያሉትን አያቶቼን በመጠየቅ ነበር። አያቶቼ ዘወትር የሚሠሩት ወላጆቼ ከሚሠሩት ዕለታዊ ሥራ ጋር ተመሳሳይ ነበር። ሴት አያቴ ኮልፖርተር ነበረች። በዚያን ጊዜ አቅኚዎች ኮልፖርተርስ ተብለው ይጠሩ ነበር። ከዚያም የግማሽ ቀን አቅኚ ሆነች። ወንድ አያቴ ደግሞ በታኅሣሥ 1929 አቅኚ ሆኖ ተሾመ። ስለዚህ የመስክ አገልግሎት በየዕለቱ የሚከናወን የተለመደ ሥራ ነበር።

አያቴ ማታ ማታ በክንዶቹ ታቅፎ የኮኮቦችን ስም ያስተምረኝ ነበር። በአእምሮው የሚያስታውሳቸውን ግጥሞች ይነግረኝ ነበር። በባቡር ሐዲድ ላይ በሚሠራበት ጊዜ አብሬው ብዙ እጓዛለሁ። ምን ጊዜም ችግር ሲኖረኝ ሮጬ የምሄደው ወደ እሱ ነበር። እሱም ያባብለኝና እንባዬን ይጠርግልኝ ነበር። ይሁን እንጂ ጥፋት አጥፍቼ ስቀጣና እንዲያባብለኝ ፈልጌ ወደ እሱ ስሄድ (በዚያን ጊዜ ትርጉማቸው በማይገባኝ ነገር ግን የድምፃቸው ቃና ጥርት ባለ ቃላት):- “የኔ ቆንጆ ያጠፋ ዋጋውን ያገኛል” ይለኝ ነበር።

የስደት ዓመታት

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ። የይሖዋ ሕዝቦችም ስደትና ሕዝባዊ ተቃውሞ ይደርስባቸው ነበር። በ1939 መጨረሻ ገደማ እማማ በጠና ታመመች፤ በመጨረሻም ቀዶ ሕክምና ስላስፈለጋት ወደ ሳን አንቶንዮ ተመልሰን ሄድን።

በሳን አንቶንዮ ጎዳናዎች ላይ ቆመን መጽሔት ስናበረክት የሕዝብ ረብሻ ይነሳ ነበር። ይሁን እንጂ በእያንዳንዱ ሳምንት በቤተሰብ እያንዳንዳችን በየተመደብንበት ማዕዘን በመሆን መጽሔት እናበረክት ነበር። ብዙ ጊዜ አባባን ጎትተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱት አይ ነበር።

ምንም እንኳን እማማ አቅኚነቷን ብታቆምም አባባ አቅኚነቱን ለመቀጠል ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጂ ግማሽ ቀን እየሠራ በቂ ገንዘብ ሊያገኝ ስላልቻለ ማቆም ግድ ሆነበት። በ1939 እኔም ትምህርት ጨረስኩና ሥራ ገባሁ።

ጀጅ (ዳኛ) የሚለው የአባባ ስም ጠቃሚነት የታወቀው በእነዚያ ዓመታት ወቅት ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ የምስክሮች ቡድን ከሳን አንቶንዮ በስተሰሜን በሚገኝ አንድ ከተማ ለመመስከር ሄደ፤ ከዚያም የፖሊስ አዛዡ ሁሉንም ወህኒ ቤት አስገባቸው። አያቶቼን ጨምሮ ወደ 35 የሚጠጉትን ይዞ አሰራቸው። ለአባባ መልእክት ላኩበትና በመኪና ወደዚያው ሄደ። ወደ ፖሊስ አዛዡ ቢሮ ገባና “ጀጅ (ዳኛ) ኖሪስ እባላለሁ ከሳን አንቶንዮ” አለ።

“አቤት ጌታዬ፣ ምን ልርዳዎት?” ሲል የፖሊስ አዛዡ ጠየቀ።

አባባም “እነዚህን ሰዎች ከእስር ቤት ለማስፈታት ነበር የመጣሁት” ሲል መለሰ። በዚህ ጊዜ የፖሊስ አዛዡ ያለምንም ዋስና ምንም ተጨማሪ ጥያቄ ሳይጠይቃቸው ለቀቃቸው!

