ደስተኛ አወዳሾች ያደረጉት ስብሰባ
የጥንቶቹ የይሖዋ አምላክ ሕዝቦች ለአምልኮ ሲሰበሰቡ ‘ፈጽሞ ደስ እንዲላቸው’ ታዝዘው ነበር። (ዘዳግም 16:15) በ1995/96 በተደረገው “ደስተኛ አወዳሾች” የአውራጃ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚደሰቱባቸው ምክንያቶች ቀርበዋል።
በተለያዩ ቦታዎች በተከታታይ የተደረጉት እነዚህ ስብሰባዎች እምነታቸውን አጠንክረውላቸዋል። እንዲሁም ደስታ በሌለበት ዓለም ውስጥ እንዴት ደስታ ማግኘት እንደሚቻል አሳይተዋል። እስኪ የስብሰባውን ቀናት አንድ በአንድ እንመልከት።
‘እግዚአብሔርን አመስግኑ . . . ደስ ይበላችሁ!’
ከላይ የተገለጸው የስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ጭብጥ የተመሠረተው በመዝሙር 149:1, 2 የ1980 ትርጉም ላይ ነበር። “በደስታ እልል የምንልበት ምክንያት አለን” የሚለው ንግግር በኢሳይያስ ምዕራፍ 35 ውስጥ ያለው ትንቢት ምን ትርጉም እንዳለው ትንተና ሰጥቷል። ይህ ትንቢት በጥንቷ እስራኤል ላይ ከመፈጸሙም በላይ በተለይ ባለንበት ጊዜ የይሖዋ አምላኪዎች በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ወደሚገኘው ብልጽግና እና ጤንነት ሲመለሱ ፍጻሜውን አግኝቷል። ስለዚህ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች ይሖዋ ለሕዝቦቹ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ባዘጋጀላቸውና በቅርቡ በሚመጣው ምድራዊ ገነት ውስጥ በሚያዘጋጅላቸው ነገሮች የተነሳ በደስታ እልል የሚሉበት ምክንያት ነበራቸው።
“በመላው ዓለም ደስተኛ አወዳሾች በመሆን ልዩ ለሆነ ዓላማ መለየት” የሚለው የስብሰባውን ጭብጥ የሚገልጸው ንግግር ከዚህ ዓለም የተለየን የሚያደርገን ነገር ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ከዚህ ዓለም የተለየን የሚያደርገን አንድ ሆነን ይሖዋን ማምለካችን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛውም የምድር ክፍል ቢኖሩ ንግግራቸውና ትምህርታቸው እርስ በርሱ ይስማማል። በተጨማሪ ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ቅዱስ ስሙን ለመባረክና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ ባለው ታላቅ ዓላማ ይደሰታሉ። ይሖዋ ባወጣው ዓላማ ውስጥ ድርሻ እንዲኖረን ያደረገው እንዴት ነው? በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ያለውን እውነት ሰጥቶናል። አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ሰጥቶናል። ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትና ንጹሕ አምልኮ በማዘጋጀት ባርኮናል። ዓለም አቀፉ ቤተሰባችን ልባችን በታላቅ ደስታ ተሞልቶ ይሖዋን እንድናገለግል ይረዳናል።
“ከዓለም ዕድፍ ተለይቶና ከዕድፈቱ ራስን ጠብቆ መኖር” የሚል ጭብጥ ያለው ንግግር የአድሎአዊነትንና ጎራ የመለየትን ዕድፍ የማስወገድን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። (ያዕቆብ 2:5-9) አንዳንዶች ድሀ የሆኑትን ወይም የእነርሱ ዓይነት አጋጣሚ ያላገኙትን መሰል ክርስቲያኖች ችላ በማለት ተመሳሳይ አስተዳደግ ወይም የኑሮ ደረጃ ካላቸው ጋር ብቻ ሊወዳጁ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ወዳላቸው ጠጋ ጠጋ ማለት ይቀናቸው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች አንድ ሰው ሊኖሩት ከሚችሉት መብቶች ሁሉ የሚበልጠው መብት የይሖዋ ምሥክር ሆኖ መቆጠሩ እንደሆነ ዘንግተዋል። ስለዚህ ዓለማዊ ዝንባሌዎች እንዲያሳድፉንና የጉባኤውን ሰላም እንዲያናጉ መፍቀድ የለብንም።—2 ጴጥሮስ 3:14
