የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w15 8/15 ገጽ 29-30
  • ከዮሐና ምን እንማራለን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዮሐና ምን እንማራለን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዮሐና ማን ነበረች?
  • በንብረቷ አገልግላለች
  • ኢየሱስ በሞተበት ወቅትና ከዚያ በኋላ
  • ‘በጌታ ሥራ የሚደክሙ’ ሴቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሰበከ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • አምላክ ሴቶችን በአክብሮትና በአሳቢነት ይይዛቸዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ክርስቲያን ሴቶች ከፍተኛ ግምትና አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
w15 8/15 ገጽ 29-30
ዮሐና ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ስታገለግል

ከዮሐና ምን እንማራለን?

ብዙ ሰዎች ኢየሱስ 12 ሐዋርያት እንደነበሩት ያውቃሉ። ይሁንና ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አብረውት የሚጓዙ ሴቶችም እንደሚገኙበት ልብ ላይሉ ይችላሉ። ከእነዚህ ሴቶች አንዷ ዮሐና ትባላለች።—ማቴ. 27:55፤ ሉቃስ 8:3

ዮሐና፣ ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ምን አስተዋጽኦ አበርክታለች? ከእሷ ምሳሌስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ዮሐና ማን ነበረች?

ዮሐና “የሄሮድስ ቤት አዛዥ የኩዛ ሚስት” ነበረች። ኩዛ የሄሮድስ አንቲጳስ ባለሟል ሊሆን ይችላል። ዮሐና፣ ኢየሱስ ከበሽታቸው ከፈወሳቸው ጥቂት የማይባሉ ሴቶች አንዷ ነች። ይህች ሴት ከኢየሱስና ከሐዋርያቱ ጋር ይጓዙ ከነበሩት ሴቶች መካከል ትገኝበታለች።—ሉቃስ 8:1-3

የአይሁድ ረቢዎች፣ ሴቶች ዘመዶቻቸው ካልሆኑ ወንዶች ጋር አብረው መሆን እንደሌለባቸው ያስተምሩ ነበር፤ አብሮ መጓዝማ የማይታሰብ ነገር ነው። እንዲያውም አይሁዳውያን ወንዶች፣ ከሴቶች ጋር ብዙ ማውራት እንደማይገባቸው ይገለጽ ነበር። ኢየሱስ ግን እንዲህ ያሉትን ወጎች ገሸሽ በማድረግ ዮሐና እና ሌሎች በእሱ ያመኑ ሴቶች ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው እንዲጓዙ ፈቅዷል።

ዮሐና ከኢየሱስና ከሐዋርያቱ ጋር መሆኗ በማኅበረሰቡ ዘንድ ነቀፋ ሊያስከትልባት እንደሚችል ታውቅ ነበር። ከኢየሱስ ጋር የሚጓዙ ሁሉ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ነበረባቸው። ኢየሱስ እንዲህ ያሉ ተከታዮቹን አስመልክቶ “እናቴና ወንድሞቼ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 8:19-21፤ 18:28-30) ኢየሱስ እሱን ለመከተል ሲሉ መሥዋዕት የሚከፍሉ ሰዎችን ይህን ያህል እንደሚያቀርባቸው ማወቁ አያበረታታም?

በንብረቷ አገልግላለች

ዮሐና እና ሌሎች ብዙ ሴቶች፣ ኢየሱስንና 12 ሐዋርያቱን “በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር።” (ሉቃስ 8:3) አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “ሉቃስ ለአንባቢዎቹ ማስተላለፍ የፈለገው ሐሳብ ሴቶቹ ምግብ ያበስሉላቸው፣ ዕቃ ያጥቡላቸውና ልብሳቸውን ይጠግኑላቸው እንደነበር አይደለም።” ጸሐፊው አክለውም “ምናልባት ሴቶቹ ይህን አድርገው ሊሆን ይችላል፤ . . . ሉቃስ ግን እንዲህ እያለ አይደለም” ብለዋል። ሴቶቹ ገንዘባቸውን፣ ንብረታቸውን ወይም ጥሪታቸውን ተጠቅመው አብረዋቸው ለሚጓዙት ሰዎች የሚያስፈልገውን ነገር እንዳቀረቡ ይገመታል።

ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ የስብከት ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት ሰብዓዊ ሥራ አይሠሩም ነበር። በመሆኑም በግምት 20 ሰዎችን ያቀፈው ቡድናቸው ለሚያስፈልገው ምግብም ሆነ ሌሎች ነገሮች በሙሉ የሚሆን ገንዘብ ላይኖራቸው ይችላል። በእንግድነት የሚቀበላቸው ሰው የሚያገኙበት ጊዜ ቢኖርም ክርስቶስና ሐዋርያቱ ‘የገንዘብ ሣጥን’ ይይዙ የነበረ መሆኑ የሚያስፈልጋቸውን የሚያገኙት ሌሎች በሚያደርጉላቸው መስተንግዶ ብቻ እንዳልነበር ይጠቁማል። (ዮሐ. 12:6፤ 13:28, 29) ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን የሚረዳቸው ገንዘብ ዮሐና እና ሌሎቹ ሴቶች አበርክተው ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች፣ አይሁዳውያን ሴቶች ገንዘብም ሆነ ንብረት ሊኖራቸው እንደማይችል ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ በወቅቱ የተዘጋጁ ጽሑፎች እንደሚጠቁሙት በአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ዘንድ አንዲት ሴት ሀብት ልታፈራ የምትችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ (1) አባቷ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ከሞተ የምትወርሰው ሀብት፣ (2) በስጦታ የምታገኘው ንብረት፣ (3) በጋብቻ ውሉ ላይ በተጠቀሰው መሠረት ከባሏ ጋር ብትፋታ የሚሰጣት ገንዘብ፣ (4) ባሏ ሲሞት ከርስቱ እንድታገኝ የተናዘዘላት ሀብት ወይም (5) በግሏ የምታገኘው ገቢ።

