ዕድሜ ልኬን ስጠባበቀው የነበረው ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም የመኖር ተስፋ
ሄክተር አር ፕሬስታ እንደተናገረው
ዶክተሩ “ካንሰር የማይድን በሽታ ነው። ከዚህ በላይ ምንም ልናደርግልህ አንችልም” አለኝ። ይህ ምርምራ የተደረገልኝ ከአሥር ዓመታት በፊት ነበር። ነገር ግን አሁንም ሞትን ሳልቀምስ በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ አደርጋለሁ። ይህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያለው ተስፋ ነው።—ዮሐንስ 11:26
ወላጆቼ አጥባቂ ሜቶዲስቶች የነበሩ ሲሆን በቤተሰባችን የእርሻ ቦታ አቅራቢያ በምትገኝ አንዲት የገጠር ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያን አዘውትረው ይሄዱ ነበር። የተወለድኩት በዋራራፓ አውራጃ ባለው ሸለቆ ውስጥ በሚገኝ ውብ የእርሻ ቦታ ነበር። ይህ ቦታ የሚገኘው ኒው ዚላንድ ውስጥ ከዌሊንግተን ከተማ ሰሜናዊ ምሥራቅ 130 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቆ ነው። እዚህ ቦታ አናታቸው በበረዶ የተሸፈኑ ተራሮችን፣ ኩልል ያሉ ታላላቅ ወንዞችን፣ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ኮረብታዎችንና የተንጣለሉ ለም መሬቶችን የመመልከት አጋጣሚ ነበረን።
በሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ሰዎች በሙሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱና መጥፎ ሰዎች ደግሞ በእሳት ወደሚሠቃዩበት ሲኦል እንደሚገቡ ተምረን ነበር። አምላክ ሰዎች በሰማይ እንዲኖሩ የሚፈልግ ከሆነ መጀመሪያውኑ ለምን እዚያው እንዳላስቀመጣቸው ግራ ያጋባኝ ነበር። ሞት እፈራ ስለ ነበር ለምን እንደምንሞት ሁልጊዜ ራሴን እጠይቅ ነበር። በ1927 የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤተሰባችን ውስጥ አንድ አሳዛኝ ነገር ተከሰተ። ለጥያቄዎቼ መልስ እንድፈልግ የገፋፋኝ ይህ ሁኔታ ነበር።
ሬጅ የሞተው ለምንድን ነው?
ወንድሜ ሬጅ የ11 ዓመት ልጅ ሳለ በጠና ታመመ። ዶክተሩ ችግሩ ምን እንደሆነ ስላላወቀ ሊረዳው አልቻለም። እናቴ አንድ የሜቶዲስ ቄስ ጠራች። ቄሱ ለሬጅ ቢጸልይለትም እናቴን አላረካትም ነበር። እንዲያውም ጸሎቱ ዋጋ እንደሌለው ለቄሱ ነገረችው።
ሬጅ ሲሞት እናቴ ይህ ገና ጨቅላ የሆነው ልጅዋ የሞተበትን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ስላደረባት ካገኘችው ሰው ጋር ሁሉ ስለ ጉዳዩ ትነጋገር ነበር። ከተማ ውስጥ ከአንድ ነጋዴ ጋር ስትነጋገር ሙታን ያሉበትን ሁኔታ ያውቅ እንደሆነ ጠየቀችው። ይህ ሰው ስለ ሙታን ሁኔታ ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረውም፤ ሆኖም “አንድ ሰው ለአንቺ የሚስማማ መጽሐፍ እዚህ ትቶ ሄዷል” አላት።
እናቴ መጽሐፉን እቤት ይዛ መጥታ ማንበብ ጀመረች። ንባቧን ማቆም አልቻለችም። በፊቷ ላይ ይነበብ የነበረው ስሜት ቀስ በቀስ እየተለወጠ መጣ። “ልክ ነው፣ እውነት ይህ ነው” በማለት ለቤተሰቡ ተናገረች። መጽሐፉ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የመጀመሪያ ጥራዝ የሆነው መለኮታዊው የዘመናት ዕቅድ የተባለው መጽሐፍ ነበር። መጀመሪያ ላይ ከመጠራጠሬም በላይ መጽሐፉ ስለ ፈጣሪ ዓላማ በሚናገረው ሐሳብ ላይ እከራከር ነበር። በመጨረሻ ክርክሬን አቆምኩ።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል
‘ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም መኖር፣ እስቲ ገምቱት!’ አንድ ሰው አፍቃሪ ከሆነ አምላክ የሚጠብቀው እንዲህ ዓይነት ተስፋ ነው። ገነት የሆነች ምድር! አዎን፣ የምፈልገው ነገር ነበር።
