ከሂማልያ ተራሮች የሚበልጥ ከፍታ ወዳለው ተራራ መውጣት
የሂማልያ ተራሮች! እነዚህ ቃላት ስለ ምን እንድታስብ ያደርጉሃል? ኃይለኛ ንፋስ ስለሚነፍስባቸውና አናታቸው በበረዶ ስለተሸፈኑ ባለ ግርማ ሞገስ የተራራ ጫፎች? ከምድራችን ተራሮች ከፍተኛ የሆነው ተራራ ጫፍ ላይ ወጥተህ ይታይሃልን? አብዛኞቻችን ኔፓል ውስጥ ከሚገኙት የሂማልያ ተራሮች አንዱ የሆነውን የኤቨረስትን ተራራ መውጣት አንችልም። ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ኔፓል ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከሂማልያ ተራሮች ይበልጥ ከፍታ ወዳለው አንድ ተራራ እየወጡ ነው! ወደ ታላቁ ተራራ ስለሚደረገው ስለዚህ ጉዞ ከማወቃችን በፊት በጣም ትንሽ ብትሆንም ውብ ስለሆነችው የኔፓል ንጉሣዊ መንግሥት እንመርምር።
ተራራማ መንግሥት የሆነችው ኔፓል
የኔፓል መንግሥት አስገራሚ ነው፤ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ ከቀሩት ጥቂት የዘውድ አገዛዞች አንዱ ከመሆኑም በተጨማሪ ይህ መንግሥት ዓለማዊ ሳይሆን ሃይማኖታዊ መንግሥት ነው። ኔፓል ከዓለማችን ብቸኛዋ ሂንዱ መንግሥት ናት። ከ20 ሚልዮን ነዋሪዎቿ መካከል አብዛኞቹ ሂንዱዎች ናቸው። ቢሆንም የሕዝቦቿ የዘር ግንድ በከፍተኛ ሁኔታ ይለያያል። በሰሜናዊው ተራራማ አካባቢ በብዛት የሚገኙት ቲቤቶ ቡርማን የተባሉ ዝርያዎች ሲሆኑ አብዛኞቹ በደቡባዊው ሜዳማ ስፍራዎች የሚኖሩት ደግሞ የኢንዶ አርያን ዝርያ አላቸው። ኔፓሊ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ከመሆኑም በላይ ከሕዝቡ 60 ከመቶ ለሚያክሉ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው። የተቀረው ሕዝብ ከ18 የሚበልጡ የተለያዩ የጎሳ ቋንቋዎች ይናገራል።
ኔፓል አራት ማዕዘን ቅርፅ ያላት ትመስላለች፤ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ 880 ኪሎ ሜትር፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ ደግሞ 200 ኪሎ ሜትር ስፋት አላት። በሰሜናዊው ድንበር የሚገኙት ግርማ ሞገስ የተላበሱት የሂማልያ ተራሮች 8,848 ሜትር ከፍታ ያለውን በርዝመት በዓለም ላይ ካሉት ተራሮች ከፍተኛ የሆነውን የኤቨረስት ተራራና ሌሎች ከ8,000 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ስምንት ተራሮች ይዘዋል። በመካከለኛው ኔፓል አነስተኛ ተራራዎች፣ ሐይቆችና ሸለቆዎች ይገኛሉ። ህንድን በሚያዋስነው ሩቅ ደቡብ ለም የሆነው ቴሪ ተብሎ የሚጠራ ዋነኛ የእርሻ ክልል ይገኛል።
በአገሪቱ እምብርት አካባቢ የምትገኘው ዋና ከተማዋ ካትማንዱ ቱሪስቶች የሚደሰቱባት ሥፍራ ነች። በጣም ውብ በሆኑት ተራሮች ላይ ለመብረር፣ የዱር አራዊቶች ወደሚኖሩባቸው መናፈሻ ቦታዎችና የቱሪስት መስሕብ ወደሆኑ ቦታዎች ለመጓዝ የሚያስችሉ የአውሮፕላን በረራዎች አሏት። ሃይማኖት በሕዝቧ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወት ኔፓል አልፎ አልፎ የአማልክት ሸለቆ ትባላለች። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሂማልያ ተራሮች ወደሚበልጠው “ተራራ” አድካሚ ጉዞ እንዲያደርጉ ያንቀሳቀሳቸው ሃይማኖት ነው።
የዛሬ 2,700 ዓመታት ገደማ ዕብራዊው ነቢይ ኢሳይያስ “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ” የሚል ትንቢት ለመናገር በመንፈስ ተገፋፍቶ ነበር። (ኢሳይያስ 2:2, 3) እዚህ ላይ ክብራማው የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪና ሉዓላዊ ገዢ የሆነው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ከየትኞቹም ተራራ መሰል የአምልኮ ዓይነቶች ከፍ ብሎ በሚገኝ አንድ ተራራ ተመስሏል። ይህም እውነትን የተራቡ ሰዎች ስለ ይሖዋ መንገዶች እንዲማሩ እየረዳ ያለው ዓለም አቀፍ የማስተማር ሥራ ርዕሰ ትምህርት ነው። ይህ ሥራ በኔፓል የተጀመረው እንዴት ነበር?
