የተሻለ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ቀርቧል!
“ገነትን በጉጉት መናፈቅ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ከሚጉላሉት ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ናፍቆቶች አንዱ ነው። ከሁሉም ምኞቶች የበለጠ ኃይል ያለውና ለብዙ ዘመናት የቀጠለ ምኞት ሳይሆን አይቀርም። በየትኛውም ሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ አንድ ዓይነት ገነታዊ ናፍቆት ይታያል” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን ይናገራል።
ሁሉም ባሕሎች አንድ የጋራ ባሕርይ ያላቸው ይመስላል። ሁሉም በጥንት ዘመን ስለጠፋ ፍጹም የሆነ ዓለም በማዘን ወደፊት በተሻለ ዓለም ውስጥ የመኖር ፍላጎት አላቸው። ይህም የመጀመሪያ ገነት የነበረች መሆኗን ያመለክታል። ነገር ግን የመጀመሪያዋ ገነት የት ነበረች? ሳይኮአናሊስቶች ይህ ምኞት በእናት ማሕፀን ውስጥ የነበረውን ሥጋት የሌለበት ኑሮ መልሶ ለማግኘት የሚደረገውን ምኞት የሚገልጽ ናፍቆት ነው ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ አገላለጽ የሃይማኖትን ታሪክ የሚያጠኑትን ምሁራን አያሳምናቸውም።
“ገነት የሚናፈቅበት” ምክንያት
አንዳንዶች እንደሚሉት እንደዚህ የመሰለው ናፍቆት የሰብአዊ ኑሮን ክብደትና የሕይወትን አጭርነት ከማስረሳት የበለጠ ዋጋ አይኖረውምን? ከዚህ የበለጠ ትርጉም ይኖረው ይሆንን?
የሰው ዘር የተሻለ ዓለም ይመጣል ብሎ የሚናፍቀው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር የመጣው ከተሻለ ዓለም ስለሆነ ነው! በማለት አጭርና ግልጽ ምክንያት ይሰጣል። በእርግጥም ገነት የነበረችበት ዘመን ነበረ። ይህች ገነት በመካከለኛው ምሥራቅ በአንድ የተወሰነ ቦታ ላይ የምትገኝ አምላክ “ለማየት ደስ የሚያሰኘውን ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር” በማብቀል የባረካት ‘የአትክልት ቦታ’ እንደነበረች የአምላክ ቃል ይገልጻል። አምላክም የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲንከባከቧት ኃላፊነት ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 2:7–15) ሰዎች እውነተኛ ደስታ አግኝተው የሚኖሩባት ፍጹም የሆነች መኖሪያ ነበረች።
እንደዚህ ያለው ገነታማ ሁኔታ ዛሬ ያልኖረው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በማመፃቸው ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:1–6, 17–19) ከዚህ የተነሣ ሰው ገነትን ብቻ ሳይሆን ፍጽምናን፣ ጤንነትንና የዘላለም ሕይወትን ጭምር አጣ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የተከሰቱት ሁኔታዎች የሰውን ኑሮ በምንም መንገድ አላሻሻሉም። እንዲያውም የሰው ልጅ ሕይወት ከምንጊዜውም ይበልጥ በተበላሸና ባዘቀጠ ሁኔታ ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል።—መክብብ 3:18–20፤ ሮሜ 5:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5, 13
ገነትን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ የሐሳቡ ታሪክ
