በብሮሹሮች ተጠቅማችሁ የመንግሥቱን ምሥራች አውጁ
1 እውነትን ማወቅና ምሥራቹን በቅንዓት ከሚያውጁ ሰዎች መካከል መሆን እንዴት የሚያስደስት ነው! ከአምላክ ድርጅት ውጪ ያሉ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች መስማታቸው አጅግ አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ ነው። በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!፣ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም፣ የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች እና የሙታን መናፍስት በተባሉት ብሮሹሮች አማካኝነት የመንግሥቱ እውነት ቀለል ባለ መንገድ ተብራርቷል። እነዚህ ብሮሹሮች የአምላክ መንግሥት በምትገዛበት ጊዜ ሕይወት ምን እንደሚመስል ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ከመስጠታቸውም በላይ አንባቢው በአምላክ ቃል ውስጥ በተገለጹት የመንግሥቱ እውነታዎች ላይ እንዲያተኩር ያደርጋሉ። እርግጥ፣ ፍላጎት ላሳየ ሰው ብሮሹር ማበርከት የሥራችን መጀመሪያ ብቻ ነው። (1 ቆሮ. 9:23) ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ወይም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ በተሰኙት መጽሐፎች አማካኝነት ጥናት የማስጀመር ግብ በመያዝ ብሮሹር ያበረከትንላቸውን ሰዎች ተከታትለን እንርዳቸው። በነሐሴ ወር ይህን መፈጸም የምንችለው እንዴት ነው?
2 “በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር!” የተሰኘውን ብሮሹር አጠር ያለ መግቢያ ተጠቅመን ልናበረክት እንችላለን። ሽፋኑን በማሳየት እንዲህ ለማለት ትችላለህ:-
◼ “አንድ በጣም አስደሳች መልእክት የያዘ ብሮሹር ላሳይዎት እፈልጋለሁ።” በደስታ ኑር! የተሰኘውን ብሮሹር ግለጥና የመግቢያውን የመጀመሪያ አንቀጽ አንብብ። በተጨማሪም ብሮሹሩ “[ከሥዕል ቁጥር 8 አናት ላይ ያለውን ርዕስ አውጥተህ] ‘ሰው ለምን ይሞታል?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል። በዚህ ብሮሹር ውስጥ ያሉትን ሥዕሎች ቢያጠኑና ጥቅሶቹን ቢያነቡ ብሮሹሩን አስደሳች ሆኖ ያገኙታል። እንዲህ ለማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ ይህን ቅጂ ሊወስዱ ይችላሉ።”
3 “በደስታ ኑር!” የተሰኘውን ብሮሹር ላበረከትክላቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ስታደርግ ምን ብለህ ልትናገር ትችላለህ? ይህንን አቀራረብ ልትጠቀም ትችላለህ:-
◼ በደስታ ኑር! በተሰኘው ብሮሹር ውስጥ የሚገኘውን ሥዕል ቁጥር 49ን ካሳየኸው በኋላ “ይህ ሥዕል ደስ አይልም?” ብለህ ጠይቅ። [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] “ሥዕሉ የሚገኘው ባለፈው ጊዜ በወሰዱት ብሮሹር ውስጥ ነው። በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚገኘውን ጥያቄ ልጠይቅዎት እፈልጋለሁ።” ሥዕል ቁጥር 50ን አውጣና “‘በዚያ ውብ ገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ትፈልጋለህ?’ የሚለውን ጥያቄ አንብብ። [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የሚፈልጉ ከሆነ ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለብዎ የሚናገረውን ልብ ይበሉ:- ‘እግዚአብሔር ምን እንዳለ ለማወቅ መማርህን ቀጥል’ ይላል። [ዮሐንስ 17:3ን አንብብ] መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ ከእርስዎ ጋር ብናጠና በጣም ደስ ይለኛል። ማጥናት ይፈልጋሉ?” ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ የሚያስችል ቁርጥ ያለ ቀጠሮ ያዝ።
4 ለውይይት የሚረዱ የተለያዩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ርዕሶችን ከመረጥክ በኋላ “ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም” የተሰኘውን ብሮሹር ማበርከት ትችላለህ። በተጨማሪም ቀጥሎ ያለውን በመናገር በቀላሉ ውይይት መጀመር ይቻላል:-
