“ሞት እስኪለየን ድረስ”
ምን ያህል ሰዎች በሠርጋቸው ዕለት ከላይ ያለውን መሐላ ለትዳር ጓደኛቸው በደስታ ቃል ገብተው ይሆን? ምናልባትም ይህን ቃል ሲገቡ አንድ ቀን ሞት ከተፍ ሊል እንደሚችል አላሰቡ ይሆናል። ይሁንና እንደ እርጅና፣ ሕመም ወይም አደጋ ያሉ የተለመዱ አሳዛኝ ክስተቶች አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን በሞት እንዲያጣና ለብቸኝነት ብሎም ለሐዘን እንዲዳረግ ሊያደርገው ይችላል።—መክብብ 9:11 NW፤ ሮም 5:12
ዕድሜያቸው 65 ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆናቸው ሴቶች መካከል ግማሽ የሚያህሉት የትዳር ጓደኛቸውን በሞት እንደተነጠቁ አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት የሚያጡት ሴቶች ቁጥር ከወንዶች ይልቅ በሦስት እጥፍ ስለሚበልጥ የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት ብዙውን ጊዜ “የሴቶች ገጠመኝ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። ይህ ሲባል ግን ወንዶች እንዲህ ያለ ሁኔታ አያጋጥማቸውም ማለት አይደለም። እውነታው እንደሚያሳየው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆን?
ወንድም ሆንክ ሴት እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘንህን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል? የትዳር ጓደኛቸውን ያጡ አንዳንድ ሰዎች ሐዘናቸውን መቋቋም የቻሉት እንዴት ነው? ለሁሉም ሰው የሚሠራ አንድ ዓይነት መፍትሔ ባይኖርም በዚህ ረገድ ሊረዱ የሚችሉ መመሪያዎችና ሐሳቦች አሉ።
ችግሩን መጋፈጥ
አንዳንድ ሰዎች ማልቀስ የድክመት ምልክት አልፎ ተርፎም ጎጂ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ፤ ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡት ዶክተር ጆይስ ብራዘርስ የተባሉ የሥነ ልቦና ባለሙያ ማልቀስን ለስሜት እረፍት ከሚሰጥ የመጀመሪያ የሕክምና እርዳታ ጋር አመሳስለውታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ማልቀስ የተለመደ የሐዘን መግለጫ መንገድ ነው፤ እንዲሁም ሥቃይን ለማስታገስ ይረዳል። አንተም በማልቀስህ አትፈር። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥሩ ምሳሌ እናገኛለን። አብርሃም በጠንካራ እምነቱ የሚታወቅ ሰው ስለነበር የአምላክ ወዳጅ ተብሎ የመጠራት መብት አግኝቷል። ያም ሆኖ የሚወዳት ሚስቱ ሣራ ስትሞት ‘አልቅሶና አዝኖ’ ነበር።—ዘፍጥረት 23:2
አንዳንድ ጊዜ ብቻህን መሆን መፈለግህ ያለ ነገር ቢሆንም ራስህን ከሰዎች አታግልል። ምሳሌ 18:1 [NW] “ራሱን የሚያገል ሰው የራስ ወዳድነት ምኞቱን ለማሟላት ይሻል” በማለት ያስጠነቅቃል። ራስህን ከማግለል ይልቅ ችግርህን ሊረዱልህ የሚችሉ ዘመዶችህና ጓደኞችህ እንዲረዱህ ጠይቅ። በዚህ ረገድ የክርስቲያን ጉባኤ ከፍተኛ እገዛ ያበረክታል፤ በዚያም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እርዳታና ምክር ሊሰጡ የሚችሉ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሰዎች ይገኛሉ።—ኢሳይያስ 32:1, 2
አንዳንዶች ለደረሷቸው የሐዘን መግለጫ ደብዳቤዎችና ካርዶች መልስ መስጠት የሚረዳ ሆኖ አግኝተውታል። ይህን አጋጣሚ ተጠቅመህ ስለ ትዳር ጓደኛህ የምታስታውሳቸውን መልካም ነገሮችና አብራችሁ ያሳለፋችኋቸውን አስደሳች ጊዜያት መጻፍ ትችላለህ። በተጨማሪም ፎቶግራፎችን፣ ደብዳቤዎችንና ማስታወሻዎችን የያዘ አልበም ማዘጋጀት ከሐዘንህ እንድትጽናና ሊረዳህ ይችላል።
