ኢሬና የምትወደው የመዝሙር መጽሐፍ
ኢሬና በቅርቡ የይሖዋ ምሥክር በመሆን የተጠመቀች በቡልጋሪያ ሶፊያ ውስጥ የምትኖር የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነች። መዘመር የምትወድ ሲሆን በተለይ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ያሉት መዝሙሮች ያስደስቷታል። በዚህ የተነሳ ኢሬና በየወሩ ጥቂት መዝሙሮች በቃሏ ለማጥናት ግብ አውጥታ ነበር።
ኢሬና ከምትወዳቸው ትምህርቶች አንዱ ሙዚቃ ነው። በዚህ ምክንያት የሙዚቃ አስተማሪዋ ኢሬና ከትምህርት ቤቱ የመዘምራን ጓድ ጋር አልዘምርም በማለቷ ግራ ተጋባች። ኢሬና አልዘምርም ያለችው ለምንድን ነው? እንድትዘምር የተጠየቀቻቸው አብዛኞቹ መዝሙሮች ብሔራዊ ጀግኖችንና አረመኔያዊ ምንጭ ያላቸውን በዓላት እንደሚያወድሱ ስለተገነዘበች ነው። ሌላው ቀርቶ አንዳንዶቹ መዝሙሮች የአገሪቱን ርዕዮተ ዓለም ለማራመድ ሲሉ ተቃውሞና ዓመፅ የሚያነሳሱ ነበሩ። አስተማሪዋ ኢሬና በዚህ ነገር ላይ ያላትን አቋም ለመረዳት አልቻለችም። ኢሬና ስለ ሃይማኖታዊ እምነቶችዋ የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፋ ለአስተማሪዋ ብትሰጣትም አልተሳካላትም።
የኢሬና አባት አንድ ሐሳብ መጣለት። ኢሬና የምትወዳቸውን መዝሙሮች የያዘውን ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ የተባለውን መጽሐፍ ለአስተማሪዋ ሰጣት። ከጥቂት ቀናት በኋላ ኢሬና ወደ ሙዚቃ ክፍል እንድትመጣ አስተማሪዋ ጠራቻት። ኢሬና የክፍል ጓደኞችዋ ባሉበት ከመጽሐፉ ውስጥ የምትወዳቸውን መዝሙሮች እንድትዘምር ጠየቀቻት። ኢሬና ስትዘምር አስተማሪዋ በፒያኖ ታጅባት ነበር። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከአንድ ሰዓት በላይ አሳለፉ! ኢሬና የምትወደው የመዝሙር መጽሐፍ ውብ የሆኑ ጣዕመ ዜማዎችን እንደያዘ አስተማሪዋ አምና ተቀበለች።