ለልጆቻችሁ የምትመኙላቸው ምን ዓይነት ሕይወት ነው?
ልጆቻችሁን የምትመለከቷቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ውርስ አድርጋችሁ ነው? (መዝሙር 127:3) ወይስ እነርሱን ማሳደግ ወጪ ከመጨመር ሌላ ምንም ዓይነት ዋስትና የሌለው ሸክም ሆኖ ይታያችኋል? ልጆችን ማሳደግ ትርፍ የሚያስገኝ ሳይሆን ራሳቸውን ችለው መኖር እስኪጀምሩ ድረስ ገንዘብ የሚያስወጣ ሥራ ነው። በውርስ የተገኘን በርካታ ገንዘብ ሥራ ላይ ለማዋል ጥሩ እቅድ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ሁሉ ስኬታማ ወላጅ ለመሆንም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ይጠይቃል።
አሳቢ የሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው ሕይወት ጥሩ መሠረት መጣል ይፈልጋሉ። በዚህ ዓለም ውስጥ አስከፊና በጣም አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች ሊከሰቱ ቢችሉም ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ ብዙ ነገር ማድረግ ይችላሉ። ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን የቨርነርን እና የኢቫን ሁኔታ ተመልከት።a
ወላጆች ተገቢ እንክብካቤ ሲያደርጉ
ቨርነር ወላጆቹ ሁሉንም ነገር በቸልታ ከማለፍ ይልቅ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮችን ለማወቅ ይፈልጉ እንደነበረ ይናገራል። “ለሰጡኝ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ እንዲሁም እንደሚያስቡልኝና እየደገፉኝ እንዳሉ ሆኖ ተሰምቶኛል። ወላጅ እንደመሆናቸው መጠን ጥብቅ ነበሩ፤ ሆኖም እውነተኛ ወዳጆቼ ነበሩ።” ኢቫ በትምህርት ውጤቷ በመበሳጨቷ ምክንያት የመንፈስ ጭንቀትና እንቅልፍ የማጣት ችግር በገጠማት ጊዜ ወላጆቿ ፍራንሲስኮ እና ኢኔዝ ረዘም ያለ ጊዜ ወስደው በማነጋገር አእምሯዊና መንፈሳዊ ሚዛኗን መጠበቅ እንድትችል ረድተዋታል።
ፍራንሲስኮ እና ኢኔዝ ልጆቻቸውን ለመንከባከብና ለጎልማሳነት የሕይወት ዘመናቸው ከወዲሁ ለማዘጋጀት ጥረት ያደረጉት እንዴት ነው? ልጆቹ ገና ጨቅላ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ እነዚህ አፍቃሪ ወላጆች ዕለታዊ ጉዳዮቻቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ሁሉ ልጆቻቸው አብረዋቸው እንዲሆኑ ያደርጉ ነበር። ኢኔዝ እና ፍራንሲስኮ እኩዮቻቸው ከሆኑ ወዳጆቻቸው ጋር ብቻ ጊዜ ከማሳለፍ ይልቅ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ልጆቻቸውን ይዘው ይሄዱ ነበር። አፍቃሪ ወላጆች እንደመሆናቸው መጠን ለወንድና ለሴት ልጆቻቸው ተገቢውን መመሪያ ይሰጡ ነበር። ኢኔዝ አንዲህ ትላለች:- “ቤት እንዲያጸዱ፣ ቆጣቢ እንዲሆኑና የራሳቸውን ልብስ እንዲያጥቡ አስተምረናቸዋል። እንዲሁም እያንዳንዳቸው የራሳቸውን ሙያ እንዲመርጡና ኃላፊነቶቻቸውን ከመንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ጎን ለጎን ማስኬድ እንዲችሉ ረድተናቸዋል።”
ልጆቻችሁን በሚገባ ማወቅና ወላጃዊ መመሪያ መስጠት ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህን ልታደርጉ የምትችሉባቸውን ሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች እንመልከት:- (1) ልጆቻችሁ ተገቢ የሆነ የሥራ ዓይነት እንዲመርጡ እርዷቸው፤ (2) በትምህርት ቤትና በሥራ ቦታ የሚገጥሟቸውን የስሜት ውጥረቶች እንዲቋቋሙ አዘጋጁአቸው፤ (3) የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች እንዴት ሊያሟሉ እንደሚችሉ አሳዩአቸው።
