ይሖዋ ምድርን ከጥፋት ያድናል
በማልዲቭ ደሴት ላይ የሚገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ በየቀኑ ለረዥም ሰዓታት ይዘጋል። ለምን? የባሕሩ ውኃ በከፍተኛ መጠን ይጨምርና የአውሮፕላን ማኮብኮብያውን በማጥለቅለቅ አውሮፕላኖች ማረፍ እንዳይችሉ ስለሚያደርግ ነው። በመጪው መቶ ዓመት በማልዲቪያን ደሴቶች ያለው የውኃ መጠን ከባሕር ወለል በላይ ቢያንስ አንድ ሜትር ያህል ሊጨምር እንደሚችል አንዳንድ ሳይንቲስቶች ስጋታቸውን ገልጠዋል። ምንም እንኳን ይኼ አነስተኛ መጠን ቢመስልም ይህ ጭማሪ ሰባት ደሴቶችን ፈጽሞ ሊያጠፋቸው ይችላል። እንዲያውም ዩ ኤን ክሮኒክል የተባለው መጽሔት እንደገለጸው ከሆነ ከባሕር ወለል በላይ ሁለት ሜትር ያህል ከፍ ቢል ውኃው ወደ 1,200 የሚጠጉ ደሴቶችን ሊውጣቸው ይችላል!
የባሕር ወለሉ እንዲጨምር የሚያደርገው ምንድን ነው? የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥናት ፕሮግራም እንዳብራራው የምድር ሙቀት በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ በሞቃታማ አካባቢ ያሉትን ባሕሮች እንዲሰፉና በረዶዎች እንዲቀልጡ በማድረግ ውኃው ከባሕር ወለል በላይ እንዲጨምር ያደርጋል። ለንደን የሚገኘው ፓኖስ የተባለ ተቋም የከባቢ አየር ብክለት “ምድርንና ባሕርን የሚያዋስነውን ድንበር ቀስ በቀስ እየለወጠ የሚሄደውን ዓለም አቀፍ ጥፋት ሊያፋጥነው ይችላል” በማለት ተናግሯል።
የመላዋ ምድር ሙቀት መጨመር ሳይንቲስቶችን እያወያየ ያለ ጉዳይ ነው። ያም ሆነ ይህ የከባቢ አየር ችግር የአምላክን ዓላማ ሊያግድ እንደማይችል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍሬያማዋ ምድር በጽኑ ስለተመሠረተች አትናወጥም” በማለት ይናገራል። (1 ዜና መዋዕል 16:30 አዓት) ይሖዋ የምድርን ከባቢ አየር ይቆጣጠራል፤ በቅርቡ ምድርንም ሆነ የሰውን ዘር ከጥፋት ስለሚያድን ልንደሰት እንችላለን።—መዝሙር 24:1, 2፤ 135:6፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
[ምንጭ]
Drawing based on NASA photo