አንድ ባላባት የወደፊት ዕጣቸውን መረመሩ
የምዕራብ አፍሪካው ባላባት በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ውስጥ እጅግ የተወደዱና በጣም የተከበሩ አለቃ ነበሩ። በ78ኛ የልደት በዓላቸው ላይ ጓደኞቻቸው፣ ቤተሰባቸውና ሌሎች በጎ አሳቢዎች እንኳን ደስ ያለዎት ለማለት ተሰባሰቡ። ባላባቱ በንግግራቸው ውስጥ በእንዲህ ዓይነት በዓል ላይ ያልተለመደ አንድ ርዕስ መረጡ። ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ያላቸውን አስተያየት ተናገሩ።
ከሞት በኋላ “ማታለል፣ ቅናትና ሥሥት የሌለበት አዲስ ዓለም አለ” በማለት ተናገሩ። ይህንን ዓለም ከአምላክ ጋር ተስማምተው በሚኖሩ ጻድቆች ብቻ የተሞላ “ምሥጢራዊ” ዓለም አድርገው ገልጸውታል።
እንዲህ ያሉ እምነቶች በመላው አፍሪካ በሚኖሩ ሕዝቦች ዘንድ የተለመዱ ናቸው። የአፍሪካ ባህላዊ ሃይማኖት እንደሚለው ከሆነ ሞት የሕይወት መቋጫ ሳይሆን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ወደሚገኝ ሕይወት የሚታለፍበት መሸጋገሪያ ብቻ ነው። አንድ ሰው ሲሞት ግለሰቡ ከገሀዱ ዓለም ወደማይታየው ዓለም ተሻገረ ይባላል። ግለሰቡ(ቧ) መንፈስ ሆኖ(ና) የቀድሞ አባቶቹ(ቿ) ወደሚኖሩበት ርስት ይገባል (ትገባለች)።
አያሌ ምዕራብ አፍሪካውያን የቀድሞ አባቶቻቸው ወይም የቀድሞ አባቶቻቸው መናፍስት በምድር ላይ የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ያስጠብቃሉ ብለው ያምናሉ። ዌስት አፍሪካን ትራዲሽናል ሪሊጅን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “እዚህ ምድር ላይ ያሉትና በወዲያኛው ዓለም የሚኖሩት የማኅበረሰቡ አባላት በሰዎች ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ረገድ ይህን ያህል የጎላ ልዩነት የላቸውም። እዚህ ምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ [የቀድሞ አባቶች] የቤተሰቦቻቸው አለቆች ነበሩ። አሁን ለእኛ ባይታዩም እስካሁን ድረስ በመናፍስት ዓለም ውስጥ አለቆች ናቸው። ለቤተሰቦቻቸው ጠቅላላ ደህንነት ማሰባቸውን አያቆሙም።”
በዚህም ምክንያት በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ሽማግሌው ባላባት ከቀድሞ አባቶቻቻው ጋር ለመኖርና በመንፈሳዊው ዓለም ከእነርሱ ጋር ለመሥራት ተስፋ አድርገው ነበር። “ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት እንዲሁም ከሞት በኋላም እንኳ ባላባት ሆኜ መቀጠል እንደምችል የጸና እምነት አለኝ” አሉ።
ነገር ግን ባላባቱ ቀጥሎ በተናገሩት ነገር የተነሳ ሰንደይ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት “ሙሉ እምነት ያላቸው አይመስሉም” በማለት ሐሳብ ሰጥቷል። ለተሰበሰበው ሕዝብ ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት የሚናገር አንድ መጽሐፍ እንዳለ መስማታቸውን ተናገሩ። ባላባቱ መጽሐፉን ለማግኘት ለአምስት ዓመታት ሲፈልጉ ነበር። ይህንን መጽሐፍ ለማንበብ ጓጉተው ስለነበር የዚህን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ለሚያመጣላቸው ማንኛውም ሰው 1,500 የአሜሪካ ዶላር የሚያክል ገንዘብ እንደሚሰጡ ቃል ገቡ።
ባላባቱ ለማግኘት አስቸጋሪ ያልሆነ አንድ መጽሐፍ በመመርመር ራሳቸውን ከብዙ ውጣ ውረድ ለማዳን ችለዋል። ይህ መጽሐፍ በቀላሉ የሚገኝ ሲሆን የተዘጋጀው በሰው ሳይሆን ሁሉንም ሰዎች በፈጠረው አምላክ ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:13) መጽሐፉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን ይላል?