አባባ መኻል ከተማ በሚገኙ የመሥሪያ ቤት ሕንፃዎች ውስጥ መመስከር ይወድ ነበር። በተለይ ደግሞ ዳኞችንና ጠበቆችን ማነጋገር ይወድ ነበር። እንግዳ ተቀባዩን “እኔ ጀጅ (ዳኛ) ኖሪስ እባላለሁ፤ ዳኛ እገሌን ለማነጋገር ነው የመጣሁት” ይላል።

ከዚያም ዳኛውን ሲያገኝ ሁልጊዜ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል:- “የመጣሁበትን ዓላማ ከመናገሬ በፊት ከእርስዎ የበለጠ ለረዥም ዓመታት ዳኛ እንደሆንኩ ለመግለጽ እፈልጋለሁ። ሕይወቴን በሙሉ ዳኛ ነኝ።” ከዚያም ስሙን እንዴት እንዳገኘው ይናገራል። ይህም በጣም ወዳጃዊ በሆነ መንገድ ውይይት እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል። አባባ በዚያን ጊዜ ከብዙ ዳኞች ጋር ጥሩ ግንኙነቶችን መስርቶ ነበር።

ላገኘሁት የወላጅ መመሪያ አመስጋኝ ነኝ

እኔ በእነዚያ አስቸጋሪ የአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ነበርኩ። አባባና እማማ እኔ የማደርገውን በመጠባበቅና በመከታተል ብዙ ጊዜ እንደተጨነቁ አውቃለሁ። ሁሉም ልጆች እንደሚያደርጉት እኔም መልሳቸው አይሆንም እንደሆነ አስቀድሜ እያውቅሁ አንድ ነገር አድርጉልኝ ወይም አንድ ቦታ እንድሄድ ፍቀዱልኝ እያልኩ አባባንና እማማን ብዙ ጊዜ ፈትኛቸዋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ልቅሶም ነበረ። በእርግጥ “ቀጥይ፤ የፈለግሽውን አድርጊ። እኛ ምን ቸገረን” ቢሉኝ ኖሮ ጠፍቼ ነበር።

የአቋም ደረጃቸውን ማስለወጥ እንደማልችል ማወቄ በእነርሱ ተማምኜ እንድኖር አድርጎኛል። እንዲያውም ወጣቶች ጥበብ በጎደለው መዝናኛ እንድገኝ ሲጋብዙኝ “አባቴ አይፈቅድልኝም” ለማለት በመቻሌ ይህ ነገሩን በጣም ቀላል አድርጎልኛል። አባባ በ16 ዓመቴ መኪና መንዳት እንድማርና መንጃ ፈቃድ እንዲኖረኝ አድርጓል። በተጨማሪም በዚህ ጊዜ የቤቱን ቁልፍ ይሰጠኝ ነበር። ስለሚያምነኝ በጣም ተነካሁ። ትልቅ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማኝና ያን ያህል እምነት ከጣሉብኝ እኔም ላሳፍራቸው አይገባም የሚል አቋም እንድይዝ አድርጎኛል።

በዚያን ዘመን ጋብቻን በተመለከተ ብዙም ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ አይሰጥም ነበር። ይሁን እንጂ አባባ መጽሐፍ ቅዱስንና “በጌታ” ብቻ ስለማግባት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ያውቅ ነበረ። (1 ቆሮንቶስ 7:​39) ዓለማዊ ወንድ ልጅ ይዤ ወደ ቤት ብመጣ ወይም ትኩር ብዬ እንኳን ብመለከት በጣም እንደሚያዝን በግልጽ ነገሮኝ ነበር። ወላጆቼ “በጌታ” በመጋባታቸው ያላቸውን ደስታና አንድነት ስለተመለከትኩ አባባሉ ትክክል እንደሆነ አውቅ ነበር።

በ1941 የ18 ዓመት ልጃገረድ ሳለሁ በጉባኤ ውስጥ ካለ ከአንድ ወጣት ጋር ፍቅር ይዞኝ ነበር። አቅኚ ነበር፤ እንዲሁም ጠበቃ ለመሆን ያጠና ነበር። በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። ልንጋባ እንደምንፈልግ ለወላጆቼ ስንነግራቸው በነገሩ እንዳልተስማሙ ከማሳየት ወይም ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ “ብሎሰም አንድ ነገር እንድታደርጊ ልንጠይቅሽ እንፈልጋለን። ገና ልጅ እንደሆንሽ ይሰማናል። ስለሆነም አንድ ዓመት እንድትቆይ ልንጠይቅሽ እንፈልጋለን። እውነተኛ ፍቅር ካላችሁ ደግሞ አንድ ዓመት ምንም አይደለችም” አሉኝ።

ይህን የጥበብ ምክር በመስማቴ በጣም ደስ ይለኛል። በአንድ ዓመት ውስጥ የተወሰነ ብስለት አገኘሁና ይህ ወጣት ለጥሩ የትዳር ጓደኝነት የሚያበቁ ባሕሪዎች እንደሌሉት ለማስተዋል ቻልኩ። በመጨረሻም ይህ ወጣት ድርጅቱን ተወ። እኔም በሕይወቴ ውስጥ ሊገጥመኝ ይችል ከነበረ ትልቅ ውድቀት አመለጥኩ። እንደዚህ ትምክኽት ሊጣልበት የሚችል ጥሩ ግምት ያላቸው ጥበበኛ ወላጆችን ማግኘት እንዴት ግሩም ነው!