አነስተኛ ጅማሬዎች
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ውስጥ የነበረ አንድ ወታደር እውነተኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ይፈልግ ነበር። የኔፓል ዜጋ የሆኑት የሂንዱ እምነት ተከታይ ወላጆቹ ወደ ካቶሊክ እምነት ተለውጠው ነበር። እያደገ ሲሄድ የጣዖት አምልኮን ከንቱነት አወቀ፣ እንደ ሲኦል እሳት የመሳሰሉትን መሠረተ ትምህርቶች አልቀበልም አለና የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትን እምነቶች መመርመር ጀመረ። ነገር ግን በዚህ አልረካም።
ጃፓኖች በጊዜው ራንጎን ተብላ ወደምትጠራው የአሁኗ በርማ እስረኛ አድርገው ሲወስዱት ይህ ወታደር እውነተኛውን አምልኮ ለማግኘት የሚያደርገውን ፍለጋ መቀጠል እንዲችል የጉልበት ሥራ ቅጣት በሚሰጥበት ካምፕ ውስጥ ካለው መከራ በሕይወት እንዲተርፍ ጸለየ። ከጊዜ በኋላ ማርከው ከያዙት ሰዎች እጅ አመለጠና አንድ አስተማሪ ይረዳው ጀመር፤ እዚህ አስተማሪ ቤት በጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የተዘጋጀውን ሙታን የት ናቸው? (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለ ቡክሌት አገኘ። በ1947 በራንጎን ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቱ መጥተው ባነጋገሩት ጊዜ የእውነትን ድምፅ ስላወቀ ለማጥናት በጉጉት ተስማማ። በጥቂት ወራት ውስጥ ተጠመቀ፤ ወጣት የነበረችው ሚስቱም ወዲያውኑ ተጠመቀች። ወደ ህንድ ተመልሰው የትውልድ ስፍራቸው በሆነው በሰሜናዊ ምሥራቅ ተራሮች በሚገኘው ካሊምፖንግ ከተማ ለመኖር ወሰኑ። ሁለቱ ልጆቻቸው ከልጅነት እስከ እውቀት ያሳለፉት እዚህ ነበር። መጋቢት 1970 ወደ ካትማንዱ ተዛወሩ።
የኔፓል ሕገ መንግሥት የሰውን እምነት ለማስቀየር መስበክ ይከለክል ነበር። የውጪ ሃይማኖት የሚሉትን ሃይማኖት አንድ ሰው ሲያሰራጭ ከተገኘ ሰባት ዓመት የሚታሰር ሲሆን እንዲህ ያለ ሃይማኖት የሚከተል ሰው ደግሞ ከባድ ከሆነ የገንዘብ ቅጣት ጋር ሦስት ዓመት ሊታሰር ይችላል። ስለዚህ ምሥክርነቱ በጥንቃቄ መሠራት ነበረበት። ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት የሚከናወነው አንድ ቤት ከተንኳኳ በኋላ ወደ ሌላ አካባቢ ደግሞ ሄዶ ሌላ ቤት በማንኳኳት ነበር። መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነትም እንዲሁ ምሥራቹን ለማሰራጨት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
እድገቱ አዝጋሚ ነበር። ይህ መስክ አሥር ሚልዮን የሚያክል ሕዝብ የሚኖርበት ሆኖ ሳለ እድገቱ አዝጋሚ መሆኑ ተስፋ አስቆራጭ ይመስል ነበር። የዚህ ብቸኛ ቤተሰብ አባላት ለጓደኞቻቸው፣ ለሚያውቋቸው ሰዎች፣ ለአሠሪዎቻቸውና ለሥራ ባልደረቦቻቸው በመመሥከራቸው ምክንያት የእውነት ዘር ሊዘራ ቻለ። እቤታቸው ውስጥ መደበኛ ስብሰባዎችን በማድረግ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ይጋብዙ ነበር። ከአራት ዓመታት ትጋት የተሞላበት የመትከልና የማጠጣት ሥራ በኋላ መጋቢት 1974 በኔፓል የመጀመሪያው ፍሬ የተገኘ ሲሆን ፍሬውም የተገኘው ከአንድ አጠራጣሪ ምንጭ ነበር!
