ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
ዘመናዊ የምርምር ውጤቶች “በማኅፀን ውስጥ ያለ ሽል ድምፅ በሚሰማበት ወቅት አንድ ዓይነት አካላዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ” ይጠቁማሉ። የኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች “እናቶች ልጆቻቸው በሆዳቸው ውስጥ እያሉ ያነበቡላቸውን ነገር ከተወለዱ በኋላ እንደገና ሲያነቡላቸው አንድ ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡ ደርሰውበታል” በማለት ዊኒፔግ ፍሪ ፕሬስ ይገልጻል። ሴቶች በእርግዝናቸው ወቅት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ማንበባቸው በልጆቹ ውስጥ ጥሩ ሥነ ምግባር ለመትከል ትልቅ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጢሞቴዎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ’ እንደነበር ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው እናቱና ሴት አያቱ ከሕፃንነት ጀምሮ የማሠልጠኑን አስፈላጊነት ተገንዘበው ነበር፤ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሳያነቡለትም አይቀሩም።
ደራሲው ጂም ትረሌስ “ዛሬ በኅብረተሰባችን ካሉት ታላላቅ ችሎታዎች ሁሉ ይበልጥ የላቀ ቦታ የሚሰጠው” የማንበብ ችሎታ ነው ብለዋል። ጮክ ብሎ ማንበብ የቋንቋና የቃላት እውቀታችንን ያሰፋልናል።
ለሕፃኑ ልጃችሁ ቢያንስ ቢያንስ ከእርሱ ጋር መነጋገር ከጀመራችሁበት ጊዜ አንሥቶ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ማንበባችሁ ጥሩ ይሆናል። ገና በማኅፀን ያለው ወይም በቅርቡ የተወለደው ጨቅላ ልጃችሁ በወቅቱ ምን እየነገራችሁት እንዳለ መረዳት ባይችልም እንኳ ወደፊት ሊገኝ የሚችለው ዘላቂ ጥቅም ግን ሊደከምለት የሚገባ ነው። ምሳሌ 22:6 “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” ይላል።
ከሁኔታው ጋር የሚስማማና ጠቃሚ የሆነ ምን ነገር ልታነቡለት ትችላላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ አንብቡለት። በተጨማሪም ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ፣ እስከዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የሚሉትን የመሳሰሉ ሌሎች ጠቃሚ ጽሑፎችን እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ርዕሶችን አንብቡለት።
እርግጥ ነው ይህን ማድረግ ጊዜ ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ ለዚህ የምታውሉት ጊዜ በከንቱ የሚባክን አይሆንም። ልጃችሁን እንደምታፈቅሩትና እንደምታስቡለት የሚያሳይ ጉልህ ማረጋገጫ ነው።