ወላጆች ሆይ፣በልጆቻችሁ ተደሰቱ
“አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው።”—ምሳሌ 23:25
1. ወላጆች በልጆቻቸው እንዲደሰቱ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
በተለይ የተከልከውና የተንከባከብከው አንተ ከሆንክ አንድ ችግኝ አድጎ አካባቢውን የሚያስውብና ለጥላ የሚሆን ትልቅ ዛፍ ሲሆን ማየት በጣም ያስደስትሃል! በተመሳሳይም በእንክብካቤ ያሳደጓቸው ልጆቻቸው የጎለመሱ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑላቸው ወላጆች የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንደሚለው በልጆቻቸው በጣም ይደሰታሉ፦ “የጻድቅ አባት እጅግ ደስ ይለዋል፣ ጠቢብንም ልጅ የወለደ ሐሤትን ያገኛል። አባትህና እናትህ ደስ ይበላቸው፣ አንተንም የወለደች ደስ ይበላት።”—ምሳሌ 23:24, 25
2, 3. (ሀ) ወላጆች ከሐዘንና ከምሬት ሊድኑ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ችግኞችም ሆኑ ልጆች የደስታ ምንጭ እንዲሆኑ ምን ያስፈልጋቸዋል?
2 ሆኖም አንድ ልጅ እንዲያው በአንዴ ‘ጻድቅ’ እና ‘ጠቢብ’ አይሆንም። አንድ ችግኝ አድጎ ትልቅ ዛፍ እንዲሆን ብዙ መድከም እንደሚያስፈልግ ሁሉ ልጆች ‘የሐዘን’ እና ‘የምሬት’ ምንጭ እንዳይሆኑ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። (ምሳሌ 17:21, 25) ለምሳሌ ያህል የእንጨት ድጋፍ አንድን ችግኝ ቀጥ ብሎና ጠንካራ ሆኖ እንዲያድግ ሊመራው ይችላል። ዘወትር ውኃ ማጠጣት በጣም አስፈላጊ ከመሆኑም በተጨማሪ አንድን ችግኝ ከጎጂ ነፍሳት መጠበቅ ሊያስፈልግ ይችላል። በመጨረሻም አንድ ዛፍ መከርከሙ ተጨማሪ ውበት እንዲጎናጸፍ ያስችለዋል።
3 ልጆች አምላካዊ ሥልጠና ማግኘት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መጠጣት፣ ከሥነ ምግባር ብክለት መጠበቅ፣ መጥፎ ጠባዮችን ለማስወገድ የሚያስችለው ፍቅራዊ ተግሣጽና የመሳሰሉት ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው የአምላክ ቃል ይናገራል። እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት በተለይ አባቶች ልጆቻቸውን ‘በይሖዋ ተግሣጽና የእሱን አስተሳሰብ በአእምሯቸው ውስጥ እየቀረጹ’ እንዲያሳድጓቸው ተመክረዋል። (ኤፌሶን 6:4 አዓት) ይህ ምን ማድረግን ይጨምራል?
ለይሖዋ ቃል ልዩ ትኩረት መስጠት
4. ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ኃላፊነት አለባቸው? ይህን ኃላፊነት ከመወጣታቸው በፊት ምን እንዲያደርጉ ይፈለግባቸዋል?
4 ‘የይሖዋን አስተሳሰብ በአእምሮ ውስጥ መቅረጽ’ ማለት አስተሳሰባችንን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር እንዲስማማ ማድረግ ማለት ነው። ስለዚህ ወላጆች በትናንሽ ልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ ይሖዋ ለነገሮች ያለውን አመለካከት መቅረጽ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በርኅራኄ ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ ወይም ከስሕተት እንዲታረሙ የሚያደርጋቸውን ሥልጠና በመስጠት ረገድ የአምላክን ምሳሌ መኮረጅ አለባቸው። (መዝሙር 103:10, 11፤ ምሳሌ 3:11, 12) ይሁን እንጂ ወላጆች ይህን ከማድረጋቸው በፊት የአምላክ ነቢይ የነበረው ሙሴ ለጥንት እስራኤላውያን “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን [የይሖዋ] ቃል በልብህ ያዝ” ሲል በሰጠው ምክር መሠረት ወላጆች ራሳቸው የይሖዋን ቃል በውስጣቸው እንዲቀረጽ ማድረግ ይኖርባቸዋል።—ዘዳግም 6:6፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
5. እስራኤላውያን ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ያለባቸው መቼና እንዴት ነበር? “መቅረጽ” ማለት ምን ማለት ነው?