እነዚህን አስገራሚ እውነቶች ከተማርን በኋላ እናቴና በዌሊንግተን የሚኖሩ ቶምሰን፣ ባርተንና ጆንስ የተባሉ ሦስት ክርስቲያን እህቶች የመንግሥቱን ዘር በገጠራማ ቦታዎች ለማሰራጨት ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ሄደው ብዙ ቀናት ያሳልፉ ነበር። አባቴ የእናቴን ዓይነት የሚስዮናዊነት መንፈስ ባይኖረውም ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ ይሰጣት ነበር።
በእውነት ላይ እምነት ቢኖረኝም ለተወሰነ ጊዜ እምነቴን በተግባር አላሳየሁም ነበር። በ1935 ሮኢና ኮርሌትን አገባሁ። በኋላም ኢንድ የተባለች ሴት ልጅና ቤሪ የተባለ ወንድ ልጅ ወለድን። ሥራዬ ከብት መግዛት ስለነበረ ከአካባቢው ገበሬዎች በጣም ብዙ ከብቶች እገዛ ነበር። ገበሬዎቹ ፖለቲካ በሚያወሩበት ወቅት “ሰዎች የሚያደርጓቸው እነዚህ ሁሉ ጥረቶች አይሳኩም። የሰዎችን ችግር የሚፈታው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው” ብዬ ስነግራቸው ደስታ ይሰማኝ ነበር።
በጣም የሚያሳዝነው የሲጋራ ሱሰኛ ሆንኩ፤ ሲጋራ ከአፌ አይለይም ነበር። በዚህ ጊዜ ጤንነቴ ተቃውሶ የነበረ ሲሆን በነበረብኝ የሚያሠቃይ የሆድ ዕቃ ሕመም ምክንያት ሆስፒታል ገባሁ። ማጨስ የሚያስከትለው ኃይለኛ የሆድ ዕቃ መታወክ እንዳለብኝ ተነገረኝ። ምንም እንኳ ማጨስ ባቆምም በሐሳቤ ቁጥር ስፍር የሌለው ሲጋራ ማጨሱ የተለመደ ነበር። ሲጋራ እንዴት ያለ መጥፎ ሱስ ነው!
ሲጋራ ካቆምኩ በኋላ ሌሎች አስፈላጊ ማስተካከያዎች አደረግሁ። በ1939 በ28 ዓመቴ ገጠር በሚገኘው ቤታችን አቅራቢያ ባለ ማቲ የሚባል ወንዝ ውስጥ ተጠመቅሁ። ኒው ዚላንድ ውስጥ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ አንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ሮበርት ሌዘንቢ ከዌሊንግተን ድረስ መጥቶ ቤታችን ውስጥ ንግግር ካቀረበ በኋላ አጠመቀኝ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ደፋር የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
የስብከቱን ሥራ ማደራጀት
እንደተጠመቅሁ የኤኬታሁን ጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ባለቤቴ ሮኢና ገና እውነተን አልተቀበለችም ነበር። ቢሆንም ወንድም አልፍ ብርያንት ከፋያቱ መጥቶ ተገቢ በሆነ መንገድ ከቤት ወደ ቤት የሚሰበከው እንዴት እንደሆነ እንዲያሳየኝ እንደምጋብዘው ነገርኳት። የስብከቱን ሥራ ለማደራጀትና ክልላችንን አንድ በአንድ ለመሸፈን ፈልጌ ነበር።
ሮኢና እንዲህ አለች፦ “ሄክተር ከቤት ወደ ቤት ለመመስከር የምትሄድ ከሆነ ስትመለስ እዚህ አታገኘኝም። ትቼህ እሄዳለሁ። የአንተ ኃላፊነት ከቤተሰቦችህ ጋር እቤት መሆን ነው።”
ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። እያመነታሁ ልብሴን ለበስሁ። ‘ሄጄ መመስከር አለብኝ። የራሴና የቤተሰቤ ሕይወት የተመካው ይህን በማድረጌ ላይ ነው’ በማለት ለራሴ ተናገርኩ። ስለዚህ በማንኛውም መንገድ እርሷን ለመጉዳት እንደማልፈልግ አረጋገጥኩላት። እርሷን በጣም እንደምወዳት፣ ነገር ግን ከቤት ወደ ቤት መሄዱ የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነት እንዲሁም ሕይወታችንን የሚመለከት ጉዳይ ስለሆነ በዚህ መንገድ መስበክ እንዳለብኝ ነገርኳት።
ከአልፍ ጋር የመጀመሪያውን በር አንኳኳንና እርሱ ማነጋገር ጀመረ። ቢሆንም ትንሽ ቆይቼ እኔም ውይይቱ ውስጥ ገባሁ። እያነጋገርነው ለነበረው ሰው በኖኅ ዘመን የተከሰተው ነገር በጊዜያችን ለሚሆነው ነገር ምሳሌ እንደሆነና ለመዳን ከፈለግን ማድረግ ያለብን ነገር እንዳለ ነገርኩት። (ማቴዎስ 24:37-39) ጥቂት ቡክሌቶች ሰጠሁት።