የትዳር ጓደኛውን ያጣ አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ግራ ሊጋባ ብሎም የሚይዘው የሚጨብጠው ሊጠፋበት እንደሚችል የታወቀ ነው፤ ሆኖም ቀድሞ ታደርጋቸው ወደነበሩ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች መመለስህ ሐዘንህን እንድትቋቋም ይረዳሃል። ለምሳሌ የምትተኛበት፣ ከእንቅልፍ የምትነሳበት፣ የምትበላበት ወይም ሌሎች ነገሮችን የምትሠራበት ቋሚ ሰዓት ከነበረህ በዚያው ሰዓት የተለመደውን ነገር ማድረግህን ቀጥል። የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ወይም የተጋባችሁበት ዕለትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ልዩ ወቅቶች የትዳር ጓደኛህን ይበልጥ እንድታስታውስ ስለሚያደርጉህ በእነዚህ ጊዜያት ምን እንደምታደርግ አስቀድመህ ፕሮግራም አውጣ። ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ ታደርጋቸው በነበሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ መካፈልህን ቀጥል።—1 ቆሮንቶስ 15:58
አንድ ሰው ከፍተኛ የስሜት ውጥረት ሲያጋጥመው የማመዛዘን ችሎታው ሊዛባ ይችላል። ምናልባትም አንዳንድ ሰዎች በመጥፎ ዓላማ ተነሳስተው ይህን አጋጣሚ የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ ይጠቀሙበት ይሆናል። በመሆኑም ቤት ከመሸጥ፣ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ንግድ ከመጀመር፣ አካባቢ ከመቀየር ወይም እንደገና ከማግባት ጋር በተያያዘ የችኮላ እርምጃ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ። አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ስለሆነም ስሜትህ እስኪረጋጋ ድረስ በሕይወትህ ውስጥ እንዲህ ያሉ ከፍተኛ ለውጦች ማድረግ አይኖርብህም።
በተለይ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ረጅም ዓመት አሳልፋችሁ ከነበረ የትዳር ጓደኛችሁ ይጠቀምባቸው የነበሩ ነገሮችን ምን እንደምታደርጉት ማሰብ ስሜታችሁን ይረብሸው ይሆናል፤ ይሁንና ይህ የሐዘን አንዱ ገጽታ ነው። ሆኖም በዚህ ረገድ አንድ ውሳኔ ላይ ካልደረሳችሁ ሐዘናችሁን ሳያስፈልግ ታራዝሙታላችሁ። (መዝሙር 6:6) አንዳንዶች ያለማንም እርዳታ ይህን ማድረግ ይፈልጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ ይህን ሲያደርጉ ስሜታቸውን ሊጋሩ የሚችሉ የቅርብ ጓደኞቻቸው አብረዋቸው እንዲሆኑ ማድረግ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። የትዳር ጓደኛህን ሞት ለመንግሥት ድርጅቶች፣ ለባንኮች፣ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ለአበዳሪ ተቋማት እንደ ማሳወቅ፣ ስም እንደ ማዘዋወር፣ የጡረታ አበል እንደ ማስከበር እንዲሁም ጋዜጣ ላይ እንደ ማሳወጅ ያሉ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ከጓደኛህ ወይም ከዘመድህ ጋር መሄድ ትፈልግ ይሆናል።
የምንኖረው ሥነ ምግባር ባዘቀጠበት ዓለም ውስጥ እንደሆነ አትዘንጋ። አሁን የምትኖረው ብቻህን ስለሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናህን ጠብቀህ መኖር ተፈታታኝ ሊሆንብህ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረው ሐሳብ የአሁኑን ያህል ወቅታዊ የሆነበት ጊዜ የለም፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ዕቃ እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው፤ ይህም አምላክን እንደማያውቁት አሕዛብ ለፍትወተ ሥጋ በመጎምጀት አይሁን።” (1 ተሰሎንቄ 4:4, 5) በመሆኑም በፍቅር ወይም በፆታ ግንኙነት ላይ የሚያተኩሩ ፊልሞችን ከማየት፣ መጻሕፍትን ከማንበብና ሙዚቃዎችን ከማዳመጥ ተቆጠብ።