ተስማሚ የሆነ ሥራ እንዲመርጡ እርዷቸው
አንድ ሰው የሚሠራው ሰብዓዊ ሥራ ገንዘብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ አብዛኛውን ጊዜውን የሚሻማበት በመሆኑ ልጆችን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ የእያንዳንዱን ልጅ ፍላጎትና ችሎታ ግምት ውስጥ ማስገባትንም የሚያጠቃልል ነው። ማንም ሕሊና ያለው ግለሰብ በሌሎች ላይ ሸክም መሆን ስለማይፈልግ ወላጆች ልጃቸው ራሱንም ሆነ ወደፊት የሚመሠርተውን ቤተሰብ ለመደገፍ እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል። ወንድ ልጃችሁ ወይም ሴት ልጃችሁ አጥጋቢ የሆነ ገቢ የሚያስገኝ ሙያ መማር ይኖርባቸው ይሆን? ልጃችሁ በትጋት የመሥራትን፣ ለመማር ፈቃደኛ የመሆንና ከሰዎች ጋር ተግባብቶ የመኖር ችሎታን የመሰሉ ባሕርያትን እንዲያዳብር ለመርዳት የማያቋርጥ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ ለልጃችሁ ከልብ የምታስቡ ወላጆች መሆናችሁን ያሳያል።
ኒኮልን እንደ ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “ወላጆቼ የጽዳት ሥራ ወደሚሠሩበት ቦታ ይዘውኝ ይሄዱና አብሬአቸው እንድሠራ ያደርጉ ነበር። ከማገኘው ገንዘብ ጥቂት ያህሉን ለቤት ወጪ አስተዋጽኦ እንዳደርግና የተረፈኝንም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እንድገዛበት ወይም እንዳጠራቅም ሐሳብ አቀረቡልኝ። ይህም ኃላፊነት የመሸከም ዝንባሌ እንዲኖረኝ ስለረዳኝ በቀሪው የሕይወት ዘመኔ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶልኛል።”
የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ምን ዓይነት ሥራ መምረጥ እንዳለበት ለይቶ አይናገርም። ሆኖም ጥሩ መመሪያ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ በማለትም ተናግሮ ነበር:- “ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፣ በሰው ነገር እየገቡ፣ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን።”—2 ተሰሎንቄ 3:10-12
ሆኖም ሕይወት ማለት ሥራ መያዝና ገንዘብ ማግኘት ማለት ብቻ አይደለም። ሁሉን ማግበስበስ የሚፈልጉ ሰዎች የኋላ ኋላ ባገኙት ነገር ላይደሰቱና ‘ነፋስን እየተከተሉ’ እንዳሉ ሊገነዘቡ ይችላሉ። (መክብብ 1:14) ወላጆች ልጆቻቸው እውቅናን እንዲያተርፉ ወይም ሃብት እንዲያካብቱ ከመገፋፋት ይልቅ ሐዋርያው ዮሐንስ በመንፈስ አነሳሽነት የጻፋቸው የሚከተሉት ቃላት ያዘሉትን ጥበብ እንዲገነዘቡ ቢረዷቸው የተሻለ ነው:- “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:15-17
ስሜታዊ ፍላጎቶቻቸውን ልታሟሉላቸው የምትችሉት እንዴት ነው?
ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን እንደ አንድ የአትሌቶች አሠልጣኝ ለመሆን ለምን አትሞክሩም? የአትሌቶች አሠልጣኝ ትኩረት የሚሰጠው አትሌቶቹ በፍጥነት ለመሮጥ ወይም ይበልጥ ለመዝለል የሚያስችላቸውን ብቃት እንዲያዳብሩ ብቻ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ እንዲኖራቸው ለማድረግ ማንኛውንም አፍራሽ ዝንባሌ እንዲቋቋሙ መርዳቱም የማይቀር ነው። እናንተስ ልጆቻችሁን ማበረታታት፣ ማነጽና ማነሳሳት የምትችሉት እንዴት ነው?