ጋብቻና የተጓዥነት ሥራ

በ1946 የበጋ ወራት ላይ የግማሽ ቀን ሥራ እየሰራሁ ለስድስት ዓመት አቅኚ ሆኜ ካገለገልኩ በኋላ ካገኘኋቸው ሁሉ የበለጠ ውብ የሆነ ወጣት ወደ መንግሥት አዳራሻችን መጣ። ጂን ብራንት ለእኛ ክልል ወንድሞች ተጓዥ አገልጋይ ለሆነው ወንድም የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን ተመድቦ ነበር የመጣው። በዚያን ጊዜ የክልል የበላይ ተመልካች እንደዚህ ተብሎ ነበር የሚጠራው። ሁለታችንም ተዋደድን። ነሐሴ 5, 1947 ተጋባን።

ወዲያው አባባና ጂን አንድ ንግድ ከፈቱ። ነገር ግን አባባ ለጂን እንዲህ ሲል ነገረው:- “ይህ ንግድ ከስብሰባና ከቲኦክራሲያዊ የሥራ ምድባችን ወደኋላ የሚያስቀረን ከሆነ እዘጋዋለሁ፤ ቁልፉንም እወረውረዋለሁ።” ይህን መንፈሳዊ አመለካከቱን ይሖዋ ባረከው፤ ይህ ንግድ ለእኛ የሚያስፈልገንን ለማቅረብና ለአቅኚነት ጊዜ ለማግኘት የሚያስችል ሆነ። አባባና ጂን ጥሩ የንግድ ሰዎች ስለነበሩ በቀላሉ ሐብታም ልንሆን እንችል ነበር። ይሁን እንጂ ግባቸው በፍጹም ይህ አልነበረም።

በ1954 ጂን ለክልል ሥራ ተጋበዘ። ይህም በሕይወታችን ውስጥ አንድ ትልቅ ለውጥ ነበር። ወላጆቼ እንዴት ተሰምቷቸው ነበር? አሁንም ቢሆን እነሱን የሚያሳስባቸው ነገር ከራሳቸው ይልቅ የመንግሥቱ ፍላጎትና የልጃቸው መንፈሳዊ ደህንነት ነው። “ለምን የልጅ ልጅ እንድናይ አታደርጉም?” በፍጹም አላሉንም። ከዚህ ይልቅ “በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እናንተን ለመርዳት ምን ለማድረግ እንችላለን?” በማለት ሁልጊዜ ይጠይቁን ነበር።

ስለዚህ የምንሄድበት ቀን ሲደርስ ላገኘነው ትልቅ መብት የሚያበረታቱና የደስታ መግለጫ የሆኑ ቃላት ብቻ ነበር የሰማነው። ጥለናቸው መሄዳችን በፍጹም እንዲሰማን አላደረጉም። ከዚህ ይልቅ ዘወትር መቶ በመቶ ከጎናችን ነበሩ። እኛ ከሄድንም በኋላ ለሌላ አሥር ዓመት ራሳቸውን በአቅኚነቱ ሥራ አስጠመዱ። አባባ የሳን አንቶንዮ የከተማ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾሞ ነበር። በዚህም ለ30 ዓመት ሠርቶበታል። በ1920ዎቹ ዓመታት በከተማዋ ውስጥ አንድ ጉባኤ ብቻ የነበረ ሲሆን በ1991 ከመሞቱ ቀደም ብሎ ይህ ቁጥር 71 ደርሶ በማየቱ ተደስቷል።

ጂንና እኔ ሕይወታችን ደስታ የሞላበት ነው። ከ31 በላይ በሚሆኑት የአሜሪካ ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙትን ውድ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን የማገልገል ትልቅ ደስታ ነበረን። ከእነዚህ ሁሉ የበለጠው ደስታ ደግሞ በ1957 በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ጊልያድ ትምህርት ቤት 29ኛው ክፍል እንድንካፈል መብት ማግኘታችን ነው። ከዚያ በኋላ ወደ ተጓዥነት ሥራችን ተመለስን። ከ30 ዓመት የክልልና የወረዳ ሥራ በኋላ ወላጆቻችን በ80ዎቹ ዕድሜያቸው ውስጥ ስለነበሩና ጥሩ ጤንነት ስላልነበራቸው በ1984 ማኅበሩ በአሳቢነት ጂንን በሳን አንቶንዮ የክልል ሥራ እንዲሠራ መደበው።

