ልጆች ማሳደግ የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ መወጣት
ዛሬ ልጆችን በተለይ ደግሞ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙትን ልጆች ማሳደግ ለወላጆች ከባድ ፈተና ሆኗል። በካናዳ ሞንትሪያል የሚታተመው ዘ ጋዜት አልኮል መጠጣትና አደገኛ ዕፆችን መውሰድ “በጉርምስና ዕድሜ ላይ ባሉት ዘንድ የተለመደ” ነገር ሆኗል ሲል ዘግቧል። ወላጆች “በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙ ልጆቻቸው ላይ የሚያዩትን የባሕርይ ለውጥ በንቃት የመከታተል ኃላፊነት” እንዳለባቸው ጋዜጣው አስምሮበታል።
ወላጆች በጎረምሶች ላይ የሚከሰቱ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ሊጠቁሙ የሚችሉትን የትኞቹ ነገሮች መከታተል አለባቸው? የአሜሪካ የልጆችና የወጣቶች የሥነ አእምሮ አካዳሚ ከደረሰባቸው አንዳንድ አካላዊ፣ ስሜታዊና ማኅበራዊ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች መካከል ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ድካም፣ የባሕርይና የስሜት መለዋወጥ፣ ከመኝታ ክፍል ሳይወጡ በጣም ረጅም ጊዜ ማሳለፍ፣ የሌሎችን ሐሳብ መቃወም እና ሕገ ወጥ በሆኑ ድርጊቶች መሳተፍ ይገኙበታል።
ወላጆች ልጆቻቸውን በእንዲህ ዓይነት ጎጂ በሆኑ ነገሮች እንዳይጠመዱና ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሚመጣው አሉታዊ ተጽእኖ መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው? በማክጊል ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶክተር ጄፍሪ ኤል ደረቭንስኪ ልጁ እድገት በሚያደርግባቸው ወሳኝ በሆኑት ዓመታት ግልጽ የሆነ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግና በመካከላቸው አክብሮት እንዲኖር ማድረጋቸው በኋላ የሚከሰቱ ችግሮችን ሊቀንስ እንደሚችል ያምናሉ። ምንም እንኳ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ሰፋ ያለ ነፃነት የማግኘት ምኞት ቢታይም በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች “የወላጆቻቸው አመራር፣ ድጋፍ፣ ቋሚ ሥርዓትና ፍቅር” እንደሚያስፈልጋቸው ዘ ጋዜት አክሎ ተናግሯል። እነዚህ አስተያየቶች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሐሳብ ያስተጋባሉ:- “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።” (ምሳሌ 22:6) አምላክ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው አርአያ፣ ጓደኛ፣ ምሥጢረኛና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ይመክራቸዋል።—ዘዳግም 6:6, 7