አቶስ “ቅዱስ ተራራ” ነውን?
በሰሜናዊ ግሪክ የሚገኘው ወጣ ገባ የሆነው ባሕረ ገቡ የአቶስ ተራራ ከ220 በሚበልጡት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ “በኦርቶዶክስ የክርስትናው ዓለም እጅግ ቅዱስ ተራራ” ተደርጎ ይታያል። አብዛኞቹ፣ “ቅዱስ ተራራ” ወደሆነው ወደ አቶስ ጉዞ ማድረግ በጣም የሚጓጉለት ነገር ነው። ይህ “ቅዱስ ተራራ” ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት የላቀ ቦታ ሊይዝ የቻለውስ እንዴት ነው? እንዲሁም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች መንፈሳዊ አመራርና እውነተኛውን አምልኮ ለማግኘት መሄድ ያለባቸው ወደዚህ “ተራራ” ነውን?
እርግጥ “ቅዱስ ተራራ” የሚለው መግለጫ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። ይህ አባባል ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ ከሚቀርበው ቅዱስ፣ ንጹሕና ከፍ ያለ አምልኮ ጋር የተያያዘ ነው። ንጉሥ ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት በጥንቷ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የጽዮን ተራራ ሲያመጣው ቦታው ‘የተቀደሰ ተራራ’ ሊሆን ችሎ ነበር። (መዝሙር 15:1፤ 43:3፤ 2 ሳሙኤል 6:12, 17) የሰሎሞን ቤተ መቅደስ በሞሪያ ተራራ ላይ ከተገነባ በኋላ “ጽዮን” የቤተ መቅደሱን ቦታ አካትቶ ይዞ ነበር። በመሆኑም ጽዮን የአምላክ “ቅዱስ ተራራ” እንደሆነ ቀጥሏል። (መዝሙር 2:6፤ ኢዩኤል 3:17) የአምላክ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ይገኝ ስለነበር አልፎ አልፎ ይህችም ከተማ የአምላክ ‘ቅዱስ ተራራ’ ተብላ ተጠርታለች።—ኢሳይያስ 66:20፤ ዳንኤል 9:16, 20
ዛሬስ ሁኔታው እንዴት ነው? ሰዎች አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ “ቅዱስ” ወደሚባለው ወደ አቶስ ተራራ ወይም ወደ ሌላ ተራራማ ቦታ ሊጎርፉ ይገባልን?
ገዳም ያለበት “ቅዱስ ተራራ”
የአቶስ ተራራ የሚገኘው በካልሲደሲ ባሕረ ገብ መሬት ምሥራቃዊ ጫፍ ላይ ልክ ከዘመናዊቷ የተሰሎናይካ ከተማ በስተ ምሥራቅ ወደ ኤጂያን ባሕር በሚሰርገው ሾጣጣ መሬት ጫፍ ላይ ነው። አናቱ በእብነ በረድ የተሸፈነ ከኤጂያን ባሕር ተነስቶ 2,032 ሜትር ቀጥ ብሎ ሽቅብ የወጣ አስደናቂ ተራራ ነው።
አቶስ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ቅዱስ ቦታ እንደሆነ ሲታሰብ ቆይቷል። በግሪካውያን አፈ ታሪክ መሠረት የኦሊምፐስ ተራራ የአማልክት መኖሪያ ከመሆኑ በፊት አቶስ መኖሪያቸው እንደነበር ይነገራል። ከታላቁ ቆስጠንጢኖስ ንግሥና (አራተኛው መቶ ዘመን እዘአ) ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አቶስ በክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ቅዱስ ቦታ ሆኖ መታየት ጀመረ። በአንድ አፈ ታሪክ መሠረት “ድንግል” ማሪያም ከወንጌላዊው ዮሐንስ ጋር ሆና አልዓዛርን ለመጠየቅ ወደ ቆጵሮስ ስትሄድ ድንገት ባጋጠማት ኃይለኛ ማዕበል ሳቢያ አቶስ ላይ እንዳረፈች ይነገራል። ማርያም በተራራው ውበት በመደነቅ ኢየሱስ እንዲሰጣት ጠየቀችው። ከዚህ የተነሳ አቶስ “የቅድስት ድንግል መናፈሻ” ተብሎም ይጠራ ጀመረ። በባይዛንታይን ዘመን አጋማሽ መላው ድንጋያማ ክምር ቅዱስ ተራራ በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር። በ1046 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ዘጠነኛ ሞናማከስ ባወጣው አዋጅ ይህ ስያሜ በኦፊሴል ተቀባይነት አግኝቶ ጸደቀ።
አቶስ ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ ወጣ ገባ በመሆኑና ገለል ብሎ የሚገኝ ተራራ በመሆኑ የብሕትውና ሕይወት ለመምራት ተስማሚ ቦታ ሆኖ ተገኝቷል። ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ ግሪኮችን፣ ሰርቦችን፣ ሮማውያንን፣ ቡልጋርያውያንን፣ ሩስያውያንን እና ሌሎችን ጨምሮ በመላው የኦርቶዶክሱ ዓለም የሚገኙ ሃይማኖታዊ ሰዎችን የማረከ ሲሆን እነርሱም አብያተ ክርስቲያናትና ኮሚኒቲ ያሏቸውን በርካታ ገዳማት ገንብተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 20 የሚያክሉት እስካሁን ድረስ አሉ።
የአቶስ ተራራ በዛሬው ጊዜ
ዛሬ አቶስ በ1926 በጸደቀ ቻርተር የሚተዳደር ራስ ገዝ ክልል ሆኗል። በዚያ የሚኖሩ የመነኮሳቱ ቁጥር ለበርካታ ዓመታት ሲያሽቆለቁል ከቆየ በኋላ አሁን እንደገና ጨምሮ ከ2,000 አልፏል።
