የቀድሞ አባቶቻችን የሚያገኙት አዲስ ሕይወት
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው ሲሞት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ እንደተለመደው በሕይወት መኖሩን ይቀጥላል ብሎ ያስተምራልን? እንደዚህ ብሎ አያስተምርም። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት አስደናቂ ተስፋ ያቀርባል፤ ነገር ግን ብዙዎች ይሆናል ብለው በሚያስቡት መንገድ አይ ደለም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጀመሪያው የቀድሞ አባታችን አዳም ምን እንደሚል ተመልከት። ይሖዋ “ከምድር አፈር” ሠራው። (ዘፍጥረት 2:7) አዳም በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ የመኖር አጋጣሚ ነበረው። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ነገር ግን በአፍቃሪ ፈጣሪው ላይ ዓመፀ፤ ውጤቱም ሞት ነበር።
አዳም በሞተ ጊዜ የሄደው ወዴት ነበር? አምላክ “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህና” ብሎታል።—ዘፍጥረት 3:19
ይሖዋ እርሱን ከአፈር ከመፍጠሩ በፊት አዳም የት ነበር? የትም አልነበረም። ኅልውና አልነበረውም። ስለዚህ አዳም ‘ወደ መሬት ይመለሳል’ ብሎ ይሖዋ ሲናገር ልክ እንደ አፈር ዳግም ሕይወት አልባ ይሆናል ማለቱ ብቻ ነበር። አዳም በቀድሞ አባቶች መናፍስት ዓለም ውስጥ አንጋፋ አባት ለመሆን ወደ ሌላ ዓለም ‘አልተሻገረም’። ሰማይ ውስጥ ወደሚገኝ የተድላና የደስታ ሕይወትም ሆነ በመሠቃያ ቦታ ወደሚገኝ ዘላለማዊ መከራ አልሄደም። የተሸጋገረው ከሕያውነት ወደ በድንነት፣ ከመኖር ወዳለመኖር ብቻ ነበር።
የተቀሩት የሰው ዘሮችስ? የአዳም ዘሮችም በሚሞቱበት ጊዜ ኅልውናቸው ያከትማልን? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልስ ይሰጣል፦ “ሁሉ [ሰዎችም ሆኑ እንስሳት] ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።”—መክብብ 3:19, 20
ሙታን ያሉበት ሁኔታ
አዎን፣ ሙታን ሕይወት አልባ ናቸው፤ መስማት፣ ማየት፣ መናገር ወይም ማሰብ አይችሉም። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳቸ አያውቁም፤ . . . ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል” ይላል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በመቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም” በማለት ይገልጻል።—መክብብ 9:5, 6, 10
የአምላክ ቃል በሚናገረው መሠረት ሰዎች በሕይወት ሳሉ ሞት እንዳለ ያውቃሉ። በሚሞቱበት ጊዜ ግን አንዳች አያውቁም። አስከሬናቸው ምን እንደሚደረግ እየተመለከቱ በራሳቸው አስከሬን አጠገብ አይቆሙም። ከኅልውና ውጪ ከሆንን ተድላም ሆነ ሕመም፣ ደስታም ሆነ ሐዘን የለም። ሞተው ያሉ ሰዎች ጊዜው እያለፈ እንዳለ አያውቁም። ያሉበት ሁኔታ ድብን አድርጎ ከሚወስድ እንቅልፍ በበለጠ ምንም ሊያውቁ የማይችሉበት ሁኔታ ነው።
በጥንት ጊዜ አምላክን ያገለግል የነበረው ኢዮብ ሰዎች ከሞት በኋላ በሌላ ቦታ በሕይወት መኖር የማይቀጥሉ መሆናቸውን ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ያለ አምላክ ጣልቃ ገብነት ወደ ሕይወት የመመለስ ተስፋ እንደሌለ ተገንዝቧል። ኢዮብ “ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፤ ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፣ እርሱስ ወዴት አለ? ሰውም ተኝቶ አይነሣም” ብሏል። (ኢዮብ 14:10, 12) ኢዮብ በሚሞትበት ጊዜ በመናፍስት ዓለም ውስጥ ከቀድሞ አባቶቹ ጋር እንደሚገናኝ በፍጹም አልጠበቀም ነበር።
የትንሣኤ ተስፋ
ሕያዋን ኅልውናቸው የሚያበቃው በሞት ከሆነ አሳሳቢው ጥያቄ “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?” በማለት ኢዮብ ቀጥሎ ያነሳው ጥያቄ ነው። ኢዮብ ራሱ የሚከተለውን መልስ ሰጠ፦ “እስከምታደስበት ጊዜ ድረስ፣ ይህን የትግል ዘመኔን [በመቃብር የማሳልፈውን ዘመን] ፍጻሜ በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። በዚያን ጊዜ አንተ [ይሖዋ] ትጠራኛለህ፣ እኔም ‘አቤት’ እልሃለሁ፣ ፍጡርህ የሆንኩትን እኔን ለማየት ትናፍቃለህ።”—ኢዮብ 14:14, 15 የ1980 ትርጉም።
በሌላ አባባል ኢዮብ ወደ አለመኖር ቢለወጥም እንኳ አምላክ አይረሳውም። ይሖዋ አምላክ በትንሣኤ አማካኝነት መልሶ ወደ ሕይወት ‘የሚጠራው’ ጊዜ እንደሚመጣ ኢዮብ እምነት ነበረው።
