ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲማሩ ለመርዳት የተዘጋጀ አዲስ መሣሪያ
“የጽሑፉ አቀራረብ ቀላል፣ ቀጥተኛና ደግነት የተንጸባረቀበት በመሆኑ ከምንገምተው የበለጠ ብዙ ውጤት ያስገኛል። ያልተወሳሰበና ማራኪ የሆነው የትምህርቱ አቀራረብ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘በእውነትም አምላክ በመካከላችሁ’ ነው እንዲሉ የሚያደርግ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 14:25) ይህ በታይላንድ አገር የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን አዲስ ብሮሹር አስመልክቶ የሰጠው አስተያየት ነው። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበሩ ይህን ጽሑፍ ያወጣው “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በሚል ጭብጥ በ1996/97 በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ነበር።
ይህ 32 ገጾች ያሉት ባለ ሙሉ ቀለም ብሮሹር የተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማካሄድ እንዲያገለግል ታስቦ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ይዳስሳል። ቀለልና እጥር ምጥን ባሉ ቃላት አምላክ ምን እንደሚፈልግብን ይገልጻል። አንባቢዎቹ ሐሳቡን ለመረዳት ምንም አይቸገሩም። በዚህ አዲስ ብሮሹር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የምትችለው እንዴት ነው?
ጥያቄዎቹን ተጠቀም። በእያንዳንዱ ክፍለ ትምህርት መጀመሪያ ላይ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ከእያንዳንዱ ጥያቄ በኋላ የጥያቄው መልሶች የሚገኙባቸውን አንቀጾች የሚጠቁም ቁጥር በቅንፍ ውስጥ ተቀምጧል። እነዚህ ጥያቄዎች ትምህርቱን በቅድሚያ ለመቃኘት ሊያገለግሉ ይችላሉ፤ እንዲሁም ከጥናቱ በኋላ ትምህርቱን ለመከለስ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ መጀመሪያ ላይ ተማሪው አስተያየቱን እንዲሰጥ ለማድረግ እነዚህን ጥያቄዎች ልትጠይቀው ትችላለህ። የተሳሳተ መልስ ከሰጠ ወዲያው ከማረም ይልቅ በጥናቱ ልትቀጥል ትችላለህ። በክፍለ ትምህርቱ መጨረሻ ላይ ተማሪው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ መልስ መስጠት ይችል እንደሆነና እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ጥያቄዎቹን መልሰህ ልትጠይቀው ትችላለህ።
ጥቅሶቹን አውጥተህ ተመልከት። በእያንዳንዱ ክፍለ ትምህርት ውስጥ አጠር ባሉ ዓረፍተ ነገሮች የቀረበውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚደግፉ ጥቅሶች ይገኛሉ። አብዛኞቹ ጥቅሶች ምዕራፍና ቁጥራቸው እንጂ ሐሳባቸው ስላልተጻፈ ተማሪው እነዚህን ጥቅሶች ከራሱ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ እንዲያነብ ማበረታታቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የአምላክን ቃል በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይችል ዘንድ ቃሉን ሊያነበውና ሊያሰላስልበት ይገባል።— ኢያሱ 1:8