ከዚህም በላይ ከሐዘን ለመጽናናት ጊዜ እንደሚጠይቅ አስታውስ። ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ የሚሺገን ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ምርምር ተቋም ያደረገውን ጥናት ጠቅሶ ሪፖርት እንዳደረገው የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች በአካልም ሆነ በአእምሮ ማገገም ለመጀመር ቢያንስ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያስፈልጋቸዋል። የመንፈስ ፍሬን በማፍራት የሚገኘውን ጽናት እንድታዳብር ወደ አምላክ ጸልይ። (ገላትያ 5:22, 23) አሁን ስታስበው የማይሆን ነገር ቢመስልህም እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር እየተጽናናህ ትሄዳለህ።
አንዳንዶች ከሐዘናቸው መጽናናት የቻሉበት መንገድ
በትዳር ዓለም 40 አስደሳች ዓመታትን ያሳለፉት አና፣ በቅርቡ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ሲያጡ ስሜታቸው በጣም ተጎድቶ ነበር። እንዲህ ብለዋል፦ “የ13 ዓመት ልጅ እያለሁ እናቴን አጣሁ ከዚያም አባቴንና ሁለቱን ወንድሞቼን እንዲሁም እህቴን በሞት ተነጠቅኩ። እውነቱን ለመናገር የባለቤቴን ሞት ያህል የጎዳኝ ሐዘን የለም። ለሁለት የተሰነጠቅኩ ያህል ሆኖ ነው የተሰማኝ። ሥቃዩ ከአቅሜ በላይ ነበር።” ታዲያ ሥቃያቸውን እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? እንዲህ ብለዋል፦ “ስለ ዳረል ግሩም ባሕርያት የሚገልጹ የፍቅርና የአድናቆት መግለጫዎችን ከኢሜይሎችና ከካርዶች ላይ በመሰብሰብ ትልቅ መጽሐፍ አዘጋጀሁ። እያንዳንዱ ሰው ዳረል ያለውን አንድ ለየት ያለ ባሕርይ ጠቅሶልኛል። ይሖዋም እንደሚያስታውሰውና በትንሣኤ እንደሚያስነሳው እርግጠኛ ነኝ።”
ሰማንያ ስምንት ዓመት የሆናቸው ኤስቴር ሐዘናቸውን እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምን እንደሆነ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ከ46 ዓመት የትዳር ሕይወት በኋላ ብቸኛ መሆን በጣም አስቸጋሪ ነው። ሆኖም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ራስን ማስጠመድ በጣም እንደሚረዳ ተገንዝቤያለሁ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች የመናገርና መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማዴን አላቆምኩም። ራሴን ከሰው አለማግለሌም ጠቅሞኛል። ጆሮ ከሚሰጡኝ ጓደኞቼ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አደርግ ነበር። ሁልጊዜ የሚያጽናና ቃል ይነግሩኛል ማለት ባይሆንም ጊዜያቸውን ስለሰጡኝና ስላዳመጡኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ።”
ከ48 የትዳር ዓመታት በኋላ ባለቤታቸውን በካንሰር ያጡት ሮበርት እንዲህ ይላሉ፦ “የሚያዋራችሁን፣ ለውሳኔ የምታማክሩትን፣ በጉዞና በእረፍት ጊዜ ከጎናችሁ የማይለየውን እንዲሁም የዕለት ውሏችሁን የምታካፍሉትን የትዳር ጓደኛችሁን በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም በጣም ከባድ ነው። ትግል የሚጠይቅብኝ ቢሆንም ተስፋ ሳልቆርጥ ሕይወቴን ለመምራት ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ። በአካልም ሆነ በመንፈስ ንቁ መሆኔ ረድቶኛል። ጸሎትም ከፍተኛ የመጽናናት ምንጭ ሆኖልኛል።”
ከደረሰብህ ሐዘን በኋላ ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት
የሚወዱትን የትዳር ጓደኛ በሞት ማጣት አሳዛኝ ከሆኑት የሕይወት ገጠመኞች መካከል አንዱ ቢሆንም ሕይወትህ አበቃለት ማለት አይደለም። በጎ የሆነውን ጎን ለመመልከት ሞክር፤ አጋጣሚውን በትርፍ ጊዜህ ማድረግ የሚያስደስቱህን ነገሮች እንደ ማድረግ ወይም ወደተለያዩ ቦታዎች እንደ መጓዝ ያሉ ቀደም ሲል ጊዜ አግኝተህ ማድረግ ያልቻልካቸውን ነገሮች ለማከናወን ተጠቀምበት። እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች መካፈልህ የባዶነት ስሜት እንዳይሰማህ ይረዳሃል። አንዳንዶች እንዲህ ያለው ሁኔታ በክርስቲያናዊ አገልግሎት ይበልጥ እንዲካፈሉ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚል ዋስትና ስለሰጠ በዚህ መንገድ ሌሎች ሰዎችን መርዳት ደስታና እርካታ ያስገኛል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ከዚህ በኋላ ደስተኛ ልትሆን እንደማትችል አድርገህ አታስብ። ወደ ይሖዋ አምላክ ከቀረብክ እሱ እንደሚንከባከብህ እርግጠኛ ሁን። መዝሙራዊው ዳዊት “[ይሖዋ] መበለቶችን ይደግፋል” ብሏል። (መዝሙር 146:9) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” እንደሆነ አድርጎ ብቻ ሳይሆን ‘እጁን ዘርግቶ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት የሚያረካ’ አምላክ እንደሆነ አድርጎ እንደሚገልጸው ማወቁ በጣም የሚያጽናና ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3፤ መዝሙር 145:16) በእርግጥም አፍቃሪው አምላክ የሆነው ይሖዋ የእሱን እርዳታ ለማግኘት የሚሹ ሰዎችን ለመርዳት አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ አለው፤ እንዲሁም ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። አንተም “ዐይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረድኤቴ ከወዴት ይመጣል? ረድኤቴ ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል” ብለው እንደዘመሩት የጥንት እስራኤላውያን ዓይነት ስሜት እንዲኖርህ እንመኛለን።—መዝሙር 121:1, 2
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው በሐዘንና በብቸኝነት ስሜት ተደቁሰዋል። አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ደርሶብሃል?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
እንደገና ስለማግባት ምን ማለት ይቻላል?
ከትዳር ጓደኛሞች መካከል አንዱ በሞት ሲለይ የጋብቻው ትስስር እንደሚያከትም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ይህ ደግሞ በሕይወት ያለው የትዳር ጓደኛ እንደገና ማግባት እንደሚችል ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ያም ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ለግለሰቡ የተተወ ነው። ይሁን እንጂ ልጆች የወላጃቸውን ውሳኔ መገንዘብና በተቻለ መጠን ድጋፍ መስጠት ይኖርባቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ለምሳሌ ያህል፣ አንድሬስ አባቱ እንደገና እንደሚያገባ ሲሰማ መጀመሪያ ላይ ተቃውሞ ነበር። እናቱን በጣም ይወዳት ስለነበር የእሷን ቦታ ማንም መተካት የለበትም የሚል አቋም ነበረው። እንዲህ ይላል፦ “አባቴ ጥሩ ውሳኔ እንዳደረገ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብኝም። እንደገና ማግባቱ ደስታው እንዲመለስ አድርጎለታል። ወደ ሌሎች ቦታዎች እንደ መጓዝ ያሉ ማድረግ አቁሟቸው የነበሩ ነገሮችን እንደገና ማድረግ እንዲጀምር ረድቶታል። ከዚህም በላይ አዲሱ ሚስቱ በአካልም ሆነ በስሜት ላደረገችለት እንክብካቤ አመስጋኝ ነኝ።”
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ራስህን በሥራ ማስጠመድህና መጽናት እንድትችል እንዲረዳህ ወደ አምላክ መጸለይህ ከሐዘንህ እንድትጽናና ይረዳሃል