ጨርሰን ስንሄድ አልፍ እንዲህ አለ፦ “ይህን ሁሉ እውቀት ከየት አገኘኸው? ከእኔ ጋር መሆን አያስፈልግህም። በል ብቻህን አገልግል። እንዲህ ካደረግን እጥፍ ክልል እንሸፍናለን።” በዚህ ዓይነት ሁኔታ አገልግሎታችንን ቀጠልን።
ወደ ቤት ስንመለስ ምን እንደሚጠብቀን አላውቅም ነበር። እቤት ስደርስ ያልጠብቅኩት አስደሳች ነገር አጋጠመኝ። ሮኢና ሻይ አፍልታ እየጠበቀችን ነበር። ከሁለት ሳምንት በኋላ ባለቤቴ አብራኝ ማገልገል የጀመረች ሲሆን በክርስቲያናዊ ቅንዓቷ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ሆነች።
በሸለቆ ውስጥ በሚገኘው እርሻችን ከሚኖሩት ሰዎች መካከል መጀመሪያ የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ሞድ ማንሰር፣ ወንድ ልጅዋ ዊሊያምና ሴት ልጅዋ ሩቢ ነበሩ። የሞድ ባል ኃይለኝነት የሚታይበት ቁጡ ሰው ነበር። አንድ ቀን እኔና ሮኢና ሞድን አገልግሎት ይዘናት ልንወጣ ወደ እርሻቸው ሄድን። ወጣቱ ዊልያም መኪናውን እንድንጠቀምባት ቢሰጠንም አባቱ አልተስማማም ነበር።
ሁኔታው እየከረረ መጣ። ሮኢና ሴት ልጃችንን ኤንድን እንድትይዛት ነገርኳት። የዊሊያም መኪና ውስጥ ገባሁና በፍጥነት አስነስቼ ስወጣ አቶ ማንሰር ከመውጣታችን በፊት ፈጠን ብሎ የመኪና ማቆሚያውን ግቢ በር ለመዝጋት ሞከረ። ቢሆንም አልተሳካለትም። ትንሽ ከሄድን በኋላ መኪናዋን አቁሜ ወረድኩና በጣም ተናዶ ወደ ነበረው አቶ ማንሰር ሄድኩ። “ወደ መስክ አገልግሎት እየሄድን ነው፤ አንተም ከእኛ ጋር መሄድ ትችላለህ” አልኩት። ሁኔታዬ ስለነካው ንዴቱ ትንሽ በረድ አለለት። መለስ ብዬ ሳስብ ችግሩን በሌላ መንገድ መፍታት እንደነበረብኝ ይሰማኛል። ነገር ግን አቶ ማንሰር ተለውጦ የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም እንኳ ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት ይዞ ነበር።
በእነዚያ ዓመታት የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች ጥቂት ብቻ ነበሩ። በእርሻ ቦታችን ሊጠይቁን ከሚመጡ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር የምናሳልፈው ጊዜ አስደሳች ከመሆኑም በላይ ብዙ ጠቅሞናል። ከእነዚህ እንግዶቻችን መካከል ሚስዮናውያን በሚሰለጥኑበት በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት በተሰጡት የመጀመሪያዎቹ ኮርሶች ተካፍለው ከአገራቸው ውጪ በጃፓንና በፓኪስታን ያገለገሉት አድሪያን ቶምሰን እና እህቱ ሞሊ ይገኙበታል።
በጦርነት ጊዜ ያገኘናቸው ተሞክሮዎች
መስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረ ሲሆን የኒው ዚላንድ መንግሥት በ1940 በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ ዕገዳ ጣለ። ብዙዎቹ ወንድሞቻችን በአገሪቱ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ፊት በግድ ቀርበው ነበር። አንዳንዶች አድካሚ ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች ውስጥ የታሰሩ ሲሆን ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው መገናኘት አይችሉም ነበር። ምንም እንኳ በግብርና ብንተዳደርም ጦርነቱ እያየለ ሲሄድ ለዘመቻ ብጠራስ ብዬ አሰብኩ። ወዲያው ማንኛውም ገበሬ የእርሻ ቦታውን ትቶ እንደማይዘምት ተነገረ።
