ከዘባቾች ተጠበቅ!
በዛሬው ጊዜ ትንበያዎች ከመበራከታቸውም በላይ የትንበያ መስኮች እንደ አሸን ፈልተዋል። “2000 ዓመት እየቀረበ ሲመጣ እንዲያው ጨርሶ ያልተጠበቀ ባይባልም እንግዳ የሆነ ክስተት እየተከሰተ ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ግራ የሚያጋቡና ብዙውን ጊዜም አስደንጋጭ የሆኑ ነገሮች እየታዩአቸው ነው” በማለት የለንደኑ ዘ ዴይሊ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ የሚደረገው ይህ ልዩ ጥረት ለብዙ ታዛቢዎች ቀደም ሲል ተስፋ ቢደረግባቸውም ሊጨበጡ ያልቻሉ ለውጦች ድግግሞሽ ከመሆን አያልፍም።
በ19ኛው መቶ ዘመን በፈረስ የሚጎተቱ ጋሪዎች በጣም በዝተው ስለነበር አንድ ሰው የአውሮፓ ከተሞች በፈረስ ፋንድያ ይሸፈናሉ ሲል ተንብዮ ነበር። የሰውየው ትንበያ እንዳለው ሳይሆን ቀርቷል። በመሆኑም ትንበያዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ከንቱ ሆነው እንደሚቀሩ ለማጋነን የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት “ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚነገሩ ትንበያዎች የፋንድያ ጥርቅም ናቸው” ብሏል።
ሌሎች ደግሞ ወደፊት አደገኛ ሁኔታ ይመጣል ብለው በሚያስቡ ሰዎች ያሾፋሉ። ለምሳሌ ያህል ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ የንግድ ሥራ ፕሮፌሰር ተፈጥሯዊ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሹ ይሄዳሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ማስጠንቀቂያ ከሚሰጡት ወገኖች ጋር ለመወራረድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደዘገበው ፕሮፌሰሩ “አኗኗራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመሄድ ላይ ነው፤ ደግሞም ለዘላለም በዚህ መልክ ይቀጥላል የሚል አቋም አላቸው” ብለዋል።
በእነዚህ እሰጥ አገባዎች መካከል ደግሞ ሁሉም ነገሮች መሠረታዊ ለውጥ ሳይታይባቸው እንዳለ ይቀጥላሉ ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ። በሰው ልጅ ጉዳዮች ውስጥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ይኖራል በሚለው ሐሳብ በመዘበት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ዘባቾችን አመለካከት ይጋራሉ።
ሁሉም ነገር እንዳለ ነውን?
በ64 እዘአ ገደማ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የክርስቲያኑ ሐዋርያ የጴጥሮስ ሁለተኛ ደብደቤ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ” የሚል ማስጠንቀቂያ ይዟል።—2 ጴጥሮስ 3:3
ዘባቾች የሚዘብቱበትን ነገር ማላገጫ እንዲሆን ይፈልጋሉ። ዘባች ሰው ብዙውን ጊዜ ሌሎች ሰዎች የእሱን አመለካከት እንዲጋሩ ስለሚፈልግ ለዘበት እጁን የሚሰጥ ሰው በራስ ወዳድነት ወጥመድ ይያዛል። ምናልባትም ጴጥሮስ ማስጠንቀቂያ የሰጠባቸው አንዳንዶቹ ዘባቾች “እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ” ነበሩ። ሐዋርያው አንባቢዎቹን ለማስጠንቀቅ ጠንከር ያለ መግለጫ ተጠቅሟል። “ዘባቾች በመዘበት” ይመጣሉ ሲል አሳስቧል።
እነዚያ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ዘባቾች “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና” በማለት የክርስቶስ “የመምጣቱ የተስፋ ቃል” እውን መሆኑን ተጠራጥረዋል። (2 ጴጥሮስ 3:4) ሁሉ እንዳለ የሚኖር መስሏቸው ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ጥፋት እንደሚመጣ በ33 እዘአ ተንብዮ ነበር። “ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፣ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም” ሲል ተናግሯል። በዚህ ማስጠንቀቂያ የዘበቱ ሰዎች ምንኛ ተሳስተው ነበር! በ70 እዘአ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከብቦ በማጥፋት አብዛኞቹን ነዋሪዎቿን ለሕልፈተ ሕይወት ዳረገ። አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ለጥፋቱ ያልተዘጋጁት ለምን ነበር? ምክንያቱም አምላክ በልጁ በኢየሱስ አማካኝነት እንደጎበኛቸው አላስተዋሉም ነበር።—ሉቃስ 19:43, 44
ሐዋርያው ጴጥሮስ ወደፊት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ጣልቃ እንደሚገባ አመልክቷል። “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል” ሲል አስጠንቅቋል። (2 ጴጥሮስ 3:10) በዚያን ጊዜ አምላክ ከምድር ላይ አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎችን አስወግዶ ጻድቅ ተደርገው የተቆጠሩትን ያድናል። ይህ መጽሔት በተደጋጋሚ እንደገለጸው የክርስቶስ ኢየሱስ ‘መገኘት’ በ1914 ጀምሯል። ይሁን እንጂ የአምላክ ፍርድ አስፈጻሚ በመሆን ክፋትን የሚያስወግደው ገና ወደፊት ነው። በዚህ ምክንያት ሐዋርያው ከዘባቾች እንድንጠበቅ የሰጠው ምክር ከምንጊዜውም በበለጠ ዛሬ ይሠራል።
በሰዎች ጉዳዮች ውስጥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የሚጀምርበትን ጊዜ በመጠበቅ ረጅም ጊዜ አሳልፈህ ይሆናል። የዘባቾች ሰለባ ሳትሆን በትዕግሥት መጠባበቅህን እንድትቀጥል ምን ሊረዳህ ይችላል? እባክህ ቀጥሎ ያለውን አንብብ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ወራት ይመጣብሻልና፣ ጠላቶችሽም . . . ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ . . . በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም።” ይህ ማስጠንቀቂያ ሊዘበትበት የሚገባ አልነበረም። የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ደመሰሰ፤ ብዙ ሕይወትም ጠፋ።