የምታፈቅሯቸው በሞት የተለዩአችሁ ሰዎች የት ናቸው?
አሌክ መሪር ሐዘን ደርሶበት ነበር። በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት ጓደኞቹን አጣ። ከእነርሱ መካከል ኔቭል የተባለው በተተኮሰበት ጥይት ቆስሎ ሞተ። ቶኒ ደግሞ በመኪና አደጋ ሕይወቱ አለፈ። የ14 ዓመቱን የደቡብ አፍሪካ ልጅ ከዚህ በፊት አስጨንቀውት የማያውቁ ጥያቄዎች አሁን በጣም ይረብሹት ጀመር። ‘ሰዎች ለምን ይሞታሉ? ከሞቱስ በኋላ ምን ያጋጥማቸዋል?’ እያለ ያወጣና ያወርድ ነበር።
ኔቭል ወደሚቀበርበት ቦታ ሲሄድ አሌክ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። “ይሁን እንጂ” ሲል አሌክ ያስታውሳል፤ “ቄሱ እንደነገሩ አንድ መጽሐፍ አነበቡና ኔቭል ወደ ሰማይ ሄዷል አሉ። ከዚያም በመቃብሩ አጠገብ ቆመው፣ ትንሣኤውን እንጠባበቃለን በማለት ተናገሩ። ግራ ተጋባሁ። ኔቭል ወደ ሰማይ ከሄደ እንዴት ሆኖ ትንሣኤውን ሊጠባበቅ ይችላል?”
ከዚያ በኋላ አሌክ በዚያው ቀን በቶኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኘ። የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ እርሱ በማይገባው ቋንቋ ተከናወነ። ሆኖም ሊያስተዛዝኑ የመጡ አንዳንዶች ራሳቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ሲጮኹና ሲያለቅሱ ሲመለከት አሌክ ምንም ማጽናኛ የሚሆን ነገር እንዳላገኙ ተገነዘበ። “በዚያ ሌሊት” በማለት አሌክ ይገልጻል፤ “እጅግ ተረበሽኩ። የተጣልኩ ሆኖ ተሰማኝ፤ ምን እንደማደርግም ግራ ገባኝ። ለጥያቄዎቼ አንድም ሰው አጥጋቢ መልስ ሊሰጠኝ አልቻለም። በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አምላክ አለን? ብዬ አሰብኩ።”
በየዓመቱ ልክ እንደ አሌክ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያፈቅሯቸውን ሰዎች በሞት ይነጠቃሉ። “በዓለም ዙሪያ” ይላል የ1992 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር “በ1991 50,418,000 ሰዎች ሞተዋል።” ከዚያን ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ምን ያህል ሰዎች ሞተው ይሆን? ዘመዶቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በሞት ያጡ በሕይወት ያሉ ሰዎች ያፈሰሱትን የእንባ ጎርፍ እስቲ አስቡት! ስለሞት የሚሰጡት እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ የተለያዩ አመለካከቶች የሚፈጥሩት ግራ መጋባት ደግሞ ሐዘናቸውን ያባብሰዋል።
በመሆኑም እንደ አሌክ ያሉ ብዙዎች ግራ ገብቷቸዋል፤ ከሞት በኋላ ሌላ ሕይወት ስለመኖሩ መሠረት የሚሆን ነገር መኖሩም አጠራጥሯቸዋል። ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅንስ እንደሚለው ከሆነ “ባለፉት ዘመናት ሁሉ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ከብዙሃኑ ሕዝብ ራሳቸውን ገለል አድርገዋል፤ . . . የአንድ ሰው ነፍስ ወይም ሕይወት ከግለሰቡ አእምሮና አካል ተለይታ እንዴት ትኖራለች ብለው ያስባሉ።”
የሚገርመው ነገር፣ ከላይ የተገለጸው ኢንሳይክሎፒዲያ ዘላለማዊዋ ነፍስ ከሰው አካል ተለይታ ትኖራለች የሚለው ሃይማኖታዊ ንድፈ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንደሌለው ያምናል። እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጥቂት ቦታዎች ላይ የሰው “ነፍስ” ከሰውዬው አካል እንደተለየችና አልፎ ተርፎም እንደገና ወደ ሞተው ሰው አካል እንደተመለሰች ይናገራል፤ ይሁን እንጂ በእነዚህ ቦታዎች ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል የገባው “ሕይወት” የሚለውን ቃል በማመልከት የሕይወትን መጥፋት ወይም እንደገና መመለስ ለመግለጽ ነው። (ዘፍጥረት 35:16–19፤ 1 ነገሥት 17:17–23) “ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ብዙ ጊዜ የተሠራበት ሥጋና ደም ያላቸውን የሚታዩ ፍጥረታትን ለመግለጽ ነው። አዎን፣ ሕያዋን ፍጥረታትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዘፍጥረት 1:20፤ 2:7 የ1879 ትርጉም) ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ነፍስ እንደምትሞት ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 18:4, 20፤ ሥራ 3:23፤ ራእይ 16:3) የአምላክ ቃል ነፍሳት አንዴ ከሞቱ በኋላ “አንዳች አያውቁም” ሲል ይገልጻል።—መክብብ 9:5, 10
በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደገና ወደ ሕይወት ስለተመለሱ የሞቱ ሰዎች የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዟል። በአልዓዛር ላይ ይህ የተፈጸመው ለአራት ቀናት ሞቶ ከቆየ በኋላ ነበር። (ዮሐንስ 11:39, 43, 44) በመቶና በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የሞቱ ሰዎችስ ምን ያጋጥማቸው ይሆን? እነዚህ ሰዎች ወደፊት እንደገና በሕይወት መኖር እንዲችሉ አምላክ ከመሞታቸው በፊት የነበራቸውን ያንኑ አካል ይዘው እንዲነሡ ማድረግ ይኖርበታልን?