አስፋፊው አንድ ቤት ሲያንኳኳ የንጉሣዊው ቤተሰብ ጸሐፊ ከሆኑ አንድ ሀብታም ሰው ጋር ተነጋገረ። ሰውዬው “ከልጄ ጋር ተነጋገር” አሉት። ልጁ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። የሚሠራው በአንድ የቁማር መጫወቻ ቦታ ስለነበር ከጊዜ በኋላ ሥራውን ቀየረ። ቀናተኛ ሂንዱ የሆኑት አባቱ ተቃወሙት። ምንም እንኳ ተቃውሞ ቢኖርበትም ይህ ወጣት ከይሖዋ ጎን ቆመ። ጽናቱ ምን አስገኘለት? ከጊዜ በኋላ አባቱ ያደርሱበት የነበረውን ተቃውሞ አቆሙ፤ እንዲሁም ዘጠኝ የቅርብ ዘመዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበሉ። በአሁኑ ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል።
በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆነው ለመቀጠልና መሰብሰባቸውን እንዳያቆሙ የሚያዘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ለመከተል በካትማንዱ የሚገኘው አነስተኛ ቡድን አባላት በመኖሪያ ቤት ውስጥ መደበኛ ስብሰባ ያደርጉ ነበረ። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ወንድሞች በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አይችሉም ነበር። በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አቅሙ ያላቸው ወንድሞች የተራራ ሰንሰለቶችን የሚያቋርጥ ረጅምና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ ጉዞ በማድረግ ወደ ህንድ ይሄዳሉ።
የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም በሙሉ በሚሰበሰቡባት ቤት ውስጥ ለመቅረብ መቻሉ እንዴት የሚያስደስት ነበር! አንድ የህንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባልን ጨምሮ አራት ወንድሞች መላውን ፕሮግራም ሲያከናውኑ በአእምሮህ ተመልከት! ሌላው ቀርቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ እንኳ ቀርቦ ነበር። ድራማው እንዴት ቀረበ? ህንድ ውስጥ ድራማውን ሲለማመዱ የስላይድ ፎቶግራፍ ተነስቶ ነበር። እነዚህ የስላይድ ፊልሞች በካሴት ከተቀረጸ ድምፅ ጋር በኔፓል እንዲታዩ ተደረጉ። ተመልካቾቹ ወደዱት። ምን ያህል ተመልካቾች ነበሩ? አሥራ ስምንት ሰዎች!