ለመገመት እንደሚቻለው “ገነትን በጉጉት መናፈቅ” የረጅም ጊዜ ታሪክ አለው። ሱሜራውያን በዓለም ላይ ሕብረትና ስምምነት የነበረበትን ጊዜ በማስታወስ “ፍርሃትና ረብሻ አልነበረም፣ ሰውም የበላዩ ለመሆን የሚፈልግ ተፎካካሪ አልነበረውም። . . . ዓለም በሙሉ፣ ሰዎች ሁሉ በአንድነት ሆነው ለኤንሊል በአንድ ቋንቋ ምስጋናቸውን ያቀርቡ ነበር” የሚል ቃል የጥንት መስጴጦምያን በጻፉት ግጥም ላይ ይገኛል። አንዳንዶች በጥንት ዘመን እንደነበሩት ግብጻውያን ከሞቱ በኋላ የተሻለ ዓለም ለማግኘት ተስፋ ያደርጉ ነበር። የማትሞተው ነፍስ የአሩ መስኮች ተብሎ ወደሚጠራ ቦታ ትደርሳለች ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጀመሪያ ላይ ይህን ዓይነት ዓለም ተስፋ ያደርጉ የነበሩት የባላባት ወገኖች ብቻ ነበሩ። ድሆች ግን እንደዚህ ያለውን አስደሳች ዓለም እናገኛለን ብለው ሊያስቡ አይችሉም ነበር።
በሌላው የሃይማኖት አቅጣጫ የተመለከትን እንደሆነ ሂንዱዎች ለብዙ መቶ ዘመናት የተሻለ ዓለም (ዩጋ) የሚመጣበትን ጊዜ ሲጠብቁ ኖረዋል። በሂንዱ ትምህርት መሠረት በማያቋርጥ ዑደት የሚደጋገሙ አራት ዩጋዎች ሲኖሩ ዛሬ እኛ የምንኖረው የመጨረሻ መጥፎ በሆነው ዩጋ ውስጥ ነው። ይህ ካሌ ዩጋ የተባለው መከራና ክፋት የበዛበት የጨለማ ዘመን አንዳንዶች እንደሚሉት እስከ 432,000 ዓመት ድረስ ይቆያል። ይሁን እንጂ ታማኝ ሂንዱዎች ክሪታ ዩጋ የተባለውን ወርቃማ ዘመን ይጠባበቃሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ግሪኮችና ሮማውያን በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ይገኛል ተብሎ በአፈ ታሪክ የሚነገረውን የብልጽግና ደሴት ያልማሉ። እንደ ሂሶይድ፣ ቨርጅል እና ኦቪድ ያሉ ብዙ ጸሐፊዎች ጥንት ስለነበረ ወርቃማ ዘመን ከተናገሩ በኋላ ይህ ዘመን ወደፊት እንደሚመለስ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከዘአበ ማለቂያ አካባቢ የላቲን ገጣሚ የነበረው ቨርጅል በቅርብ ስለሚመጣው አዲስና ዘላቂ አይታስ አውሪያ (ወርቃማ ዘመን) ትንቢት ተናግሮ ነበር። ከዚያ ቀጥለው በመጡት መቶ ዘመናት ከ“አሥራ ስድስት ያላነሱ የሮማ ነገሥታት የራሳቸው ግዛት ወርቃማውን ዘመን መልሶ እንዳመጣ ተናግረዋል” በማለት ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን ተናግሯል። ነገር ግን በዛሬው ዘመን የምንኖረው አሳምረን እንደምናውቀው ይህ አባባል ፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነበር።
ብዙ ሴልታውያን (የጥንት እንግሊዛውያን) ሰዎች ፍጹም ደስታ አግኝተው ይኖራሉ ብለው በሚያምኑበት ከባሕር ማዶ ባለ ደሴት (ወይም የደሴቶች ስብስብ) ውስጥ ደስ የሚያሰኝ አገር አለ ብለው ያስቡ ነበር። አንድ አፈ ታሪክ እንደሚለው ንጉሥ አርተር በከባድ ሁኔታ ቢቆስልም አቭለን የተባለችውን አስደናቂ ደሴት ካገኘ በኋላ በሕይወት ሊኖር ችሏል።
በጥንትና በመካከለኛው ዘመን ብዙ ሰዎች “ለመውጣት አስቸጋሪ በሆነ ተራራ ጫፍ ላይ ወይም ለመሻገር አስቸጋሪ ከሆነ ውቅያኖስ ማዶ” በአንድ ስፍራ ላይ ደስታ የሚገኝባት የአትክልት ቦታ የሆነች የኤደን ገነት ትገኛለች ብለው እንደሚያስቡ ዢን ዴሉሞ የተባሉት ታሪክ ጸሐፊ ያስረዳሉ። ዳንቴ የተባለው ኢጣልያዊ ባለቅኔ በሰማያዊ ገነት ቢያምንም ከመንጽሔ ተራራ ጫፍ ላይ ከኢየሩሳሌም ትይዩ ምድራዊ ገነት አለች ብሎ ያስብ ነበር። አንዳንዶች ገነት በእስያ፣ በመስጴጦምያ ወይም በሂማሊያ ተራሮች ውስጥ ትገኛለች ብለው ያምኑ ነበር። ስለ ኤደናዊ ገነት የሚናገሩ የመካከለኛው ዘመን አፈ ታሪኮች በጣም ብዙ ናቸው። ከዚያች ገነት አጠገብ ፕሪስተር ጆን በሚባል ንጉሥ የሚገዛ አስደናቂ መንግሥት እንዳለ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ነበሩ። የፕሪስተር ጆን ግዛት በገነት