◼ “በጌታ ጸሎት ውስጥ በመጀመሪያ የምናቀርበውን ልመና የበለጠ ለማወቅ እንዲችሉ የአምስት ደቂቃ ጊዜ እንደሚሰጡን ተስፋ እናደርጋለን። [ከዚያም ማቴ. 6:9ን ካወጣህ በኋላ ፈጣሪያችን ብዙ የማዕረግ ስሞች ቢኖሩትም አንድ ቅዱስ ስም ብቻ እንዳለው ግለጽ። ከዚያም የሚከተለውን መጨመር ትችላለህ:-] አንድ ሰው የአምላክን ቃል እንዲያውቅና እንዲያከብር ከተፈለገ አምላክን በሚገባ ማወቅ ይኖርበታል። እኛም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳውን ይህን ትምህርት ሰጪ ጽሑፍ ለሰዎች የምናበረክተው አንደኛው ምክንያት ይህ ነው። [ብሮሹሩን አሳየው።] ይህ ብሮሹር የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን እዚህ ገጽ 31 ላይ እንደሚናገረው የአምላክን ስም ማወቅ የሚያስገኘውን ጥቅም ጭምር ያብራራል። [አንቀጽ 1ን አንብብ።] - - አስተዋጽኦ አድርገው ይህን ቅጂ መውሰድ ይችላሉ።”
5 ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወቅት ከዚህ ቀጥሎ በቀረበው ቀለል ያለ ሐሳብ በመጠቀም በዚሁ ብሮሹር አማካኝነት ጥናት ማስጀመር ትችላለህ:-
◼ የቤቱ ባለቤት የወሰደውን ቅጂ ገጽ 6 ላይ እንዲያወጣ ጠይቅ። “የአምላክ ስም— ትርጉሙና አነባበቡ” የሚለውን ርዕስ አንብብ። የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ማወቅ ብንችል ምን እንደሚሰማው ጠይቀው። መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት። ይህ የብሮሹሩ ክፍል ለዚህ ጥያቄ መልስ እንደሚሰጥ ንገረው። የምታነጋግረው ሰው የመጀመሪያውን አንቀጽ አብሮህ እንዲያነብ ጋብዘውና የተጠቀሱትን ጥቅሶች እያወጣችሁ ተወያዩ። ፈጣሪ ራሱ ባይነግረን ኖሮ ስሙን ልናውቅ የምንችልበት መንገድ እንደሌለ የሚገልጸውን ነጥብ ጎላ አድርገህ ግለጽ። አንቀጹንና ጥቅሶቹን ማንበባችሁንና መወያየታችሁን ቀጥሉ።
6 “የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች” የተሰኘውን ብሮሹር ስታበረክት የሚከተለውን አቀራረብ ልትሞክር ትችላለህ:-
◼ “ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ያሉት ትልልቅ ችግሮች በሌሉበት ዓለም ውስጥ መኖር እንደሚፈልጉ ሰምቻለሁ። [እንደ ሥራ አጥነት፣ የዓመፅ ብዛት፣ ድህነት፣ በሽታና የቤተሰብ ግጭት የመሳሰሉትን በአካባቢህ የሚገኙ ችግሮች ጥቀስ።] እነዚህ ችግሮች የወደፊቱ ጊዜ ለእኛም ሆነ ለምንወዳቸው ሰዎች አስተማማኝ ሆኖ እንዳይሰማን አድርገዋል። የሰው ልጆች እነዚህን ችግሮች ማስወገድ ይችላሉ ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] የጌታን ጸሎት ጸልየው ይሆናል። ጸልየው ከነበረ ጻድቅ የሆነ መስተዳድር ከሰማይ እንዲመጣ እንደጸለዩ ልብ ብለውታል?” መንግሥት የተሰኘውን ብሮሹር ገጽ 3 ላይ አውጣና እስከ አንቀጹ መሃል ድረስ አንብብ። ከዚያም ብሮሹሩን እንዲወስዱ ጋብዛቸው።
7 “የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች” የተሰኘውን ብሮሹር አበርክተህ ከነበረ ተመላልሶ መጠየቅ በምታደርግበት ወቅት ውይይታችሁን እንዲህ በማለት መጀመር ትችላለህ:-
◼ “ባለፈው ጊዜ ሰዎች ያሉባቸው ችግሮች መፍትሄ ማግኘት እንደሚኖርባቸው ተወያይተን ነበር። የወሰዱት ብሮሹር የአምላክ መንግሥት ብቸኛ ተስፋችን እንደሆነ ይናገራል። አንዳንድ ሰዎች ይህ መንግሥት ኑሯችንን ለማሻሻል ምን ሊያደርግ እንደሚችል ለማወቅ ይፈልጋሉ። ክርስቶስ ሰብዓዊ መሪዎች ማድረግ ያቃታቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ ማድረግ እንደሚችል ቀደም ሲል እንዳረጋገጠ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል።” መንግሥት የተሰኘውን ብሮሹር ገጽ 29 ላይ አውጣና የመጨረሻዎቹን አራት አንቀጾች አንብብ። ከዚያም “ይህ ተስፋ አስደሳች አይደለም? ይህንን ጊዜ ለማየት ይፈልጋሉ?” በማለት ጠይቅ። [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ዮሐንስ 17:3ን አንብብ። በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ተጨማሪ ትምህርት እንዲቀስም አበረታታው።
8 ሌሎች ብሮሹሮችን የምትጠቀም ከሆነ ከላይ የቀረቡትን ሐሳቦች እንደ ናሙና አድርገህ በመጠቀም የራስህን አቀራረብ ልታዘጋጅ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል ክፋትና ችግር በምድር ላይ እየበዙ የሄዱት ለምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት “የሙታን መናፍስት” የተሰኘውን ብሮሹር ልታበረክት ትችላለህ። ከዚያም በገጽ 10 ላይ የሚገኘውን ሥዕል አውጥተህ በገጹ ላይ ከሚገኘው ጥቅስ ውስጥ አንዳንድ ክፍሎችን መርጠህ አንብብ። ገጽ 12ን አውጣና በሥዕሎቹ ላይ ሐሳብ ከሰጠህ በኋላ ብሮሹሩን አበርክት። የመንግሥቱን ምሥራች በምትሰብክበት ጊዜ ጥሩ አድርገህ ተዘጋጅ፤ እንዲሁም የይሖዋን በረከት ለማግኘት ጣር።