የስብከቱን ሥራ ለማገዝ የተገኘው የውጪ አገር ምሥክሮች ድጋፍ ውስን ነበር። ሚስዮናውያንን መመደብ የማይቻል ከመሆኑም በላይ የውጪ አገር ዜጋ ሆኖ ሰብዓዊ ሥራ ማግኘቱ ቀላል አልነበረም። ቢሆንም ሁለት ህንዳውያን የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ ጊዜያት ኔፓል ውስጥ ሥራ ስላገኙ አዲስ የተመሠረተው ጉባኤ እንዲጠናከር በመርዳት በካትማንዱ ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል። በ1976 በካትማንዱ 17 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ። በ1985 ወንድሞች የራሳቸውን የመንግሥት አዳራሽ ሠሩ። የመንግሥት አዳራሹ ተሠርቶ ሲያልቅ ዓመታዊው የአውራጃ ስብሰባና ሌሎች ትልልቅ ስብሰባዎች እዚያው በቋሚነት ይደረጉ ጀመር። በጣም ሩቅ በሆነው በዚህ ተራራማ አካባቢ አዳራሹ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነበር።
አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ዕድገት ማድረግ
ምሥክሮቹ ሥራቸውን በጀመሩባቸው በእነዚህ የመጀመሪያ ዓመታት የስብከቱ ሥራ በታላቅ ጥንቃቄ ይሠራ ስለነበር ይህን ያህልም የባለሥልጣኖችን ትኩረት አልሳበም ነበር። ነገር ግን ከ1984 ማብቂያ ወዲህ ዕገዳዎች መጣል ጀመሩ። አንድ ወንድምና ሦስት እህቶች ተይዘው አራት ቀናት ማረፊያ ቤት ካሳለፉ በኋላ ሁለተኛ እንዳይሰብኩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ተለቀቁ። አንድ መንደር ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች ቤታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲያደርጉ ተያዙ። ስድስቱ ለ43 ቀናት ታሰሩ። ሌሎችም ብዙዎች ተያዙ፤ ነገር ግን ክስ አልቀረበባቸውም።
በቅርቡ በ1989 በአንድ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወንድሞችና እህቶች በቁጥጥር ሥር ውለው ከሦስት ቀናት በኋላ ተለቀቁ። አንድ ጊዜ ደግሞ ወደ ፊት አንሰብክም ብለው እንዲፈርሙ ተጠይቀው ነበር። ወንድሞች አንፈርምም አሉ። አንዳንዶች እንደገና ሲሰብኩ ከተያዙ የሚደርስባቸውን መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ በመሆን ፈርመው ወዲያውኑ ተለቀቁ።
እንዲህ ያለ ተቃውሞ ቢኖርም ወንድሞች የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት መስበካቸውን ቀጠሉ። ለምሳሌ በ1985 ማለትም መንግሥት ጣልቃ መግባት ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ በስብከቱ ሥራ ላይ 21 በመቶ ጭማሪ ተገኝቷል። 35ቱ አስፋፊዎች ለሌሎች ስለ ንጹሕ አምልኮ በመናገር በወር በአማካይ 20 ሰዓታት ያሳልፉ ነበር።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ኔፓል ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ መከሰት ጀመረ። የመንግሥት ባለሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮች አስጊ እንዳልሆኑ መገንዘብ ጀመሩ። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራቸው በሕዝቡ ውስጥ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረና የይሖዋ ምሥክሮችን የተሻለ ዜጎች እያደረጋቸው ያለ ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ተገነዘቡ። ሐቀኝነት፣ ጠንክሮ መሥራትና ትክክለኛ ሥነ ምግባር ከይሖዋ አምላኪዎቸ የሚፈለጉ ዋነኛ ብቃቶች ተደርገው ትኩረት እንደሚሰጥባቸው ባለሥልጣኖች ተመለከቱ።
ቀድሞ ቀናተኛ ሂንዱ የነበሩ አንዲት ሴት አሁን የይሖዋ ምሥክር ሆነው ደም አልወስድም በማለታቸው ጥሩ ሕዝባዊ ምሥክርነት ተሰጥቷል። ዶክተሮች ሴትየዋ በወሰዱት በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አቋም ተገረሙ። እኚህ ሴት በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው ብሮሹር በመታገዝ እውነትን ተምረው ነበር። ከቤተሰባቸው ተቃውሞ ቢደርስባቸውና መሣቂያ ቢያደርጓቸውም 70 ዓመት ሊሞላቸው ትንሽ ሲቀራቸው በ1990 ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ እግራቸው ተሰበረ፤ በዚህና በሌሎች ውስብስብ ችግሮች የተነሳ ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ነበረባቸው። ዶክተሮችና ዘመድ አዝማድ ደም እንዲወስዱ ሲያቀርቡላቸው የነበረውን ውትወታ ለሁለት ሳምንታት ተቋቋሙ። በመጨረሻ የቀዶ ሕክምና ቡድኑ ያለ ደም የተሳካ ቀዶ ሕክምና አደረገላቸው። ምንም እንኳ አሁን እንደ ልባቸው መንቀሳቀስ ባይችሉም እኝህ ታማኝ እህት ጠዋት ጠዋት በራፋቸው ላይ ይቀመጡና አብረዋቸው ተቀምጠው ጥቂት የምሥራች እንዲያዳምጡ አላፊ አግዳሚውን ይጋብዛሉ።