የኢየሱስ ተከታዮች የሚችሉትን ያህል መዋጮ ያደርጉ እንደነበር ጥርጥር የለውም። አብረውት ከሚጓዙት መካከል ሀብታም የሆኑ ሴቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ዮሐና የሄሮድስ የቤት አስተዳዳሪ ሚስት እንደሆነች ስለተገለጸ አንዳንዶች ባለጸጋ እንደነበረች ይገምታሉ። ኢየሱስ ይለብስ የነበረውን ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለስፌት የተሠራ ውድ ልብስ ያገኘው እንደ እሷ ካለ ሰው ሊሆን ይችላል። አንዲት ጸሐፊ፣ “የዓሣ አጥማጆች ሚስቶች” እንዲህ ያለ ልብስ ሊሰጡት እንደማይችሉ ተናግረዋል።—ዮሐ. 19:23, 24

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ዮሐና የገንዘብ መዋጮ ስለ ማድረጓ በቀጥታ የሚናገሩት ነገር የለም። ይሁንና አቅሟ የፈቀደውን አድርጋለች፤ ይህም ትምህርት ይሰጠናል። የአምላክን መንግሥት ለመደገፍ የምንሰጠው ነገርም ሆነ መስጠት አለመስጠታችን በግል ውሳኔያችን ላይ የተመካ ነው። አምላክ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው፣ የምንችለውን ያህል በደስታ መስጠታችንን ነው።—ማቴ. 6:33፤ ማር. 14:8፤ 2 ቆሮ. 9:7

ኢየሱስ በሞተበት ወቅትና ከዚያ በኋላ

ኢየሱስ በተገደለበት ወቅት በቦታው ከነበሩት ሴቶች አንዷ ዮሐና ሳትሆን አትቀርም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እነዚህም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ከእሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች በርካታ ሴቶችም ነበሩ።” (ማር. 15:41) የኢየሱስ አስከሬን ከተሰቀለበት እንጨት ላይ ወርዶ ሊቀበር ሲል “ከገሊላ ከኢየሱስ ጋር አብረው የመጡት ሴቶች . . . ተከትለው በመሄድ መቃብሩን አዩ፤ አስከሬኑም እንዴት እንዳረፈ ተመለከቱ። ጥሩ መዓዛ ያላቸው ቅመሞችና ዘይቶች ለማዘጋጀትም ተመልሰው ሄዱ።” እነዚህ ሴቶች “መግደላዊቷ ማርያም፣ ዮሐናና የያዕቆብ እናት ማርያም” እንደሆኑ ሉቃስ ገልጿል፤ እነሱም ከሰንበት በኋላ ወደ መቃብሩ ተመልሰው የሄዱ ሲሆን በዚያም መላእክቱ ኢየሱስ እንደተነሳ ነገሯቸው።—ሉቃስ 23:55 እስከ 24:10

ዮሐና እና ሌሎች ሴቶች ለኢየሱስ አስከሬን ቅመሞች ሲያዘጋጁ

ዮሐና እና ሌሎች አማኝ ሴቶች ለጌታቸው የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል

በ33 ዓ.ም. በተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ የኢየሱስን እናትና ወንድሞቹን ጨምሮ በኢየሩሳሌም ከተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርት አንዷ ዮሐና ልትሆን ትችላለች። (ሥራ 1:12-14) ዮሐና ለቤተ መንግሥት ቅርብ ሰው ስለነበረች ሉቃስ የሄሮድስ አንቲጳስን የግል ሕይወት በተመለከተ የጻፈውን ሐሳብ ያገኘው ከእሷ ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች ያስባሉ፤ በተለይ ከወንጌል ጸሐፊዎች መካከል እሷን በስም የጠቀሳት ሉቃስ ብቻ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ይመስላል።—ሉቃስ 8:3፤ 9:7-9፤ 23:8-12፤ 24:10

የዮሐና ታሪክ በጥልቅ ልናስብባቸው የሚገቡ ትምህርቶችን ይዟል። አቅሟ በሚፈቅደው ሁሉ ኢየሱስን አገልግላዋለች። ያደረገችው የገንዘብ ድጋፍ እሱ፣ 12 ሐዋርያቱና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ አብረው ለስብከት በሚጓዙበት ጊዜ ጠቅሟቸው ከሆነም በዚህ እንደምትደሰት ምንም ጥያቄ የለውም። ዮሐና ኢየሱስን ያገለገለችው ከመሆኑም ሌላ በመከራው ወቅት በታማኝነት ከጎኑ ቆማለች። በእርግጥም ክርስቲያን ሴቶች እንደ እሷ ዓይነት መንፈሳዊ አመለካከት ቢያንጸባርቁ ይጠቀማሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