ለሌሎች ልባዊ ኣሳቢነት በማሳየት ይሖዋን ምሰል
1 ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት በማሳየት በኩል ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። እርሱ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ በመሆኑ ሰብዓዊ ፍጥረታቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ጠንቅቆ ከማወቁም በላይ ለእነሱ ያስብላቸዋል። (1 ጴጥ. 5:7) ኢየሱስ በጻድቃንና በኃጢአተኞች ላይ ፀሐይ እንዲወጣና ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርገውን የአባቱን ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ተከታዮቹን አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 5:45) አንተም ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት በማሳየት ማለትም ለምታገኘው ሰው ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት ለማካፈል ዝግጁ በመሆን ይሖዋን መምሰል ትችላለህ። በሐምሌ ወር በሚደረገው አገልግሎት ከምንጠቀምባቸው ብሮሹሮች ጋር በሚገባ ከተዋወቅህ ሌሎች ሰዎችን በመንፈሳዊ ሊረዱ የሚችሉትን እነዚህን ብሮሹሮች ለማበርከት ብቁ ትሆናለህ። ሰዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማነጋገርና ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ቀጣይ የሆነ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ እንዴት መዘጋጀት እንደምትችል የሚከተሉት ሐሳቦች አንዳንድ ፍንጭ ይሰጡሃል።
2 “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተሰኘውን ብሮሹር ስታበረክት እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “አምላክ በእርግጥ የሚያስብላቸው ከሆነ ሰዎች ሥቃይና መከራ እንዲደርስባቸው የሚፈቅደው ለምንድን ነው ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ይህ ብሮሹር ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ የሆነ መልስ ከመስጠቱም በላይ ሰው በራሱና በሚኖርባት ምድር ላይ ያደረሰውን ጉዳት ሁሉ አምላክ እንደሚያስተካክል የገባውን ቃል ይገልጻል።” ገጽ 27 አንቀጽ 23ን አንብብ። ከታች በኩል የሚገኘውን ሥዕል አሳየውና በአንቀጽ 22 ላይ ያለውን መዝሙር 145:16ን አንብብ። ከዚያም ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው። ብሮሹሩን ከተቀበለ በሚቀጥለው ጉብኝትህ የሚመለስ አንድ ጥያቄ አቅርብ፤ ለምሳሌ “አምላክ የሰውን ዘር ለመባረክ ሲል ዓላማውን ወደ ፍጻሜ የሚያመጣውና ምድርን ወደ ገነትነት የሚለውጠው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ይፈልጋሉ?” የሚል ጥያቄ ልታቀርብ ትችላለህ።
3 “አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን?” የተሰኘውን ብሮሹር ወዳበረከትክላቸው ሰዎች ተመልሰህ ስትሄድ በዚህ መንገድ ውይይት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ አምላክ በእርግጥ እንደሚያስብልንና ሰው በራሱና በሚኖርባት ምድር ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ዓላማ እንዳለው ተመልክተን ነበር።” ብሮሹሩን ገልጠህ በገጽ 2ና 3 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየውና እንዲህ በለው:- “ውይይታችንን ያቆምነው አምላክ የሰውን ዘር ለመባረክና ምድርን ወደ ገነትነት ለመለወጥ ያለውን ዓላማ ወደ ፍጻሜው የሚያመጣው እንዴት ነው? የሚለውን ጥያቄ አንስተን ነበር። ታዲያ እርስዎ ምን ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ገጽ 17ን ግለጥና አንቀጽ 2ንና ዳንኤል 2:44ን አንብብ። ከዚያም ገጽ 18 አንቀጽ 12ን አንብብ። ከብሮሹሩ ውስጥ ክፍል 9ን አብራችሁ እንድትመለከቱት ይፈልግ እንደሆነ የቤቱን ባለቤት ጠይቅ። ፍላጎት ካለው አብራችሁ አጥኑት።
4 “የምትወዱት ሰው ሲሞት” የተሰኘውን ብሮሹር ለማበርከት የሚከተለውን አቀራረብ መጠቀም ትፈልግ ይሆናል። ሽፋኑን አሳይና እንዲህ በል:-