“ለጋብቻ ዝግጁ ነኝን?” የሚለው ንግግር ብዙዎች ተቻኩለው እንደሚያገቡ ገልጿል። አንዳንዶች የሚያገቡት በቤት ካለ አንድ አስቸጋሪ ሁኔታ ለመገላገል አሊያም ደግሞ እኩዮቻቸው ስላገቡ ነው። ነገር ግን የጋራ የሆኑ ቲኦክራሲያዊ ግቦች፣ እውነተኛ ፍቅር፣ የቅርብ አጋርና የተረጋጋ ኑሮ የማግኘት ፍላጎት እንዲሁም ልጅ የመውለድና የማሳደግ ምኞት ለጋብቻ ከሚገፋፉን ተገቢ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ለጋብቻ ዝግጅት ሲደረግ መንፈሳዊ ሥልጠና ማግኘት የግድ አስፈላጊ ነገር ነው። አዲሱን ሰው በመልበስ ተፈላጊ ባሕርያትን መኮትኮትም ያስፈልጋል። በተጨማሪም ለጋብቻ የታሰበው ሰው ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳለውና ለሌሎች አክብሮት እንደሚያሳይ ማረጋገጥ ጥበብ ነው። ከበሰሉ ክርስቲያኖች ምክር መጠየቁም ጥበብ ነው።—ምሳሌ 11:14
መንፈሳዊ ማስተዋል ከሚያስገኘው ከዚህ ንግግር ቀጥሎ “በልጆቻቸው የሚደሰቱ ወላጆች” የሚለው ንግግር ቀጠለ። አብዛኛውን ጊዜ ልጅ መውለድ ደስታ ያመጣል። ይሁን እንጂ ልጅ መውለድ ትልቅ ኃላፊነትም ያስከትላል። (መዝሙር 127:3) ልጆች ይሖዋን እንዲወዱ ማስተማር አስፈላጊ ነው። ወላጆች ዘወትር ለልጆቻቸው ስለ ይሖዋ በመንገርና በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቤተሰቡ ውስጥ በተግባር ላይ በማዋል እንደዚህ ሊያደርጉ ይችላሉ።
የመጀመሪያው ቀን የተደመደመው የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለው አዲስ ብሮሹር መውጣቱን በማብሰር ነበር። ብሮሹሩ የይሖዋ ምሥክሮች “ወጣቶቻቸው ተግተው እንዲሠሩና በትምህርት ቤት የሚሰጧቸውን ሥራዎች ችላ እንዳይሉ ያበረታታሉ” በማለት ያብራራል። በተጨማሪም ይህ ጽሑፍ የይሖዋ ምሥክሮች በናይጄሪያ፣ በሜክሲኮና በሌሎች አገሮች ለበርካታ ዓመታት ባከናወኑት የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራሞች ስለተገኙት አስደናቂ ውጤቶች ይናገራል። ብሮሹሩ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጥ መሆናችንን አስተማሪዎች እንዲገነዘቡ ይረዳል።
“የምስጋና መሥዋዕት ዘወትር ለእግዚአብሔር እናቅርብ”
ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የሁለተኛው ቀን ጭብጥ የተመሠረተው በዕብራውያን 13:15 የ1980 ትርጉም ላይ ነበር። በጠዋቱ ፕሮግራም ላይ “ይሖዋን እንድናወድስ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ መስጠት” በሚል ጭብጥ አንድ ሲምፖዚየም ቀርቧል። ዕድሜ ለዚህ ጥሪ ምላሽ ከመስጠት አያግድም። መዝሙር 148:12, 13 ጎበዛዝት፣ ቆነጃጅት፣ ሽማግሌዎችና ልጆች ይሖዋን እንዲያወድሱ ጥሪ ያቀርባል። አብዛኞቹ የይሖዋ ደስተኛ አገልጋዮች የሚያቀርቡትን ውዳሴ ከፍ ለማድረግ ችለዋል። በዓለም ዙሪያ ከ600,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ወይም በአቅኚነት አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። ከ15,000 የሚበልጡት በልዩ አቅኚነት መስክ እንዲሁም ወደ 15,000 የሚጠጉ በቤቴል አገልግሎት ተሰማርተው ይገኛሉ።