5 ወላጆች ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው፣ ማሰላሰላቸውና መጸለያቸው ሙሴ “[የይሖዋን ቃል] ለልጆችህም አስተምረው፣ [“በልጆችህ አእምሮ ውስጥ ቅረጸው፣” አዓት] በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው” በማለት ቀጥሎ የሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ያስችላቸዋል። “መቅረጽ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “መድገም፣” “ደግሞ ደጋግሞ መናገር” እና “ቁልጭ ብሎ በሚታይ መንገድ ማተም” ማለት ነው። በተጨማሪም ሙሴ የይሖዋን ቃል አስፈላጊነት እንዴት እንዳጎላ ልብ በሉ፦ “በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደ ክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” ይሖዋ ወላጆች ለልጆቻቸው ዘወትር ፍቅራዊ እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸው እንደሚፈልግ ግልጽ ነው!—ዘዳግም 6:7-9፣ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
6. ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ መቅረጽ ያለባቸው ነገር ምንድን ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
6 ወላጆች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ መቅረጽ የሚኖሩባቸው ‘እነዚህ’ የይሖዋ ‘ቃላት’ የትኞቹ ናቸው? ሙሴ ይህን የገለጸው አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክርና አትመኝ የሚሉትን ጨምሮ ብዙውን ጊዜ አሥርቱ ትእዛዛት ተብለው የሚጠሩትን ትእዛዛት በድጋሚ ከተናገረ በኋላ ነው። እስራኤላውያን ወላጆች በተለይ እነዚህን የመሳሰሉትን የሥነ ምግባር ሕግጋትና “አምላክህን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” አዓት] በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” የሚለውን ትእዛዝ በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ መቅረጽ ያስፈልጋቸው ነበር። (ዘዳግም 5:6-21፤ 6:1-5) በዛሬው ጊዜ ልጆች የሚያስፈልጋቸው ትምህርት እንዲህ ዓይነት ነው ቢባል አትስማማምን?
7. (ሀ) ልጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምን ጋር ተነጻጽረዋል? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ የምንመረምረው ምንድን ነው?
7 እስራኤላዊው አባት እንዲህ ተብሏል፦ “ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው።” (መዝሙር 128:3) ሆኖም ወላጆች “በችግኞቻቸው” ከማዘን ይልቅ ለመደሰት ከፈለጉ ለልጆቻቸው በየቀኑ በግል ትኩረት ሊሰጧቸው ያስፈልጋል። (ምሳሌ 10:1፤ 13:24፤ 29:15, 17) ወላጆች ወደፊት በልጆቻቸው ከልብ ለመደሰት በሚያስችላቸው መንገድ ልጆቻቸውን ማሠልጠን፣ በመንፈሳዊ ውኃ ማጠጣት፣ መጠበቅና በፍቅር መገሠጽ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
ከሕፃንነት ጀምሮ ማሠልጠን
8. (ሀ) ለጢሞቴዎስ እንደ ድጋፍ እንጨት ሆነው ያገለገሉት እነማን ነበሩ? (ለ) ሥልጠናው የጀመረው መቼ ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
8 ከእናቱና ከአያቱ እርዳታ የተቀበለውን የጢሞቴዎስን ሁኔታ ተመልከት። ጢሞቴዎስ በምሳሌያዊ አነጋገር ከሁለት አጥብቀው የተተከሉ የድጋፍ እንጨቶች አመራር አግኝቷል። የጢሞቴዎስ አባት ግሪካዊና ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የማያምን ስለ ነበረ ጢሞቴዎስን ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን ጽሑፎችን’ ያስተማሩት አይሁዳዊት እናቱ ኤውንቄና እናቷ ሎይድ ነበሩ። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:15፤ ሥራ 16:1) ጢሞቴዎስን ገና ከሕፃንነቱ ጀምረው ‘[ይሖዋ] ስላደረጋቸው አስደናቂ ነገሮች’ በማስተማር ረገድ ያሳዩት ትጋት ትልቅ ወሮታ አስገኝቶላቸዋል። (መዝሙር 78:1, 3, 4) ጢሞቴዎስ ሩቅ ወደሆኑ አገሮች በመሄድ ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለገለው ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ሳይሆን አይቀርም፤ በተጨማሪም የጥንት ክርስቲያን ጉባኤዎችን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል።—ሥራ 16:2-5፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17፤ ፊልጵስዩስ 2:19-23
9. ልጆች ከፍቅረ ነዋይ ወጥመዶች እንዲርቁ ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?
