የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
ሲና—የሙሴና የምሕረት ተራራ
ስለ ሲና ተራራ ስታስብ ምናልባት ሙሴ ትዝ ይልህ ይሆናል። ለምን? ምክንያቱም ሙሴ የአምላክን ሕግ የተቀበለው በሲና ሰርጥ ላይ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ስለነበረ ነው። ግን የትኛው ተራራ ነው? ምናልባት ከላይ የሚታየው ሳይሆን አይቀርም።a
በዚህ ሰርጥ ደቡባዊ ክፍል፣ በሁለቱ የቀይ ባሕር ሰላጤዎች መካከል ሁለት ጉብታዎች አሉ። አጠቃላይ አቀማመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሙሴ ጋር በማያያዝ ከሚሰጠው ትረካ ጋር ይስማማል። አንደኛው ጉብታ ጀበል ሙሴ በመባል የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙ “የሙሴ ተራራ“ ማለት ነው።
የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትረካዎች ይህን አሰያየም ማለትም ጉብታው “የሙሴ ተራራ“ መባሉን ይደግፉታል። ሙሴ በሚነደው ቁጥቋጦ ውስጥ አንድ መልአክ ሲገለጥለት የዮቶርን በጎች ይጠበቅ እንደነበረ ታስታውሳለህን? ይህ ሥፍራ የት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ’በእግዚአብሔር ተራራ ኮሬብ’ላይ እንደነበረ ይናገራል። ኮሬብ የሲና ተራራ ተብሎም ተጠርቷል። (ዘጸአት 3:1-10፤ 1 ነገሥት 19:8) ሙሴ የአምላክን ሕዝብ እየመራ ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ያመጣቸው ወደዚህ ቦታ ነበር። ዘጸአት “እሥራኤል [በሲና] ተራራ ፊት ሰፈረ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ [ተናገረው አዓት]“ ይላል።
ይህም ሙሴ በሲና ተራራ ላይ የወጣበት የመጀመሪያው ጊዜ ሲሆን እርሱም ለአጭር ርቀት ዳገትን ከመውጣት የሚበልጥ ነገር አድርጓል። “እግዚአብሔርም [ይሖዋ አዓት] በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም [ይሖዋ አዓት]ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው” የሚል እናነባለን።—ዘጸአት 19:20
በሺዎች የሚቆጠሩ ዘመናዊ ጎብኚዎች ወደ ተራራው ራስ ለመድረስ የእግር መንገድ ምልክቶችን ተከትለው ለመውጣት ሌሊቱን በብዙ ድካም ሲሄዱ አድረው ፀሐይ ስትወጣ ከጫፉ ላይ ይደርሱና በእኩለ ቀን ላይ ወደ ታች መውረድ ይጀምራሉ። በሙሴ ረገድ ግን እንዲህ አልነበረም። አምላክ “ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፣ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ“ በማለት ነግሮት ነበር። በዚያም ወቅት “ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።“—ዘጸአት 24:12-18
ስለዚህ የሙሴ ስም ከዚህ ተራራ ጋር የተቆራኘበትን ምክንያት ለመረዳት አያዳግትም። ይሁን እንጂ “ምሕረት“ ከዚህ ተራራ ጋር የተያያዘው ለምንድን ነው? ሙሴ ሕጉን ለመቀበል በተራራው ላይ በነበረበት ጊዜ በፎቶግራፉ ላይ በሚታየው ሜዳ ላይ (ኤርረሃ በሚባለው ሜዳ ላይ ሳይሆን አይቀርም) የሠፈሩት እሥራኤላውያን የሞኝነት ድርጊት ፈጽመው ነበር። የሙሴን ወንድም አሮንን አምላክ ሥራልን ብለው አስገድደውት ነበር። አሮንም “በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ“ አላቸው። እንዲህ በማድረግም የሚያመልኩት የወርቅ ጥጃ ሠሩ። ይህም እውነተኛውን አምላክ ስላስቆጣው በሺዎች የሚቆጠሩ ሞት ደረሰባቸው። (ዘጸአት 32:1-35) አሮን ግን ምሕረት ተሰጥቶት ስለነበረ ከሞት ተርፏል። ለምን?
አምላክ በዘጸአት 32:10 ላይ የተናገራቸው ቃላት እሥራኤላውያን መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሳሳው አሮን እንደሆነ አድርጎ እንዳልተመለከተው ያሳያሉ። [ሙሴ] ከአምላክ ጎን በመቆም ለመዋጋት ራሱን የሚያቀርብ ማን እንደሆነ በጠየቀ ጊዜ “የሌዊ ልጆች ሁሉ“ በአምላክ ጎን ለመቆም መረጡ፤ ከመካከላቸው አሮንም እንደነበረ ጥርጥር የለውም። (ዘጸአት 32:26) ስለዚህ አሮንም መጠነኛ ጥፋት ቢኖርበትም በሲና ተራራ ግርጌ የአምላክን ምሕረት አግኝቷል።
በኋላ ሙሴ ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅና ክብሩን ለማየት እንደሚፈልግ ተናገረ። (ዘጸአት 33:13, 18) የአምላክን ፊት ማየት የማይቻል በመሆኑ ይሖዋ “የሚምረውን [ሰው] እንደሚምረው“ አጥብቆ በመግለጽ ከክብሩ ጥቂቱን ለሙሴ አሳይቶታል። (ዘጸአት 33:17 እስከ 34:7) አምላክ በሲና በቃል ኪዳን ከተሣሠራቸው እሥራኤላውያን ጋር ከነበረው አሠራር ጋር በተያያዘ “ምሕረት“ የሚለውን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ አዘውትሮ ስለሚጠቀምበት አምላክ ይህን ባሕርይ አጥብቆ መግለጹ ተገቢ ነበር።—መዝሙር 103:7-13, 18
በአሁኑ ጊዜ የሲና ተራራን የሚጎበኙ ሰዎች ሙሴ በተራራው ራስ ላይ የተማረውን እውነተኛ አምልኮ ለማስታወስ የማይረዳ አንድ ገዳም በተራራው ግርጌ ያገኛሉ። ከዚህ ይልቅ የገዳሙ ሃይማኖት በምስሎች ላይ የሚያተኩር ነው። እዚህ ላይ በሥዕል የሚታየው “የገነት መሰላል“ የሚባለው ነው። ይህ ሐሳብ የተመሠረተው ጆን ክሊማኩስ የተባሉ ባይዛንቲናዊ መነኩሴ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ነው። እኚህ መነኩሴ በገዳሙ ጠባብ ክፍል ውስጥ 40 ዓመት ካሳለፉ በኋላ የገዳሙ አለቃ ሆኑና ወደ ሰማይ ስለሚወስደው ምሳሌያዊ መሰላል ጻፉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ቀሳውስት በአጋንንት እየተጎተቱ ወደ ሲኦል ዘላለማዊ ሥቃይ ሲገቡ የሚያሳይ ሥዕልም እንደተሳለ ተመልከቱ። በጣም ግልጽ የሆነ ሥዕል ቢሆንም ቅዱስ ጽሑፋዊ አይደለም።—መክብብ 9:5, 10፤ ኤርምያስ 7:31
ከዚህ የሐሰት ትምህርት በተቃራኒው ያለው እውነት ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ “ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት የሆነ አምላክ“ መሆኑ ነው። (ዘጸአት 34:6) ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ከዚህ አምላክ ጋር በጣም ተቀራርቦ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፎቶግራፉን በትልቁ ለማየት የ1993ን የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ ተመልከት።
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.