ኔፓል በዛሬው ጊዜ
ዛሬ ኔፖል ውስጥ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? በኔፓል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ እንዳሉ ወንድሞቻቸው ሁሉ በተወሰነ መጠን የአምልኮ ነፃነት አግኝተዋል። አንድ ወይም ሁለት ምሳሌያዊ ተራራ ወጪዎች የእውነተኛውን አምልኮ ተራራ እየወጡ ካሉት ጋር መተባበር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እየጨመረ የሚሄድ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ‘ኑ፣ ወደ ይሖዋ ተራራ እንውጣ’ እያሉ ነው። በ1989 በእያንዳንዱ ወር በአማካኝ 43 የሚሆኑ ሰዎች በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ የነበረ ሲሆን በዚያው ዓመት በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 204 ሰዎች ተገኝተዋል።
ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ከዚያን ጊዜ ወዲህ እውነትን ለማግኘት የሚጥሩትን ሰዎች ወደ ቤቱ የመሰብሰቡን ሥራ ማፋጠን ጀምሯል። (ኢሳይያስ 60:22) በቅርቡ በካትማንዱ ሁለተኛው ጉባኤ ከመቋቋሙም በላይ በአሁኑ ጊዜ ከዋና ከተማው ውጪ ሁለት ገለልተኛ ቡድኖች አሉ። በ1994 ሚያዝያ ወር የስብከት ሥራቸውን በተመለከተ ሪፖርት ያደረጉት 153 ክርስቲያኖች ሲሆኑ ይህም ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 350 በመቶ ጭማሪ መሆኑ ነው! ፍላጎት ላሳዩ 386 ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መርተዋል። በ1994 በተደረገው የመታሰቢያው በዓል ላይ 580 ሰዎች መገኘታቸው ያስደንቃል። ለልዩ ስብሰባ ቀን 635 ሰዎች አዳራሹን ሞልተውት የነበረ ሲሆን ከመካከላቸው 20 ሰዎች ተጠምቀዋል። ስለዚህ በዓለም ዙሪያ በይሖዋ ምሥክሮች እየተገኘ ያለው ታላቅ እድገት በትንሿ ኔፓልም እየተከናወነ ነው።
ትሑት የሆኑ ሰዎች እውነትን አጥብቀው እንዲይዙ ለመርዳት በቅርብ ዓመታት በኔፓሊ ቋንቋ የሚዘጋጁ ጽሑፎች መጠን በጣም ጨምሯል። ተርጓሚዎች በህንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በትርጉም ሥራ ጥበብና በኮምፒዩተር አጠቃቀም ሰልጥነው አሁን በካትማንዱ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነዋል። የኔፓል ቲኦክራሲያዊ ተራራ ወጪዎች ለዕድገት በመዘጋጀት ወደ ፊት እየገፉ ናቸው!
ከሂማልያ ተራሮች የሚበልጥ ተራራ መውጣት
አንተም ብትሆን ከሂማልያ ተራሮች የሚበልጠውን ተራራ መውጣት ትችላለህ። እንዲህ ብታደርግ ኔፓል ውስጥ ከሚገኙት ብቻ ሳይሆን “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም” ከተውጣጡ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ትተባበራለህ። (ራእይ 7:9) ከእነርሱ ጋር በመሆን ኔፓል ውስጥ ያሉትን የሚመስሉ ባለ ግርማ ሞገስ ተራሮችን በፈጠረው አምላክ የተማርክ ትሆናለህ። ወደፊት ፈጣሪ “ነገሮችን ሲያስተካክል” ከማየትህም በተጨማሪ በጸዳችው ውብ ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር በጉጉት መጠባበቅ ትችላለህ።—ኢሳይያስ 2:4 አዓት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ካትማንዱ
የኤቨረስት ተራራ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካትማንዱ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በስተውጪ በኩል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ኔፓላውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተጠቀሙ ናቸው