ከሮኢና ጋር ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ተያያዝነው። እያንዳንዳችን በየወሩ ከ60 የሚበልጥ ሰዓት ለስብከቱ ሥራ እናውል ነበር። በዚህ ጊዜ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን የጠበቁ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችን የመርዳት መብት አግኝቼ ነበር። እነርሱን ወክዬ ዌሊንግተን፣ ሰሜን ፓመርስተን፣ ፋያቱ እና ማስተርተን ከተማ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ቀርቤያለሁ። በምልመላ ቦርዱ ውስጥ ቀሳውስት መኖራቸው የተለመደ ስለነበር ለጦርነት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የሚሠሩትን ክርስቲያናዊ ያልሆነ ተግባር ማጋለጡ ከፍተኛ ደስታ ይሰጠን ነበር።—1 ዮሐንስ 3:10-12
አንድ ቀን ምሽት ከሮኢና ጋር መጠበቂያ ግንብ ስናጠና ፖሊሶች ቤታችንን ከበቡት። ቤታችንን ሲያስሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አገኙ። “ይህ ጽሑፍ እቤታችሁ በመገኘቱ ልትታሰሩ ትችሉ ነበር” አሉን። ፖሊሶቹ ለመሄድ መኪናቸው ውስጥ ሲገቡ የመኪናዋ ፍሬን ተቀርቅሮ ስለነበር መኪናዋ አልነሳም አለች። ዊሊያም ማንሰር መኪናውን ጠገነላቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ተመልሰው አልመጡም።
በዕገዳ ሥር በነበርንበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን በእርሻ ቦታችን ውስጥ ራቅ ብሎ በሚገኝ አንድ ሕንፃ ውስጥ እንደብቃቸው ነበር። እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ኒው ዚላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ እሄድና ጽሑፎቹን በመኪናዬ ጭኜ አመጣ ነበር። ከዚያም ገለል ብሎ በሚገኘው ሕንፃ ውስጥ አስቀምጠው ነበር። አንድ ቀን ማታ የታገዱትን ጽሑፎች ለመውሰድ ቅርንጫፍ ቢሮው ስደርስ ሳይታሰብ አካባቢው ሁሉ በመብራት ወገግ አለ! አንድ ፖሊስ “ተይዘሃል!” በማለት ጮኸ። የሚያስገርመው ግን ብዙም ሳይነዘንዙኝ ለቀቁኝ።
በ1949 እኔና ሮኢና የእርሻ ቦታውን ሸጥንና ገንዘባችን እስኪያልቅ ድረስ በአቅኚነት ለማገልገል ወሰንን። ቤት ቀይረን ወደ ማስተርተን ሄድንና በማስተርተን ጉባኤ ውስጥ በአቅኚነት ቀጠልን። በሁለት ዓመት ውስጥ 24 አስፋፊዎች ያሉት ፌዘርስተን የተባለ ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ውስጥ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግል ነበር። ከዚያም በ1953 በኒው ዮርክ ከተማ ያንኪ ስታዲዬም ውስጥ በተደረገው ስምንት ቀን በፈጀው ብሔራት አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጓዝ መብት አግኝቼ ነበር። ሮኢና ከእኔ ጋር መሄድ አልቻለችም። ምክንያቱም ሴት ልጃችን ኤንድ እጅና እግር እንዲሁም ጡንቻ በቀላሉ እንዳይታዘዝ የሚያደርግ ሴሬብራል ፓልሲ የተባለ በሽታ ስለነበረባት እርሷን መንከባከብ ነበረባት።
ወደ ኒው ዚላንድ ከተመለስኩ በኋላ ሥጋዊ ሥራ መሥራት ነበረብኝ። ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ ወደ ተሾምኩበት ወደ ማስተርተን ጉባኤ ተመለስኩ። በዚህ ጊዜ ዊሊያም ማንሰር ማስተርተን ውስጥ የሚገኝ አነስተኛ ቲያትር ቤት ገዛና ይህ ቲያትር ቤት የመጀመሪያው የዋራራፓ የመንግሥት አዳራሽ ሆነ። በ1950ዎቹ ዓመታት ጉባኤያችን በመንፈሳዊም በቁጥርም ጥሩ እድገት አደረገ። ስለዚህ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሲጎበኘን ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍል ሄደው እዚያ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ እንዲያግዙ የጎለመሱ ወንድሞችን ያበረታታ ነበረ። ብዙዎቹ ማበረታቻውን ሠርተውበታል።
ቤተሰባችን ማስተርተን ውስጥ የቆየ ሲሆን በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት በጉባኤ ውስጥ ካገኘኋቸው ብዙ መብቶች በተጨማሪ በአገር አቀፍና በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ተመድቤ የመሥራትም መብት አግኝቼ ነበር። ሮኢና በመስክ አገልግሎት በቅንዓት ከመካፈሏም በላይ ሌሎችም በቅንዓት እንዲያገለግሉ ታበረታታ ነበር።
