የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w13 6/1 ገጽ 3-4
  • ጭፍን ጥላቻ ዓለም አቀፍ ችግር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጭፍን ጥላቻ ዓለም አቀፍ ችግር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በግለሰብ ደረጃ ራስን መመርመር
  • ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም ይመጣ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • ጭፍን ጥላቻ—አንተንም አጥቅቶህ ይሆን?
    ንቁ!—2020
  • ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ ደርሶብሃልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ጭፍን ጥላቻ የሚያከትምበት ጊዜ
    ንቁ!—2004
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
w13 6/1 ገጽ 3-4
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም​—ይመጣ ይሆን?

ጭፍን ጥላቻ ዓለም አቀፍ ችግር

ከኮሪያዊ ቤተሰብ የተወለደው አሜሪካዊው ጆናታን ከልጅነቱ ጀምሮ ጭፍን ጥላቻ ይደርስበት ነበር። እያደገ ሲሄድ ግን በመልኩ ወይም በዘሩ ምክንያት የጭፍን ጥላቻ ሰለባ የማይሆንበትን ቦታ ማፈላለግ ጀመረ። በኋላም ጆናታን በሰሜናዊ አላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ አንድ ከተማ የሕክምና ዶክተር ሆነ፤ ብርዳማ በሆነው በዚህ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኞቹ ታካሚዎች ከእሱ ጋር የሚመሳሰል የፊት ገጽታ ስላላቸው ከአካባቢው ቅዝቃዜ ከባሰው ጭፍን ጥላቻ እንደሚገላገል ተስፋ አድርጎ ነበር።

ይሁንና ለአንዲት የ25 ዓመት ሴት የሕክምና እርዳታ በሰጠበት ጊዜ ይህ ተስፋው በንኖ ጠፋ። ይህች በሽተኛ ከኮማ ነቅታ የጆናታንን ፊት ስታይ ለኮርያውያን ያላትን ሥር የሰደደ ጥላቻ የሚያሳይ የንቀት አነጋገር ተናገረች። ይህ አሳዛኝ አጋጣሚ ጆናታን የእሱ ዓይነት የፊት ገጽታ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ለመኖር ያደረገው ጥረት የጭፍን ጥላቻ ሰለባ ከመሆን እንዳላዳነው አስገንዝቦታል።

የጆናታን ተሞክሮ አንድን አሳዛኝ እውነታ አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ጭፍን ጥላቻ ያልዳሰሰው የምድር ክፍል የለም። ሰዎች ባሉበት ቦታ ሁሉ ጭፍን ጥላቻ አለ ማለት ይቻላል።

ጭፍን ጥላቻ የተስፋፋ ቢሆንም እንዲህ ያለውን ድርጊት የሚያወግዙ ብዙ ሰዎች አሉ። ነገሩ በእርግጥ ግራ የሚያጋባ ነው። በጣም የተጠላ ነገር ይህን ያህል ሊስፋፋ የቻለው ለምንድን ነው? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጭፍን ጥላቻን የሚቃወሙ ብዙ ሰዎች ጥላቻው በውስጣቸው እንዳለ አያውቁም። እንዲህ ያለው ጥላቻ በአንተስ ውስጥ ይኖር ይሆን? ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?

ጭፍን ጥላቻ ምንድን ነው?

ተመራማሪዎች ለጭፍን ጥላቻ ፍቺ መስጠት ይከብዳቸዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት “ጭፍን ጥላቻ አንድ ግለሰብ የአንድ ቡድን አባል ስለሆነ ብቻ ለእሱ አሉታዊ አመለካከት መያዝ ወይም መጥፎ ስሜት ማዳበር ማለት ነው።” ሌሎች እንደሚሉት ደግሞ “በቂ ባልሆነ መረጃ” ላይ ተንተርሶ ‘በአንድ ቡድን አባላት ላይ ወደ መፍረድ’ ሊያመራ የሚችል ዝንባሌ ነው። ያም ሆነ ይህ ጭፍን ጥላቻ የአንድን ሰው ዘር፣ ክብደት፣ ፆታ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ወይም ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት በመንተራስ ሊመጣ ይችላል።

በግለሰብ ደረጃ ራስን መመርመር

ተቀበልነውም አልተቀበልነው፣ ጭፍን ጥላቻ በተወሰነ መጠንም እንኳ በልባችን ውስጥ መኖሩን ለይቶ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ” ወይም አታላይ እንደሆነ ይናገራል። (ኤርምያስ 17:9) በመሆኑም ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ተቻችለን እንደምንኖር በማሰብ ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። ወይም ደግሞ ስለተወሰኑ የሰዎች ቡድኖች አሉታዊ አመለካከት የያዝነው በቂ ምክንያት ስላለን እንደሆነ በማሰብ ራሳችንን ለማሳመን እንሞክር ይሆናል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታስባለህ?