ወላጆችን መጦር

ወደ ሳን አንቶንዮ ከተመለስን ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ እማማ በከፊል ሕይወቷን ከሳተች በኋላ ነበር የሞተችው። ልነግራት የምፈልጋቸውን አንዳንድ ነገሮች እንኳን ሳልነግራት ነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሞተችው። ይህም ከአባባ ጋር ብዙ መጫወት እንዳለብኝ አስተምሮኛል። አባባ ከ65 የጋብቻ ዓመታት በኋላ እማማን በማጣቱ በጣም ይሰማው ነበር። ይሁን እንጂ እኛ አጠገቡ ሆነን እናፈቅረውና ድጋፍ እንሰጠው ነበር።

ክርስቲያናዊ ስብሰባ በመካፈል፣ በጥናትና በአገልግሎት አባባ የነበረው ምሳሌነት እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ቀጥሏል። ማንበብ ይወድ ነበር። እኛ አገልግሎት በምንሄድበት ጊዜ ብቻውን መሆን ነበረበት፤ ከአገልግሎት ስመጣ “ብቻህን ሆንክ አይደለም?” ብዬ እጠይቀዋለሁ። እሱ ግን በንባብና በጥናት ራሱን ስለሚያስይዝ የብቸኝነት ሐሳቡም እንኳን ወደ አእምሮው አይመጣም።

ሌላም ከእሱ ያገኘነው የዕድሜ ልክ ልማድ አለ። አባባ ቤተሰቡ አንድ ላይ ምግብ እንዲበላ ይገፋፋ ነበር። በተለይ ደግሞ የዕለት ጥቅስ በሚደረግበት በቁርስ ሰዓት ቤተሰቡ አንድ ላይ እንዲሆን ይፈልጋል። ልጅ እያለሁ የዕለት ጥቅስ ሳላደርግ ከቤት እንድወጣ በፍጹም አይፈቀድልኝም ነበር። አንዳንድ ጊዜ “ኧረ አባባ ትምህርት ቤት (ወይም ሥራ) ይረፍድብኛል” እል ነበር።

“የዕለት ጥቅስ ማድረጉ አይደለም የሚያስረፍድሽ፤ በጊዜ አለመነሳትሽ ነው” ይለኝ ነበር። ስለዚህ የግድ ቁጭ ማለትና መስማት ነበረብኝ። ይህን ጥሩ ምሳሌ እስከሞተበት የመጨረሻ ቀን ድረስ እንዲቀጥል አድርጓል። ይህም እሱ የተወልኝ ሌላው ውርስ ነው።

አባባ እስከሞተበት ቀን ድረስ አእምሮው ንቁ ነበር። እሱን መጦር ቀላል የነበረው በፍጹም ስለማይነዛነዝና ስለማያጉረመርም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ያለበትን የአርተራይተስ በሽታ ያነሳል። ይሁን እንጂ የያዘው በሽታ አርተራይተስ ሳይሆን “አዳማይተስ” [አዳም ያመጣው] መሆኑን ሳስታውሰው ይስቃል። ኅዳር 30, 1991 ጠዋት ጂንና እኔ አጠገቡ ቁጭ እንዳልን አባባ በሰላም አንቀላፋ።

አሁን ዕድሜዬ ከ70 ዓመት በላይ ነው። አፍቃሪ ክርስቲያን ወላጆቼ ከተዉልኝ ጥሩ ምሳሌ አሁንም ቢሆን እየተጠቀምኩ ነው። ከፊቴ ባሉት ዘመናት ሁሉ በዚህ ከወላጆቼ ባገኘሁት ውርስ በሚገባ በመጠቀም ለውርሱ ያለኝን አድናቆት ሙሉ በሙሉ ማሳየት እችል ዘንድ ልባዊ ጸሎቴ ነው። — መዝሙር 71:​17, 18

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እማማ ከእኔ ጋር

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. መስከረም 1923 ሳን ማርኮስ ቴክሳስ:- ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁበት የወረዳ ስብሰባ

2. ሰኔ 1991 ፎርት ዋርዝ ቴክሳስ:- አባባ የተገኘበት የመጨረሻው የወረዳ ስብሰባ (አባባ ተቀምጧል )

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጂንና ብሎሰም ብራንት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