አቅራቢያ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት በዚህች መንግሥት የሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ረዥም፣ ደስታ የሞላበትና ከዓመት እስከ ዓመት የማያቋርጥ የብልጽግና ወንዝ የሚፈስበት ነው ተብሎ ይታመን ነበር። ሌሎች የጥንታውያኑን ግሪኮች አፈ ታሪክ በአእምሯቸው በመያዝ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ገነት የሆነች ደሴት ትገኛለች ብለው አስበዋል። በመካከለኛው ዘመን የተነሡ ካርታዎች የኤደን ገነት የምትገኝበትን ቦታ በማመልከት ይህ እምነት ምን ያህል እርግጠኛ እንደነበረ አሳይተዋል።
በ15ኛውና በ16ኛው መቶ ዘመን የአትላንቲክን ውቅያኖስ የሚያቋርጡ መርከበኞች ጥንታዊ ሆኖ ሳለ አዲስ የሆነውን ይህን ዓለም ለማግኘት ፈልገው ነበር። ከውቅያኖሱ ባሻገር የኢንዲስን ደሴቶች ብቻ ሳይሆን ኤደን ገነትንም እናገኛለን የሚል አሳብ ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል ክርስቶፈር ኮለምበስ በደቡብና በመካከለኛው አሜሪካ ነፋሻማ ከሆኑት ተራሮች መካከል ኤደንን ለማግኘት ፍለጋ አድርጓል። አውሮፓውያን አሳሾች ብራዚል ደርሰው የአየሩ ጠባይ ወይና ደጋ መሆኑን እንዲሁም ምግብና ተክሎች በብዛት መኖራቸውን ሲመለከቱ የጠፋችው ገነት ይህች ናት ብለው በእርግጠኝነት አስበው ነበር። ብዙም ሳይቆዩ ግን እውነተኛውን ሁኔታ ለመቀበል ተገደዋል።
ዩቶፒያዎች—ተስማሚ ቦታዎች ናቸውን?
ሌሎች ደግሞ በጣም ሩቅ በሆነ የምድር ክፍል ላይ ፍጹም የሆነ ዓለም ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ይህ ፍጹም የሆነ ዓለም የሚገኝበትን መንገድ ለመግለጽ ሞክረዋል። ከዚህም የተነሣ በ1516 የሰብአዊ መብት ተከራካሪ የነበረው እንግሊዛዊው ቶማስ ሞር እርሱ ከሚያውቀው ዓለም ፈጽሞ የተለየ ስለሆነውና ሰላምና ምቾት ስለሰፈነበት ዩቶፒያ የተባለ ደሴት ገልጿል። ሌሎችም እንዲሁ የተሻለና ደስ የሚያሰኝ ዓለም ምን ዓይነት መሆን እንደሚገባው ለመግለጽ ሙከራ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በፕላቶ የተደረሰው ሪፑብሊክ፣ በ1602 ደግሞ በኢጣልያዊው ቶማዞ ካምፓኔላ የተገለጸችው በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀችው የፀሐይ ከተማ፣ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ እንግሊዛዊው ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከን ኒው አትላንቲስ በተባለው መጽሐፉ የተናገረላት “ደስተኛዋና ለምለሟ ርስት” ይገኛሉ። ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ የተለያዩ ሃይማኖቶችና ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ሊቃውንት ዓይነታቸው ብዙ ስለሆኑ ፍጹም የሆኑ ዓለማት ጽፈዋል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የተናገሩት ነገር አልታመነላቸውም።
የራሳቸውን ፍጹም የሆነ ዓለም ለመገንባት የሞከሩ ሰዎችም ነበሩ። ለምሳሌ ያህል በ1824 ሮበርት ኦውን የተባለ ሀብታም እንግሊዛዊ ሰው በአሜሪካ ወደምትገኘው ኢንዲያና የተባለች አገር ለመሄድና አዲሱ ሕብረት (ኒው ሐርሞኒ) ብሎ በሰየመው መንደር ውስጥ የራሱን ፍጹም የሆነ ዓለም ለመመሥረት ወስኖ ነበር። ተስማሚ ሁኔታዎች ከተገኙ ሰዎች ሊሻሻሉ ይችላሉ የሚል እምነት ስለነበረው ያለውን ጥሪት ሁሉ ራሱ በአእምሮው የሣለውን አዲስ ሥነ ምግባራዊ ዓለም ለመመሥረት ተጠቅሞበታል። ነገር ግን የተገኘው ውጤት አዲስ የኑሮ ሁኔታዎች መኖራቸው ብቻ አዲስ ሰው ለማስገኘት በቂ አለመሆኑን አረጋግጧል።