ስውር የሆነ ጭፍን ጥላቻ በውስጣችን መኖሩን ማወቅ ቀላል እንዳልሆነ በምሳሌ ለማስረዳት ቀጥሎ የቀረበውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት፦ ምሽት ላይ ብቻህን በእግር እየሄድክ ነው እንበል። ከዚህ በፊት አይተሃቸው የማታውቃቸው ሁለት ወጣቶች ወደ አንተ እየቀረቡ ነው። ፈርጣማ ሰውነት ያላቸው ሲሆን አንደኛው ወጣት በእጁ የሆነ ነገር የያዘ ይመስላል።

እነዚህ ወጣቶች ጥቃት ሊሰነዝሩብኝ ነው ብለህ ታስባለህ? እርግጥ ነው፣ ከዚህ በፊት ካሳለፍከው ተሞክሮ በመነሳት ጠንቃቃ መሆን እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ያሳለፍከው ተሞክሮ በእርግጥ እነዚህ ወጣቶች አደገኛ ናቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ በቂ ነው? ይበልጥ የሚያሳስበው ጥያቄ ግን ‘እነዚህ ወጣቶች ከየትኛው ዘር ወይም ጎሣ ናቸው ብለህ አሰብክ?’ የሚለው ነው። ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ በልብህ ውስጥ ያለውን ነገር የሚገልጥ ሊሆን ይችላል። የሰጠኸው መልስ በትንሹም ቢሆን የጭፍን ጥላቻ እርሾ በውስጥህ እንዳለ ሊያመለክት ይችላል።

ለራሳችን ሐቀኞች ከሆንን፣ ሁላችንም መጠኑ ይለያይ እንጂ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ጭፍን ጥላቻ በልባችን ጓዳ ተደብቆ እንደሚገኝ አምነን እንቀበላለን። መጽሐፍ ቅዱስም “ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል” በማለት በጣም የተለመደውን ዓይነት መድልዎ ይገልጻል። (1 ሳሙኤል 16:7) ሁላችንም ፊትን አይቶ የመፍረድ አባዜ ተጠናውቶናል፤ እንዲያውም ብዙውን ጊዜ መጥፎ ውጤት ያስከትልብናል። ታዲያ ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ ወይም ከናካቴው ማስወገድ የምንችልበት ተስፋ ይኖረን ይሆን? ደግሞስ ከጭፍን ጥላቻ የጸዳ ዓለም የምናይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ዓለም አቀፍ ችግር

ካናዳ፦ “[አገሪቱ] የተለያዩ ዓይነት ዘሮች የሚኖሩባት ከመሆኑም ሌላ የተለያዩ ማኅበረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ በርካታ ሕጎችንና ፖሊሲዎችን ያወጣች ብትሆንም ዘረኝነት አሁንም ድረስ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ችግር ሆኗል።”—አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለ ካናዳ ያወጣው ሪፖርት፣ 2012

አውሮፓ፦ “[አርባ ስምንት] በመቶ የሚሆኑት አውሮፓውያን በአገራቸው ያለውን መድልዎ ለማስወገድ ምንም ያህል ጥረት እንዳልተደረገ ይሰማቸዋል።”—ኢንቶለረንስ፣ ፕሬጅዲስ ኤንድ ዲስክሪሚኔሽን፦ ኤ ዩሮፒየን ሪፖርት፣ 2011

አፍሪካ፦ “በብዙ አገሮች ተስፋፍቶ የሚገኘው በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ዓመፅና መድልዎ አሁንም አልቀነሰም።”—አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት 2012

ኔፓል፦ “ዳሊቶች (“የማይነኩ”) በተለይ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በባሕላዊ መስኮች ሥር በሰደደ መድልዎ ይሠቃያሉ።”—ሂውመን ራይትስ ዎች ዎርልድ ሪፖርት፣ 2012

ምሥራቅ አውሮፓ፦ “የምሥራቅ አውሮፓ ሮማዎች ወደ ሌላ አገር ሲሄዱ ሁሉም ሰው በክፉ ዓይን ስለሚያያቸው እንዲሁም በአገራቸው የጭፍን ጥላቻ ሰለባ ስለሚሆኑ የእነሱን ችግር ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚፈልግ ፖለቲከኛ የለም።”—ዚ ኢኮኖሚስት፣ መስከረም 4, 2010

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