◼ “የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ላጡ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መጽናኛና ተስፋ የሚሰጠውን ይህንን ብሮሹር በዛሬው ዕለት ለሌሎች ሰዎች በማዳረስ ላይ ነን። የሞቱ ሰዎች ምን ተስፋ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] አምላክ የሞቱ ሰዎችን በትንሣኤ እንደሚያስነሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ይናገራል።” ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ። ብሮሹሩን ገልጠህ በገጽ 28 ላይ የሚገኘውን የመጨረሻ አንቀጽና በገጽ 31 የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ ያሉትን ነጥቦች አብራራ። ከአንቀጾቹ ሐሳብ ጋር የሚሄዱትን ሁለቱን ሥዕሎች አሳየው። ከዚያም ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘው። “በመጨረሻም ሞት ለዘለቄታው እንደሚጠፋ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?” ብለህ በመጠየቅ ለተመላልሶ መጠየቅ መንገድ ልትከፍት ትችላለህ።
5 “የምትወዱት ሰው ሲሞት” የተሰኘውን ብሮሹር ላበረከትክላቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ይህን መግቢያ ለመጠቀም ትፈልግ ይሆናል።
◼ “ባለፈው ጊዜ ስለ ትንሣኤ አስደናቂ ተስፋ ተወያይተናል። ትቼልዎት የሄድኩት ብሮሹር በመጨረሻ ሞት ለዘለቄታው እንደሚጠፋ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምን እንደሆነ ያብራራል። አምላክ የገባው ቃል የሚያጽናና እና መንፈስን የሚያረጋጋ ሆኖ አላገኙትም?” መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ከዚያም ብሮሹሩን ገጽ 31 ላይ ግለጥና ሁለተኛውንና ሦስተኛውን አንቀጽ ከራእይ 21:1-4 ጋር አንብብ። ሳይሞቱ ለዘላለም በመኖር ረገድ ያለንን አስደሳች ተስፋ ጎላ አድርገህ ግለጽ። ሰውየው በሚያሳየው ፍላጎትና በወቅቱ ባሉት ሁኔታዎች ላይ ተመርኩዘህ ለዘላለም መኖር ወይም እውቀት በተባሉት መጽሐፎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልትጀምርለት አለዚያም ለሚቀጥለው ተመላልሶ መጠየቅ መንገድ የሚከፍት ሌላ ጥያቄ ልታቀርብ ትችላለህ።
6 “የሙታን መናፍስት” የተሰኘውን ብሮሹር ስታስተዋውቅ እንዲህ ማለት ትችላለህ:-
◼ “በዓለም ዙሪያ ክፋት ለምን እየበዛ እንደሚሄድ ብዙ ሰዎች ይጠይቃሉ። አምላክ ሰይጣን የማይኖርበት አንድ አስደሳች ዓለም እንደሚያመጣ ቃል መግባቱን ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እባክዎ ይህን ሥዕል ይመልከቱ።” የሙታን መናፍስት የተሰኘውን ብሮሹር ገጽ 28 ላይ አውጣና ማብራሪያ ስጥ። ጊዜ ካለህ በገጽ 28 ላይ ያለውን ሐሳብ አንብብ። ከዚያም በገጽ 29 እና 30 ላይ ያሉትን ንዑስ ርዕሶች አሳይና ብሮሹሩን አበርክት።
7 “የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች” የተሰኘውን ብሮሹርም ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትጠቀምበት ትችላለህ። ይህን አቀራረብ እንድትጠቀም ሐሳብ እናቀርባለን:-
◼ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የተነሳበት ቀን እንደሆነ አድርገው በማመን ብዙ ሰዎች የትንሣኤን በዓል ካከበሩ ብዙም አልቆዩም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ እንዳለ ለማወቅ ብዙዎች አይጨነቁም። ጥቂት ሥዕሎችን በመጠቀም በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ መሆኑን ባጭሩ ላሳይዎት እፈልጋለሁ። [ብሮሹሩን ገጽ 12ና 13 ላይ አውጣ። ገጽ 12 ላይ የሚገኘውን ሁለተኛውን አንቀጽ ተመርኩዘህ መልአኩ ለማርያም ያበሰራትን መልእክት ልታብራራ ትችላለህ። ከዚያም በገጽ 13 ላይ የሚገኙትን ሥዕሎች ካሳየህ በኋላ በዚሁ ገጽ ላይ ያለውን የመጨረሻ አረፍተ ነገር አንብብ።] ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ምን ነገሮችን እንደሚያከናውን የሚገልጹትን አስደሳች ነገር ከዚህ ብሮሹር መማር ይችላሉ።” ገጽ 21ን ግለጥና አሳየው። ብሮሹሩን እንዲወስድ ጋብዘውና በገጽ 21 ላይ የሚገኘውን ትንቢት በሚቀጥለው ጊዜ እንደምታብራራ ግለጽ።
8 አገልግሎታችን ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች “እውነትን እንዲያውቁ” ለመርዳት ልባዊ ምኞት እንዳለን ማንጸባረቅ ይኖርበታል። (1 ጢሞ. 2:4 የ1980 ትርጉም) ስለዚህ ብሮሹር ላበረከትክለት ለእያንዳንዱ ሰው ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ በአገልግሎት ፕሮግራምህ ውስጥ ጊዜ መድብ። ለእነርሱ የምታሳየው ልባዊ አሳቢነት በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ በሚፈጸሙት እርኩስ ድርጊቶች የሚያዝኑና የሚተክዙ ሰዎች ከጥፋት በሕይወት ለመትረፍ እንዲችሉ ይረዳቸው ይሆናል። (ሕዝ. 9:4, 6) በተጨማሪም ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት በማሳየት ይሖዋን እየመሰልክ እንዳለህ በማወቅህ ደስታና እርካታ ታገኛለህ።— ከፊልጵስዩስ 2:20 ጋር አወዳድር።