አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ዋጋ ያወጣል?
በቅርቡ የብሪቲሽ ቤተ መጻሕፍት ለዊልያም ቲንደል የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የእንግሊዝኛ ትርጉም አንድ ቅጂ 1,600,000 የአሜሪካን ዶላር (9,920,000 ብር) ለመክፈል ተስማምቶ ነበር። ከ468 ዓመታት በፊት የታተመውና ከመጀመሪያዎቹ የቲንደል መጽሐፍ ቅዱስ የተሟሉ እትሞች መካከል አንዱ የሆነው ይህ መጽሐፍ ደብዛው እንዲጠፋ ለማድረግ የተካሄደበትን ከፍተኛ ጥረት ተቋቁሞ ያለፈ ብቸኛ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ በለንደን ከተማ ለሕዝብ እንዲታይ ቀርቦ ነበር።
የቲንደል መጽሐፍ ቅዱስ የተገዛው ከ1784 ጀምሮ በቅርስነት ከተቀመጠበት በእንግሊዝ አገር ከሚገኘው የብሪስቶል ባፕቲስት ኮሌጅ ነው። የኮሌጁ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት ደክተር ሮጀር ሄይደን “ይህ መጽሐፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ባሕላዊና ክርስቲያናዊ የአገር ቅርስ ነው። እንዲህ በተከበረ ቦታ ጠብቀን እንዳስቀመጥነው ሁሉ በብዛትና በስፋት እንዲዳረስም እንፈልጋለን” ብለዋል።
ለብዙ መቶ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ በላቲን ቋንቋ ብቻ ይገኝ የነበረ ሲሆን ያንንም እንኳ ቢሆን ሊያነቡ የሚችሉት የሃይማኖት መሪዎችና ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው የተማሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ከሱ በፊት እንደነበረው እንደ ጆን ዊክሊፍ ቲንደልም ማንም ሰው በቀላሉ ሊያነበውና ሊረዳው የሚችል መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት ፈልጎ ነበር። አንድ ጊዜ ይቃወመው ለነበረ አንድ ቄስ ‘ከብዙ ዓመታት በፊት አምላክ በሕይወት እንድኖር ፈቅዶልኝ ቢሆን ኖሮ ምንም የማያውቀውን የባላገር ልጅ ቅዱሳን ጽሑፎችን አንተ ከምታውቀው የበለጠ እንዲያውቅ አደርገው ነበር’ ብሎታል።
የሃይማኖት መሪዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለተራው ሕዝብ ለማዳረስ የሚደረገውን ማንኛውንም ዓይነት ጥረት በኃይል በሚቃወሙበት በዚያ ወቅት እንዲህ ዓይነቱን እቅድ መወጠን በጣም አደገኛ ነበር። በዚህ ምክንያት ቲንደል ከእዝንግሊዝ ወደ ጀርመን ኮበለለ። እዚያ ሆኖም ከግሪክኛው በኩረ ጽሑፍ ‘አዲስ ኪዳንን’ ተረጎመ። ወደ 3,000 የሚሆኑ ቅጂዎች ታተሙና በድብቅ ወደ እንግሊዝ ገቡ። የለንደኑ ጳጳስ ያገኙትን እያንዳንዱን ቅጂ ገዝተው በቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሕዝብ ፊት አቃጠሉት። በመጨረሻም ቲንደል ተይዞ ተንገላታ፤ መናፍቅ ነው ተብሎም ተወነጀለ። ከዚያም በ1536 በእንጨት ላይ ሰቅለው አቃጥለው ገደሉት። ያ በሃይማኖት መሪዎች እንደዛ ይጠላ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ይህን ያህል ዋጋ ማውጣቱ እንዴት የሚያስደንቅ ነው!
የይሖዋ ምሥክሮች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ ለማዳረስ በቅንነት ይጥራሉ። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ከማተምና ከማሰራጨት በተጨማሪ ትክክለኛና በቀላሉ ሊነበብ የሚችል ሙሉዉን መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች በቀጥታ ተርጉመው አዘጋጅተዋል። እስከ 1995 ድረስ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም በ12 ቋንቋዎች ከ74,000,000 ቅጂዎች በላይ ታትሟል። በእርግጥ የማንኛውም መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ዋጋ ሕይወት ሰጪ መልእክቱ ነው።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዊልያም ቲንደል
[ምንጭ]
From an old engraving in the Bibliothèque Nationale