ስታገለግሉ በተለያዩ ብሮሹሮች ተጠቀሙ
1 በአሁኑ ጊዜ የሰዎችን ስሜት የሚስቡት ርዕሰ ጉዳዮች የተለያዩ ናቸው። በሐምሌ ወር ስታገለግሉ በተለይ በአገልግሎት ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን የሚማርኩ በርከት ያሉ የተለያዩ ዓይነት ብሮሹሮች ልትይዙ ትችላላችሁ። ምናልባትም ከሚከተሉት አቀራረቦች መካከል አንዱን ለመጠቀም ትፈልጉ ይሆናል:-
2 “የአምላክ መንግሥት ገነትን ታመጣለች ” የተባለውን ብሮሹር ስታበረክቱ እንዲህ ብላችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ:-
◼ “አንድ ያልተለመደ ጥያቄ ልንጠይቅዎት ፈልገን ነበር። አምላክ ብቻ ገዢ ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖር ነበር ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረንን አቡነ ዘበሰማያት ወይም አባታችን ሆይ ብለን ስንጸልይ አምላክ መላውን ምድር እንዲገዛ መጠየቃችን ነው። [ገጽ 3 አውጣና ማቴዎስ 6:10 የተጠቀሰበትን የመጀመሪያውን አንቀጽ አንብብ።] በዚህ ዓይነቱ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚፈልጉ ከሆነ ይህንን ብሮሹር ማንበብ ይኖርብዎታል።” ብሮሹሩን እንዲወስደው ሐሳብ አቅርብለት።
3 “የምትወዱት ሰው ሲሞት” የተባለውን ብሮሹር በሚከተለው መንገድ ማበርከት ይቻላል:-
◼ “ሁላችንም የምንወደውን ሰው በሞት የማናጣበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] ስሜትን በሚማርክ መንገድ የተጻፈው ይህ ብሮሹር በቅርቡ እንዲህ ያለ ጊዜ እንደሚመጣ በሚናገረው አስተማማኝ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አማካኝነት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን አጽናንቷል። [ገጽ 5ን አውጣና 1 ቆሮንቶስ 15:21, 22ን ጨምሮ አምስተኛውን አንቀጽ በሙሉ አንብብ። ከዚያም ገጽ 30 ላይ ያለውን ሥዕል አሳየው።] በሞት የተለዩንን የምንወዳቸውን ሰዎች በትንሣኤ ስንቀበል የሚኖረንን ደስታ ሠዓሊው በዚህ መልኩ ገልጾታል። ነገር ግን ይህ አስደሳች ሁኔታ የሚከናወነው የት ነው? ይህ ብሮሹር መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ ይገልጽልዎታል።” ብሮሹሩን ከወሰደ እንዲህ ማለት ትችላለህ:- “ሌላ ጊዜ ተመልሼ በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ውይይት ብናደርግ ደስ ይለኛል።”
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር በሚከተለው ቀጥተኛ አቀራረብ በመጠቀም “በደስታ ኑር! ” የተባለውን ብሮሹር ማበርከት ትችላላችሁ:-
◼ በዚህ አካባቢ ያሉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ ጥያቄዎች እንዳሏቸው እየጠየቅኋቸው ነበር። ይህ ጽሑፍ ብዙውን ጊዜ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን ይዘረዝራል። [ገጽ 2ን አውጥተህ አሳየውና አንዳንድ ጥያቄዎችን ምረጥ።] ከዚያም ስለ ትንሣኤ ከሚያሳየው ከሥዕል 48 ጋር በማያያዝ ከ15–17 ያሉትን ስለ ሞት የሚገልጹ ሥዕሎች አውጥተህ ልታሳየው ትችላለህ። ወይም ደግሞ ከ20–23 ያሉትን ሥዕሎች ከ2 ጢሞ. 3:1–5 ጋር በማያያዝ በአማራጭነት ልትጠቀም ትችላለህ። ብሮሹሩን በማበርከትና ከተቀሩት ጥያቄዎች መካከል በአንዳንዶቹ ላይ ለመወያየት የምትችሉበትን ጊዜ በማመቻቸት ደምድም።
5 “ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም” በተባለው ብሮሹር አማካኝነት የሚከተለውን ቀላል አቀራረብ ለመጠቀም ትፈልጉ ይሆናል:-
◼ “መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጀመሪያ ከተማርኳቸው ነገሮች መካከል አንዱ የአምላክ ስም ነበር። የአምላክ ስም ማን እንደሆነ ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] እስኪ ላሳይዎት። ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዝሙር 83:18 ላይ ይገኛል። [አንብብ።] (የ1980 ትርጉም በገጽ 301 በሚገኘው የቃላት መፍቻው ላይ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ይሖዋ የሚለውን ስም እንደሚያመለክት ይናገራል።) ይህ ብሮሹር የአምላክ ስም የሆነው ይሖዋ ብዛት ባላቸው የተለያዩ ቋንቋዎች እንዴት እንደሚጠራ ያሳያል። [ገጽ 8 ላይ ያለውን ሣጥን አሳየው።] ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎች ይበልጥ ለመማር የሚፈልጉ ከሆነ ይህንን ብሮሹር ማንበብ ይኖርብዎታል።” ብሮሹሩን ለቤቱ ባለቤት ስጠው።
6 በተጨማሪም “የሙታን መናፍስት ሊረዱህ ወይም ሊጎዱህ ይችላሉን? ” ወይም “በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? ” የተባሉትንና እነዚህን የመሳሰሉትን ብሮሹሮች ማበርከት ትችላላችሁ። ልንጠቀም የምንችልባቸው እንደነዚህ ያሉ ግሩም የሆኑ የተለያዩ ብሮሹሮች ስላሉን በእርግጥም “ለገሮች ምሥራቹን ለማካፈል” በደንብ ታጥቀናል።— ኢሳ. 61:1 አዓት