ኢዮብ በትንሣኤ ላይ የነበረው ተስፋ ትክክለኛ እንደነበረ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አሳይቷል። ኢየሱስ ሙታን ሊነሱ እንደሚችሉ አረጋግጧል። እንዴት? ራሱ ሙታንን በማስነሳት ነው! ኢዮብን ለማስነሳት በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በምድር ላይ ባይኖርም ምድር ላይ ሳለ በናይን ከተማ የምትኖር የአንዲት መበለትን ወንድ ልጅ ከሞት አስነስቷል። በተጨማሪም ኢየሱስ የኢያኢሮስን የ12 ዓመት ሴት ልጅ ከሞት አስነስቷል። እንዲሁም ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረውን ጓደኛውን አልዓዛርን ከሞት አስነስቷል።—ሉቃስ 7:11–15፤ 8:41, 42, 49–56፤ ዮሐንስ 11:38–44
ኢየሱስ እነዚህን ተአምራት ከመፈጸሙም በተጨማሪ ወደፊት የሚፈጸም አንድ ታላቅ ትንሣኤ አመልክቷል። እንዲህ አለ፦ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር” አዓት] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል።” (ዮሐንስ 5:28, 29) ከጊዜ በኋላም አንድን ወጣት ከሞት እንዲያስነሳ ይሖዋ የተጠቀመበት ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ፊት በሚፈጸመው ትንሣኤ ላይ እምነት እንዳለው ገልጿል። “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ . . . ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ብሏል።—ሥራ 20:7–12፤ 24:15
ወደፊት ስለሚፈጸመው ትንሣኤ የሚናገሩት እነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎች በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ በሕይወት ስለመቀጠል የሚናገሩት ነገር የለም። የሚጠቁሙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሙታን እዚሁ ምድር ላይ በሥጋዊ አካላቸው ወደ ሕይወት የሚመለሱበትን ጊዜ ነው። ከሞት የሚነሱት እነዚህ ሰዎች ቀድሞ በምድር ላይ ስላሳለፉት ሕይወት ትዝታ የሌላቸው ሰዎች አይሆኑም። ሕፃናት ሆነው እንደገና አይወለዱም። ከዚህ ይልቅ የቀድሞውን ትዝታና ስብዕና በመያዝ ሲሞቱ የነበሩትን ዓይነት ሰዎች ይሆናሉ። የራሳቸውን ማንነት ለይተው የሚያውቁ ይሆናሉ፤ ሌሎችም ለይተው ያውቋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደገና ሲቀላቀሉ እንዴት ያለ ደስታ ይሆናል! እንዲሁም የቀድሞ አባቶቻችንን ማግኘቱ እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!
ለሰማያዊው ሕይወት ትንሣኤ ማግኘት
አንዳንዶች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ኢየሱስ አልተናገረምን? አዎን፣ ተናግሯል። የሞቱ ዋዜማ በሆነው ምሽት ላይ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ . . . ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:2, 3) ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ እየተናገረ ነበር እንጂ ሁሉም ጥሩ ሰዎች ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ማለቱ አልነበረም።
ሰማያዊውን ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ጥሩ ዓይነት ሕይወት መምራት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብቃቶችንም ማሟላት እንዳለባቸው ኢየሱስ አሳይቷል። አንዱ ብቃት ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ነው። (ዮሐንስ 17:3) ሌሎቹ መሟላት ያለባቸው ብቃቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመንና አምላክን መታዘዝ ናቸው። (ዮሐንስ 3:16፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ከዚህም በተጨማሪ የተጠመቀና በአምላክ መንፈስ የተወለደ ክርስቲያን በመሆን ‘ዳግመኛ መወለድ’ ሌላኛው ብቃት ነው። (ዮሐንስ 1:12, 13፤ 3:3–6) ለሰማያዊው ሕይወት የሚያስፈልገው ሌላኛው ብቃት እስከ ሞት ድረስ እንኳ ለአምላክ ታማኝ በመሆን ልክ እንደ ኢየሱስ መጽናት ነው።—ሉቃስ 22:29፤ ራእይ 2:10
እነዚህ ብቃቶች እንዲህ ላቅ ማለታቸው ምክንያት አለው። ሰማያዊውን ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች የሚያከናውኑት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሥራ አለ። ሰብዓዊ መንግሥታት በምድር ላይ ያሉትን ጉዳዮች በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር ፈጽሞ እንዳልቻሉ ይሖዋ ያውቃል። ስለዚህ የሰውን ዘር የሚገዛ ሰማያዊ መስተዳድር ወይም መንግሥት አዘጋጀ። (ማቴዎስ 6:9, 10) ኢየሱስ የዚያ መንግሥት ንጉሥ ይሆናል። (ዳንኤል 7:13, 14) ከምድር ተመርጠው ሰማያዊ ትንሣኤ ያገኙ ጥቂት ሰዎች አብረውት ይገዛሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ከሞት የሚነሱ ሰዎች ‘ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት እንደሚሆኑና በምድርም ላይ እንደሚነግሡ’ አስቀድሞ ተናግሯል።—ራእይ 5:10
ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለሰማያዊው ትንሣኤ የወጣውን ብቃት ያሟሉ ይሆን? አያሟሉም። ከራሳቸው ጉድለት የተነሳ ባይሆንም በሞት አንቀላፍተው ካሉት ውስጥ ብዙዎቹ ብቁ አይሆኑም። ብዙዎቹ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን ለመማር የነበራቸው አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነበር፤ ወይም ደግሞ ምንም አጋጣሚ አላገኙም። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወይም ስለ አምላክ መንግሥት ምንም ዓይነት እውቀት ሳያገኙ ኖረው ሞተዋል።
ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚሄዱትን ሰዎች “ታናሽ መንጋ” ብሎ ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32) በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ለመግዛት ‘ከምድር የተዋጁት’ ሰዎች ቁጥር 144,000 እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተገልጿል። (ራእይ 14:1–3፤ 20:6) 144,000 ኢየሱስ የጠቀሰውን “ብዙ መኖሪያ” ለመሙላት የሚበቃ ቁጥር ቢሆንም በቢልዮን ከሚቆጠሩት የአዳም ዝርያዎች ጋር ሲወዳደር ግን ትንሽ ነው።—ዮሐንስ 14:2
ከምድራዊው ትንሣኤ በፊት የሚከናወኑ ሁኔታዎች
እስቲ እስከ አሁን የተወያየንበትን እንከልስ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሞተው ያሉ ሰዎች ይሖዋ አምላክ ከሞት እስከሚያስነሳቸው ድረስ በድን ናቸው። ጥቂቶቹ በንጉሣዊው መስተዳድር ውስጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው በሚገዙበት በሰማይ ለመኖር ከሞት ይነሳሉ። አብዛኞቹ ሰዎች የዚህ መንግሥት ዜጎች ለመሆን በምድር ላይ ከሞት ይነሣሉ።
በምድራዊው ትንሣኤ አማካኝነት ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ በከፊል ይፈጽማል። ይሖዋ ምድርን የፈጠራት ‘መኖሪያ እንድትሆን’ ነው። (ኢሳይያስ 45:18) የሰው ዘር ቋሚ መኖሪያ እንድትሆን ነበር። ከዚህ የተነሳ መዝሙራዊው “የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 115:16
የምድራዊ ሕይወት ትንሣኤ ከመጀመሩ በፊት ታላላቅ ለውጦች መከናወን አለባቸው። የአምላክ ዓላማ ምድራችን በጦርነት፣ በአካባቢ መበከል፣ በወንጀልና በዓመፅ እንድትሞላ እንዳልነበረ ሳትስማማ አትቀርም። እነዚህ ችግሮች የመጡት ለአምላክና ለጽድቅ ሕግጋቱ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ነው። ስለዚህ የአምላክ መንግሥት ‘ምድርን የሚያጠፏትን በማጥፋት’ ፍቃዱ በምድር ላይ እንዲሆን ትልቅ እርምጃ ትወስዳለች። (ራእይ 11:18) መንግሥቲቱ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ጻድቃንን አስቀርታ ክፉ አድራጊዎችን በሙሉ ታጠፋቸዋለች።—መዝሙር 37:9, 29
ምድራዊ ገነት
በጸዳችው ምድር ላይ ትንሣኤ አግኝተው የሚነሱት ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ ሰዎችን የሚያፈቅሩ የዋሆች ይሆናሉ። (ከማቴዎስ 5:5 ጋር አወዳድር።) በአምላክ መንግሥት ፍቅራዊ የበላይ ጥበቃ ሥር ደህንነት አግኝተው በደስታ ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት በዚያን ጊዜ የሚፈጸሙትን አስደናቂ ሁኔታዎች አሻግረን እንድንመለከት ያደርገናል፦ “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:4
አዎን፣ ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። (ሉቃስ 23:43) ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ! ሆስፒታሎችና የአቅመ ደካሞች መንከባከቢያ ተቋሞች ጊዜ ያለፈባቸው ይሆናሉ። በዕድሜ መግፋት ምክንያት በሚመጡ ችግሮች እየተሠቃዩ ያሉ ሰዎች በገነት ውስጥ እንደገና ጠንካራና ጤናማ ይሆናሉ። (ኢዮብ 33:25፤ ኢሳይያስ 35:5, 6) የሬሳ ማቆያ ቤቶች፣ የቀብር ቦታዎችና የመቃብር ሐውልቶች አይኖሩም። ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት “ሞትን ለዘላለም ይውጣል።” (ኢሳይያስ 25:8) እንዲህ ያሉ በረከቶች ለእኛና ለቀድሞ አባቶቻችን በእርግጥም አዲስ ሕይወት ማለት ሊሆኑ ይችላሉ።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሞት ተነስተው በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች የመንግሥቲቱ ዜጎች ይሆናሉ