በሕግ የተገኘ ድል
ሚያዝያ 1995 አንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ድል ተገኘ። ነገሩ የጀመረው የ24 ዓመቷ ሉስ ኔሬዳ አሲቬዶ ክዊለስ ጥር 28, 1992 በራሷ ምርጫ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በፖርቶሪኮ ወደሚገኘው ኤል ቡአን ፓስተር ሆስፒታል ስትገባ ነበር። የይሖዋ ምሥክር ስለሆነች ደም እንደማትወስድ ወደ ሆስፒታሉ እንደገባች በቃሏም ሆነ በጽሑፍ ገልጻ ነበር። (ሥራ 15:28, 29) ሕክምና ያደረገላትን ዶክተር ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሆስፒታሉ ሠራተኞች ፍላጎቷን አሳምረው ያውቁ ነበር።
ሉስ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት ከሁለት ቀናት በኋላ ብዙ ደም ስለፈሰሳት ኃይለኛ የደም ማነስ ያዛት። በወቅቱ ይከታተላት የነበረው ዶክተር ሆሴ ሮድሪጌዝ ሮድሪጌዝ እሷን መርዳት የሚቻለው ደም በመስጠት ብቻ እንደሆነ አመነ። ስለዚህ ሉስ ሳታውቅ ወይም ሳትስማማ ደም ለመስጠት የሚያስችለውን የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት ፈለገ።
ምንም እንኳ ሉስ ሕሊናዋን ያልሳተችና ስለ ራሷ መናገር የምትችል ብትሆንም ዶክተር ሮድሪጌዝ ሮድሪጌዝ በጉዳዩ አጣዳፊነት ምክንያት የማንንም ፈቃድ ለመጠየቅ ምንም ጊዜ የለኝም አለ። የአውራጃው አቃቢ ሕግ የሆኑት ኤድዋርዶ ፔሬዝ ሶቶ ቅጹን ከሞሉ በኋላ የአውራጃው ዳኛ የሆኑት ክቡር ኤንጅል ሉዌስ ሮድሪጌዝ ራሞስ ደም ለመስጠት የሚያስችለውን የፍርድ ቤት ትእዛዝ አስተላለፉ።
በዚህ መንገድ ጥር 31, 1992 ሉስ ኦፕራሲዮን ወደሚደረግበት ክፍል ተወሰደችና ደም ተሰጣት። ሉስ ደም ሲሰጣት ከሆስፒታሉ ሠራተኞች አንዳንዶቹ ሲስቁ ሰማች። ሌሎች ሠራተኞች ደግሞ እየተደረጋላት ያለው ነገር እሷን የሚጠቅም እንደሆነ በመናገር አሾፉባት። ደም ላለመውሰድ የምትችለውን ያህል ብትታገልም ያደረገችው ጥረት ሁሉ ከንቱ ሆነ። ሉስ አመሻሹ ላይ አራት ዩኒት ደም ወስዳ ነበር።
ሉስ ደም መውሰድን በተመለከተ የገጠማት ሁኔታ በፖርቶሪኮ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያም የመጨረሻም አልነበረም። በእሷ ላይ ይህ ሁኔታ ከመድረሱ በፊት በዕድሜ የጎለመሱ የይሖዋ ምሥክሮች አለፍላጎታቸው ደም እንዲወስዱ 15 የፍርድ ቤት ትእዛዞች ተላልፈው ነበር። ይህ ሁኔታ ከደረሰ በኋላም ቢሆን ከዚህ የበለጠ ብዛት ያላቸው የፍርድ ቤት ትእዛዞች ተላልፈዋል። የሚያሳዝነው አንደኛው የፍርድ ቤት ትእዛዝ የተፈጸመው በሽተኛዋ ራሷን በማታውቅበት ወቅት ደም በግድ እንድትወስድ በማድረግ ነው።
ሆኖም የሉስ ትግል በቀዶ ሕክምናው ክፍል ውስጥ አላበቃም። በጥቅምት 1993 የጋራ ብልጽግና አባል አገር በሆነችው በፖርቶሪኮ ላይ ክስ ተመሠረተባት። ጉዳዩ በዋናው ፍርድ ቤት ታየና ሚያዝያ 18, 1995 ለሉስ ተፈረደላት። ፍርድ ቤቱ ደም እንድትወስድ የተሰጠው ትእዛዝ “በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያልሰፈረ ከመሆኑም በተጨማሪ ሃይማኖቷን በነፃነት ለማራመድ ያላትን መብት፣ የግል ነፃነቷንና በአካሏ ላይ ለመወሰን ያላትን መብት የሚገፍ ነው” በማለት ገለጸ።
በፖርቶሪኮ ውስጥ የሚገኝ አንድ ፍርድ ቤት ደም መውሰድን በተመለከተ ለይሖዋ ምሥክሮች ሲፈርድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነበር። የተላለፈው ውሳኔ ብዙዎች አስተያየታቸውን እንዲሰነዝሩ አድርጓል። በዚሁ ሳቢያ ዋና ዋናዎቹ የጋዜጣ፣ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በተገኙበት አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
በዚያው ምሽት አንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ከሉስ ጠበቆች ከአንዱ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ አስተላልፏል። አድማጮች በስልክ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ተጋብዘው ነበር። ብዙ ዶክተሮችና ጠበቆች ስልክ ደውለው የተላለፈውን የፍርድ ውሳኔ እንደሚደግፉ ገልጸዋል። ስልክ ደውለው አስተያየታቸውን ከሰነዘሩት ሰዎች አንዱ “ሳይንስ ደም መውሰድ ሕይወትን ለማዳን ዋስትና እንደሚሆን ለማረጋገጥ አልቻለም፤ እንደዚያ ብሎ ማሰብ ስሕተት ነው” ብሏል። በተጨማሪም “ከቅርብ ጊዜ በኋላ ደም መውሰድ ዘመናዊ ሕክምና ከፈጸማቸው የሥነ ምግባር ጉድለቶች ወይም ስሕተቶች አንዱ እንደሆነ በታሪክ መዝገብ ላይ ይሰፍራል” ሲል ገልጿል።
አንድ እውቅ የሕግ ፕሮፌሰር ወደ መጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ ደውለው በውሳኔው በጣም እንደረኩ ከገለጹ በኋላ ይህ “ታላቅ ድል” ነው በማለት ተናግረዋል። አክለውም ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ያስከበረው ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን ለመላው የፖርቶሪኮ ሕዝብ ጭምር ነው ብለዋል።