ስለ ሥዕሎቹ ጎላ አድርገህ ግለጽ። ብሮሹሩ በበርካታ ሥዕሎችና ፎቶግራፎች የተዋበ ሲሆን በጠቅላላ ከ50 የሚበልጡ የሥዕል ሥራዎች ይዟል። እነዚህ ሥዕሎች የቀረቡት ብሮሹሩን ለማሳመር ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የማስተማሪያ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለገልሉ ሲባል ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል (በትይዩ ገጾች ላይ የሚገኙትና እያንዳንዳቸው አንድ ገጽ ያላቸው) የመጨረሻዎቹ ሁለት ክፍለ ትምህርቶች “ሌሎች የአምላክን ፈቃድ እንዲያደርጉ መርዳት” እና “አምላክን ለማገልገል የምታደርገው ውሳኔ” የሚል ርዕስ አላቸው። በሁለቱ ገጾች ላይ ያሉት ፎቶግራፎች አንድ ሰው ያደረገውን መንፈሳዊ መሻሻል የሚያሳዩ ናቸው። መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሲመሠክር፣ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ ሲካፈል፣ ራሱን ሲወስን እና በመጨረሻም ሲጠመቅ ይታያል። ተማሪው በእነዚህ ሥዕሎች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ አምላክን ለማገልገል ምን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልገው እንዲያስተውል ትረዳዋለህ።
ፍላጎት ያሳየ አንድ ሰው ማንበብ የሚቸግረው ወይም ጭራሹኑ ማንበብ የማይችል ከሆነስ? ማኅበሩ ይህን ብሮሹር በበርካታ ቋንቋዎች በካሴት አዘጋጅቷል። ካሴቱ የብሮሹሩን አንቀጾች እንዲሁም ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ብዙ ጥቅሶች ይዟል። አቀዳዱ እንደሚከተለው ነው:- የመጀመሪያው ጥያቄ ከተነበበ በኋላ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን አንዳንዶቹን ጥቅሶች ጨምሮ የጥያቄው መልስ የሚገኝበት አንቀጽ ወይም አንቀጾች ይነበባሉ። ከዚያ እንደገና የሚቀጥለው ጥያቄ ይነበባል፣ መልሱን የያዘው አንቀጽና ጥቅሶቹ ይነበባሉ፤ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። ተማሪው ለጥናቱ በሚዘጋጅበት ጊዜ የተቀዳውን ካሴት ሊያዳምጥ ይችላል። ጥናት በሚመራበትም ጊዜ ይህንን ካሴት መጠቀም ይቻላል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ይህን አዲስ ብሮሹር በመስክ አገልግሎታቸው ለመጠቀም በጣም ጓጉተው ነበር። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ሁለት አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን) ብሮሹሩን ካገኙ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተመላልሶ መጠየቅ ለሚያደርጉላቸው አንድ ወጣት ባልና ሚስት ያበረክቱላቸዋል። ባልና ሚስቱ የርዕስ ማውጫውን ሲመለከቱ “አምላክ የሚጠላቸው ድርጊቶች” የሚለው ትምህርት ላይ ዓይናቸው አረፈ። ወጣቷ ሚስት እንዲህ አለች:- “አምላክ ፈጽሞ የሚጠላው ነገር የለም፤ እርሱ ፍቅር ነው እየተባልኩ ስማር ኖሬአለሁ። አሁን መጀመሪያ ማንበብ የምፈልገው ይህንን ርዕስ ነው።” ሁለቱ አቅኚዎች በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሰው ሲሄዱ ወጣቷ ሴት እንዲህ አለች:- “አዲሱን ብሮሹር አንብቤዋለሁ። ልናደርገው የሚገባንን ነገር ሁሉ አሟልቶ መገኘት ቀላል አይደለም። በሕግ ባለመጋባታችን ይሖዋ በእኛ አይደሰትም። ይሁን እንጂ አንድ ውሳኔ ላይ ደርሰናል። በሚቀጥለው ዓርብ ጋብቻችንን እንፈጽማለን።” አቅኚዎቹን ባልና ሚስት እቅፍ አድርገው ይዘው “እስካሁን ቋሚ ጥናት ባለመጀመራችን ይቅርታ አድርጉልን፤ አሁን ትልቅ ሸክም ከትከሻችን ላይ ወርዶልናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ይህን አዲስ ብሮሹር ለመጠቀም ወደኋላ አትበሉ። ሌሎች ሰዎች አምላክ የሚፈልግባቸውን እንዲማሩ ለመርዳት የተዘጋጀ ግሩም መሣሪያ ነው።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አዲሱን ብሮሹር እንዴት ልትጠቀምበት አስብሃል?