እያንዳንዱ ገዳም እርስ በርሱ የሚደጋገፍ የራሱ እርሻ፣ ጸሎት ቤትና መኖሪያዎች አሉት። የመጨረሻው የባሕታውያኑ ቤተ መቅደስ የሚገኘው በካሮውሊያ የሰፈራ ቦታ ሲሆን የአቶስ ተራራ ጫፍ ላይ ባሉት ተዳፋት በሆኑ ጠርዞች ላይ ጉብ ብሎ ይታያል። በዚያ ወዳሉት ሰብሰብ ብለው የሚገኙ ጎጆዎች መድረስ የሚቻለው ውስብስብ የሆኑ የእግር መንገዶችን፣ የድንጋይ ደረጃዎችንና ሰንሰለቶችን በመጠቀም ብቻ ነው። በአቶስ የሚኖሩ መነኮሳት የባይዛንታይንን የሰዓት አቆጣጠር (ቀኑ የሚጀምረው ፀሐይ ሲጠልቅ ነው) እና የጁሊያንን ቀን መቁጠሪያ (ከግሪጎሪያን አቆጣጠር 13 ቀናት ወደኋላ ይቀራል) በመጠቀም አሁንም ዕለታዊ ሕይወታቸውን የሚመሩት ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት በመከተል ነው።
ምንም እንኳ ይህ ሃይማኖታዊ ቦታ “ቅድስናውን” ያገኘው በአንዲት ሴት ምክንያት እንደሆነ ቢነገርም ለ1,000 ዓመታት ያህል መነኮሳቱና ባሕታውያኑ መላው ባሕረ ገብ መሬት ሰውም ሆነ የእንስሳ ማንኛውም አንስታይ ጾታ እንዲሁም ጃንደረባ ወይም ጢም የሌለው ሰው ወደዚያ መድረስ እንደሌለበት በይፋ ደንግገው ቆይተዋል። በቅርቡ ጢም የሌላቸውን ሰዎችና አንዳንድ አንስታይ ጾታ ያላቸውን እንስሳትን በተመለከተ ያለው ደንብ ላላ ብሏል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሴቶች ከአቶስ ተራራ የባሕር ዳርቻ እስከ 500 ሜትር ባለው ክልል ውስጥ እንዳይገቡ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ለሁሉም የሚሆን “ቅዱስ ተራራ”
አቶስ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ክርስቲያኖች አምልኮ ለመፈጸም ሊሄዱበት የሚገባ “ቅዱስ ተራራ” ነውን? ኢየሱስ፣ አምላክ መመለክ ያለበት በገሪዛን ተራራ ላይ እንደሆነ ታምን ከነበረች ሴት ጋር ሲነጋገር የትኛውም ግዑዝ ተራራ አምላክን ለማምለክ የሚያገለግል ቦታ ተደርጎ ሊቆጠር እንደማይችል ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስ “በዚህ ተራራ [በገሪዛን] ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” ብሏል። ለምን? “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል።”—ዮሐንስ 4:21, 24
ነቢዩ ኢሳይያስ እኛ ያለንበትን ጊዜ በማስመልከት ምሳሌያዊው “የእግዚአብሔር ቤት ተራራ” ‘በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ እንደሚቆም’ እና ‘ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ እንደሚል’ እንዲሁም ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦች በምሳሌያዊ አነጋገር ወደዚያ እንደሚጎርፉ በትንቢት ተናግሯል።—ኢሳይያስ 2:2, 3
ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው ዝምድና መመሥረት የሚፈልጉ ወንዶች እና ሴቶች ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” እንዲያመልኩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ‘ይሖዋ ተራራ’ የሚያደርሰውን መንገድ አግኝተዋል። እንደ ሌሎች ሁሉ እነርሱም አቶስን በተመለከተ እንዲህ በማለት በተናገረችው አንዲት ግሪካዊ ሕግ ዐዋቂ ሐሳብ ይስማማሉ:- “መንፈሳዊነት የሚገኘው በተከለሉ ቦታዎች ወይም በገዳማት ብቻ መሆኑን እጠራጠራለሁ።”—ከሥራ 17:24 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለረጅም ጊዜ ተሰውሮ የቆየ ውድ ሀብት
ባለፉት መቶ ዘመናት በአቶስ የሚኖሩ መነኮሳት አንዳንዶቹ በአራተኛው መቶ ዓመት የነበሩ ናቸው የሚባሉትን ጨምሮ በግምት 15,000 የሚያህሉ የብራና ጽሑፎችን ያካተተ ውድ ሀብት አከማችተዋል። ይህም በዓለም ካሉት እጅግ ውድ ስብስቦች መካከል አንዱ እንዲሆን አስችሎታል። በዚያ በጣም ጥንታዊ ከሆኑ ሥዕሎች፣ ምስሎች፣ ቅርጻ ቅርጾችና የብረት ሥራዎች በተጨማሪ የወንጌሎችና የመዝሙራት ጥቅሎች፣ የተሟሉ ጥራዞችና ነጠላ ገጾች ይገኛሉ። ምንም እንኳ ገና በዓይነት በዓይነታቸው በሥርዓት ተለይተው መቀመጥ ያለባቸው ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች ብዙ ቢሆኑም በዓለም ላይ ካሉት የግሪክኛ የእጅ ግልባጭ ቅጂዎች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆነው በአቶስ ተራራ እንደሚገኝ ይገመታል። በ1997 መነኮሳቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ካሏቸው ውድ ቅርሶች መካከል አንዳንዶቹ በተሰሎናይካ ለሕዝብ እንዲታዩ ፈቅደዋል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Telis/Greek National Tourist Organization