ሁሉም የፖለቲካ ፍልስፍናዎች ለማለት ይቻላል፣ የሰው ልጆች የሚመኙትን ገነት ወደ ምድር ለማምጣት ባገኙት እውቀትና እውነት ዓላማቸውን መምራትና መቆጣጠር እንደሚኖርባቸው ያምናሉ። ሆኖም እንደነዚህ ያሉትን ምኞቶች እውን ለማድረግ የተደረጉት ሙከራዎች በ1789 የተደረገውን የፈረንሳይ አብዮትና በ1917 የተደረገውን የቦልሼቪክ አብዮት የመሳሰሉትን ጦርነቶችና አብዮቶች ማስከተሉ ያስደንቃል። እነዚህ ጥረቶች ገነታዊ ሁኔታዎችን ከማምጣት ይልቅ ሰዎችን እየጨመረ ለሚሄድ ሥቃይና መከራ ዳርገዋል።
ምኞቶች፣ እቅዶች፣ ፍጹም የሆነ ዓለም ለማስገኘት የተደረጉት ሙከራዎች ሁሉ ከኀዘንና ከብስጭት የተለየ ውጤት አላስገኙም። በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች “ያልተፈጸመ ሕልም” እና “ፍጹም የሆነ ዓለም መመኘት ያከተመበት ዘመን” በማለት “ፍጹም የሆነ ዓለም እናገኛለን ብላችሁ ሳታልሙ ኑሩ” የሚል ግብዣ እያቀረቡልን ነው። የተሻለ ዓለም የሚመጣበት ሌላ ተስፋ ይኖራል ወይስ ይህ የተሻለ ዓለም ሕልም ብቻ ሆኖ ይቀር ይሆን?
ክርስቲያኖችና የተሻለ ዓለም
የአዲስ ዓለም ምኞት ሕልም ብቻ ሆኖ አይቀርም። መፈጸሙ የማይቀር አስተማማኝ ተስፋ ነው። የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ ከአሁኑ ዓለም የተሻለ ዓለም ሊኖር እንደማይችል አልተናገረም። የዋሆች ምድርን እንደሚወርሱና የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንደሚፈጸም አስተምሯል። (ማቴዎስ 5:5፤ 6:9, 10) እሱም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ ይህ ዓለም የአምላክ ጠላት በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያለ መሆኑንና ዋነኛው የሰው ዘር ወዮታ ምክንያትም ይኸው መሆኑን ያውቁ ነበር። (ዮሐንስ 12:31፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 12:12) ታማኝ አይሁዶች አምላክ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምድርን ከጦርነት፣ ከሥቃይና ከበሽታ አጽድቶ ሰላምና ፍትሕ በሚወዱ ሰዎች እንድትሞላ የሚያደርግበትን ጊዜ በተስፋ ይጠብቁ ነበር። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ የአሁኑ ዓለም በአዲስ ሥርዓት ማለትም በ“አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚተካ በልበ ሙሉነት ይጠባበቁ ነበር።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ መዝሙር 37:11፤ 46:8, 9፤ ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24፤ 45:18፤ ራእይ 21:1
ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራው እንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ጊዜ እርሱን ላመነው ክፉ አድራጊ የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ በድጋሚ አረጋግጧል። “ኢየሱስም እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።” (ሉቃስ 23:40–43) ይህ ክፉ አድራጊ የሰማቸውን ቃላት የተረዳቸው እንዴት ነበር? አንዳንድ የካቶሊክና የፕሮቴስታንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ለማስመሰል እንደሚሞከሩት ኢየሱስ ክፉ አድራጊውን በዚያኑ ዕለት ‘ከእርሱ ጋር እንደሚሆን’ መናገሩ ነበርን? የለም፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም ‘ገና ወደ አባቱ እንዳላረገ’ ስለነገራት እንደዚያ ማለቱ አልነበረም። (ዮሐንስ 20:11–18) ሐዋርያት እንኳ ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ሲያስተምራቸው የቆየ ቢሆንም በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን በፊት በሰማያዊ ገነት የመኖር ሐሳብ አልነበራቸውም። (ሥራ 1:6–11) ያ ክፉ አድራጊ በዚያ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩት እንደ አብዛኞቹ አይሁዶች ኢየሱስ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የተሻለ ሕይወት እንደሚገኝ ቃል መግባቱ እንደነበረ ተረድቷል። አንድ ጀርመናዊ ምሁር “ከሞት በኋላ ብድራትን ስለመቀበል የሚናገሩ ትምህርቶች በብሉይ ኪዳን ውስጥ አልተጠቀሱም” በማለት አምነዋል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ምድር ገነት እንደምትሆን አረጋግጧል። የእምነት ጓደኞቹን ‘በኢየሱስ ክርስቶስ መነገር የጀመረውን ታላቅ መዳን ቸል’ እንዳይሉ በሚያበረታታበት ጊዜ ይሖዋ አምላክ “የሚመጣውን ዓለም [በግሪክኛ ኦይኮሜኔ]” በኢየሱስ ሥልጣን ሥር እንዲገዛ ማድረጉን አረጋግጦልናል። (ዕብራውያን 2:3, 5) በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ኦይኮሜኔ የሚለው ቃል ሁልጊዜ የሚሠራበት ሰዎች የሚኖሩበትን ምድር ለማመልከት እንጂ ሰማያዊውን ዓለም ለማመልከት አይደለም። (ከማቴዎስ 24:14፤ ሉቃስ 2:1፤ 21:26፤ ሥራ 17:31 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ የሚገዛው የአምላክ መንግሥት የሰዎች መኖሪያ የምትሆነውን ምድር ያስተዳድራል።
ይህች መንግሥት ሰማያዊ ብትሆንም በምድር ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ትገባለች። ይህስ ምን ውጤት ያስከትላል? አካለ ጐደሎነት፣ ግፍ፣ ድህነትና ሞት የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። ብስጭትና ቅሬታ ፈጽሞ ይወገዳል። (ራእይ 21:3–5) መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ እጆቹን ከፍቶ ሕይወት ላላቸው ሁሉ መልካም ነገርን ያጠግባል’ ይላል። (መዝሙር 145:16) እንደ ሥራ አጥነትና የአካባቢ መቆሸሽ ያሉ ችግሮች ተግባራዊና ዘላቂ መፍትሔ ያገኛሉ። (ኢሳይያስ 65:21–23፤ ራእይ 11:18) ከሁሉም በላይ የአምላክ በረከት ስለሚፈስ ፈጽሞ የጠፉ የሚመስሉት እንደ እውነት፣ ፍትሕና ሰላም ያሉት ባሕርዮች ድል ያደርጋሉ።—መዝሙር 85:7–13፤ ገላትያ 5:22, 23
ይህ ሁሉ ሕልም ወይም የማይፈጸም የፍጹም ዓለም ምኞት ነውን? አይደለም። ከዘመናት ሁሉ አስጨናቂ የሆነው ይህ አሁን የምንኖርበት ዘመን በዚህ ዓለም “የመጨረሻ ቀኖች” ውስጥ እንደምንኖርና አዲሱ ዓለም ቅርብ እንደሆነ ማረጋገጫ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) በዚህ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ትፈልጋለህን? ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እንዴት በዚህ ዓለም ውስጥ መኖር እንደሚቻል ተማር። ይህ የተሻለ ዓለም ከምናስበው በላይ ቀርቧል። ይህ ዓለም የማይፈጸም የፍጹም ነገሮች ሕልም ሳይሆን እውን ሊሆን የሚችል ዓለም ነው!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቅርቡ እውን የሚሆን የተሻለ ዓለም