የገና በዓል በምሥራቃውያን ዘንድ
•ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት አንድ ታዋቂ የኮሪያ ምሁር ቻይና፣ ፔኪንግን ጎብኚተው ነበር። በአንድ ካቴድራል ኮርኒስ ላይ የተሳሉ ሥዕሎችን ትኩር ብለው እየተመለከቱ ሳለ ማርያም ሕፃኑን ኢየሱስን ታቅፋ በሚያሳይ አንድ ሥዕል ላይ ዓይናቸው አረፈ። ይህን አስገራሚ ሥዕል በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል:-
“አንዲት ሴት አንድ ከሲታ የአምስት ወይም የስድስት ዓመት ልጅ ጭኗ ላይ ታቅፋለች። የወላጅ አንጀቷ ልጁዋን ቀና ብላ ለማየት እምቢ ያላት ይመስል አንገቷን አቀርቅራለች። ከበስተጀርባቸው በርቀት በርካታ የሙታን መናፍስትና በክንፍ የሚበሩ ሕፃናት ይታያሉ። ትኩር ብዬ ስመለከታቸው ድንገት እላዬ ላይ የሚወድቁብኝ መሰለኝ። ደንግጬ ልይዛቸው እጄን ዘረጋሁ።”
ይህ ሁኔታ የተከሰተው የጨለማ ዘመን እየተባለ የሚጠራው መካከለኛው ዘመን ካለፈና በአውሮፓ የተሃድሶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው። ሆኖም ልክ እንደ ሥዕሉ ሁሉ የክርስትና እምነትም ለአብዛኞቹ ምሥራቃውያን እንግዳ ነበር። ታዲያ ይህ ሁኔታ እንዴት ተለወጠ? የገና ወቅት በመጣ ቁጥር ሕፃኑን ኢየሱስን የሚያሳዩ ምስሎች በየቦታው ይታያሉ። አሁን ምሥራቃውያን ከእነዚህ ምስሎች ጋር የተላመዱ ሲሆን በገና ወቅት ጎዳናዎቻቸውን ከአውሮፓ ጎዳናዎች ጋር በሚመሳሰል መንገድ ያሸበርቋቸዋል።
ኅዳር 25, 1998 ምሽት፣ የገና በዓል ከመከበሩ ከአንድ ወር በፊት ማለት ነው ፓሪስ በሚገኘው በታወቀው ሾንዜሊዜ አውራ ጎዳና ላይ በተርታ በተተከሉ 300 ዛፎች ላይ ከ100,000 የሚበልጡ በብርሃን ያሸበረቁ አምፑሎች ተሰቅለው ነበር። በተመሳሳይም አንድ የታወቀ ሱፐርማርኬት በኮሪያ ሴዉል መሀል ከተማ በሚገኝ አውራ ጎዳና ላይ አንድ ግዙፍ የገና ዛፍ በማቆም በምሽት ከተማዋን አድምቋት ነበር። ወዲያው የሴዉል አውራ ጎዳናዎች ሁሉ በገና መብራቶች አሸበረቁ።
ቴሌቪዥን፣ ራዲዮና ጋዜጦች በየዕለቱ ከገና ጋር የተያያዙ ፕሮግራሞች ያቀርባሉ። በገና መንፈስ ስሜቱ የተቀሰቀሰው መላው የአገሪቱ ሕዝብ የዓመቱን መጨረሻ በፈንጠዝያ ለማሳለፍ መሯሯጥ ይጀምራል። ጎብኚዎችን የሚያስገርም ቁጥር ያላቸው በሴዉል የሚገኙ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ጀምበር አሸብርቀው ይታያሉ። በዚህ መንገድ ዩናይትድ ስቴትስ በኅዳር መጨረሻ ላይ “ታንክስጊቪንግ ዴይ” የተባለውን በዓል በምታከብርበት ጊዜ ኮሪያና ሌሎች ምሥራቃውያን አገሮች ለገና በዓል ከወዲሁ ሽር ጉድ ይላሉ።
አብዛኞቹ ምሥራቃውያን አገሮች ከሕዝበ ክርስትና አገሮች የሚመደቡ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል ከኮሪያ ሕዝብ ውስጥ ክርስቲያን ነን የሚሉት 26.3 ከመቶ ብቻ ናቸው። በሆንግ ኮንግ 7.9 ከመቶ፣ በታይዋን 7.4 ከመቶ እንዲሁም በጃፓን 1.2 ከመቶ ብቻ ናቸው። አብዛኞቹ ምሥራቃውያን አገሮች የክርስትናን እምነት እንደማይከተሉ ግልጽ ነው፤ ሆኖም የገናን በዓል ማክበርን በተመለከተ ተቃውሞ የላቸውም። እንዲያውም በዓሉን ከምዕራባውያን መሰሎቻቸው ይበልጥ በደመቀ ሁኔታ የሚያከብሩት እነሱ ሳይሆኑ አይቀሩም። ለምሳሌ ያህል አብዛኞቹ ነዋሪዎቿ የቡድሂስት ወይም የታኦይስት እምነት ተከታዮች ቢሆኑም ሆንግ ኮንግ የገናን በዓል በከፍተኛ ድምቀት በማክበር የታወቀች ናት። ሌላው ቀርቶ 0.1 በመቶ ብቻ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ባሉባት ቻይና እንኳ የገና በዓል በከፍተኛ ፍጥነት ተወዳጅነት እያገኘ መጥቷል።
የገና በዓል በምሥራቃውያን ዘንድ እንዲህ በሰፊው የሚከበረው ለምንድን ነው? ኢየሱስን እንደ መሲህ አድርገው የማይቀበሉ ሰዎች ክርስቲያን ነን የሚሉ አብዛኞቹ ሰዎች የኢየሱስ ልደት ነው ብለው የሚያስቡትን ገናን የሚያከብሩት ለምንድን ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች የእነሱን አመለካከት መኮረጅ ይኖርባቸዋልን? ጥንታዊ ምሥራቃዊት አገር በሆነችው በኮሪያ የገና በዓል እንዴት ተወዳጅ እየሆነ እንደመጣ በምንመረምርበት ጊዜ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።