“ማዕበል በሚያናውጠው ባሕር ላይ መጓዝ”
ይህ ዓይነቱን ጉዞ አጉል ሰዓት ላይ የተደረገ፣ የቂልነትና በጣም አደገኛ አድርገህ አትመለከተውምን? ይሁን እንጂ አንዳንዶች ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ራሳቸውን እንዲህ በመሰለ ሁኔታ ውስጥ ያስገባሉ። እንዴት? የ17ኛው መቶ ዘመን እንግሊዛዊ ደራሲ ቶማስ ፉለር እንዲህ ብለዋል:- “በምትናደድበት ጊዜ ምንም ዓይነት እርምጃ አትውሰድ። እንዲህ ማድረግ ማዕበል በሚያናውጠው ባሕር ላይ ከመጓዝ ተለይቶ አይታይም።”
በጦፈ የንዴት ስሜት ውስጥ እያሉ አንድ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አሳዛኝ ውጤቶች ሊያስከትል ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ አንድ ክንውን ይህ ነገር ትክክል መሆኑን መስክሯል። የጥንቱ አበው የያዕቆብ ልጆች የሆኑት ስምኦንና ሌዊ እህታቸው ዲና በመደፈርዋ ምክንያት በበቀል ስሜት ተነሳስተው በአጸፋው የኃይል እርምጃ ወስደዋል። ይህ ድርጊት የጅምላ ጭፍጨፋና ዝርፊያ አስከትሏል። ያዕቆብ ክፉ ድርጊታቸውን በማውገዝ “በዚች አገር በሚኖሩ . . . ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ” ማለቱ ምንም አያስደንቅም።—ዘፍጥረት 34:25-30
የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አካሄድ እንድንከተል ይመክረናል። “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና” ይላል። (መዝሙር 37:8) ይህን ምክር በመከተል ከባድ ኃጢአቶችን ከመሥራት ልንጠበቅ እንችላለን።—መክብብ 10:4፤ በተጨማሪም ምሳሌ 22:24, 25ን ተመልከት።