ሮዛሪዮ የተባለውን የ13 ዓመት ወጣት እንውሰድ። በአካላዊ ለውጥ ምክንያት ካደረበት ጭንቀት በተጨማሪ በወላጆቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባትና በቂ ትኩረት ማጣቱ የስሜት ውጥረት አስከትሎበት ነበር። እርሱን ለመሰሉ ወጣቶች ምን ሊደረግ ይችላል? ልጆቻችሁ ምንም ዓይነት ጭንቀትና መጥፎ ተጽዕኖዎች እንዳይደርስባቸው ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻልም የወላጅነት ድርሻችሁን ከመወጣት ወደ ኋላ ማለት የለባችሁም። ከመጠን በላይ ጥብቅ ሳትሆኑ አንዱ ልጅ ከሌላው የተለየ እንደሆነ ምንጊዜም በማስታወስ ለልጆቻችሁ በአሳቢነት ላይ የተመሠረተ ማሠልጠኛ ስጡ። ደግነትና ፍቅር በማሳየት ልጁ ከስጋት ነፃ የሆነ ስሜት እንዲያድርበት ማድረግ ትችላላችሁ። ይህም በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲያዳብርና ለራሱ አክብሮት እንዲኖረው ይረዳዋል።
የእናንተ ወላጆች ስሜታዊ ፍላጎታችሁን በማሟላት ረገድ ተሳካላቸውም አልተሳካላቸው ልጆቻችሁን በመርዳት ረገድ የተሳካላችሁ ወላጆች መሆን እንድትችሉ ሦስት ነገሮች እገዛ ሊያበረክቱላችሁ ይችላሉ:- (1) ራሳችሁ በሚገጥሟችሁ ችግሮች ከመጠን በላይ በመዋጥ ልጆቻችሁ ያሉባቸውን ጥቃቅን የሚመስሉ ችግሮች ችላ ከማለት ተጠበቁ፤ (2) ከልጆቻችሁ ጋር በየዕለቱ አስደሳችና ትርጉም ያለው ውይይት ለማድረግ ጥረት አድርጉ፤ (3) ችግሮችን መፍታትና ከሰዎች ጋር ተግባብቶ መኖርን በተመለከተ አዎንታዊ ዝንባሌ እንዲያዳብሩ አድርጉ።
ቢርጊት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የነበረችበትን ጊዜ መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ትላለች:- “ሰዎችን እኔ በምፈልገው መንገድ መለወጥ እንደማልችል መማር ነበረብኝ። አንድ የማልወደው ባሕርይ በሌሎች ሰዎች ላይ ብመለከት ማድረግ የምችለው ነገር ቢኖር እነርሱን ላለመምሰል መጣር ብቻ እንደሆነ እናቴ ጥሩ አድርጋ ገልጻልኛለች። በተጨማሪም የራሴን አካሄድ ላቀና የምችልበት ከሁሉ የተሻለው ወቅት የወጣትነት ጊዜዬ እንደሆነም ነግራኛለች።”
ሆኖም ልጆቻችሁ የሚያስፈልጋቸው ሥራና የተረጋጋ ስሜት ብቻ አይደለም። ‘ወላጅነት ከአምላክ የተሰጠ ኃላፊነት እንደሆነ ይሰማኛል?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። እንዲህ የሚሰማችሁ ከሆነ ልጆቻችሁ የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ለማሟላት ትነሳሳላችሁ።
የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ለማሟላት የሚያስችሉ መንገዶች
ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ “በመንፈሳዊ የጐደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 5:3 NW) አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ነገሮችን ማሟላት ምን ማድረግን ይጨምራል? ወላጆች በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት በማሳየት ምሳሌ ሲሆኑ ልጆች ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ያለ እምነትም [አምላክን] ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና።” (ዕብራውያን 11:6) ይሁን እንጂ እምነት እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ከተፈለገ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ ነው። (ሮሜ 12:12) እናንተም በመንፈሳዊ የሚጎድላችሁ ነገር እንዳለ አምናችሁ የምትቀበሉ ከሆነ የእውቁ የእስራኤል መስፍን የሳምሶን አባት እንዳደረገው መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት ትሻላችሁ። (መሳፍንት 13:8) እርዳታ ለማግኘት ከመጸለያችሁም ባሻገር በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ወደ ተጻፈው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር ትላላችሁ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17b