9 ወላጆች ሆይ፣ ምን ዓይነት የድጋፍ እንጨቶች ናችሁ? ለምሳሌ ያህል ልጆቻችሁ ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ትፈልጋላችሁ? እንግዲያውስ የግድ የማያስፈልጓችሁን በየጊዜው የሚወጡትን አዳዲስ ዕቃዎች ሁሉ ወይም ሌሎች ነገሮችን ከማሳደድ በመቆጠብ ራሳችሁ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይኖርባችኋል። በቁሳዊ ነገሮች ከሌሎች ልቃችሁ ለመታየት የምትሯሯጡ ከሆነ ልጆቻችሁ እናንተን ቢመስሉ አይግረማችሁ። (ማቴዎስ 6:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) በእርግጥም የድጋፍ እንጨቱ ቀጥ ያለ ካልሆነ አንድ ችግኝ እንዴት ቀጥ ብሎ ሊያድግ ይችላል?
10. ወላጆች ዘወትር የማንን መመሪያ መሻት ያስፈልጋቸዋል? ምን ዝንባሌስ ሊኖራቸው ይገባል?
10 በልጆቻቸው የሚደሰቱ ወላጆች ዘወትር ለልጆቻቸው በመንፈሳዊ የሚጠቅማቸው ነገር ምን እንደሆነ በማሰብ ልጆቻቸውን ለማሠልጠን የሚያስችላቸውን መለኮታዊ እርዳታ ለማግኘት ይጥራሉ። አንዲት የአራት ልጆች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ገና ልጆቻችን ከመወለዳቸው በፊት እንኳ ጥሩ ወላጆች እንድንሆን፣ በቃሉ እንድንመራና በሕይወታችን ውስጥ እንድንሠራበት እንዲረዳን ዘወትር ወደ ይሖዋ እንጸልይ ነበር።” በተጨማሪም “‘ይሖዋን ማስቀደም’ የሚለው ሐረግ በቤታችን ውስጥ የተለመደ ብቻ ሳይሆን በኑሯችን የሚንጸባረቅ ነገር ነበር” ብላለች።—መሳፍንት 13:8
ዘወትር “ውኃ” ማጠጣት
11. ችግኞችም ሆኑ ልጆች ለማደግ ምን ያስፈልጋቸዋል?
11 ዛፎች በወንዝ አጠገብ ሲበቅሉ ተመችቷቸው እንደሚያድጉ ሁሉ በተለይ ችግኞች ዘወትር ውኃ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። (ከራእይ 22:1, 2 ጋር አወዳድር።) ልጆችም ዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ውኃ ከጠጡ በመንፈሳዊ በደንብ ያድጋሉ። ሆኖም ወላጆች ልጆቻቸው ለምን ያህል ጊዜ በትኩረት መከታተል እንደሚችሉ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋቸዋል። በአንዴ ረዘም ላለ ጊዜ ለማስተማር ከመሞከር ይልቅ የትምህርቱ ጊዜ አጠር ያለ ግን የሚዘወተር ቢሆን ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን ይችላል። እንደነዚህ ያሉ አጫጭር የማስተማሪያ ጊዜያት ያላቸውን ጠቀሜታ አቅልላችሁ አትመልከቱ። አንድ ወላጅና ልጅ አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ በመካከላቸው ፍቅራዊ ትስስር ለመፍጠር ወሳኝነት አለው፤ ብዙውን ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎች እርስ በርስ መቀራረብን ያበረታታሉ።—ዘዳግም 6:6-9፤ 11:18-21፤ ምሳሌ 22:6
12. ከትናንሽ ልጆች ጋር አብሮ መጸለይ ምን ጥቅም አለው?