አይኖርበትም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሞተው አካል የተገነባባቸው አቶሞች ከሚደርስባቸው ሁኔታ ጋር አይስማማም። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ አቶሞች መካከል አንዳንዶቹን አረንጓዴ ተክሎች ይመገቧቸዋል። ከዚያም በመቀጠል አረንጓዴ ተክሎቹን ሌሎች ፍጥረታት ይመገቧቸውና አቶሞቹ የእነርሱ አካል ክፍል ይሆናሉ።
ይህ ማለት ከሞቱ ብዙ ጊዜ የሆናቸው ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም ማለት ነውን? አይደለም። ግዙፉን አጽናፈ ዓለማችንን የሠራው ፈጣሪ ይህ ነው የማይባል ወሰን የሌለው የማስታወስ ችሎታ አለው። ፍጹም በሆነው ያለፉ ነገሮችን ዘግቦ በሚያስቀምጠው አእምሮው ውስጥ ለማስታወስ የሚፈልገውን የማንኛውንም ሰው ጠቅላላ ተፈጥሮና ባሕርይ እንዲሁም በዘር የወረሳቸውን ጠባዮች በሙሉ የማስቀመጥ ችሎታ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ አምላክ አንድ ሰው ከመሞቱ በፊት የነበረውን ያንኑ ወደ ቀጣይ ዘሮች የሚተላለፉትን ሁለንተናዊ ባሕርያት የሚወስነውን ንድፍ የያዘ የሰው አካል እንደገና ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል አለው። በውስጡም አምላክ እንደ አብርሃም ያሉ የሚያስታውሳቸው ሰዎች የነበሯቸውን ትዝታዎችና ተፈጥሮአዊ ባሕርይዎች ማስቀመጥ ይችላል።
አብርሃም ከሞተ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቷል፦ “ሙታን እንዲነሡ . . . ሙሴ ደግሞ በቁጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም እምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፣ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።” (ሉቃስ 20:37, 38) ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ሌላ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች የሞቱ ሰዎችም አምላክ ለማስታወስ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ዘግቦ በሚያስቀምጥበት አእምሮ ውስጥ ሕያዋን ናቸው። ወደፊት የሚከናወነውን ትንሣኤ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን’ ይነሣሉ ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል።—ሥራ 24:15
አሌክ ጓደኞቹ ከሞቱበት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለጥያቄዎቹ መልስ አገኘ። አንድ የይሖዋ ምሥክር እቤቱ መጥቶ አነጋገረውና የአምላክ ቃል ስለሞትና ስለ ትንሣኤ ምን እንደሚል አሳየው። ይህ አሌክን ከማጽናናቱም በላይ ለሕይወቱ አዲስ ትርጉም አስገኘለት።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው የትንሣኤ ተስፋ የበለጠ ማወቅ ትፈልጋላችሁን? ለምሳሌ ያህል አብዛኛዎቹ ትንሣኤዎች የሚከናወኑት በሰማይ ነው ወይስ በምድር? አንድ ሰው በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘትና ሰዎች ከሚያፈቅሩአቸው በሞት የተለዩአቸው ሰዎች ጋር እንደገና ሊገናኙ የሚችሉበት አስደናቂ የአምላክ ተስፋ ሲፈጸም በዓይኑ ማየት እንዲችል ምን ማድረግ አለበት?