ጥሩ መመሪያ፣ ስሜታዊ ድጋፍና መንፈሳዊ እርዳታ መስጠት ጠንክሮ መሥራት የሚጠይቅ ቢሆንም ወላጅ መሆን የኋላ ኋላ መልሶ የሚክስ ነው። ሁለት ልጆች ያሉት በብራዚል የሚኖር አንድ አባት እንዲህ ብሏል:- “ልጆች ባልወለድኩ ኖሮ የሚለው ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሮዬ አይመጣም። በጋራ ልንደሰትባቸው የምንችልባቸው በርካታ ነገሮች አሉ።” እናትየው ልጆቹ ጥሩ የሆኑበትን ምክንያት ስታብራራ እንዲህ በማለት አክላ ተናግራለች:- “ከልጆቻችን ምንጊዜም አንለይም። ነገሮች ሁሉ የሚማርኩና የሚያስደስቱ እንዲሆኑ እንጥራለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ አዘውትረን ስለ ልጆቹ እንጸልያለን።”
ፕሪሲላ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ሁሉ ወላጆቿ ያሳዩአት የነበረውን ፍቅርና ትዕግሥት መለስ ብላ ታስታውሳለች። “እውነተኛ ወዳጆቼ ከመሆናቸውም በላይ በሁሉ ነገር ይረዱኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። “ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ልክ ‘ከይሖዋ እንደተገኘሁ ስጦታ’ አድርገው ይንከባከቡኝ አንደነበር ይሰማኝ ነበር።” (መዝሙር 127:3) ሌሎች በርካታ ወላጆች እንደሚያደርጉት እናንተም መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ከልጆቻችሁ ጋር አብራችሁ ልታነቡ የምትችሉበትን ጊዜ ለምን አትመድቡም? ጥሩ መንፈስ በሰፈነበት ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን መመርመራችሁ ልጆቻችሁ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እውነተኛ ተስፋ እንዲኖራቸው ሊረዳቸው ይችላል።
ሁሉም ልጆች ደህንነት የሚያገኙበት ጊዜ
የወደፊቱ ጊዜ በአሁኑ ጊዜ ላሉ ብዙ ልጆች ጨለማ ሆኖ ቢታይም እንኳ ምድር መላው የሰው ዘር ደህንነት የሚያገኝባት መኖሪያ እንደምትሆን የአምላክ ቃል ዋስትና ይሰጣል። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ደህንነት የማይሰጉበትን ጊዜ እስቲ በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ! (2 ጴጥሮስ 3:13) የሚከተለው ትንቢት ታላቅ ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናችሁ ለማየት ሞክሩ:- “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል።” (ኢሳይያስ 11:6) በእነዚህ ቃላት የተገለጸው መንፈሳዊ ደህንነት በአሁኑ ጊዜ እንኳን ሳይቀር ይሖዋን በሚያገለግሉ ሰዎች መካከል በምሳሌያዊ መንገድ ፍጻሜውን አግኝቷል። በእነርሱ መካከል ሆነህ የአምላክን ፍቅራዊ እንክብካቤ ልትቋደስ ትችላለህ። አምላክን የምታፈቅር ከሆነ እርሱም የወላጅነት ስሜቶችህን እንደሚረዳልህና የሚያጋጥሙህን አስጨናቂ ሁኔታዎችና ፈተናዎች እንድትቋቋም እንደሚረዳህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። ቃሉን አጥና፤ ተስፋህንም በመንግሥቱ ላይ አድርግ።
ጥሩ ምሳሌ በመተው ልጆችህ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው። ይሖዋ አምላክን መሸሸጊያህ ካደረግክ የአንተም ሆነ የልጆችህ የወደፊት ሕይወት ከጠበቅከው በላይ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ። “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፣ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል” ብሎ የዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት እምነት ሊኖርህ ይችላል።—መዝሙር 37:4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ስሞች ቀይረናቸዋል።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን ከ5 እስከ 7 ያሉትን ምዕራፎች ተመልከት።