12 ከትናንሽ ልጆች ጋር ከምታሳልፏቸው ጊዜያት አንዱ በቀኑ መገባደጃ ላይ ሊሆን ይችላል። አንዲት ወጣት “ወላጆቼ ሁልጊዜ ማታ ማታ አልጋችን ጫፍ ላይ ተቀምጠው የምናቀርበውን ጸሎት ያዳምጡ ነበር” ስትል ታስታውሳለች። ሌላ ወጣት ደግሞ ይህን ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ ስትገልጽ “ከመተኛቴ በፊት ማታ ማታ ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማድ እንዲኖረኝ ረድቶኛል” ብላለች። ልጆች ወላጆቻቸው በየቀኑ ስለ ይሖዋ ሲናገሩና ወደ እሱ ሲጸልዩ ሲሰሙ ይሖዋ እውን ሆኖ ይታያቸዋል። አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ዓይኖቼን ስከድን ከአያቴ ጋር እንደምነጋገር ሆኖ ይሰማኛል። ወላጆቼ የምናደርጋቸውና የምንናገራቸው ነገሮች ሁሉ ይሖዋን እንደሚነኩት እንዳስተውል ረድተውኛል።”
13. ቋሚ የማስተማሪያ ጊዜያት ምን ነገሮችን ሊያካትቱ ይችላሉ?
13 ትናንሽ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት ውኃ እንዲጠጡ ለመርዳት ሲባል ወላጆች በመደበኛው የማስተማሪያ ጊዜ ብዙ ተግባራዊ ነገሮችን ሊያክሉ ይችላሉ። ከ13 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሁለት ልጆች ያሏቸው ወላጆች “ሁለቱም ልጆች በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በጸጥታ ስለ መቀመጥ ሥልጠና ማግኘት የጀመሩት ገና ከሕፃንነታቸው ነው” ብለዋል። አንድ አባት ቤተሰቡ ያደረገውን እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስም በተለያዩ ካርዶች ላይ ከጻፍን በኋላ እያንዳንዳችን በየተራ በቅደም ተከተላቸው ማስቀመጥ እንለማመድ ነበር። ልጆቹ ሁልጊዜ ይህን በጉጉት ይጠባበቁ ነበር።” ብዙ ቤተሰቦች ከምግብ በፊት ወይም በኋላ አጠር ያለ ትምህርት ያክላሉ። አንድ አባት “የእራት ሰዓት የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የምንወያይበት አመቺ ጊዜ ሆኖልናል” ብሏል።
14. (ሀ) ከትናንሽ ልጆች ጋር በመንፈሳዊ ሊክሱ የሚችሉ የትኞቹን ነገሮች ማድረግ ይቻላል? (ለ) የልጆች የመማር ችሎታ ምን ያህል ነው?
14 በተጨማሪም ትናንሽ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለው መጽሐፍ የያዛቸውን ሕያው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መስማት ያስደስታቸዋል።a አንድ ባልና ሚስት የሚከተለውን ሐሳብ ገልጸዋል፦ “ልጆቹ ሕፃን በነበሩበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ከተባለው መጽሐፍ አንድ ትምህርት ከሸፈንን በኋላ ከዚያ ልጆቹ ለድራማ የሚስማማ ልብስ ይለብሱና በትምህርቱ ውስጥ የሚገኙትን ገጸ ባሕርያት በመወከል አጭር ድራማ ያቀርባሉ። ልጆቹ ይህን ይወዱት ነበር፤ ብዙውን ጊዜ በአንድ ጥናት ወቅት ከአንድ በላይ ታሪክ እንዲጠና ይጠይቁ ነበር።” የልጆቻችሁን የመማር ችሎታ አቅልላችሁ አትመልከቱ! የአራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች በሙሉ በቃላቸው ያጠኑ ከመሆናቸውም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ማንብብ ለመማር ችለዋል! አንዲት ወጣት የሦስት ዓመት ተኩል ያህል ዕድሜ በነበራት ወቅት “ጁዲሻል ዲስሽንስ” የሚሉትን የእንግሊዝኛ ቃላት በተደጋጋሚ ጊዜያት በትክክል ማንበብ አቅቷት እንደ ነበር ታስታውሳለች፤ ሆኖም አባቷ መለማመዷን እንድትቀጥል አበረታታት።
15. ከልጆች ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ውስጥ ምን ነገሮች ሊካተቱ ይችላሉ? እንዲህ ዓይነቶቹ ውይይቶች ጠቃሚ መሆናቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?
15 በተጨማሪም ከትናንሽ ልጆቻችሁ ጋር የምታሳልፏቸውን የማስተማሪያ ጊዜያት የእውነትን ውኃ ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁዎች እንዲሆኑ ለመርዳት ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ። የእውነትን ውኃ ለሌሎች ከሚያካፍሉባቸው መንገዶች አንዱ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) አንድ ወጣት “በልምምድ ፕሮግራማችን ወቅት በራሴ አገላለጽ ሐሳብ እንድሰጥ ይጠበቅብኝ ነበር። ምንም ሳይገባኝ እንዲሁ እንዳነብ አይፈቀድልኝም ነበር” ሲል ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ልጆች በመስክ አገልግሎት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሊሠለጥኑ ይችላሉ። ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ወላጆች ያደገች አንዲት ሴት እንዲህ ስትል ገልጻለች፦ “በስብከት ሥራቸው ከወላጆቻችን ጋር የምንሄደው እንዲሁ እነሱን ለመከተል ብቻ አልነበረም። ምንም እንኳ የምናደርገው ተሳትፎ የበር ደወል በመደወልና የስብሰባ የጥሪ ወረቀት በመስጠት ብቻ የተወሰነ ቢሆንም አንድ ዓይነት ተሳትፎ ማድረግ እንዳለብን እናውቅ ነበር። ቅዳሜና እሑድ ወደ አገልግሎት ከመውጣታችን በፊት በጥንቃቄ ስለምንዘጋጅ ምን መናገር እንዳለብን እናውቅ ነበር። ቅዳሜ ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነቃ አገልግሎት ስለ መሄዳችን ጠይቀን አናውቅም። አገልግሎት እንደምንሄድ እናውቅ ነበር።”
16. ከልጆች ጋር የሚደረገው የቤተሰብ ጥናት ቋሚ መሆን የሚኖርበት ለምንድን ነው?
16 ለትናንሽ ልጆች ዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን የማጠጣት አስፈላጊነት ከመጠን በላይ ተጋንኗል ሊባል አይችልም። ይህ ማለት በየሳምንቱ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው ማለት ነው። አንድ የሁለት ልጆች አባት “ልጆችን የሚያበሳጫቸው ዋነኛው ነገር ያዝ ለቀቅ ማድረግ ነው” ይላል። (ኤፌሶን 6:4) እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ የቤተሰብ ጥናት የሚደረግበትን ቀንና ሰዓት ከወሰንን በኋላ በዚያ ፕሮግራም መሠረት የቤተሰብ ጥናቱ ሁልጊዜ ሳይተጓጎል ይመራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ልጆቹ ጊዜው ሲደርስ ጥናቱን መጠባበቅ ጀመሩ።” ‘አንድ ችግኝ የሰጠኸውን ቅርጽ ተከትሎ ያድጋል’ እንዲሉ ከሕፃንነት ጀምሮ የሚሰጡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሥልጠናዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው።
17. ለትናንሽ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መመገብ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ለትናንሽ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መመገብ አስፈላጊ የሆነውን ያህል የወላጅ ምሳሌነትም አስፈላጊ ነው። ልጆችህ የግል ጥናት ስታደርግ፣ ዘወትር በስብሰባዎች ላይ ስትገኝና በመስክ አገልግሎት ስትሳተፍ አዎን፣ የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ስትደሰት ያዩሃል? (መዝሙር 40:8) እንዲህ ስታደርግ ማየታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። አንዲት ልጅ ከባሏ የደረሰባትን ተቃውሞ ተቋቁማ ስድስት ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ልጆች ስላሳደገችው እናቷ ስትገልጽ “እኛን የማረከን ከቃላት ይልቅ የጎላ ድምፅ የነበረው የራስዋ የእማማ ምሳሌነት ነበር” ብላለች።
ለትናንሽ ልጆች ጥበቃ ማድረግ
18. (ሀ) ወላጆች ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ጥበቃ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) በእስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ትናንሽ ልጆች ስለ መዋለጃ አካላት ምን ዓይነት ትምህርት ይሰጣቸው ነበር?
