ተሞክሮ የሌላቸውን እንዲያስተውሉ እርዷቸው
1 ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ አማካኝነት ሌሎች አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው እንዲያስተውሉ እናስተምራለን። (ማቴ. 28:19, 20) በዓለም ዙሪያ ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ ምሥክሮች ከፍተኛ ሥራ እያከናወኑ ነው። ስኬታማነት በስብከቱ ሥራ ላይ በዋለው ሰዓት፣ በተበረከቱ ጽሑፎች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጀመሩ ሰዎች ብዛት አይለካም። ሰዎች የተማሩትን ነገሮች ሲያስተውሉና በሥራ ላይ ሲያውሉት ያን ጊዜ ግባችን ላይ እንደርሳለን።
2 ሌሎችን በመንፈሳዊ መርዳት ‘ተሞክሮ የሌላቸውን አስተዋዮች ማድረግንም’ ይጨምራል። (መዝ. 119:130 NW ) ሰዎች ልባቸው የሚነካውና ለተግባር የሚንቀሳቀሱት “ትርጉሙን ሲያስተውሉ” ብቻ ነው። (ማቴ. 15:10 NW ) ሥራችን እየተስፋፋና እያደገ በሄደ መጠን ቀለል ባለ መንገድ የመናገርንና የማስተማርን አስፈላጊነት የበለጠ እየተገነዘብን እንሄዳለን። ማኅበሩ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር ያዘጋጀውም በዚህ ምክንያት ነው። ብሮሹሩ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶችን ጠቅለል ባለ መንገድ ይሸፍናል። ትምህርቶቹ አጠር ያሉ፣ ቃላቱ ቀላልና ትምህርቱ በቀላሉ የሚገባ መሆኑ ብሮሹሩን በስፋት እንዲታወቅ አድርጎታል።
3 ቀለል ያለ አቀራረብ ተጠቀሙ:- አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተሰኘውን ብሮሹር በምታስተዋውቁበት ጊዜ በገጽ 2 ላይ “ይህ ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀ ነው” የሚለውን ሐሳብ ጥቀሱ። ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚኖርበት ለምን እንደሆነ ለመግለጽ ገጽ 3 አንቀጽ 3 ላይ የሰፈረውን ትምህርት አሳዩ። ቀለል ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን የሚያብራሩትን አንዳንድ የትምህርቱን ርዕሶች በማንበብ የሰውየውን ፍላጎት ቀስቅሱ። ይህን ብሮሹር ማጥናት እንዴት ደስታ እንደሚያስገኝ አሳዩ። በግል ልትረዱት እንደምትፈልጉም ግለጹለት።
4 እድገት የሚያደርጉ ጥናቶችን ምሩ:- ግባችን ጥናቶችን መምራት ብቻ ሳይሆን አለማወላወል እውነተኛ አምልኮን የሚደግፉ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ነው። ብሮሹሩ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ተሸፍኖ ካለቀ በኋላ እውቀት ወደተሰኘው መጽሐፍ መሸጋገር ይገባል። (ገጽ 31 ላይ ያለውን የብሮሹሩን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።) ገና ከጅምሩ ተማሪው የይሖዋ ምድራዊ ድርጅትን ለይቶ እንዲያውቅ እርዱት። (ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 283-4 ተመልከት።) የጉባኤ ስብሰባዎችን ጠቀሜታ ጠበቅ አድርጋችሁ ግለጹ፤ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ መገኘት እውነተኛውን አምልኮ በሥራ ላይ እንዴት መተግበር እንደሚቻል አጠቃላይ ግንዛቤ እንደሚያስጨብጥ አብራሩለት።— ዕብ. 10:24, 25
5 በዚህ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ማድረጋችን ቅን የሆኑ ሰዎች ሕይወት የሚያስገኝላቸውን ‘ማስተዋል እንዲያገኙ’ በመርዳት የሚገኘውን ደስታ እንደሚያሳጭደን የተረጋገጠ ነው።— ምሳሌ 4:5