“ከይሖዋ ድርጅት ጎን በታማኝነት ቆሞ ማገልገል” የሚለው ንግግር የአምላክ አገልጋዮች በታማኝነት መቆም እንደሚያስፈልጋቸው አሳይቷል። ለይሖዋ በታማኝነት መቆም ማለት እንደ ኃይለኛ ማጣበቂያ ሙጭጭ አድርጎ በሚይዝ ኃይለኛ ፍቅር ከእርሱ ጋር መጣበቅ ማለት ነው። ታማኝ ሆኖ መቆም ሌሎች ቢያዩንም ባያዩንም ሆነ ብለን የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዛት ከማፍረስ መቆጠብን ይጠይቅብናል። በተጨማሪም ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚቀርቡልንን በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች የሚወጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጨምሮ ሌሎች መንፈሳዊ ምግቦችን በታማኝነት መደገፍ ይጠይቅብናል። ከዚያም የጥምቀት ንግግር ቀረበ። የጥምቀት ዕጩዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በግልጽ ሲያሳዩ እንዴት ያስደስት ነበር!
በሆሴዕ 4:1-3 ላይ የሚገኙት ቃላት ከሰዓት በኋላ በቀረበው “የምትከታተሉት በጎነትን ነው ወይስ ምግባረ ብልሹነትን?” በሚለው ንግግር ውስጥ በምሳሌነት አገልግለዋል። ዓለም በጎነትን አቅልሎ ቢመለከተውም ክርስቲያኖች ሥነ ምግባራዊ በጎነትን “በትጋት” መከታተል አለባቸው። (2 ጴጥሮስ 1:5) በጎነት አንድ ሰው በአእምሮው ከሚያሳድረው ሐሳብ ይጀምራል። አንድ ሰው አስተሳሰቡ በጎ ከሆነ ንጹሕ፣ ጤናማና የሚያንጹ ቃላት ከመናገሩም በላይ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ሐቀኛ ለመሆን ይጥራል። በተጨማሪም በጎነትን መከታተል አንድ ዓይነት ውጥረት ወይም የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ክርስቲያኖች ያሉባቸውን ችግሮች መረዳትንና ርኅራኄ ማሳየትን ያጠቃልላል።—1 ተሰሎንቄ 5:14
“ራሳችሁን ከዲያብሎስ ወጥመዶች ጠብቁ” የሚለው ሌላኛው ንግግር ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለአጋንንታዊ ተጽዕኖዎች እንዳያጋልጡ አስጠንቅቋል። ክርስቲያኖች በሕክምናው መስክ እንደ ሂፕኖቲዝም ከመሳሰሉ በምትሐታዊ ኃይል የሚከናወኑ የሕክምና ዘዴዎች መጠንቀቅ አለባቸው። በተረፈ ግን ክርስቲያኖች ጤንነታቸውን ለመንከባከብ የሚያደርጉት ውሳኔ የግል ጉዳይ ነው።
ልበ ቅን ሰዎች ፈጣን እድገት አድርገው ራሳቸውን እንዲወስኑና እንዲጠመቁ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ በኪስ ሊያዝ የሚችል አዲስ መጽሐፍ መውጣቱ የሁለተኛው ቀን ስብሰባ በደስታ እንዲደመደም አድርጓል። ይህ ባለ 192 ገጽ አዲስ መጽሐፍ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የሚል ርዕስ አለው። እውቀት የተባለው መጽሐፍ እውነትን ገንቢ በሆነ መንገድ ያቀርባል። የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን ማጋለጥን በተመለከተ ብዙም ትኩረት አይሰጥም። አቀራረቡና የሐሳቦቹ ቅደም ተከተል በጣም ግልጽ ስለሆኑ መጽሐፉን ተጠቅሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራትና ሰዎች ከአምላክ የሚገኘውን አስደሳች እውቀት እንዲጨብጡ ለማድረግ አስቸጋሪ አይሆንም።
“ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ”
እነዚህ ከኢሳይያስ 65:18 የተወሰዱ ቃላት የሦስተኛው ቀን ስብሰባ ጭብጥ ነበሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እየተፈጸሙ መሆናቸው ይህ ክፉ ሥርዓት ከ1914 ጀምሮ ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት እንደገባ ያሳያሉ። ስለዚህ “በዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ዘመን የሚኖሩ ደስተኛ አወዳሾች” በሚል ርዕስ የቀረበው ሲምፖዚየም አድማጮች በተመስጦ ተከታትለውት