18 ብዙውን ጊዜ ችግኞችን ከጎጂ ነፍሳት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ሁሉ በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ትናንሽ ልጆች ‘ከክፉ ሰዎች’ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ያስፈልጋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) ወላጆች ይህን ጥበቃ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? ልጆቻቸው መለኮታዊ ጥበብ እንዲያገኙ በመርዳት ነው! (መክብብ 7:12) ይሖዋ ‘ትናንሽ ልጆችን’ ጨምሮ እስራኤላውያንን ሕጉ ሲነበብ እንዲያዳምጡ አዝዞ ነበር። ይህም ተገቢ ስለ ሆነውና ተገቢ ስላልሆነው የጾታ ሥነ ምግባር የሚገልጹትን ሕጎች ይጨምራል። (ዘዳግም 31:12፤ ዘሌዋውያን 18:6-24) “የወንድ የዘር ፍሬ”ን እና “የወንድና የሴት አባለ ዘር”ን ጨምሮ የመዋለጃ አካሎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሰዋል። (ዘሌዋውያን 15:1-3, 16 አዓት፤ 21:20 አዓት፤ 22:24 አዓት፤ ዘኁልቁ 25:8 አዓት፤ ዘዳግም 23:10) በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም በሥነ ምግባር በጣም ስለተበላሸ ትናንሽ ልጆች አምላክ “እጅግ መልካም” ካላቸው የፍጥረት ሥራዎች መካከል ስለሆኑት ስለነዚህ የአካል ክፍሎች ተገቢ ስለ ሆነውና ተገቢ ስላልሆነው አጠቃቀም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።—ዘፍጥረት 1:31፤ 1 ቆሮንቶስ 12:21-24
19. ለትናንሽ ልጆች ስለ ራሳቸው የአካል ክፍሎች ምን ተገቢ ትምህርት ሊሰጣቸው ይገባል?
19 ቢቻል ሁለቱም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች አንድ ላይ ሆነው ለልጁ የራሱን የአካል ክፍሎች ማሳወቅ አለባቸው። ከዚያም ማንኛውም ሌላ ግለሰብ እነዚህን የአካል ክፍሎች መንካት እንደማይፈቀድለት መግለጽ ይኖርባቸዋል። ልጆችን በጾታ የሚያስነውሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ትናንሽ ልጆች ወሲብ ሲቃጣባቸው ምን ዓይነት ስሜት እንደሚያሳዩ ለማወቅ ስለሚፈልጉ አንድ ልጅ እንዴት አጥብቆ መቃወምና “እናገርብሃለሁ!” ማለት እንደሚችል መማር አለበት። ትናንሽ ልጆቻችሁ ቢያስፈራራቸውም እንኳ በማይፈልጉት መልኩ ሊደባብሳቸው የሚሞክረውን ሰው ሁልጊዜ እንዲነግሯችሁ አስተምሯቸው።
ፍቅራዊ ተግሣጽ መስጠት
20. (ሀ) ተግሣጽ ዛፎችን ከመከርከም ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ተግሣጽ መጀመሪያ ላይ የሚያስገኘው ውጤት ምንድን ነው? ይሁን እንጂ የመጨረሻው ውጤት ምንድን ነው?