የእምነት ፈተናዎችን መቋቋም
በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው በ1985 ተመርምሬ የማይድን ካንሰር እንዳለብኝ አወቅሁ። እኔና ታማኟ ባለቤቴ ሮኢና ከልጆቻችን ጋር በመሆን አሁን ካሉት ፈጽሞ ሞትን ከማይቀምሱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንዱ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን! ነገር ግን ዶክተሮች ወደ ቤቴ ሄጄ የምሞትበትን ቀን እንድጠባበቅ ነገሩኝ። ቢሆንም በምርመራው ውጤት የተገኘውን በሽታ እንዴት እንደምመለከተው አስቀድመው ጠየቁኝ።
“የአእምሮዬን ሰላም እንደምጠብቅና ብሩህ አመለካከት እንደምይዝ” ነገርኳቸው። “ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዳልናወጥ ረድቶኛል።—ምሳሌ 14:30 የ1980 ትርጉም
የካንሰር ስፔሻሊስቶች ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አድንቀውታል። “እንዲህ ዓይነቱ ሥነ ልቦናዊ ሁኔታ የካንሰር በሽተኞች 90 በመቶ እንዲሻላቸው ረድቷቸዋል” አሉ። በተጨማሪም ለሰባት ሳምንታት የጨረር ሕክምና እንዳደርግ መከሩኝ። ከካንሰር ጋር የማደርገው ትግል ተሳክቶልኝ ነበር።
በዚህ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ እጅግ የሚያሳዝን ነገር ደረሰብኝ። ውቧና ታማኟ ባለቤቴ አንጎሏ ውስጥ ደም ፈስሶ ሞተች። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ታማኝ ሰዎች ምሳሌና እነዚህ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው ሲኖሩ ይሖዋ ችግራቸውን እንዴት እንደፈታላቸው ማወቁ አጽናንቶኛል። ስለዚህ በአዲሱ ዓለም ላይ ያለኝ ተስፋ አሁንም ብሩህ ነው።—ሮሜ 15:4
ቢሆንም በመንፈስ ጭንቀት ስለ ተዋጥኩ ሽማግሌ ሆኖ ማገልገሉን ለማቆም ፈለግሁ። በጉባኤ ያሉ ወንድሞች ባለኝ የአገልግሎት መብት ለመቀጠል የሚያስችለኝን ኃይል እስከማገኝ ድረስ ያበረታቱኝ ነበር። በዚህ የተነሳ ላለፉት 57 ዓመታት ሳላቋርጥ በሽምግልናና በበላይ ተመልካችነት ለማገልገል ችዬአለሁ።
የወደፊቱን ጊዜ በእምነት መጠበቅ
እነዚህን ሁሉ ዓመታት ይሖዋን ማገልገል በዋጋ የማይተመን መብት ነው። ምንኛ ተባርኬአለሁ! እናቴ የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ “ልክ ነው። እውነት ይህ ነው!” ብላ ስትናገር ከሰማሁ ብዙ ጊዜ ያለፈ አይመስለኝም። እናቴ ከ100 ዓመት በላይ ኖራ በ1979 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ቀናተኛ ምሥክር በመሆን በታማኝነቷ ጸንታለች። ሴት ልጅዋና ስድስት ወንዶች ልጆችዋ ካቋማቸው ዝንፍ የማይሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
የይሖዋ ስም ከስድብ ሁሉ ነፃ ሲሆን በሕይወት ኖሬ ለማየት በጣም እመኛለሁ። ዕድሜ ልኬን ስጠባበቀው የነበረው ሞትን ሳይቀምሱ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እውን ይሆንልኝ ይሆን? ሲደርስ ይታያል። ያም ሆነ ይህ ብዙዎች አዎን፣ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህንን በረከት እንደሚያገኙ እምነቴ የጸና ነው። ስለዚህ በሕይወት እስካለሁ ድረስ ሞትን ከማይቀምሱት ሰዎች ጋር የመቆጠር ተስፋ አለኝ።—ዮሐንስ 11:26
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እናቴ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር