የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w09 4/1 ገጽ 31
  • አባት ለሌላቸው ልጆች አባት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አባት ለሌላቸው ልጆች አባት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • “አባት ለሌላቸው ልጆች” ፍቅራዊ አሳቢነት አሳዩአቸው
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
  • ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ለችግሩ መቋጫ ማበጀት
    ንቁ!—2000
  • ያለ አባት የቀሩ ቤተሰቦች—ያለንበትን ዘመን የሚጠቁም ችግር
    ንቁ!—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
w09 4/1 ገጽ 31

ወደ አምላክ ቅረብ

አባት ለሌላቸው ልጆች አባት

ዘፀአት 22:22-25

“በተቀደሰ መኖሪያው ያለ አምላክ፣ አባት ለሌላቸው ልጆች አባት ነው።” (መዝሙር 68:5 የ1980 ትርጉም) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ሐሳብ ስለ ይሖዋ አምላክ ልብ የሚነካ ትምህርት ይሰጠናል፤ ይሖዋ እርዳታ ለሚያሻቸው ሰዎች ያስባል። አምላክ ከወላጆቻቸው አንዱን በሞት ላጡ ልጆች እንደሚያስብላቸው ለእስራኤላውያን ከተሰጠው ሕግ በግልጽ መመልከት ይቻላል። ‘አባትና እናት ስለሌለው ልጅ’a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበትን በ⁠ዘፀአት 22:22-24 ላይ ያለውን ሐሳብ እስቲ እንመርምር።

አምላክ “አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ” በማለት አስጠንቅቋል። (ቁጥር 22) ይህ ጥቅስ ሰዎች ወላጆች ለሌሏቸው ልጆች ሰብዓዊነት እንዲያሳዩ የሚጠይቅ ሐሳብ ሳይሆን መለኮታዊ ትእዛዝ ነበር። አባቱን ያጣ ልጅ ከጥቃት የሚጠብቀውና የሚንከባከበው ሰው ስለሌለ ሌሎች ግፍ ሊፈጽሙበት ይችላሉ። ማንም ሰው እንዲህ ባለው ልጅ ላይ በማንኛውም መንገድ “ግፍ” እንዳይፈጽም ሕጉ ይከለክላል። “ግፍ አትዋሉ” የሚለው ሐረግ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “አታስጨንቁ” እና “አታጉላሉ” ተብሏል። አባት በሌለው ልጅ ላይ በደል መፈጸም በአምላክ ዘንድ በቀላሉ የሚታይ ነገር አልነበረም። አምላክ ይህን ጉዳይ ምን ያህል አክብዶ ይመለከተዋል?

ሕጉ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ።” (ቁጥር 23) የጥንቱ የዕብራይስጥ ቅጂ፣ ቁጥር 22 ላይ “ግፍ አትዋሉ” በማለት በብዙ ቁጥር የሚናገር ሲሆን ቁጥር 23 ላይ ግን “ግፍ ብትውልባቸው” በማለት በነጠላ ቁጥር ተጠቅሟል። ይህም እስራኤላውያን በግለሰብም ሆነ በብሔር ደረጃ ይህንን መለኮታዊ ሕግ የማክበር ኃላፊነት እንደነበረባቸው ያሳያል። እስራኤላውያን አባት የሌላቸውን ልጆች እንዴት እንደሚይዙ ይሖዋ ይመለከት ነበር። እነዚህን ልጆች ይሰማቸው ነበር፤ ለእርዳታ ለሚያሰሙት ጩኸት ምላሽ ለመስጠት ምንጊዜም ዝግጁ ነበር።—መዝሙር 10:14 የ1980 ትርጉም፤ ምሳሌ 23:10, 11

አንድ ሰው አባት የሌለውን ልጅ ቢበድለውና ልጁ ወደ አምላክ ቢጮህስ? አምላክ ምን ይሰማዋል? ይሖዋ “ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ” ብሏል። (ቁጥር 24) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ይህ ሐሳብ “ቃል በቃል ሲቀመጥ ‘አፍንጫዬ ይግላል’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም በጣም መበሳጨትን የሚያመለክት ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።” ይሖዋ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ፍርድ የመስጠቱን ኃላፊነት በእስራኤል ለነበሩ ሰብዓዊ ዳኞች እንዳልተወው ልብ በል። ራሱን መከላከል በማይችል ልጅ ላይ በደል በሚፈጽም በማንኛውም ሰው ላይ አምላክ ራሱ ይፈርድበታል።—ዘዳግም 10:17, 18

ይሖዋ ዛሬም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) አንዱንም ይሁን ሁለቱን ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ከልቡ ይራራል። (ያዕቆብ 1:27) ምንም በማያውቁ ልጆች ላይ ግፍ ወይም ጥቃት ሲፈጸም፣ አባት ለሌላቸው ልጆች አባት የሆነው ይሖዋ የጽድቅ ቁጣ ይቆጣል። ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ልጆችን የሚበድሉ ሰዎች ከይሖዋ “ጽኑ ቍጣ” አያመልጡም። (ሶፎንያስ 2:2) እንደነዚህ ያሉ ክፉ ሰዎች “በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር” መሆኑን ይማራሉ።—ዕብራውያን 10:31

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ‘አባት የሌለው ልጅ’ የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች በአምላክ ቃል ውስጥ 40 ጊዜ ያህል ይገኛል። እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል ወንዶች ልጆችን የሚያመለክት ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለሴት ልጆች እንደማይሠራ አድርገን ማሰብ የለብንም። የሙሴ ሕግ አባት የሌላቸውን ሴት ልጆችም መብት ያስጠብቅ ነበር።—ዘኍልቍ 27:1-8

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