ይሖዋን በንጹሕ እጆች አምልከው
መዝሙራዊው ዳዊት በመንፈስ አነሣሽነት “[ይሖዋ ሆይ] እጆቼን በንጽሕና [“በቅንነት” አዓት] አጥባለሁ፤ አቤቱ መሠዊያህን እዞራለሁ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 26:6
ዳዊት እነዚህን ቃላት በሚደርስበት ወቅት ሌዋውያን የሆኑ እስራኤላውያን ካህናት ወደ መሠዊያው ወጥተው በእሳቱ ላይ መሥዋዕቶቻቸውን ሲያቀርቡ የነበራቸውን ልማድ በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ካህናት ይህን የአምልኮ ተግባር ከመፈጸመማቸው በፊት እጃቸውንና እግራቸውን እንዲታጠቡ ይፈለግባቸው ነበር። ይህ አነስተኛ ግምት የሚሰጠው ዝርዝር መግለጫ አልነበረም። ካህኑ ይህን የመጀመሪያ እርምጃ ሳያደርግ መቅረቱ ሕይወቱን ሊያሳጣው ይችል ነበር!—ዘጸአት 30:18-21
ምሳሌያዊ እጥበት መንፈሳዊና የሥነ ምግባር ንጽሕና ያስገኛል። (ኢሳይያስ 1:16፤ ኤፌሶን 5:26) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ እሱን በማገልገል ‘መሠዊያውን እንድንዞር’ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ እሱን እንድናገለግል የሚፈልገው በንጹሕ እጃችን ወይም ዳዊት በግልጽ እንዳስቀመጠው “በቅንነት” በመታጠብ ነው። ርኩሰት የሚፈጽሙ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ስለማይወርሱ ይህ ተራ ብቃት አይደለም። (ገላትያ 5:19-21) አንድ ሰው አምላካዊ ተግባሮችን ማከናወኑ ሥነ ምግባር የጎደለው አድራጎት ለመፈጸም ፈቃድ አይሰጠውም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” በማለት ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 9:27
መለኮታዊ ተቀባይነትና እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ይሖዋን በንጹሕ እጆች ማምለክ ይኖርባቸዋል። ልክ እንደ ዳዊት “በየዋህ ልብና በቅንነት” ይሄዳሉ።—1 ነገሥት 9:4