ነበር። ተናጋሪዎቹ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስግብግብና ዓመፀኛ በሆነው የዓለም መንፈስ እንዴት እንደተዋጡ አሳይተዋል። እነዚህ ሰዎች ሰይጣን የሚቆጣጠረው ዓለም ክፍል እንደመሆናቸው መጠን በመጨረሻ ለፍርድ ይቀርባሉ። ስለዚህ ያለንበት ጊዜ ምርጫ የሚደረግበት ጊዜ ነው። በየትኛው ወገን መሆን እንፈልጋለን? ይሖዋን ማምለክና ሉዓላዊነቱን መደገፍ እንፈልጋለንን? ወይስ ሰይጣንን የሚያስደስት ነገር በማድረግ ገዢያችን እንዲሆን እየፈቀድንለት ነው? ሁላችንም በማያሻማ ሁኔታ በይሖዋ ጎን መቆም አለብን።
“የዘላለሙን ንጉሥ አወድሱ!” የሚለው የስብሰባው የሕዝብ ንግግር በስብሰባው ላይ የተገኙትን ሁሉ የሚያሳስብ ጠንካራ ምግብ አቅርቧል። ዘላለማዊነት ምንም እንኳ ከሰብዓዊ አእምሯችን የመረዳት ችሎታ በላይ ቢሆንም ይሖዋ በሚገባ ይረዳዋል። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 10:16) ይህ የዘላለም ንጉሥ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት መንገድ ከፍቶላቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) ተናጋሪው “አዎን፣ እኛ ኃጢአተኛ የሆንን የሰው ልጆች መለኮታዊ ትምህርት በመቀበልና በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በማመን ለዘላለም ሕይወት ልንበቃ እንችላለን” በማለት ተናግሯል።
ስብሰባው ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች “ዕለት ዕለት ይሖዋን በደስታ ማወደስ” በሚለው የመደምደሚያ ንግግር ታንጸው ነበር። ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በምድር ዙሪያ እያሳየ ስላለው እድገት ሪፖርት መስማቱ የሚያበረታታ ነበር። የስብሰባው ተካፋዮች ‘ይሖዋን በየቀኑ ለመባረክና ስሙን ለዘላለም ዓለም ለማመስገን [‘ለማወደስ’ አዓት ] ተገፋፍተው ነበር።’—መዝሙር 145:2
በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ዓለምን ደስታ አሳጥተዋታል። ሆኖም በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ያላቸው ግለሰቦች አምላካዊ ደስታ ማግኘት ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን በመዝሙር 35:27, 28 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን ቃላት ደግመው ሊናገሩ ይችላሉ፦ “ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሤትንም ያድርጉ፤ የባሪያውን ሰላም የሚወድድ እግዚአብሔር ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ። ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን [“ውዳሴህን” አዓት] ይናገራል።”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ብዙ ቤተሰቦች “የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት” ከተባለው ብሮሹር ጥቅም ማግኘት ይችላሉ
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት” የተባለው አዲሱ መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ገንቢ በሆነ መንገድ ያቀርባል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት ተጠምቀዋል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች “ብድራት የሚገባቸውን አረጋውያን በክብር መያዝ” በተሰኘው ድራማ በጣም ተነክተዋል