20 አንድ ዛፍ መከርከሙ ጠቃሚ እንደሆነ ሁሉ ትናንሽ ልጆችም ፍቅራዊ ተግሣጽ ሲሰጣቸው ይጠቀማሉ። (ምሳሌ 1:8, 9፤ 4:13፤ 13:1) አንድ የማይፈለግ ቅርንጫፍ ሲቆረጥ ሌሎቹ ቅርንጫፎች በቀላሉ ማደግ ይችላሉ። ስለዚህ ልጆችህ በተለይ ቁሳዊ ንብረቶች ላይ የሚያተኩሩ ከሆነ ወይም መጥፎ ጓደኛ መያዝ ከጀመሩ ወይም ጤናማ ያልሆነ መዝናኛ የሚያዘወትሩ ከሆነ እነዚህ መጥፎ ዝንባሌዎች መቆረጥ እንደሚያስፈልጋቸው ቅርንጫፎች ናቸው። እነዚህ ነገሮች መወገዳቸው ልጆቻችሁ መንፈሳዊ አቅጣጫ ይዘው እንዲያድጉ ይረዳቸዋል። አንድ ዛፍ ሲከረከም ለጊዜው አንድ ዓይነት ጉዳት ሊደርስበት እንደሚችል ሁሉ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ዓይነቱ ተግሣጽ ደስ አያሰኝም። ይሁን እንጂ ተግሣጽ መጨረሻ ላይ የሚያስገኘው ጥሩ ውጤት ልጅህ እንዲያድግ በምትፈልግበት አቅጣጫ ማደግ መቀጠሉ ነው።—ዕብራውያን 12:5-11
21, 22. (ሀ) ተግሣጽ መስጠትም ሆነ መቀበል አስደሳች አለመሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ወላጆች ተግሣጽ ከመስጠት ወደ ኋላ ማለት የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
21 ተግሣጽ መስጠትም ሆነ መቀበል አስደሳች እንዳልሆነ የታወቀ ነው። አንድ አባት እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ልጄ ከአንድ ወጣት ጋር ብዙ ጊዜ አብሮ ያሳልፍ ስለነበር ሽማግሌዎች ልጄ ከዚህ ወጣት ጋር መግጠሙ ጥሩ እንዳልሆነ በመግለጽ አስጠነቀቁኝ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ነበረብኝ። ምንም እንኳ ልጄ ከበድ ያለ መጥፎ ድርጊት ያልፈጸመ ቢሆንም አመለካከቱን እንደገና ለማስተካከል ብዙ ጊዜ ወስዶብኛል።” ልጁ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰንዝሯል፦ “በጣም ከምወደው ጓደኛዬ ስለይ በጣም አዝኜ ነበር።” ሆኖም አክሎ እንዲህ አለ፦ “ይህ ውሳኔ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም ይህ ጓደኛዬ የተወገደው ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ነው።”
22 የአምላክ ቃል “የተግሣጽ ዘለፋ የሕይወት መንገድ ነው” ይላል። ስለዚህ ተግሣጹ የቱንም ያህል ከባድ ቢሆን ልጆችህን ከመገሠጽ ወደ ኋላ አትበል። (ምሳሌ 6:23፤ 23:13፤ 29:17) ከጊዜ በኋላ አንተ ስለ ሰጠሃቸው እርማት አመስጋኞች ይሆናሉ። አንድ ወጣት “ተግሣጽ ሲሰጠኝ በወላጆቼ በጣም እናደድ የነበርኩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ሆኖም ወላጆቼ ያንን ተግሣጽ ሳይሰጡኝ ቀርተው ቢሆን ኖሮ አሁን ከዚያ የበለጠ እናደድ ነበር” በማለት ያስታውሳል።
የሚገኘው ወሮታ ሲታይ ቢደከምለትም አይቆጭም
23. ለልጆች የሚደረገው ፍቅራዊ እንክብካቤ የማያስቆጭ የሆነው ለምንድን ነው?
23 ወላጆችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች የሚደሰቱባቸው ልጆች በየዕለቱ የተደረጉ ብዙ ፍቅራዊ እንክብካቤዎች ውጤት እንደሆኑ ምንም አያጠያይቅም። ሆኖም ለመንፈሳዊ ልጆችም ሆነ ለሥጋዊ ልጆች የቱንም ያህል ቢደከም ከሚያስገኘው አስደሳች ወሮታ አንፃር ሲታይ የሚያስቆጭ አይደለም። አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” ሲል በጻፈበት ወቅት ይህን ገልጿል።—3 ዮሐንስ 4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
ታስታውሳለህን?
◻ ችግኞችም ሆኑ ልጆች የሚያስደስቱ እንዲሆኑ ምን ያስፈልጋቸዋል?
◻ ወላጆች ውጤታማ የድጋፍ እንጨት ሆነው ማገልገል የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ የትናንሽ ልጆች የማስተማሪያ ጊዜያት ምን ነገሮችን ሊያካትቱ ይችላሉ? ልጆች ምን መቋቋም እንዲችሉ መማር ያስፈልጋቸዋል?
◻ አንድ ዛፍ መከርከሙ ጠቃሚ እንደሆነ ሁሉ ተግሣጽ ለልጆች ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
[ምንጭ]
Courtesy of Green Chimney’s farm